መስከረም ለኢትዮጵያውያን የተለየ ወር ነው፡፡ሜዳው ሸንተረሩ በአበባ ያጌጣል፤ አዲስ መንፈስ በሰው ልብ ውስጥ ይሰርጻል፡፡ መስከረምን ስናስብ ከአበቦች ውበትና መዓዛ ባሻገር በወሩ ውስጥ የሚከበሩ ልዩ ልዩ የአደባባይ በዓላት ልዩ መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡
ኢትዮጵያ በየአመቱ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል የአደባባይ በዓል የሆነው የመስቀል ደመራ አንዱ ነው። በዓሉ መስከረም 16 (ደመራ) እና 17 (መስቀል) የሚከበር ሲሆን፤ በ2006 በዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቧል።
በዚሁ ወር የሚከበረው ደመራ በዓል አጠቃላይ ምንነቱ፣ ዓላማና ፋይዳው፤ እንዲሁም ኃይማኖታዊ ትርጓሜው፤ ባህላዊ ገጽታውና እሴቱ ፤ ምን ይመስላል? ወሰኑስ? እንደሚከተለው እናያቸዋለን።
የበዓሉ አከባበር ታሪካዊ ዳራ
የመስቀል በዓል በባህላዊ እሴቶች (አለባበስ፣ አመጋገብ፣ አከባበር …) የታጀበ ኃይማኖታዊ ይዘት ያለው ነው፤ የክርስቶስ መስቀል በቁፋሮ ስለተገኘ እርሱን ለማመልከት የሚከበር፤ በዓል ነው።
የኢትዮጵያ ልዩነት
የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር ከሌሎች ቤተክርስቲያናት አከባበር ጋር ሲታይ፤
- በዓለ-መስቀሉ የምዕራብም፣ የምሥራቅም አብያተክርስቲያናት ለዚሁ መታሰቢያነት መስከረም 3 ቀን ሲያከብሩ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ማክበሯ፤
- ከኢትዮጵያ በስተቀር ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ፈልጋ ባገኘችበት መንገድ የሚያከብር አገር አለመኖሩ፤
- ንግሥት እሌኒ የክርስቶስን መስቀል ለማግኘት ደመራ ደምራ ስለነበርና ጭሱም ወደታች ወርዶ መስቀሉ ያለበትን ስፍራ (የተቀበረበትን ተራራ) በማመልከቱ (ተምሳሌትነቱ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ደመራ መደመሯ፤ እና የመሳሰሉት ለየት ያደርጉታል።
በዓሉ እና የየዘመናቱ መንግሥታት አቋም
በንግሥት እሌኒ
ንግሥት እሌኒ የክርስቶስን መስቀል ማግኘት ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ደመራን ትደምራለች።
በአፄ ዳዊት
ኃይማኖታዊ ማስረጃዎችን ስንመለከት ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት፣ ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ተቀመጠ።
አፄ ዳዊት ‹መስቀሌን በመስቀያ ስፍራ አስቀምጠው› የሚል መለኮታዊ ምሪትን በመስማታቸው ወደ ግሸን ማርያም ተወስዶ በዛ እንዲቀመጥ አደረጉ። ስለዚህም መስከረም 21 ቀን ግሸን ማርያም ላይ በዓሉ ይከበራል። (መምህራን ፋንታሁን) “ይህ ግማደ መስቀል በግሸን ማርያም ገዳም፣ በእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ሆኖ ኢትዮጵያን እየባረከ ይገኛል::”
በአጼ ምኒልክ
የመስቀል በዓል እስከ በ1879 በእንጦጦ ማርያምና ራጉኤል ቤተክርስቲያን፣ ከ1879 እስከ 1922 ደግሞ በአዲሱ ቤተ-መንግሥት ይካሄድ ነበር። በድምቀት የአደባባይ በዓል ሆኖ መከበር የጀመረው በ1898፣ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው። የበዓል ስነስርዓቱም በጃንሜዳ፣ ከዛም ከአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ፣ በስተደቡብ ወረድ ብሎ በሚገኘው ባዶ ስፍራ ላይ ይከናወን እንደነበረ የታሪክ ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
በንግሥት ዘውዲቱ
ከላይ በተጠቀሰው መንገድ በአዲሱ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ይካሄድ ነበር።
በቀዳማዊ አጼ ኃይሌሥላሴ
ንጉሡ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ከ1933 እስከ 1966 በእስጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያን ሲከበር ቢቆይም፣ ራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን “ለመስቀል ደመራ ማክበሪያ” ይሆን ዘንድ ከግል ርስታቸው በመክፈል በኋላ “መስቀል አደባባይ” የተባለውን ስፍራ ሰጡ። እስከ 1967ም ንጉሱ በሚገኙበት በዚያው መከበር ጀመረ።
በበዓሉ እለትም፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ይመጡና ጀርባቸውን ለራስ ብሩ ቤት ሰጥተው ይቀመጣሉ። ሜዳው ላይ ደመራው ይደመራል።
ክቡር ዘበኛ፣ ፖሊስ ሰራዊት፣ የባህር ኃይል እንዲሁም የአየር ኃይል ሰልፈኞች ያልፋሉ። ሰው የዛን እለት ነጭ በነጭ የሆነ የበዓል ልብሱን ለብሶ በጣም ልዩ የሆነ ስነ ስርዓትን ለማክበር ነው የሚመጣው። እንስሳት ሁሉ ለልዩ ትርኢት ይወጡ ነበር። ጃንሆይ መኩሪያ የሚባል አንበሳ ነበራቸው። […] ያጓራል።
[…] ጃንሆይ ወደ ደመራ ማብሪያው ስፍራ ሲመጡ በጭብጨባ እና በእልልታ ምድር ነው የምትርደው… ሰልፉ በእሳቸው ፊት ካለፈ፤ ደመራውም በቤተክህነት አባቶች ከተባረከና የጸሎት ስነስርዕት ከተካሄደ በኋላ ይለኮሳል።
በደርግ
በ1967 ደርግ ወደ ሥልጣን ሲወጣ በጃንሆይ ዘመነ መንግሥት በዓሉ ይከናወንበት የነበረውን የመስቀል አደባባይ ስያሜ ወደ አብዮት አደባባይነት ተቀየረ። የደመራው ሥርዓትም ከአደባባዩ ተነጥሎ ቀድሞ ይከበርበት ወደነበረበት፣ ወደ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እንዲመለስ ሆነ።
በኢህአዴግ
ከ1983 ወዲህ በብጹዕ አቡነ ጳውሎስና በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መካከል በተደረገ ስምምነት ወደ ነበረበት ተመልሶ በአሁኑ መስቀል አደባባይ ላይ እንዲከበር ተወሰነ።
የበዓሉ መከበር ዐቢይ ምክንያት፣ አከባበሩ፣ እና የክብረ-በዓሉ ወሰን
ዐቢይ ምክንያት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩል ለበዓሉ መከበር ሁለት ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፤ እነሱም፡-
- በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንግሥት እሌኒ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ለማውጣት ያደረገችውን ጥረት እና በመጨረሻም መስቀሉ መገኘቱን በማስታወስ መሆኑ፤ እንዲሁም፣
- በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ክርስቶሰ የተሰቀለበትን ቀኝ ግማደ መስቀል እና የተለያዩ ነዋየ ቅዱሳት ከግብፅ አሌክሳንድሪያ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን በማስመልከት መሆኑ፤ናቸው።
አከባበሩ
ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ የሠራቸው የተለያዩ ዜማዎች አሉ። ዜማዎቹ በካህናት አማካኝነት በተለያየ ሁኔታ ይቀርባሉ። በዓሉን የሚያመለክተው ወረብ ይወረባል። የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ሊቃውንቱን ተከትለው እንደዚሁ ለእለቱ የሚገባውን ያሬዳዊ ዜማ ያቀርባሉ። በአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የማህበረ ቅዱሳን መዘምራን፣ መስማት የተሳናቸው በምልክት ቋንቋ እንዲሁም የፖሊስ ማርሽ ባንድ ዝማሬና ዜማዎችን ያቀርባሉ። አባት አርበኞች በትርዒት ይሳተፋሉ። በመጨረሻም በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን አማካኝነት ንግሥት እሌኒ እንዴት አድርጋ መስቀሉን እንዳገኘችው የሚያሳይ ልዩ ትርዒት ይቀርባል።
በነገሥታቱ ዘመን መሪዎች በበዓሉ ላይ ይገኙ ነበረ። ከበዓሉ የሚቀር ንጉሥ አልነበረም። በተለየ ሁኔታ ነገሥታቱ ሲመጡ ክብሩም እጅግ የተለየ ነውና በዓሉም በተለየ ስሜት ይከበር ነበር። ነገሥታቱ ደግሞ ከበዓሉ በኋላ በማግስቱ ግብር ያገቡና ሕዝቡን ያበሉ ነበረ።›› (ሊቀ መምህራን ፋንታሁን፣)
የአከባበሩ አካል የሆነው የደመራ አበራር ስነስርዓቱ (እዚህ ጋ የቅዱስ ያሬድን “ጢሱ ሰገደ” አገላለፅ ያስታውሷል) በአብዛኛው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በወሩ 17ኛ ቀን፣ ወይንም የበዓሉ ዕለት የሚከናወን ሲሆን፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በ16 ይበራል። በዓሉ ሲከበር ኃይማኖታዊውን ይዘት ጠብቆ እንዲሁም ከክረምት ጨለማ መገፈፍ እና ደፍርሶ ከነበረው ከውሃው መጥራት ጋር የመልካም ዘመን ተምሳሌትነት በማያያዝም ነው።
ወሰን
በዓሉ በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ይከበራል። በደቡብ፣ አማራ እና ሌሎች የተለያዩ ቦታዎች (ክልሎች)፤ እንዲሁም፣ በትግራይ ለየት ባለ መልኩ ይከበራል።
በዓሉ፣ በተለይ በጉራጌ አካባቢ (ለምሳሌ ጉራጌ ዞን፣ እዣ ወረዳ እና ሌሎችም) በደማቁ ይከበራል። ከትውልድ ስፍራቸው ውጭ የሚኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተወላጆች ወደ ቤተሰቦቻቸው በመጓዝ በዓሉን አብረው ያሳልፋሉ።
ከጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝም እና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ 500ሺህ የሚጠጉ የጉራጌ ተወላጆች በመስቀል እና አረፋ በዓላት ወቅት ወደ አካባቢው ይጎርፋሉ፡፡
(በሰሜን ኢትዮጵያ፣ አዲግራትን በመሳሰሉት አካባቢዎች በመስቀል በዓል ለቤተሰብ ጥየቃ ወደ አገር ቤት መግባት ባህል መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። መቀሌ አካባቢ፣ ጮማአ በተባለ ተራራ ላይ ‘ካሁን በፊት ግማደ መስቀሉ በአጼ ዳዊት ጊዜ ሲመጣ ያረፈበት ነው’ በሚል፣ ከጥንት ጀምሮ እየተከበረ የመጣ መሆኑ በመታመኑ ምክንያት 52 ሜትር መስቀል በግለሰብ ደረጃ ተተክሏል።)
በዓሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ወሎ እና ጎንደር፤ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ባሌና አካባቢው፣ እንደ ምን ግዜውም፣ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ የሚውል ሲሆን፤ የዘንድሮውም በተመሳሳይ እንደሚከበር በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እየተገለፀ ይገኛል። በባህር ማዶም ያው ነው።
በስደት (ለምሳሌ ጅቡቲ) የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ ፈተናዎች ጋር እየታገሉም ቢሆን ደመራ ደምረው በዓሉን ከማክበር ተቆጥበው አያውቁም። ዘንድሮም ይህንኑ እንደሚያደርጉ ከማህበራዊ ሚዲያ መልእክቶቻቸው መገንዘብ ተችሏል። በዩጋንዳ መዲና ካምፓላም እንዲሁ፣ በየአመቱ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር በዶቸቬሌ ፕሮግራም መግለፁ ይታወቃል። በጀርመን፣ ፍራንክፈርትም እንዲሁ።
መስከረም እና አውዳመታት
(“መስከረም በአበባው፣ ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃል”)
በዚሁ፣ በአበባው (ወርኃ አደይ ወርኃ ጽጌ በመሆኑ) ብቻ ሳይሆን በክብረ በዓላትም (“ርዕሰ ዓውደ ዓመት” እና “የዘመን መለወጫ” በመሆኑም ጭምር) በሚታወቀው፤ ኢትዮጵያዊያን በርዕሰ በዓልነት ታላቅ ማዕዘን ላይ ባስቀመጡት ወርኃ መስከረም በርካታ ዓመት መጣ በዓላት በየክልሎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ ከመስቀል በተጨማሪ “እሬቻ”፣ “ጊፋታ”፣ “ያሆዴ” … እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ከእሬቻ እንጀምር፤
እሬቻ
የኦሮሞ ሕዝብ ለፈጣሪ ዋቃ (WAKKA) ምስጋና እሚያቀርብባቸው ቱባ ባህሎችና እሴቶች መካከል አንዱ በየአመቱ መስከረም 21 ቀን በሆራ አርሰዴ የሚከበረው የእሬቻ በዓል ነው። ዘንድሮ ለሚከበረው ለዚሁ በዓል ድምቀት፣ ከፀጥታ አጠባበቅ ጀምሮ አስፈላጊው ዝግጅት የተደረገ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶችም በበዓሉ ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከትናንት በስቲያ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የቢሾፍቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱልሰላም መሐመድ እንደገለፁት በዓሉን ለመቀበል በሁሉም ዘርፍ በቂ ዝግጅት ተደርጓል። ሕብረተሰቡን በማስተባበር ከተማውን ውብና ጽዱ የማድረግ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። ሰላምና ፀጥታን በተመለከተ የፎሌና የጸጥታ አካላት በቂ ዝግጅት እንዳለ ሆኖ ሕዝቡም ሰላሙን ለማስጠበቅ የተለመደውንና አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ሲሆን፤ ሕብረተሰቡን ለማገዝም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ ይገኛል።
ጊፋታ
ጊፋታ በወላይታ የሚካሄድ ክብረ በዓል ነው፡፡ጊፋታ የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡የበዓሉን ዋዜማ የሚያበስሩ/ገበያ/ ቀናቶች መካከል የመጨረሻው ሰኞ /Saggaa/ ከዛሬ ጀምሮ ጎሻ /Gooshsha/ ገበያዎች እስከ ጊፋታ እርድ ዕለት ድርስ ከጠዋት ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች በከፍተኛ ሁኔታ የንግድ ግብይት ይካሄዳል።
በጊፋታው ዋዜማ በሚውለው ሳምንት /Goshsho/ ገበያዎች፣ በተለይም የሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ ቀናት (ከዓርብ እስከ እሁድ) የተለያዩ ሥራዎች የሚሰሩበት ዕለት ነው። koosetaa Hamussa /Shaagaa/ ሐሙስ፣ Sudhdh”a arbbaa/ bizzaa /ዓርብ/፣ Baacciraa qeeraa /ቅዳሜ/፣ Shuha Woggaa /እሁድ/ የጊፋታ እርድ ዕለት – ለወላይታ ብሔር የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ዕለትና ታላቅ የደስታና የፍቅር ዕለት ነው።
ያሆዴ
መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም በልዩ ድምቀት የሚከበረው፣ የሀዲያ የዘመን መለወጫ የሆነው የ”ያሆዴ” በዓልንም ከዚሁ ጋር አያይዞ መረዳትና የመስከረምን ወር ልዩ ገጽታና ስጦታ የበለጠ መረዳት ይቻላል። (በአሁኑ ሰዓት፣ ይህ በዓል የክልሉ የስራ ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት፣ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር እየተገለፀ፤ ሰፊ የህዝብ ግንኙነት ስራ እየተሰራ ይገኛል።)
በመጨረሻም
(በገጠሩ ከዘመን መለወጫ በዓል በኋላ የመስቀል በዓል እስኪደርስ ድረስ ወጣት ወንድና ሴቶች በግጥም መልክ እየተቀባበሉ ከሚያዜሙት አንዱ)፤
እዩት እዝያ ላይ የግራሩን መንታ፣
አይንሽ ያበራል እንደ ሎሚታ
ከሎሚታውስ ያንቺ አይን ይበልጣል፣
እንደመስታወት ከሩቅ ያበራል።
ካንቺማ ወዳጅ ይሻላል ትል፣
አጥር ላይ ዘምቶ ያገለግል።
ካንቺማ ወዳጅ ይሻላል ዱባ፣
አጥር ላይ ዘምቶ ያደምቃል አንባ።
እዮሃ እዮሃ አደራ ደመራ፣
አደራ መስቀሎ
ጥባ ጥባ ቶሎ!
ለመስከረም በዓላት እድምተኞች በሙሉ፣ መልካም በዓል!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2015 ዓ.ም