ፍትህን ሳይሆን የሴራ ተልዕኮን ተሸክሞ፤ እውነትን ሳይሆን ውሸትን አስቀድሞ፤ ሰላምን ሳይሆን ጦርነትን ምርጫው አድርጎ፤ ከባዕዳንና ከአገር ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብሮ፤ ወገኑን በወገኑ ላይ ነፍጥ እንዲያነሳ በማድረግ ኢትዮጵያም በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድትኖር የማድረግ ግብ ተሰጥቶት በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ጫካ የገባው አሸባሪው ትህነግ፤ ለዚህ ግቡ መሳካት የሚያስችለው ትልቁ ኃይሉ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ነበር። ከጫካ ተነስቶ በ1983 ለመንግስትነት እንዲበቃ ያደረገው ቁልፉ ምስጢርም ይሄው በራሱና በተባባሪዎቹ ተቀምሞ የሚቀርብ የሃሰት ወሬ፤ በተባባሪ አገሮችና ታሪካዊ ጠላቶች ሚዲያዎችና ተቋማት እየተራገበ በሚፈጥረው ሽብር ነበር። ዛሬም በእነ አሸባሪው ትህነግ ቤት ታሪክ ራሱን ይደግማል በሚል የቀን ቅዠት በተመሳሳይ መንገድና ስልት ይጓዝ ከጀመረ ውሎ አድሯል።
ይሄው ሃቅ፣ አሸባሪው ትህነግ “የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ” በሚል ስያሜ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ወደ ስራ እንዲገባ ያጸቀደውና አፈትልኮ የወጣበት ምስጢራዊ መረጃ ላይ “አንዱና ዋነኛው የውስጣችን ጥንካሬ፣ ውስጣዊ አቅማችንና የአሸናፊነት ስነልቦናን ከፍ የሚያደርጉና የሚያነቃቁ የዶክመንተሪ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። …በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያም ውጭ ለሚገኙ የትግል አጋሮቻችን እስከ መጨረሻ መዳረሻችን አብረውን እንዲጓዙ የሚያስችል የመረጃ ልውውጥና ፕሮፖጋንዳ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፤” በሚል በግልጽ ተመላክቷል።
ለዚህ ደግሞ ከባህር ማዶ ተቀምጦ በምናባዊ ምኞት በሚሰሩ የሰብዓዊ ተቋማት “ጥናቶች”ን እንደ ዋና ግብዓት በመጠቀም የሃሰት ፕሮፖጋንዳን ጠላት በሚሉት ሕዝብ ላይ ሽብር፣ ፍርሃትና የስነ ልቦና ጫና መፍጠሪያ ማድረግ ትልቁ ትኩረታቸው ነው። በመሆኑም ሽብር የሚያስፋፉ እና ሕዝብ በመንግሥት አቅም ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር የሚያደርጉ መረጃዎች በአገር ውስጥና በውጭ ሚዲያዎች በሙሉ ማዳረስ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን በዚሁ ምስጢራዊ ሰነድ ገልጸውታል። ለዚህም ባለቤቶቻቸው አዲስ አበባ የሚገኙ ሚዲያዎችና ዩቲዩብ ቻናሎች ከፍተኛ ድጋፍ ስለሚኖራቸው የመረጃና ፋይናንስ ድጋፋቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው በአጽንዖት ያሰፈሩት።
እርግጥ ነው፤ አሸባሪው ትህነግም ሆነ በውስጥም በውጭም ያሉ የሚዲያ አጋሮቻቸው መሰል ተግባር ሲያከናውኑ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም። በሰነድም በአቅጣጫም የታገዙ በርካታ መሰል የጥፋት አጀንዳዎችን በመቅረጽ በርካቶችን በሃሰት ፕሮፖጋንዳቸው እና በተባባሪ ተቋሞቻቸው አማካኝነት የፈጠራ ድርሰን በሚመስል መልኩ በሚያዘጋጁት ጥናት መሰል ሪፖርቶች ከውልደት እስከ ሽበት ዘልቀዋል። በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ አሸባሪው ትህነግ እና በውጭ ያሉ አጋሮቻቸው (አንዳንድ አገራት፣ ሚዲያዎቻቸው እና ተቋሞቻቸው) አሁን ላይ በኢትዮጵያ እያደረጉ ያለው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እና በሃሰት ወሬ የማሸበር ሂደት በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግስትን ለመጣል ካደረጉት ጋር ተመሳሳይ ስልት ስለመሆኑ ያስረዱበት አግባብን ለተመከተ ደግሞ፤ በርግጥ የሽብር ቡድኑን ሕልውና ለማቆየት ከውስጥም ከውጪም የተናበበና የተመጋገበ አሰራር ስለመፈጠሩ ለመረዳት እምብዛም አያዳግትም።
በተመሳሳይ መልኩ “ታሪክ በጥፋት ራሱን እንዳይደግም!” በሚል የተዘጋጀ አንድ ሰነድ ውስጥ “የወያኔ ተመሳሳይ ስልት ከጫካ እስከ ከተማ” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር የ1980ዎቹን ሁኔታ ከአሁኑ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ባሰፈረው ሃተታ እንዳመላከተው፤ አሸባሪው ትህነግ ትናንትና ዛሬ፣ በአንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች፣ ሚዲያዎቻቸውና የተለያዩ ተቋሞቻቸው አንቀልባ ታዝሎ በኢትዮጵያ ላይ እየፈጸመ ላለው ሴራ ተመሳሳይ ስልት የተከተለ ስለመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ሃሳብ በሚያጠናክር መልኩ በማሳያ ጭምር አስደግፎ አቅርቦታል። በዚህ ሰነድ እንደተመላከተው፣ በአሸባሪው ትህነግ እና በአንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት፣ ሚዲያዎቻቸው እንዲሁም ተቋሞቻቸው መካከል ያለው የተቀናጀ የትግል ሂደት ውስጥ ዛሬም እየተከተሉት ያለው በ1980ዎቹ የተከተሉትን የትግል ስልት ሲሆን፤ ትናንትም ሆነ ዛሬ በዋናነት አራት ዋና ዋና ስልቶችን እየተገበሩ ይገኛል። እነዚህ ዋና ዋና ስልቶቹም የሀሰት ፕሮፓጋንዳን መጠቀም፤ የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ድጋፍ መጠቀምና እንደባቡር የስልጣን ጉዞው ማሳለጫ ማድረግ፤ ሰርጎ ገቦችን በመጠቀም በውዥንብር ከተሞችን በመቆጣጠር ሰራዊቱንና አመራሩን መበተን፣ እንዲሁም የጭካኔ ግድያን ጨምሮ ዝርፊያና አፈናን እንደ ማስፈራሪያና መቀጣጫ መጠቀም መሆናቸውን በዝርዝር ያስቀምጣል።
ከእነዚህ አራት የአሸባሪው ትህነግ ስልቶች መካከል ዛሬ ላነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ አጋዥ ማስረጃ ይሆነኝ ዘንድ የሀሰት ፕሮፓጋንዳን መጠቀምን ከትናንት እስከ ዛሬ እንዴት የማሸነፊያ እና አጋሮቹን ከጎኑ አሰልፎ ሕልውናውን ለማቆየት ተጠቀመበት የሚለውን በወፍ በረር ለመዳሰስ ልሞክር። ለዚህ ይረዳኝ ዘንድም፣ ይሄንኑ ሰነድ እንደ መስፈንጠሪያ አውድ ልጠቀም። በዚህ ሰነድ እንደተመላከተው፤ አሸባሪው ትህነግ እና ተባባሪዎቹ ፕሮፓጋንዳን በሶስት መንገድ በተጠናና በታቀደ መልኩ ይተግብሩታል። አንደኛ፣ የራሳቸውን ሰዎች ታላሚ ባደረገ መልኩ፤ ሁለተኛ፣ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ከጎናቸው ሊያሰልፍላቸው በሚያስችል መልኩ፤ ሦስተኛው፣ እነሱ ጠላት ብለው የሚጠሩትን የኢትዮጵያ ህዝብ ታሳቢ በማድረግ ነው። ለእነዚህ ሶስት አካላት የሚያስተላልፉት ፕሮፓጋንዳ የቋንቋ አጠቃቀም፣ የተግባቦት ማስተላለፊያ መንገዶች፣ መልእክቶችና መልእክቶቹ የሚተላለፉበት ድምጸት(ቶን) አንዱ ከአንዱ ፈጽሞ የተለያዩ ስለመሆናቸውም በሰነዱ ከማመላከቱም በላይ፤ ይሄው ሃቅ ትናንትም ዛሬም ከሽብር ቡድኑ አመራሮችም ሆነ ከሚዲያዎቻቸው በአደባባይ የሚደመጥ ሃቅ ሆኖ ቀጥሏል።
ከሰሞኑም በሽብር ቡድኑ አመራሮች የሚደመጠው፤ በአንድ በኩል በትግርኛ ጠላትን ድባቅ መታን፣ ክፍለ ጦሮችንም ደመሰስን፤ ድላችን በክንዳችን፤ እና ትግራይ ታሸንፋለችን የመሳሰሉ የትግራይን ሕዝብና ዲያስፖራውን ታላሚ ያደረጉ መልዕክቶች ሲተላለፉ ይደመጣል። በሌላ በኩል በአማርኛ፣ ትናንት ሂሳብ እናወራርድብሃለን ያሉትን የአማራ ሕዝብ ጨምሮ ወዳጆች ነን፣ የምናወራርደው ሂሳብ የለም፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣… ሕዝብ ከአንተጋ ፀብ የለንም፤ ፀባችን ከብልጽግናና ከዐቢይ ጋር ነው፤… የሚሉ የተማጽኖ ይሁኑ የመከፋፈል በውሉ ያልተለዩ የመግለጫ ጋጋታ ያከታትሉት ይዘዋል። በተመሳሳይ መልኩ፣ በእንግሊዘኛ፣ ለሰላም ዝግጁ ነን፤ ወረራ እና መጠነ ሰፊ ማጥቃት ተከፍቶብናል፤ ጄኖሳይድ እየተፈጸመብን ነው፤ የፀጥታው ምክር ቤት ይድረስልን፤… የሚሉ ኡኡታዎችን ሲያስተጋባና ተጎጂ መስሎ በመቅረብ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከጎኑ እንዲሆን ሲያግባባ ይደመጣል።
ይሄ ድላችን በክንዳችን፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጸብ የለንም እና መጠነ ሰፊ ማጥቃት ተከፍቶብናልና ድረሱልን የሚሉ አውድ ለይተውና ተደራሲያቸውን አውቀው የሚላኩ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ድምጾች ትናንትም የነበሩ፤ ዛሬም የቀጠሉ የአሸባሪው ትህነት ለአሸናፊነት በሚያደርገው መንፈራገጥ ውስጥ የሚጠቀማቸው አቅም ማሰባሰቢያ ስልቶቹ ናቸው። በዚህ ሰነድም ይሄው እውነት፤ “ለራሳቸው ሰዎች በአብዛኛው ትእዛዝ እና ማነሳሳትን የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ለውጭው ማህበረሰብ ደግሞ ለቅሶና ዋይታ እንዲሁም ለጠላቶቻቸው(ኢትዮጵያውያን) ደግሞ ንቀትና እያሸነፍናችሁ ነው የሚል መልእክት በአንድ ጊዜ ያስተላልፋሉ፤” በሚል ተገልጿል። በዚህም አሸባሪው ትህነግ እና ተባባሪዎቹ በተመሳሳይ ድምጸት በትግርኛ ትእዛዝን፣ በእንግሊዝኛ ልቅሶን፣ በአማርኛ ደግሞ ፉከራን ያዘሉ በአንድ ጊዜ ሶስት መልክቶችን የማስተላለፍ የኖረና ያለ ልምድ ባለቤት ናቸው።
ለዚህ የፕሮፓጋንዳ ስራቸው ደግሞ የውጭ ሚዲያዎችን፣ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያን በተጠናና በታቀደ መልኩ ነው የሚጠቀሙት። ይሄንን ለማረጋገጥ ሩቅ መሄድ አይጠይቅም፤ በቅርቡ አፈትልኮ የወጣባቸው ምስጢራዊ ሰነዳቸው ሕያው ምስክር ነው። የሃሰት መረጃዎች እንዲያሰራጩ ከተመደቡና ዳጎስ ያለን ክፍያ ከሚያገኙት መካከል ደግሞ፤ ቀደም ሲል ከተጠቀሱ የዩቲዩብ ቻናሎች በተጨማሪ “ከአገር ውጭ የሚገኙ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ሊሂቃን የሚመሯቸው በውጭ አገር ያሉ ሚዲያዎች፣ የጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋይ ርእዮት ሚዲያ፣ የጋዜጠኛ ኤርሚያስ ለገሰ ኢትዮ 360 እና ሌሎች በትግራይ ተወላጆች የሚመሩ ሚዲያዎች፤” ሲሉ የገለጿቸው ይገኙበታል። አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም በሽብር ቡድኑ እና ተባባሪ ተቋሞች አማካኝነት ተፈብርኮ በእነዚህ ኃይሎች የሚለቀቀውን መረጃ እንደ በቀቀን በማስተጋባት የበኩላቸውን አጋርነት ሲያሳዩ ተመልክተናል። ለዚህ የ1983ቱን አብነት ለመጥቀስ ብዙ መራቅ ሳያስፈልገን፤ አሸባሪው ትህነግ አገር የማፍረስ ተልዕኮን አንግቦ በጥፋት መንገድ እስከ ሰሜን ሸዋ በመጣበት ወቅት የነበሩትን እነ ሲ.ኤን.ኤን፣ አልጀዚራ፣ ቢቢሲ እና ሌሎችም እነሱን መሰል ሚዲያዎች የበሬ ወለደ ዘገባዎች መመልከቱ በቂ ነው።
እነዚህን መሰል አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አሸባሪው ትህነግ ያሸነፈ መስሎ ሲሰማቸው ደብረ ሲና እያለ አዲስ አበባ ገባ ማለታቸው የሽብር ወሬን በመንዛት የቡድኑን መንገድ የማሳለጥ ሚና እየተወጡ ስለመሆናቸው ግልጽ ነው። ይህ ብቻም አይደለም፣ አሸባሪው ትሕነግ በአማራ እና አፋር ክልሎች በማይካድራ፣ በጭና፣ በቆቦ፣ ጭፍራ፣ በጋሊኮማ እና ሌሎችም በርካታ ቦታዎች ላይ ንጹሃንን በጅምላ ሲጨፈጭፍ፤ ሴቶችን (ከህጻን እስከ አዛውንት ብሎም መነኮሳት) በቡድን ሲደፍር፤ ለህጻናትና ሌሎችም የእለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖችን ሬሽን ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት መጋዘን ዘርፎ ለተዋጊ ታጣቂዎቹ ቀለብ ሲያውል እና ንጹሃን በረሃብ ሲረግፉ፤… እውነቱን ለዓለም ሕዝብ ለማድረስ አንድም ቀን አንደበታቸው ያልተከፈተው እነዚህ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፤ አሸባሪው ትህነግ አንድ ቃል በተናገረና አንድ መስመር መግለጫ ባወጣ ቁጥር ያንን ለማራገብ እንቅልፍ አይወስዳቸውም።
ለዚህ እንደ ማሳያ ለማቅረብ ያህል፤ አሸባሪው ሕወሓት የዘር ጭፍጨፋ ተፈጸመብኝ ብሎ የአዞ እንባውን ሲያወርድ፤ እነሱም በተራቸው የቡድኑን የተቀነባበረ ድራማ ለመተወን ወደ ወንዝ ወርደው አስከሬን የሚፈልጉና አንድ አስከሬን ይዘው ከወንዝ በመውጣት የዘር ማጣፍት ተፈጽሟል የሚል ሙያ ያልታከለበት ድፍረትን የተላበሱ ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም፤ እነ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ እነ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ እና ሌሎችም ዋሽንግተን ሆነው በኢትዮጵያ ጉዳይ “ጥናት” አደረግን ብለው የሚያወጧቸውን ሪፖርቶች በመቀባበል እረፍት አጥተው የኖሩበት ጊዜም ቀላል አይደለም። አሸባሪው ትህነግ የትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርሰው መንገዶችን በመዝጋት ረሃብን ለጦር መሳሪያ የማዋል የቆየ ስልቱን ሊተገብር በጣረበት ወቅት፤ የራሱን ተግባር ለፌዴራሉ መንግስት ሊያሸክም አስቦ መንግስት እርዳታ ወደክልሉ እንዳይደርስ ከልክሎ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው ሲል፤ እንዴት ብለው ሳይጠይቁ፣ ለምን ብለው ሳያጣሩ ተከሽኖ የቀረበላቸውን ተረክ ተቀብለው ማስተጋባት ያዙ።
በአንጻሩ ይሄን ክስ ውድቅ ያደረገውን የመንግስት እርምጃ፣ ማለትም መንግስት የትግራይ ሕዝብ በየብስም በአየርም የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሰው ያደረገበትን ሂደት ለመዘገብ አቅሙ አልነበራቸውም። ይልቁንም የሽብር ቡድኑ ድጋፉ ለሕዝብ እንዳይደርስ በየመጋዘኑ አከማችቶ በማስቀመጥ የዕለት ሰብዓዊ ድጋፍን የዓላማው ማስፈጸሚያ የማድረጉን እውነት መንግስት እወቁልኝ ሲል፤ በተገላቢጦሽ ድጋፉ ከመቀሌ ወደ ሕዝብ ሊደርስ ያልቻለው በነዳጅ ችግር ነው ሲሉ ተደመጡ። ሆኖም እውነቱ እሱ እንዳልነበረ ቡድኑ ከ570 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ዲፖ ዘረፈ በተባለበት ወቅት ገሃድ ሊወጣ ችሏል። የአሸባሪው ትህነግ እና የእነዚህ አጋሮቹ (አንዳንድ አገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሚዲያዎቻቸው) ስልታዊ ጉዞ በዚህ የሚያበቃ አይደለም። ይልቁንም አንዱ ውሸት ሲጋለጥ ሌላ ውሸት ፈጥሮ የውስጡንም የውጭውንም ማህበረሰብ ለማደናገር መትጋታቸው የተለመደ ነው። ሰሞኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ታማኝ ምንጮች ይሄንኑ የሚያረጋግጥ መረጃ ለተቋሙ ማቀበላቸው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዞት በወጣው የዜና ዘገባ ነግሮናል።
ነገሩ እንዲህ ነው። ጋዜጣው “መርማሪ ኮሚሽኑ ሊያወጣ ያዘጋጀው ሪፖርት ዓላማ ፖለቲካዊ ነው” በሚል ርዕስ መስከረም 08 ቀን 2015 ዓ.ም በፊት ገጹ ይዞት በወጣው ዜና፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት “የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለተፈጸሙ አጣራለሁ” በሚል የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ስራውን ሳያከናውን ፖለቲካዊ አላማ አንግቦ መደምደሚያ ያበጀለትን “የጥናት” ሪፖርት ያዘጋጀ መሆኑን የኢፕድ ምንጮች ያረጋገጡት ሃቅ ስለመሆኑ እነሆ ብሏል። በዘገባው እንደተመላከተው፤ ኮሚሽኑ “ጥናት” በሚል ያቀናበረውና ይፋ ሊያደርግ የተዘጋጀው (ይሄ “የጥናት” ሪፖርት ትናንት ይፋ መሆኑን ልብ ይሏል) ሰነድ ዓላማም የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ለማጠልሸት፣ የአሸባሪውን ትህነግ ፍላጎት ከፍ አድርጎ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያሳዩልኛል የሚላቸውን ጉዳዮች ባልተጨበጡና ሊረጋገጡ በማይችሉ አሉባልታዎች ላይ ተመስርቶ በማቅረብ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር መነሻ የሚሆን ፖለቲካዊ ድምዳሜ ላይ የደረሰ ነው።
ምንጮቼ አረጋግጠውልኛም ሲል ጋዜጣው ይዞት በወጣው መረጃ ላይ እንዳመላከተውም ሆነ ሰነዱ ትናንት ይፋ ሲሆን መመልከት እንደተቻለው፤ ተፈጸሙ የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲያጣራ የተሰየመው ኮሚሽን የመደባቸው ሰዎች ችግሩ ተፈጥሯል በተባለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ከማጣራት ይልቅ ኢንቴቤ/ኡጋንዳ ተቀምጠው ጥቂት ግለሰቦችን በስልክ አነጋገርኩ በማለትና መሰል ተጨባጭነት በሌላቸው አሉባልታዎች ላይ በመመስረት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰ፤ ይሄንኑ በተሳሳተና ባልተጨበጠ መረጃ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ዓላማን ያነገበ የ“ጥናት” ሪፖርታቸውን ይፋ ያደረጉበት ነው።
ይህ ደግሞ የኮሚሽኑን ሪፖርት ተዓማኒነት ከማሳጣቱም በላይ የኮሚሽኑን ተቀባይነት/ክሬዲተብሊቲ/ ጥያቄ ውስጥ የሚከትተው ሃቅ ነው። ምክንያቱም ከወጣው ሰነድ መመልከት እንደሚቻለው ቡድኑ ራሱ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ካውንስል ባቀረበው ሪፖርት፣ በግብአት እጥረትና መሰል ምክንያቶች የተጣለበትን ጥልቅ ምርመራ ማካሄድ እንደማይችል ማስታወቁ እየታወቀ፣ አገሪቱ ላይ የዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር የታለመ ኢፍትሃዊና ሀቅ ላይ ያልተመሰረተ ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ይሄ ደግሞ ቀደም ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቦታው ጭምር በመሄድ በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ላይ ተመስርተው ያወጡት ሪፖርት እውነትን እንጂ የአሸባሪውን ትህነግ ፍላጎት ያልተከተለ በመሆኑ፤ ይሄኛው ኮሚሽን የጋራ ሪፖርቱን በሚቃረን መልኩ የሽብር ቡድኑን ፍላጎት ባማከለና እውነትን በደፈጠጠ መልኩ እንዲያዘጋጅ “ጥናቱን” ከመጀመሩ በፊት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚገባው ተወስኖ የተከናወነ ስለመሆኑ ያስረዳል።
ይህ ብቻም አይደለም፤ ኮሚሽኑ የተጠቀመው የጥናት ዘዴ፣ ከጥናቱ ወሰንና ከዳሰሳው ስፋት፣ ከመረጃ አሰባሰብም ሆነ አተናተኑ ሳይንሳዊ መንገድን ያልተከተለና ከዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ጋር የተቃረነ፤ የተቃረነም ብቻ ሳይሆን የተሳሳተም ነው። ይሄንኑ የተሳሳተና ቀድሞ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚገባው ተወስኖለት የተዘጋጀውንና አንድ ዓመት ፈጅቷል የተባለውን “የጥናት” ግኝት ሪፖርት ነው ይፋ የተደረገው። ሆኖም ቡድኑ ስራውን ሙሉ ለሙሉ እንዳላከናወነና ተጨማሪ በጀትና የሰው ሃይል እንዲፈቀድለትም ጠይቆ እንደነበር፤ ሌላው ቀርቶ የተመድ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተቋማት በጋራ ላከናወኑት ጥናት የተጠቀሙትን ጥሬ መረጃ ለመጠቀም ተቋማቱን ጠይቆ እንደተከለከለ፤ ይሄም ኮሚሽኑ ከሰው ኃይል ጀምሮ በአካባቢው የተፈፀመውን ችግር ለማጣራት በቂ አቅምና ዝግጁነት ያልነበረው፤ ይልቁንም ቡድኑ ሁለት ባለሙያዎችና ሶስት ኮሚሽነሮችን በመያዝ ብቻ ወደ ስራ መግባቱም ይሄንኑ የፖለቲካ ፍላጎት ተሸካሚነቱን እውነት የሚያረጋግጥ ሆኖ ተገኝቷል።
የቡድኑ የመጨረሻ ግብ መንግስት ሰብዓዊ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል በሚል የሀሰት ክስን ማስተጋባት፤ የኢትዮጵያን፣ የመከላከያ ሰራዊቷንና መንግስቷን ስም የማጠልሸት፤ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጫና እንዲበረታባት ማድረግ ነው። ሰሞንኛ የአሸባሪው ትህነግ አፈቀላጤዎች እና በውስጥም በውጭም ያሉ ተባባሪዎቻቸው (አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም አገራት ጭምር) “ትግራይ ጄኖሳይድ፣ ጭፍጨፋ፣ የሰብዓዊ ድጋፍን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም፣ የነዳጅ አቅርቦት፣…” የሚሉ ጫጫታዎችን ከኮሚሽኑ የድርሰት ሰነድ ጋር የተናበበ ነው። ይሄም የአሸባሪው ትህነግ እና ተባባሪዎቹ ለሪፖርቱ ተዓማኒነት ማግኘት ቅድሚያ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ወይም ፈርታይል ግራውንድ የመፍጠር አካሄድ መሆኑ ነው።
ይህ ደግሞ ትናንትን የነበረ እና ዛሬም የቀጠለ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ መንገድና ስልታቸው ነው። ሆኖም ዛሬ ትናንት አይደለም፤ ታሪክም በጥፋት ራሱን እንዳይደግም፤ አሸባሪው ትህነግና ተባባሪዎቹም በአንድ መንገድ ተጉዘው ሁለት ጊዜ አይረቱንም፤ ጊዜውና ሁኔታውም ይሄን አይፈቅድም። በመሆኑም አሸባሪው ትህነግና ተባባሪዎቹ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እና እንደ በቀቀን እያስተጋቡት የሚገኙት አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር እንደ ትናንቱ ሰሚ ጆሮም፣ የሚቀበለው ተላላ ሕዝብም የለም። ይልቁንም የሽብር ኃይሉ ዓይንና ጆሮ ሆነው የቆሙ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራትና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፣ ተቋሞቻቸውና ሚዲያዎቻቸው ከሴራ ይልቅ ለእውነት ሊቆሙ እና የሽብር ቡድኑን የጥፋት መንገድ በመገንዘብ የትግራይን ሕዝብ በአሸባሪው ትህነግ ከተጫነበት መከራ እንዲወጣ ሊያግዙት የተገባ ነው። ኢትዮጵያውያንም ለሴረኞች ወጥመድ ባለመገዛት፤ ለኢትዮጵያችን ሰላም፣ አንድነትና ሁለንተናዊ ከፍታ በአንድ ቆመው ሁሉንም የጥፋት ኃይሎች ሊታገሉ ይገባል።
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2015 ዓ.ም