ድህነትና የኑሮ ውድነት ዓለማቀፋዊ ችግሮች ቢሆኑም በእኛ አገር እየተስተዋለ የሚገኘው የኑሮ ውድነት ግን በዓይነቱ ለየት ያለ ነው። ከሌሎች አገራት የሚለይበት ዋነኛ መገለጫ ባህሪውም አንዴ ወረድ ሌላ ጊዜ ከፍ የሚል አለመሆኑ ነው። ሁሌም መጨመር እንጂ መቀነስ የሚባል ነገር አያውቅም። ወያኔ አገር ይገዛ በነበረበት ጊዜ በሥራ ምክንያት ወደ አንድ የአገራችን አካባቢ በሄድኩበት አጋጣሚ በተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት በየመንገድ ዳሩ ተሰቅለው እንዳየኋቸው የማስታወቂያ ሰሌዳ መፈክሮች “ሁሌም በዕድገት ጎዳና” መሆኑ ነው የእኛን አገር የኑሮ ውድነት ከሌላው የሚለየው።
በዚህች አገር በአሁኑ ወቅት ያልጨመረ ነገር የለም። ከምግብ እስከ መድሃኒት፣ ከትንሿ መርፌ እስከ ትልልቆቹ የግንባታ መሣሪያዎችና ማሽነሪዎች ሁሉም ዋጋቸው ጣሪያ ነክቷል። ምላጭ እንኳን በአቅሟ አምስት ብር ገብታለች። መቶ ሃምሳ ግራም ለማይሞላ ዳቦ ከአምስት እስከ አስራ ሁለት ብር እንደየ ጥራት ደረጃው ይከፈላል። በተዓምር ካልሆነ በስተቀር ከምጣዱ ላይ እንዴት እንደተላቀቀ ለማወቅ የሚያዳግት፣ እፍ ቢሉት አርባ ክንድ የሚበር፣ ህጻን ልጅ የማያጠግብ አንድ እንጀራ ከአስር ብር ካለፈ ሰነባብቷል። እርሱም ጀሶ ወይም ሰጋቱራ ያልተቀላቀለበት ከሆነ ነው። አባቶቻችን በጦር ሜዳ ሳይቀር እንደልብ እየቆረጡ ጣሊያንን ያሸበሩበት ሥጋማ ዋጋው የማይቀመስ ከመሆኑ የተነሳ ለብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን የቅንጦት ምግብ ከሆነ ዓመታት ተቆጠሩ። የታባቱና! ካደጉ አይቀር እንደ እኛ ነው እንጅ ዕድገት¡
እናም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ እጅጉን እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ እየፈተነው ይገኛል። በተለይም ደግሞ በዓለም አቀፉ መመዘኛ መሰረት ከ1 ነጥብ 25 ዶላር በታች በሆነ የቀን ገቢ የሚተዳደረውንና ከድህነት ወለል በታች ሚኖረው ድሃ ሕዝብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲገባና የሰቀቀን ኑሮ እንዲመራ አስገድዶታል። በአጠቃላይ ሕዝቡ የኑሮ ውድነቱ ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል። ብሶቱንና እሮሮውንም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየገለጸ ይገኛል። በተለይም በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች “ፍጹም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ከአቅማችን በላይ ሆኗል። መብላት እንኳን የማንችልበት ደረጃ እየደረስን ነው፤ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው” እያሉ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል።
አንድ የመዲናዋ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ፤ “ከአስር ለሚልቁ ዓመታት በሚኒባስ ታክሲ ሾፌርነት ቤተሰቤን ሳስተዳድር ኖሬያለሁ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የኑሮ መወደድ ከአቅሜ በላይ ሆኖ እያንገዳደገደኝ ነው” ሲሉ አጫውተውኛል። “በዋጋ ላይ ያለውን ለውጥ ከቀን ወደ ቀን እያየሁት የመጣሁት ጉዳይ ነው፤ በእኔ ህይወት እንኳን ታክሲ ሠርቼ ብሩን ይዤ ብገባም ምንም የሚገዛው ነገር የለም። የልጆች ትምህርት ቤት፣ የእህሉ ውድነት፣ እንዲያውም ተስፋ ወደማስቆረጥ ደረጃ እየደረሰ ያለ ይመስለኛል። የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ፣ የአልባሳት፣ የምግብ ወጪዎች ሲደመሩበት “ናላን የሚያዞር” ሆኗል። በዚህ ላይ የቤት ኪራይ ወጪ ይታከልበታል። ህይወታችንን ለማቆየት እየሰራን ነው እንጅ እየኖርን ነው ብዬ አላወራውም” በማለት ምሬታቸውን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። ይህ ምሬት የብዙሃኑን አዲስ አበቤ ብሎም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያለበትን የኑሮ ሁኔታን የሚያመላክት መሆኑንም በገሃድ እያየነው ያለ ሃቅ ነው።
ይህን ለመሰለው መረን የለቀቀ የዋጋ ንረትና በህብረተሰቡ ላይ ለተፈጠረው የከፋ የኑሮ ውድነት በርካታ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ግን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን መሆኑን መንግሥት በጉዳዩ ላይ በሚሰጣቸው መግለጫዎች ሲያስረዳ እናያለን። ከዚህ በተጨማሪ በንግድ ሰንሰለቱ ውስጥ በርካታ ህገ ወጥ ደላሎች መኖራቸውና ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች መበራከታቸው የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ዓይነተኛ ምክንያት መሆኑን ብዙዎች
ይስማሙበታል።
በሕብረተሰቡ ውስጥ “መንግሥት በህገ ወጦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ አይደለም” የሚል ከፍተኛ ቅሬታና ወቀሳ ቢኖርም መንግሥት በበኩሉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ በሕገ ወጦች ላይም የእርምት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ሲናገር ይደመጣል። የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መንግሥት መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን እንደሚያቀርብና ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ በመከተል ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑንም በየጊዜው ሲገልጽ ይሰማል። ሆኖም ችግሩ ተባብሶ ሲቀጥል እንጂ ሲቀንስ አልተመለከትንም።
ታዲያ አገሩን እንደሚወድና የሰው ልጆች ሁሉ መልካም ነገር እንጂ ችግርና ስቃይ ሲደርስባቸው ማየት እንደማይፈልግ አንድ ሰው ጉዳዩን በቅርበት ከመረመርነው ኢኮኖሚያዊ ምክንያቱ እንዳለ ሆኖ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ አንድ ሌላ ያልተነቃበት መንስኤ መኖሩን መታዘብ አይቀርም። እንደሚታወቀው በምጣኔ ሃብት ሳይንሱ በመሰረታዊነት የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በህብረተሰቡ የፍጆታ ፍላጎትና በአምራቹ የምርት አቅርቦት መካከል አለመመጣጠን ሲኖር ነው። አሁን ላይ በእኛ አገር እየተከሰተ ያለው የዋጋ ንረትና ይህንን ተከትሎ የተፈጠረውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ስንመለከተው ግን ከዚህም ያለፈ መሆኑን እንታዘባለን። ምክንያቱም አቅርቦት ቢኖርም ባይኖርም ምርትና አገልግሎቶች የሚሸጡት በውድ ዋጋ ነው። አቅርቦቱ ሙሉ በሆነበት ወቅትም የዋጋ ንረት አለ፤ ሁሌም የኑሮ ውድነት አለ። ለምን ?
ለምን ለሚለው ጥያቄ በግሌ የደረስኩበት ድምዳሜ “በአገሪቱ ውስጥ አምራች፣ ነጋዴ ወይም ሻጭ ሁል ጊዜ ተጠቃሚ፤ ሸማችና ገዥ ደግሞ ሁልጊዜ ተጎጅ ለመሆን የተስማሙበት ያልተጻፈ ህግ አለ” የሚል ነው። ይሕም ለዘመናት በሕዝቡ ልቦና ውስጥ ሰርጾ የኖረ እምቢ ማለትን የማያውቅ፣ ጭቆናን የተላመደ፣ ተገዥነትን የሚያወድስ መጥፎ ባህል መሆኑን በበኩሌ በጥናት ጭምር አረጋግጫለሁ! ይህን ለማለት ያስቻለኝን መሞገቻ አመክንዮ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ እስኪ። ልብ በሉ፤ በእኛ አገር ሻጩ ወይም ነጋዴው በምክንያትም ያለምክንያትም በየጊዜው እንደፈለገ ዋጋ መጨመር ይችላል።
ምክንያቱም የገንዘብ እንጅ የወገን ፍቅር የሌላቸው ስግብግብ ነጋዴዎች የአስር ብሩን ዕቃ በአስራ አምስት ብር ሲሸጡልን ዝም እንላለን፣ ትንሽ ቆይተው ሃያ ብር ሲያደርጉትም ዝም ብለን እንገዛቸዋለን። በዚህ የልብ ልብ የተሰማቸው ሻጮቻችንም ከቀናት ልዩነት በኋላ “መቶ ብር ገብቷል፣ ከገዛህ ግዛ ካልፈለክ ተወው” ማለት ይጀምራሉ። እነርሱ ምን ያድርጉ፣ ዝም ብሎ የሚገዛ(ላ)ቸው ሲያገኙ እንዴት እንደፈለጉ አይሆኑ? ምክንያቱም የፈለገውን ቢያደርግ “እምቢ” የሚለው ገዥ የለማ! ይህ ነው ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ ከመጣው ከአሳሳቢው የኑሮ ውድነት ጀርባ ያለው ያልተነቃበት መንስኤ።
በበኩሌ በኢትዮጵያውነቴ አብዝቼ የምደሰትና የምኮራ ሰው ነኝ። ነገር ግን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነታችን ከመውደድ ባሻገር ያሉብን መጥፎ ልማዶችና ባህሎች ማሻሻልና መቅረፍም እጅጉን አስፈላጊና ለአገራችንና ለራሳችን የበለጠ ጠቃሚ መሆኑንም አጥብቄ አምናለሁ። ኢትዮጵያውያን ካሉብን ድክመቶችና ተሃድሶ ከሚያስፈልጋቸው ባህሎቻችን ውስጥም አንዱና ዋነኛው ይኸው ሰዎች እንደፈለጉ እንዲሆኑብን የመፍቀድ አባዜ ነው። ይህም ከፖለቲካው አልፎ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ኑሯችን ውስጥም ስር ሰዶ ከባድ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል።
ስለሆነም በከፊልም ቢሆን ራሱ የፈጠረውንና እያባባሰው የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል ሕብረተሰቡ ከዚህ ጭቆና ታጋሽነትና አንባገነን ፈልፋይነት ልማዱ ተላቆ የአስተሳሰብና የባህል ለውጥ ማምጣትና የባህል አብዮት ማካሄድ ችግሩን ለመፍታት ዓይነተኛ መንገድ መሆኑ ይሰማኛል። አለበለዚያ “እሽ ይበልጣል ከሺ” የሚለው አባባል ለእግዜሩ ታዞ ገነት ለመግባት እንጂ ዳቦ ይዞ ቤት ለመግባት አያስችልምና እሽን እንጂ እምቢን የማያውቀው የህዝባችን ባህል ባለበት የሚቀጥል ከሆነ እኛው ራሳችን በምንፈጥራቸው የነጋዴ ፈርኦኖች ከዚህም የባሰ የኑሮ ውድነት መጋፈጣችን የማይቀር ይሆናል።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2015 ዓም