እንደ አሜሪካ ያሉ አንዳንድ ሀያላን አገራት ዘመን የተሻገረ የስኬት ሚስጥር አላቸው..እርሱም ከላይ ለርዕሴ የተጠቀምኩት አባባል ነው። ዛሬም ድረስ አሜሪካና አሜሪካውያን በዚህ ‹አገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን አደረኩት› በሚል እሳቤ ውስጥ ናቸው። አሜሪካውያን እንዴት አደጉ? እንዴት ሰለጠኑ? እንዴትስ ይሄን ልዕልና አገኙ? ብሎ ለጠየቀ መልሱ ይኸው ነው ።
አእምሮና ልብን የሚያነሳሱ። አንዳንድ አንደበቶች ፈዋሽ ናቸው። ተደምጠው የሚያበቁ ብቻ ሳይሆኑ በሰሚ ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ህይወት የሚዘሩ፤ አንዳንድ ጥያቄዎች ተራ መስለው ከብዙ መከራና እንግልት የሚያወጡ ሆነው እናገኛቸዋለን። አሜሪካውያን ከምንምነት የወጡት በዚሁ በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ኬኔዲ አገር አቀፍ ፍልስፍና ነበር።
አንዳንድ ጥያቄዎች አገር ይፈጥራሉ። አንዳንድ ጥያቄዎች ደግሞ አገር ይሰውራሉ። ቃላትን በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው ተዐምር የመፍጠር አቅም አላቸው። እድገትና ስልጣኔ በምኞት ብቻ የሚመጡ ነገሮች አይደሉም። ህልሞቻችን እውነትነትን እንዲያገኙ አነቃቂና አበረታች ሀሳብና አንደበቶች ይሻሉ። ብዙዎቻችን ጠባቂዎች በሆኑበት፤ ከጠባቂነትም በላይ የምንፈልጋቸው ነገሮች ደጆቻችን ላይ እንዲሆኑ የምንጠብቅ በሆንበት አገር ውስጥ፤ ብዙዎቻችን ተምረንም ሆነ ተመርቀን የመንግስትን እጅ በምንጠብቅበት አገር ውስጥ ነገዎቻችን ብሩህ ናቸው ብሎ መጠበቅ የዋሕነት ነው።
በመጠበቅ ውስጥ ለውጥ የለም። በመጠበቅ ውስጥ የሚፈጠር እድል የለም። እድሎቻችን ያሉት ዛሬን በመጠቀም ውስጥ ነው። ኢትዮጵያ አገራችን በየአመቱ ከሁለት መቶ ሀምሳ ሺ ተማሪ በላይ አዲስ ስራ ፈላጊ ተመሪዎችን ታስመርቃለች። ያለው ስራ ሳያገኝ..ተመርቆ ቁጭ ያለው እንጀራ ፍለጋ መንግስትንና አገሩን በሚጠብቅበት ሁኔታ ላይ ሌላ ስራ ፈላጊ መጨመሩ ሁኔታውን ምን ያክል አስቸጋሪ እንደሚያደርገው መገመት አይከብድም።
ከተማረውም ሆነ እየተማረ ካለው የሚጠበቀው መንግስትን ሳይጠብቅ በተማረው ትምህርት ለራሱም ሆነ ለሌሎች እድሎችን መፍጠር ነው። በመጠበቅ ውስጥ ልዕልና የለም። ለምሳሌ ተመርቆ ስራ በመፈለግ ሶስት አመት ያሳለፈ አንድ ተማሪ ከመጠበቅ ወጥቶ እነዛን በስራ መፈለግ የባከኑ ሶስት አመታቶች ስራ ፈጥሮ ቢሰራባቸውና ራሱን ለመለወጥ ቢጠቀምባቸው ዛሬ ላይ ተመርቀው ስራ ላጡ ተማሪዎች እንጀራ መሆን ይችል ነበር።
ሁለትና ሶስት ዓመት ስራ ፍለጋ ስንባዝን ምንም የማይመስለን ስራ በማጣታችን እንቆጫለን። ስራ እየሰሩ ስራ መፈለግ እኮ ይቻላል። ህልምና ራዕይን እየኖሩ የተሻለ ነገር መጠበቅ እኮ ይቻላል። እኛ ግን ጋዋናችንን ባወለቅን ማግስት መንግስት ስራ ፈልጎ እንዲሰጠን እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥ ነን። አንዳንዶች ጭራሽ ለመንግስት ብለው የተማሩ የሚመስላቸው አሉ..መንግስት ቤታቸው ድረስ መጥቶ ካልቀጠራቸው በአገራቸው ላይ ለንቦጫቸውን የሚጥሉ።
ከመጠበቅ እስካልወጣን ድረስ ከፍ ማለት አንችልም። ከመጠበቅ እስካልተላቀቅን ድረስ ራሳችንን የምንለውጥበት አንድም አጋጣሚ አይገኝም። አገሬ ምን አደረገችልኝ? ከሚል አመለካከት ወጥተን እኔ ለአገሬ ምን አደረጉላት? እስካላልን ድረስ የህልሞቻችንን ጥግ አንደርስበትም። ድሀና በብዙ ማጣት ውስጥ ያለች አገር ዜጎቿን እንደፍቃዳቸው ማስተናገድ አትችልም። አሁን ባለው ኢኮኖሚ፣ አሁን ባለው ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ መንግስት ፍላጎቶቻችንን ማሟላት አይችልም።
ራሳችንን የምንለውጠው ራሳችን ነን። እኛ ከመጠበቅ እስካልወጣን ድረስ ሊለውጠን የሚችል ኃይል ምድር ላይ የለም። የዓለም ስልጣኔ የግለሰቦች ስልጣኔ ነው። ግለሰብ ሲሰለጥንና ሲለወጥ ነው አገርና ማህበረሰብ የሚለወጠው። በራሳችን ውስጥ ራሳችንን ገለንና አኮስሰን መንግስት ካለወጠኝ የምንል ከሆነ በጊዜ ከፈናችንን ብንገዛ ይሻለናል። ዓለም በግለሰቦች ለውጥ ውስጥ ናት..እየተራመደች ያለችውም በጥቂት ሀሳባውያን እምነት ውስጥ ነው።
ጆሴፍ ኬኔዲ አሜሪካንን ለመለወጥ ሲነሳ መጀመሪያ ከራሱ ነበር የጀመረው። ፕሬዚዳንት ሆኖ ኋይት ሀውስ ሲገባ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ለዘላለም የሚታወስ አንድ በጎ ነገር መስራት አለብኝ ብሎ ነበር። እንዳሰበውም ለሁላችንም ቀላል በሚመስል ግን ደግሞ በአይደለ ንግግር ‹አገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት› በሚል ፍልስፍና አገሩን ወደፊት ማራመድ ቻለ። አሁን ላይ መላው አሜሪካውያን ለአገራቸው የሚለፉ ናቸው። ዓለም ላይ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ከሚወዱ ጥቂት አገራት ውስጥ አሜሪካውያን ተጠቃሽ ናቸው።
ራስን ለመቀየር መጀመሪያ አስተሳሰብን መቀየር ያስፈልጋል። አገር ለመቀየር መጀመሪያ ራስን መቀየር ግድ ይላል። የጠፋን እውነት ይሄ ነው። ተመርቀን መንግስትን የምንጠብቅ ከሆነ፣ ምንም ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር መንግስትን የምንጠራ ከሆነ፣ በአካባቢያችን ላለ ረብሻ፣ ላለ ቆሻሻ፣ ላለ የውሀ ቱቦ፣ ላለ ኮረኮንች መንገድ መንግስትን ተጠያቂ የምናደርግ ከሆነ ገና አስተሳሰባችንን አልቀየርንም ማለት ነው።
በገቡን ጥቂት እውነቶች ላይ ተረማምደን ያልገቡንን እልፍ እውነቶች ሀሰት ናቸው ማለት የለብንም። አገራችን የምሰጠን ምንም የላትም። ከሰጠችንም እኛ የሰጠናትን ነው፤ ካልሰጠናት የምሰጠን አንዳች የላትም። እንድሰጠን ልንሰጣት ይገባል። ተመርቀን ስራ እንድናገኝ በተመረቅንበት የሙያ ዘርፍ በተዐማኝነት ልናገለግላት ይገባል። ወልደን እንድንስምባት፣ ዘርተን እንድንቅምባት ፍቅርና ትህትናን የሚያውቁ ዜጎች ልንሆን ይገባል።
አገራችን እንድትሞላ ከራሳችን ላይ የምናጎለው እውነት ያስፈልጋል። ትውልዱ እንዲባረክ ጥላቻን ያስቀደመ ልብ ሳይሆን ለይቅርታ የበረታ ሰውነት ያስፈልገናል። ለምንም ነገር አገር እየጠበቅን፣ ለምንም ነገር አገራችንን ሰበብ እያደረግን የምንሞላው ባዶነት የለም። መጀመሪያ በውስጣችን ያለውን የጥላቻ ስፍራ፣ የመገፋፋት ባዶነት እንሙላ። እኛ ሳንሞላ የምትሞላ አገር የለችንም። እኛ ሳንለወጥ፣ እኛ ልክ ሳንሆን የምትለወጥና ልክ የምትሆን አገር አልተሰጠችንም።
አገር ማለት ከራሳችን ለራሳችን የምንሰጠው ክብር ማለት ነው። ትውልድ ማለት ከራሳችን ለራሳችን የምንቆርሰው እውነትና ማለት ነው። ክብራችንን አጉድለን፣ እውነታችንን አሳንሰን የምንወጣው የስኬት ተራራ የለም። የስኬት ተራራዎች በበረቱ እግሮች የሚወጡ ናቸው። የስኬት ከፍታዎች በማሰብና በትጋት የሚገፉ ናቸው። እግሮቻችንን አንድ ቦታ ላይ ተክለን መጠበቅ አስለምደናቸው የምንወጣው የስኬት ተራራ የለም።
መጀመሪያ ልማዶቻችንን እንቀይር። እንዳንቀሳቀስ፣ እንዳንበረታ ያደረጉንን አጉል እምነቶቻችንን እናጥፋ። ልማድ አደገኛ ነገር ነው..አባቶቻችን ‹ከሰይጣን በላይ ልማድህን ፍራ› ይላሉ። ሰይጣን በስመ አብ ስትለው ይሄዳል ልማድ ግን ምንም ብንለው አይሸሸንም። የዛሬ የድህነት ምክንያቶቻችን በስመ መስቀል ያላባረርነው የአጉል ልማድ ውጤታችን ነው እላለው። የመጠበቅ ልማዳችንን፣ የጥላቻ ልማዳችንን፣ ያለመነጋገር ልማዳችንን፣ የተንኮል ልማዳችንን፣ እውቀትን ልህቀትን ያለመፈለግ ልማዳችንን፣ ሳይሰሩ የመብላት ልማዳችንን፣ ባጠቃላይ የእኩይ አስተሳሰብ ልማዳችንን መስበር ይኖርብናል።
አገር፣ ህዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ ወግ ስርዐት እውነት የሚሆኑት እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት? ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ ነው። እስከዛሬ ባለመጠየቅ ውስጥ ነበርን። እስከዛሬ እውነት በሚመስል ውሸት ውስጥ ነበርን። እስከዛሬ ያልሰጠነውን ፍቅር፣ ያልሰጠነውን ክብር፣ ያልሰጠነውን እውነት ከአገራችን ስንጠብቅ ነበር። አገራችን እንድትሰጠን ልንሰጣት ይገባል። እናም ፍቅራችንን አንድነታችንን እንስጣት። ይቅርታን በጎነትን እንስጣት። እርቅን፣ ተነጋግሮ መግባባትን እናውርሳት። ይሄን ስናደርግ ነው የምሰጠን። ይሄን ስናደርግ ነው ፍላጎታችንን ለማሟላት አቅም የምታገኘው።
ተማሪ ከሆንን ችግሮቿን ሊቀርፍ በሚችል ብርታት ውስጥ እንሁን። ስራ ፈላጊ ከሆንን ከመጠበቅ ወጥተን ለጠባቂዎች አርዐያ እንሁን። በስራ ዓለም ላይ ከሆንን ደግሞ በእውነት ልናገለግላት ለራሳችን እንታመን ይሄን ስናደርግ የምትሰጠን ብዙ ነገር ይኖራታል። ያለዛ ግን ምንም የሌላትን እናታችንን ማስጨነቅ ነው የሚሆነው። ያለዛ ግን አንዳች የሌለው ድሀ ህዝብን መክዳት ነው የሚሆነው።
ከነበርንበት አስተሳሰብ ወጥተን ‹እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት? ወደሚል ተገቢ ጥያቄ እንመለስ። እስከዛሬ ጠይቀን ያልመለስነው ጥያቄ ይሄ ነው እላለው። በዚህ ጥያቄ ውስጥ ነው ለዘመናት ፈልገን ያጣነውን እውነት የምንደርስበት። በዚህ ጥያቄ ውስጥ ነው፤ ለዘመናት ተራምደን ያልደረስንበትን የእድገትና የስልጣኔ መልሶች የምናገኘው። ራሳችንን በማይጠቅመን እውነት ውስጥ ሸሽገን መኖራችን ይብቃን።
ከእንግዲህ አገሬ ለኔ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን አደረኩ? ምን ሰራሁ? ምን ፈጠርኩ? ወደሚል እውነት ልንሸጋገር ይገባል። እንደ ዜጋ እንደ መንግስት እንደየትኛውም አገር ወዳድ ልቦች የጠፋችብንን ኢትዮጵያ፣ የጠፋብንን ስልጣኔ፣ የጠፋብንን አንድነት በዚህ ‹እኔ ለአገሬ ምን አደረኩ? በሚለው ጥያቄ ውስጥ ልንፈልገው ይገባል። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደ ህይወት መርህ ልንመራበት የሚገባን ፍልስፍና ነው።
አንዳንድ ጊዜ ስልጣኔ በቀላል ቀመር የተቀመረ ጥበብ ነው። ቀመሩን አጠገባችን አስቀምጠን ሩቅ የምናይ፣ ለፍለጋ ሩቅ የምንሄድ ሞልተናል። አሜሪካውያን ሚስጥሩን ፍለጋ ሩቅ አልሄዱም..ሩቅ አላዩም ዛሬም ድረስ በዛ ሚስጥር ውስጥ ናቸው። ሚስጥሩ ራስን መጠየቅ ነው..ሚስጥሩ ወደሌሎች ጣትን ከመቀሰር ይልቅ እኔ ለአገሬ ምን አደረኩ? ለወገኔ ምን ሰራሁ? ብሎ ራስን መጠየቅ፤ ጠይቆም መልስ ማግኘት ነው።
ራሳችንን ከመጥቀም፣ ራሳችንን ከማገልገል፣ ብሄር እየለየን፣ ዘርና ጎሳ እየመረጥን ከመጮህ ወጥተን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መሀል አድርገን ለጋራ ጥቅማችን ራሳችንን እናዘጋጅ። ተባብረን አገር ማሳደግ ያቃተን እኮ በአባቶቻችን የጋራ ሀሳብና ህልም የቆሙ ታሪኮቻችንን ተለያይተን ስላነበብናቸው ነው። በጋራ የተጻፉ ታሪኮች በጋራ ነው የሚነበቡት። በጋራ የተፈጠሩ እውነቶች በጋራ ነው የሚጸኑት። በአሁኑ ሰዐት ራሳችንንም ሆነ አገራችንን ልንለውጥበት የምንችልበት አንድ መንገድ ብቻ አለን እርሱም ‹እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት? በሚለው የተፈጠነ ጽንሰ ሀሳብ ነው። በዚህ እውነት ውስጥ እንብቀል..በዚህ እውነት ውስጥ ወጥተን እንግባ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2015 ዓ.ም