
አዲስ አበባ፦ የከተማ ልማት ሚኒስቴር ለ67 ከተሞች 72 የመስክ ተሽከርካሪዎችን እና 144 ሞተር ሳይክሎችን ለገሰ። ድጋፉ በምግብ ዋስትና ፕሮግራም የተካተቱ ዜጎችን ሕይወት ለመቀየር አቅም እንደሚፈጥርም ተመልክቷል።
ከተማ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የተሽከርካሪዎች ርክክብ መርሀ ግብር ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ መንግሥት የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር በተለያዩ ፈርጀ ብዙ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። ከእነዚህ ስራዎች መካከልም የከተሞች የምግብ ዋስትና (ልማታዊ ሰፊትኔት) ፕሮግራም ይገኝበታል። ይህ ፕሮግራም የዜጎችን ሕይወት በመቀየር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ በማሳየት ላይ ነው።
ከተማ ልማት ሚኒስቴር ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሥራዎችን ለማሳለጥ የሚያችሉ 72 የመስክ መኪናዎችና 144 ሞተር ሳይክሎችን በፕሮግራሙ ለተካተቱ ከተሞች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል ።
ድጋፉ የዜጎችን ሕይወት በተጨባጭ ለመቀየር የሚያስችል አቅም ለመፍጠርና ፕሮግራሙን ተፈጻሚ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ዓላማ መስራት የሚችሉ እጆችንና አእምሮዎች በአነስተኛ ድጋፋ ስራ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግና ጥሪት እንዲያፈሩ ማድረግ መሆኑን አመልክተው፤ ፕሮግራሙ 68 በመቶ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ የሕብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል ።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም አማካኝነት ፈርጀ ብዙ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ናቸው። በተለያዩ ምክንያቶች የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሰው እንዲያገግሙ የማልማት ስራዎች ተሰርተዋል። መንገድና መሰል አስፈላጊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተካሂደዋል።
በምግብ ዋስትና ፕሮግራም አማካኝነት የተገዙት ተሽከርካሪዎችን ከተሞቹ ለተቀመጠላቸው ዓላማ ማዋል እንደሚገባ ሚንስትሯ አሳስበዋል። የከተሞች ልማት ቢሮ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የተሸከርካሪዎች የርክክብ መርሐ ግብሩ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የከተሞቹ ተወካዮች እንደገለጹት፤ ድጋፉ በከተሞቹ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የከተሞች ነዋሪዎችን ሕይወት ለመቀየር የሚያስችል አቅም ይፈጥራል። በፕሮግራሙ የታቀፉ ዜጎች በከተማ ጽዳት ስራ፣ በአረጓዴ ልማትና መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በመሳተፍ የገቢ አቅማቸውን እንደሚያሳድጉ ተገልጿል።
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2015 ዓ.ም