ያለንበትን መስከረም ወር ጨምሮ መጪዎቹ ጥቂት ወራት በመላው ዓለም የጎዳና ላይ ውድድሮች በስፋት የሚካሄዱበት ነው። በየሳምንቱ መጨረሻ በሚካሄዱ የሃያ አንድ ኪሎ ሜትር እና የተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ላይም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የተለመደ ድላቸውን እያስመዘገቡ ይገኛሉ። ከትናንት በስቲያ በዴንማርክ ኮፐንሃገን በተካሄደው ግማሽ ማራቶን ውድድርም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸናፊዎች በመሆን እንደተለመደው የአገራቸውን ስም አስጠርተዋል። ውድድሩ በዓለም አትሌቲክስ የኤሊት ደረጃ የተሰጠውም ነው።
ፈጣን በነበረው በዚህ ውድድር ላይ 15 የሚሆኑ አትሌቶች ከ1 ሰዓት በታች ውድድራቸውን መፈጸም እንደቻሉም ነው አወዳዳሪው አካል ያስታወቀው። በወንዶች በኩል በተካሄደው ውድድር ሚልኬሳ መንገሻ የአገሩን ልጅ አስከትሎ በመግባት አሸናፊ ሆኗል። እአአ በ2019 ከ20 ዓመት በታች አገር አቋራጭ ቻምፒዮን የነበረው ሚልኬሳ ይህንን ርቀት ለመጨረስ የፈጀበት ሰዓት 58:58 ሆኖ ተመዝግቧል። እስከ 15ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ በምስራቅ አፍሪካዊያን ተፎካካሪዎች ተከቦ የሮጠው አትሌት ሚልኬሳ አፈትልኮ በመውጣትና ሩጫውን በማፍጠን ባለድል መሆኑን አረጋግጧል።
እርሱን ተከትሎም እጅግ ተቀራራቢ በሆነ ሰዓት የአገሩ ልጅ አምደወርቅ ዋለልኝ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ማጠናቀቅ ችሏል። ለአሸናፊነት በተለይ ሲፎካከር የቆየው ይህ አትሌት የገባበት ሰዓት በአንድ ደቂያ ዘግይቶ 59:05 ተመዝግቧል። የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ቀዳሚ ተፎካካሪ የሆኑት ኬንያዊያን አትሌቶች ደግሞ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል። ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ፍሌክስ ኪፕኮች ለአምደወርቅ ፈታኝ ተፎካካሪው ሆኖ በውድድሩ ላይ የታየ ሲሆን፤ ያስመዘገበው ሰዓትም ከኢትዮጵያዊው አትሌት በሁለት ሰከንዶች ብቻ የዘገየ 59:07 ነው። ሌላኛው ኬንያዊ ቪንሰንት ኪፕኬሞይ ደግሞ 59:09 በሆነ ሰዓት አራተኛ ሆኗል።
በሴቶች በኩልም በተመሳሳይ የበላይነቱ በኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ሲያዝ፤ አትሌቶቹ የገቡበት ሰዓት እጅግ ተቀራራቢ መሆኑ ብርቱ ፉክክር ማድረጋቸውን ያመላከተ ነበር። አሸናፊዋ አትሌት ታዱ ተሾመ የግሏን ፈጣን ሰዓት ያሻሻለችበት ውድድርም ነው። ውድድሩ ከመነሻው አንስቶ በታዱ እና በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጽጌ ገብረሰላማ ሲመራ የቆየ ሲሆን፤ ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ ግን ታዱ ፈጥና በመሮጥ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ወደ 30 ሰከንድ ማስፋት ችላለች። በዚህም አሸናፊዋ አትሌት የገባችበት ሰዓት 1:06:13 ሆኖ ተመዝግቧል።
ለማሸነፍ ብርቱ ፉክር ስታደርግ የቆየችው ጽጌ በበኩሏ ልዩነቱን ወደ 22 ሰከንዶች በማጥበብ 1:06:35 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቃለች። ሌላኛዋ አትሌት ጥሩዬ መስፍንም ከአገሯ ልጆች ሰከንዶችን ብቻ በመዘግየት 1:06:42 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችላለች።
ሌላኛው በሳምንቱ መጨረሻ የተካሄደና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ቀዳሚ በመሆን ያጠናቀቁበት ውድድር ደግሞ በአውስትራሊያ ሲድኒ የተካሄደው የማራቶን ውድድር ነው። በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ተከታትለው ሲገቡ፤ አንዲት ኤርትራዊ አትሌትን በመሃል በማስገባት እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል። 2:25:10 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ የሆነችው አትሌት ትዕግስት ግርማ፤ ከሃገሯ ልጅ ለተብርሃን ኃይላይ ጋር ከፍተኛ ፉክክር አድርጋለች። በዚህም ለተብርሃን በሰከንዶች ብቻ ተበልጣ 2:25:45 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ልትይዝ ችላለች። ሶስተኛ የሆነችው ኤርትራዊት አትሌት ናዝሬት ወልዱ በ2:26:14 ገብታለች። ራህማ ቱሳ፣ የኔነሽ ጥላሁን እና ፋንቱ ጂማ ደግሞ እስከ ስድስት ባለው ደረጃ ተከታትለው የገቡ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው።
በተመሳሳይ በወንዶች መካከል እጅግ ፈታኝ በነበረው ውድድር አራት አትሌቶች ለአሸናፊነት ከፍተኛ ትግል ያደረጉ ሲሆን፤ በማራቶን ውድድር ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ አንገት ለአንገት ተያይዘው በመግባት በሰከንዶች ብቻ ተለያይተው ማጠናቀቅ ችለዋል። አሸናፊው አትሌት ኬንያዊው ሞሰስ ኪቤት 2:07:03 በሆነ ሰዓት በመግባት በአውስትራሊያ ፈጣኑን የማራቶን ሰዓት ሊያስመዘግብ ችሏል። ሌላኛው ኬንያዊ ኮስማስ ማቶሎ ደግሞ 2:07:05 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኗል። በሶስት ሰከንዶች የዘገየው ኢትዮጵያዊው ጫሉ ዴሶ 2:07:08 ሶስተኛ ሲሆን፤ አበበ ነገዎ 2:07:26 በሆነ ሰዓት አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ኦሊቃ አዱኛ ደግሞ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆኗል።
ወጣቶቹ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ሚልኬሳ መንገሻና ታዱ ተሾመ በኮፐንሃገን ግማሽ ማራቶን ፈጣን ሰአት በማስመዝገብ አሸንፈዋል፣
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2015 ዓ.ም