የቴክኖሎጂው በረከተ መርገምነት፤
ካሁን ቀደም በዚሁ አንጋፋ ጋዜጣ ላይ ለንባብ ካበቃኋቸው በርካታ ጽሑፎቼ መካከል “ከድምጽ በማይተናነስ ፍጥነት” እየተጣደፈ ስለሚገሰግሰውና እንኳን “ተራ ተጠቃሚ” የሰው ዝርያዎችን ቀርቶ “ራሳቸው የቴክኖሎጂዎቹ ፈላስፎችና ወጣኞች” ሳይቀሩ ከኋላው “ኩስ ኩስ” እያሉ ስለሚከተሉት የዘመነ ቴክኖሎጂ ባህርያት ደጋግሜ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። ዘመኑ የቴክኖሎጂ ስለመሆኑ፣ ከዘመን መኳረፍ ስለማይቻልና ስለማይሞከረም የቴክኖሎጂውን አሰስ ገሰስ ወደንም ይሁን ተገደን ለማጋበስ “አሜን!” ብለን እንደገበርንለትም ማሳያዎችን እያጣቀስኩ ሞግቻለሁ።
የቴክኖሎጂው ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች ሕይወ ታችንን እንደምን እንዳቀለሉት ጫን ብሎ መዘርዘሩ ግን “ሃሳቡንም ሆነ ሃሳብ አቅራቢውን” ግምት ላይ ስለሚጥል እንዲያው በደፈናው “በረከቱን” ቆጥረን የምንዘልቀው አይደለም፤ ማለቱ ይበጃል። ሁላችንም በቀላል ልንረዳው በምንችለው ማሳያ እናመላክት ከተባለ ግን ሺህ ምንተ ሺህ ጉዳዮችን የምንከውንበት የእጅ ስልካችን (ሞባይል) አገልግሎት ላይ ባልዋለባቸው ዓመታትና ከዚያ በፊት እንዴት እንደኖርን በንጽጽሮሽ ማስተያየቱ በቂ ሊሆን ይችላል። ያውም ሠላሳ ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ።
አይበለውና በሌሊትና በቀን በእጃችን ላይ የምናሽሞነሙናት የእጅ ስልካችን ወይንም ኮምፒው ተሮቻችን አገልግሎታቸው አብቅቶ ይቁሙና ወደ ጥንቱ ሕይወት ተመለሱ ብንባልና ቢፈረድብን ምን እንደምንመልስ ለመተንበይ ያዳግታል። የአብዛኞቻችን መልስ ሊሆን ይችላል ብለን የምንገምተው ግን “የሰይጣን ጆሮ ይደፈን” የሚለው ብርቱ እርግማን ነው።
ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ከሌጣ እስከ ውስብስብ ጉዳዮችን ለመከወን በምድርና በህዋ ላይ ተልእኮ የተሰጣቸው ዘመን ወለድ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዓለማችንን ከጠባብ መንደርነት ወደ ጣታችን አንደርድረው አቃርበውልናል። በየዕለቱ “ዓለምና አገራችን እንዴት ሰነበቱ” በማለት አብዛኞቻችን የእጅ ስልካችንን ወይንም ኮምፒውተራችንን በጣታችን ሳንደነቋቁል ከዋልን “ባዶነት ወይንም የውስጥ ርሃብ” እየተሰማን “ሱሱ” ፋታ ስለማይሰጠን ጣታችንን ሰብስበን የማዋል ፈተናውን ለመቋቋም ሳንቸገር የሚቀር አይመስለንም።
የቴክኖሎጂው ጠቀሜታና “በረከት” ከዚህም በላይ ብዙ የሚሰበክለትና የሚዘመርለት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ “በእርግማን” የመሰልናቸው ህፀጾቹም ተነቅሰው ይብራሩ ቢባል ዘርዝሮ ለመጨረስ በእጅጉ ይፈትናል። በአጭሩ ዘመንኛው ቴክኖሎጂ ከግል እስከ ቤተሰብ፣ ከማሕበረሰብ እስከ አገር፣ አልፎም እስከ ዓለም ዳርቻ ሕይወትን ማቅለል ብቻ ሳይሆን ያቀለለውን ሕይወት ለአደጋ አሳልፎ እየሰጠ እንዳለም በብዙ ማሳያዎች ማመላከት ይቻላል።
በዚሁ በቴክኖሎጂ “ትሩፋት” አማካይነት ቤተሰባዊ ሕይወት እየተሸረሸረ በመሄድ ላይ ነው። ማሕበረሰብ በማይረቡ የውሸትና ኢሥነምግባራዊ በሆኑ በኢንፎርሜሽኖችና በገለባ እውቀቶችና ርኩሰቶች ወጀብ እየተላጋና እየተናጠ አሳሩን በመብላት ላይ ይገኛል። በዚሁ በእኛው ቀዬ በውሸት በተፈበረኩ መረጃዎች ሕዝባችን ቁም ስቅሉን ሲያይ መዋሉ አይጠፋንም። በተለይም አገርና ትውልዱ “ከወረቀት ፀጋ” እየራቀ፣ በቴክኖሎጂው ግኝቶች አውሎ ነፋስ እየተላጋ መንሳፈፍን ስለመረጠ በአኗኗራችንና በጋራ ጉዳዮቻችን ሁሉ ለወረቀት አገልግሎት ጥዩፍ ሆነን ቴክኖሎጂውን የሙጥኝ ወደማለቱ ተበረታተናል።
በቡሃ ላይ ቆረቆር፤
የዘርፉ ባለሙያዎች ጥናት እንደሚጠቁመው በተለይም አብዛኛው የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ እውቀትንና ጥበብን ሲቀዳ የኖረው ከመጻሕፍት ይልቅ በቃል ሲወራረዱ ከመጡ ምንጮች ነው። “ፊርማና ወረቀት ጠፊ ነው ተቀዳጅ፤ መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ” እየተባባልን መኖራችንን ብናስታውስ ሃሳባችንን ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል። ስለዚህም ከሥነ ጽሐፍ ሀብት ይልቅ “የሥነ ቃል” እሴቶቻችን ይበልጥ ዋጋ ነበራቸው ማለቱ ያስማማ ይመስለናል።
በአግባቡና በሚፈለገው ደረጃ ሕዝባችን የንባብ ባህሉ ተጠናክሮ ወላጆችም ሆንን ልጆቻችን አፕታይታችን አድጎ “የወረቀት ፍቅራችን ሳይበረታ” በፊት ቴክኖሎጂው እንደ ማዕበል ከተፍ ስላለብን “ልጓሙን ይዘን” ልንገራው አልቻልንም። የሽምጥ ግልቢያው ከእኛ ሩጫ ስለፈጠነም እነሆ ዛሬ የደረስንበት ግልብ አጠቃቀም ላይ ለመድረስ ግድ ብሎናል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዘመናዊ እናቶች ሕጻናት ልጆቻቸውን ቀድመው ከማቀፍ ይልቅ ሞባይላቸውን ፈጥነው በማንሳት “እሹሩሩ” ማለትን ሲቀናቸው እያስተዋልን ነው። ጎልማሶችና አረጋውያን አበውና እመውም ሳይቀሩ “የእጅ ስልካቸው” ከአጠገባቸው እንዳይርቅ የሚከታተሉት በዐይነ ቁራኛ እስከመሆን ተደርሷል። የወጣቶቻችን የቴክኖሎጂ ፍቅርና ቁርኝትማ ጦዞ የከረረ ስለመሆኑ ማናችንም የምንመ ሰክረው ነው።
የኅትመት ውጤቶች የንባብ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ አሽቆልቁሎ “ተረት” ወደ መሆን ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ስጋቱ በርትቶብናል። የየቤቶቻችን ታዳጊዎችና ወጣቶች “አንብቡ፣ የመጻሕፍት ፍቅር ይደርባችሁ” ብሎ መምከርም የሚያስደስት ሳይሆን “ከወላጆች ጋር የሚያቃቅር ምክር” እስከ መሆን ደርሷል። ገና የንባብ ጉልበታችን ሳይበረታና ከወረቀት ጋር ያለን ቁርኝት ከዳዴ እንፉቅቅ ሳይላቀቅ ዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ እያባበለ “እጅ ወደ ላይ” በማለት ማርኮ አስገብሮናል። ስለዚህም ነው “በቡሃ ላይ ቆረቆር” የሚለውን ብሂል ለመጠቀም የተገደድነው።
ጥናቱን ይስጥሽ አገሬ፤
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “አሰራራችንን ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ እናደርጋለን” የሚል መፈክር በብዙ መንግሥታዊና የግል ተቋማት ሲነገር እያደመጥን ነው። ይህንን “አዋጅ” ቀድሞ በማስተጋባት “እዩልኝ! ስሙልኝ!” በማለት ይፋ ያደረገው የአገራችን ኩራት የሆነው አየር መንገዳችን መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል። አየር መንገዳችን “ከወረቀት ጋር ተፋትቻለሁ” የሚለውን የጸና አቋሙን ያስተዋወቀው እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም ነበር። ይህንን አቋሙን በወቅቱ የገለጸበት መንገድ ባያቀያይመንም አስኮርፎን እንደነበር እውነቱን ባንናገር ህሊናችን ይወቅሰናል።
የሚሆንለት ከሆነ “አየር መንገዳችን አሠራሩን ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ ማድረግ” መብቱም ፈቃዱም መሆኑን አንክድም። በፍጥነት ከሚዘምነው ዓለም ጋር መጎዳኘቱ ግድ ስላለው እንደሆነም አይጠፋንም። ነገር ግን “ወደ ወረቀት አልባ አገልግሎት” መግባቱን በወቅቱ ይፋ ያደረገው የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች አንድ ላይ ተሰብስበው “የወረቀት ክምር በእሳት እያቀጣጠሉ” በማጨብጨብ ጭምር ነበር። “አገሬ ሆይ! ጥናቱን ይስጥሽ!” ብለን ለመቆዘም ምክንያት የሆነን ይሄው ድርጊት ነበር።
ይህንን “ተቀባይነት የሌለው ድርጊት” እንደ ዘርፉ ባለሙያ በቁዘማ ብቻ ማለፉን ስላልወደድን በወቅቱ ሰፊ ሽፋን በነበረው አንድ አገራዊ ጋዜጣ ላይ ስህተት መሆኑን ደፈር ብለን ለሕዝብ አሳውቀናል። ቴክኖሎጂው ለማክበር ሲባልም “ወረቀትን የኃጢያት ማስተሰረያ” ማድረጉ ተገቢነት እንደሌለውም በየሚዲያው ሳንታክት አውግዘን ጮኸናል። አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ ለጅብ እንደሚወረወሩት የቢሾፍቱ ፈረሶች “ወረቀትን በእሳት እያቃጠሉ” ቴክኖሎጂን ማሞገስ ምን የሚሉት አመለካከት እንደሆነ ሊገባን አልቻለም ነበር፤ ፈጻሚዎቹ ራሳቸውም ገብቷቸው ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ያዳግታል።
“ምንትስ በቀደደው አጥር ምንትስ ይገባል” እንዲል ብሂላችን፤ አየር መንገዳችን በቀደደው መንገድ ብዙ መንግሥታዊ ተቋማት እየተቀባበሉ ወደ “ወረቀት አልባ አገልግሎት” ገብተናል ማለትን ፋሽን አድርገውታል። እ.ኤ.አ በ2020 መስከረም ወር ላይ “ወረቀት አልባ የጉምሩክ አገልግሎት ተጀመረ” ብሎ የተከተለው የገቢዎች ሚኒስቴር መ/ቤት ነበር። “ይህንን የመሰሉ ዝመናዎች በየዘርፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል” የሚለው መንግሥታዊ ውሳኔ የተሰማውም “የወረቀት ነባር አገልግሎት ፊት በተነሳበት” በዚያው ዕለት ነበር።
“የመረጃ አስተዳደርና ልውውጥ ሥርዓት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማዘመን፤ በጉምሩክ ሥርዓት ሂደት ተጠያቂነት እና ግልጸኝነትን በመፍጠር የሰነድ ማጭበርበርን በማስቀረት ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ” መታመኑን አንቃወምም። እርግጥ ነው፤ ከዘመን ጋር መዘመን ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር መሆኑ አይጠፋንም። የቴክኖሎጂ ፀር እንደሆነንም መታሰብ አይገባውም።
“አሰራራችንን በቴክኖሎጂ እናዘምናለን” ማለት እየተቻለ “ወረቀትን ማውገዝ” ምን ይባላል? ምንስ ረብ ይኖረዋል? ምኞቱን ይሁን ብለን በአመኔታ ብንቀበል እንኳን በርግጡ ወረቀትን ሙሉ ለሙሉ ከአገልግሎት ውጭ ለማድረግ ተቋማቱ ተሳክቶላቸው ግባቸውን መትተዋል? አየር መንገዳችንም ሆነ የጉምሩክ ተቋም “ምኞታቸው ግቡን መትቶ” የወረቀት አገልግሎት አሰጣጣቸው ተጠራርጎ ጠፍቶ ከሆነ ቆመን እናጨበጭብላቸዋለን። እንደ ባህል የለመድነውን የኃይል መቆራረጥ ተቋቁመው በአሸናፊነት ተወጥተው ከሆነም በእልልታ እናደንቃቸዋለን።
የእነዚህ ሁለት ተቋማት “የወረቀት አልባ አገልግሎት” ምኞት ገና መሬት መርገጡ ሳይረጋገጥ የተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከበሩ አፈ ጉባዔው አማካይነት “የምክር ቤቱ ሥራዎች ወረቀት አልባ እንዲሆኑ” መወሰኑን የሰማነው ከቀናት በፊት ነው። ሙግታችንን ደግምን ጠንከር በማድረግ እንጫነውና “ተቋማቸውን በቴክኖሎጂ ማዘመናቸውን” ብቻ መገለጽ እየቻሉ ስለምን በወረቀት ላይ ይፈርዳሉ? የፈለገ ሥልጣኔ ማማ ላይ ደረስኩ እንኳን አሰኝቶ ቢያስፎክር የሰው ልጅ ከወረቀት አገልግሎት “ሙሉ ለሙሉ” አርነት ወጥቶ የቴክኖሎጂው ምርኮኛ መሆን ይቻለዋልን?
ያውም በኢትዮጵያ ዐውድ ገና ከወረቀትና ከንባብ ጋር ተያይዞ ብዙ መሠራት በሚገባው አገር “የወረቀትን ጥንብ እርኩስ” ማውጣት ተገቢ ነው የሚል እምነት ላይ እንዴት ሊደረስ ቻለ? ይህንን መሰል አገራዊ ውሳኔ የሚሰሙ ልጆቻችን ነገ ጠዋት “መጽሐፍ አንብቡ! ጻፉ!” እያልን ስንመክራቸው ምን ሊመልሱ ይችላሉ። “እናንተ ወረቀት አልባ አገልግሎት ለመስጠት እየፎከራችሁ እኛን ለምን ወደ ወረቀት ትገፉናላችሁ?” በማለት አይታዘቡንም፤ በእምቢታቸውስ አያሳፍሩንም? እንዲህ ዓይቱን መግለጫ የሚሰጡን የሕዝብ አገልጋዮችስ ነገ ጠዋት “ሕዝቤ ከንባብ ተፋታ፣ ለኅትመት ውጤቶች ባዕድ ሆነ” ብለው ሮሮ ቢያሰሙ ማን “አባ ከና” ብሎ ያደምጣቸዋል?
ይህ ጸሐፊ የዛሬ 20 ዓመታት ግድም አሜሪካን አገር በትምህርት ላይ በነበረበት ወቅት ልክ እንደ ዛሬው እንደኛ ከአምስት ዓመታት በኋላ በመላው የአሜሪካ ግዛቶች ሙሉ ለሙሉ ወደ “ወረቀት አልባ አገልግሎት” እንደሚገቡ ፎክረውና አስፎክረው ነበር። እንኳን ከአምስት ዓመት በኋላ ቀርቶ ዛሬም ድረስ ከወረቀት ጋር ፍቺ መፈጸም አልቻሉም። አልፎም ተርፎ የቴክኖሎጂው ጥፋት አገራዊ እንግልቱን ስላበረታባቸው “back to paper!” ወደሚል እንቅስቃሴ ለመግባት ሙከራ መደረጉን ጸሐፊው ያስታውሳል።
ይህ ጸሐፊ በፍጹም ከቴክኖሎጂ ጋር ጠብ እንደሌለው አስረግጦ መናገር ይፈልጋል። የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ መልዕክት “ላይሆንልን ብቻ ሳይሆን፤ ቢሆንልን እንኳን የወረቀትን አገልግሎት አናንኳስስ” ካስፈለገ ቴክኖሎጂውን ደመቅ አድርጎ ማሞገሱ ባይከፋም የወረቀትን ዕድሜ ጠገብ አገልግሎትን በፍጹም ልንዘነጋ አይገባም። ትውልዳችን “እንኳንም ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ” እንዲሉ የወረቀትን አገልግሎት እንኳንስ አካኪሴን ቀርቶ “ከኅትመት መጻሕፍት ጋር ተቆራኙ!” እያልን እየወተወትንም ሰሚ እየጠፋ ስለሆነ ጉዳዩ በጥልቅ ይፈተሽ ለማለት ነው።
ወረቀት ከሰው ልጅ ጋር ያለው የወዳጅነት ቁርኝት ጠንካራ መሆኑ ብቻም ሳይሆን የተሸከመው ፋይዳም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ወረቀትን ከአመራረቱ የጎንዮሽ ጉዳት ጋር እያስተያዩ ወይንም የባዮ ዳይቨርሲቲን መሳሳት እንደ ምክንያት እየቆጠሩ፣ አለያም የካርቦን ዳዮክሳይድን ልቀት ሰበብ እያደረጉ “ወረቀትን ከደን ጭፍጨፋ ጋር በማስተያየት” የወረቀት አገልግሎትን ዐይንህ ላፈር ማለት ተገቢ አይደለም፤ ተመስጋኝም አያደርግም። በቴክኖሎጂ መዘመን ግድ ነው? – አዎን ግድ ነው። የወረቀት አገልግሎትስ መቀጠል አለበት? – አዎን ሊቀጥል ይገባል። እናስ በየተቋማቱ አመለካከታችንን እንዴት እናስተካክል ከተባለ “ወረቀትን በክብሩ፤ ቴክኖሎጂንም በመስመሩ እያሞገሱ” አገልግሎትን መፈጸም ይችላል። ጉዳዩ “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ!” እንዳይሆንም አገሬ ልትጠነቀቅ ይገባል። ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን መስክረም 14 ቀን 2015 ዓም