በሞሮኮ አዘጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ለመሳተፍ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአቻ ውጤት ተለያይቷል። ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴድየም የተከናወነው ጨዋታ ካለ ግብ 0ለ0 የተጠናቀቀ ሲሆን በአሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ግብ የማስቆጠር ችግር ጎልቶ ታይቶበታል። አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙም “ግብ ያለማስቆጠራችን አንዱ ደካማ ጎናችን ነው” ሲሉ የቡድናቸውን ችግር ተናግረዋል። ይህም በመልሱ ጨዋታ ከባድ ፈተና እንዲገጥመው አድርጓል። በአንጻሩ ቡድኑ በሜዳው ግብ አለማስተናገዱ በመልሱ ጨዋታ ያለውን ተስፋ እንዳይጨልም ያደረገ ሲሆን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ግን የማሸነፍ ወይም ግብ አስቆጥሮ አቻ የመለያየት ግዴታ ውስጥ ከቶታል።
የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ የፊታችን ሰኞ ኪንሻሳ ላይ ይካሄዳል። በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት የሰጡት አሰልጣኝ አጥናፉ “ቡድኑ የምንችለውን ሁሉ አድርጓል። ተጋጣሚያችንም ጥሩ ነው ምክንያቱም ከሜዳ ውጭ ያለውን ውድድር በሙሉ ያለውን ዕድል ተጠቅመው እዚህ ዘግቶ ለመሄድ የመጣ ነው። በዚህ አደረጃጀት የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ተጭነው ለመጫወት ወይም የአየር ንብረታችንን ከፍታ ተጠቅመው በጣም ተጭነውን ለመጫወት ሞክረዋል፤ ያንንም ተቋቁመን ተጫውተናል። በዚህ አጋጣሚ የተለያዩ ዕድሎችን ፈጥሯል ጥሩ ሆኖ ለማቀናጀት ችሏል። በእንቅስቃሴው መሠረት እንግዲህ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ባሉብን ክፍተቶች ሁሉ ተጫዋቾቹን በበለጠ ዕይታ ኖሯቸው ወደፊት እንዲጫወቱ በማድረጋችን ብዙ ዕድሎችን ፈጥረናል፤ ግን ግብ ማስቆጠር አልቻልንም፤ የሚፈጠር ነው። በተሻለ እንቅስቃሴ በሁለተኛውን አጋማሽ ቡድኑን እንቅስቃሴ ውስጥ በመክተት ከሜዳ ውጭ ዘግቶ የመጫወት ዕድላቸውን በማስከፈት የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገናል። እንዳያችሁት ግብ ያለማስቆጠራችን አንዱ ደካማ ጎናችን ነው። ከዚህ አንጻር ለሚቀጥለው ባሉን ድክመቶች ዙሪያ ሰርተን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥሩ መልስ ሆኖናል እንቅስቃሴው። ተጫዋቾች ነገ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የሚሆኑ ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው ፤ ከዚህ አንጻር ተወዳዳሪ ቡድን ነው” በማለት ተናግረዋል።
በጨዋታው የተሻለ ሊባል የሚችል ውጤት ይዘው የወጡት የዲሞክራቲክ ኮንጎ አሰልጣኝ ኪሞቶ ፒፓ በበኩላቸው፣ “ውጤቱ በጣም ጥሩ ነው ፤ ተጫዋቾቼ ጥሩ አድርገዋል። ጨዋታውን ኪንሻሳ ላይ እንጨርሰዋለን ብዬ አስባለሁ” በማለት በውጤቱ እንዳልተከፉ ተናግረዋል።
በጨዋታው የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ወደነሱ ሜዳ እስኪመጡ መጠበቅ እና ኳሱን ሲያገኙ በፍጥነት ወደፊት መሄድ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት አቅደው እንደነበር የገለጹት አሰልጣኙ፣ በመልሱ ጨዋታ ኪንሻሳ ላይ ቡድናቸው ጥሩ ይጫወታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
“ስለ ዳኞች ማውራት አልፈልግም፤ አፍሪካ ውስጥ ነው ያለነው። ቡድናችን ላይ ነው ትኩረት የማደርገው እና ቡድናችንም በጣም ጥሩ ተጫውቷል። በመልሱ ጨዋታ በጣም ጥሩ እንጫወታለን ብዬም አስባለሁ፤ እና ከዳኞች ምንም አልጠብቅም። ሁሉም ሥራውን ነው የሚሠራው እኛም ሥራችን ላይ እናተኩራለን ጠንክሮ የሰራ ደግሞ ጥሩ ውጤት ያገኛል።” ሲሉም አሰልጣኙ አክለዋል።
ስለ ተጋጣሚያቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሰጡት አስተያየትም “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጣም ጥሩ ቡድን ነው ፤ አድንቄያቼዋለሁ። መስመሮቹን ዘግተን ለመጫወት ሞክረናል። የመጀመሪያው አጋማሽ ለኛ ጥሩ ነበር አንድ ሁለት የግብ ዕድሎች ነበሩን ግን ይሄ እግር ኳስ ነው። ለመዘጋጀት አራት ቀናት አሉን ጨዋታው ገና አላለቀም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ነው ለእነሱ ጥሩ ስሜት ነው ያለኝ። የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ኪንሻሳ ላይ የምናየው ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2015 ዓ.ም