የስፖርቱ ዓለም የዘወትር ስጋትና አስከፊ ገጽታ አበረታች ንጥረነገሮችን ተጠቅሞ ውድድሮች ላይ ከመካፈል ጋር ይያያዛል፡፡ ይህ በአቋራጭ መንገድ በስፖርቱ ውጤታማ ለመሆን የሚደረግ ህገወጥ ተግባር ደግሞ እአአ 2013-2019 በመላው ዓለም ያለው እየጨመረ መምጣቱን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከኦሊምፒክ ስፖርቶች መካከል አበረታች ንጥረነገሮችን ተጠቅሞ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ቀዳሚ ከሆኑት ስፖርቶች መካከል አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ የክብደት ማንሳት፣ እግር ኳስ እና ራግቢ ውድድሮች ቀዳሚ ናቸው፡፡ ሩሲያ፣ ጣሊያን፣ ህንድ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም እና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ እንደ አገር ይህ ስጋት በተለየ የሚታይባቸው ናቸው፡፡
አትሌቲክስ በዚህ ረገድ የጎላ አበረታች ንጥረነገር ተጠቃሚነት የሚታይበት ስፖርት እንደመሆኑ፤ በስፖርቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ያላቸው አገራት በዓለም አቀፉ የጸረ አበረታች ንጥረነገሮች ኤጀንሲ የትኩረት ማዕከል ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሁሉ ልዩ ክትትል የሚደረግባት አገር ናት፡፡ በእርግጥም የአበረታች ንጥረነገሮቹ ተጠቃሚነት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያም እየታየ ሲሆን፤ በ2010 ዓ.ም ስድስት አትሌቶች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለቅጣት መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን መረጃ ያሳያል፡፡ ከ2011 ዓ.ም-2014 ዓ.ም ባሉት እያንዳንዱ ዓመታት ደግሞ ሶስት ሶስት አትሌቶች ተጠቃሚ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለስልጣኑ የአበረታች ንጥረነገሮች መመርመሪያ ቤተሙከራ ለማቋቋም እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥጥር ከማድረግ አኳያ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ለ4ኛ ጊዜ ባካሄደው ጉባኤው አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የስፖርት አበረታች ንጥረነገር ተጠቃሚ መሆናቸው የተጠረጠሩ አትሌቶችን ናሙና ወደ ሌሎች አገራት በመላክ ምርመራ እንደሚደረግ ይታወቃል፡፡ ይህም አገሪቷ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እንድታወጣ ያደርጋል። በመሆኑም በአገር ውስጥ ቤተሙከራውን በመክፈት ወጪውን ለማስቀረትና ሌሎች አገራትንም ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
ቤተሙከራውን በሚመለከትም አስቀድሞ ጥናቱ የተሰራ መሆኑን በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ማዕከሉን ዕውን ለማድረግ አስፈላጊ ነገሮች ምንድን ናቸው የሚለውን፣ የባለሙያ (የሰው ኃይል)፣ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን እንዲሁም እንደ አገር ቤተሙከራውን ለማቋቋም የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለው ላይ ልየታ ተደርጓል፡፡ ጥናቱ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትውት ጋር በትብብር የተሰራ ሲሆን፤ ሰነዱን የመጨረሻውን ቅርጽ ማስያዝ ብቻ ይቀረዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ደግሞ ቀጣይ ስራዎችን ወደማከናወን የሚገባ መሆኑን እና በዓለም አቀፉ ተቋም በኩልም የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚደረግለት ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በስፖርት ጸረ አበረታች ንጥረነገሮች ቁጥጥር ላይ መልካም የሚባል ስራ እያከናወነች መሆኑን የገለጹት ደግሞ በተንቀሳቃሽ ምስል ጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የዓለም አትሌቲክስ ኢንቲግሪቲ ዩኒቲ ዳይሬክተር ቶማስ ካፕዴቪሌ ናቸው፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ ላይ የስፖርት አበረታች ቅመም ቤተሙከራ እንዲኖር እንደሚደግፉና ለዚህ የሚረዳውን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ እንዲሁም በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡
ቁጥጥርን በሚመለከትም ከተጠቃሚዎቹ ባሻገር አበረታች ንጥረነገሮችን ለስፖርተኛው የሚያቀርቡና ከአትሌቱ ኋላ በመሆን በድብቅ የሚሰሩ አካላትን በመቆጣጠር ረገድም ኤጀንሲው የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ጉዳዩ ከወንጀል ጋር የተያያዘ በመሆኑ ባለስልጣኑ ከፖሊስ፣ ከፍትህ ሚኒስትር እንዲሁም ከመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ላይ የሚሰራ ቡድን እየተዋቀረ ሲሆን፤ በቀጣይም ይህንን አጠናክሮ ለመስራት ጥረት ይደረጋል፡፡ አትሌቶች ንጥረነገሩን ተጠቅመው ሲገኙ ከጀርባቸው ያለውን ምንጭ ለማግኘት ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ከአስተዳደራዊ ቅጣት ባለፈ በወንጀል ህጉም ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ባለፉት አምስት ዓመታት የተለያዩ ተግባራት ሲከናውን የቆየ ሲሆን፤ ይህም በአፍሪካ ደረጃ አበረታችና ለሌሎችም ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል በዓለም አቀፉ ተቋም ተመስክሮለታል፡፡ ባለስልጣኑ በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስፖርተኛው ድረስ የግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ በየክልሉ ወርዶ እንዲሰራበት አድርጓል። ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ጋር በመሆን በመደበኛ ስርዓተ ትምህርት እንዲሁም የስፖርት ስልጠና ማዕከላት ማንዋሎች ውስጥም ጉዳዩ እንዲካተትም ተደርጓል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2015 ዓ.ም