በመጪው ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ የተሰጠው የአምስተርዳም ማራቶን ይካሄዳል። እ.አ.አ በ1975 በተጀመረው በዚህ ውድድር ላይም ኢትዮጵያውያን ከዋክብት አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አዘጋጆቹ አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ጀግና አትሌቶች በዚህ ውድድር መሳተፋቸው የዘንድሮውን የአምስተርዳም ማራቶን ታሪካዊ አድርጎታል። ኢትዮጵያውያኑ የኦሊምፒክ ጀግኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚታወቁባቸው ርቀቶች ውጪ ማራቶንን አንድ ብለው የሚሮጡበት እንደሚሆንም ታውቋል።
በረጅም ርቀት የመም ውድድር እ.አ.አ የ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ዓለምን ካስደመሙ አትሌቶች መካከል አንዷ ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና ናት። በ10ሺ ሜትር ለረጅም ዓመታት ሳይደፈር የቆየውን ክብረወሰን በማሻሻል አድናቆትን ያተረፈችው አልማዝ፤ በ5ሺ ሜትርም የነሐስ ሜዳሊያ በማጥለቅ ስኬታማ እንደነበረች አይዘነጋም። ይሁን እንጂ አልማዝ ከ2017 የዓለም ቻምፒዮና ድሏ በኋላ በጉዳትና በወሊድ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከውድድሮች ርቃ ቆይታለች። አልማዝ ባለፈው አመት መገባደጃ ላይ ወደ ውድድር ተመልሳ ጥቂት የዳይመንድሊግ ውድድሮችን ብታደርግም ወደ አሸናፊነት መመለስ አልቻለችም። ከዚህ በኋላ ግን አልማዝ ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች በተለይም ወደ ማራቶን ፊቷን እንዳዞረች የሚያረጋግጡ እውነታዎች እየታዩ ናቸው። አልማዝ እውቁን የማራቶን ሯጮች ስብስብ የኤን ኤን ረኒንግ ግሩፕን ተቀላቅላ ልምምድ ማድረግ ከጀመረች ሰንብታለች። በዚህም ባለፈው መስከረም 1/2015 የመጀመሪያዋን የግማሽ ማራቶን ውድድር በእንግሊዝ ግሬት ኖርዝ ረን አድርጋ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል። ከዚህ ውድድሯ ከሳምንት በኋላ በዘንድሮው የአምስተርዳም ማራቶን ተሳታፊ መሆኗ መታወቁም ፊቷን ሙሉ በሙሉ ወደ ማራቶን ለማዞሯ አመላካች ሆኗል።
የ30 ዓመቷ አትሌት አልማዝ አያና በሪዮ ኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር ለ23 ዓመታት በቻይናዊቷ አትሌት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በመስበር (29.17.45) የወርቅ ሜዳሊያ ከማጥለቅ ባሻገር በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆኗ በዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ምርጫ ላይ አሸናፊ መሆኗ የሚታወስ ነው። እ.አ.አ በ2015 እና 2017 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ባለድል የሆነችው አትሌቷ፤ በ2017 እና 2013 ቻምፒዮናዎች የብርና ነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ እንዲሁም የሁለት ጊዜ የዳይመንድሊግ አሸናፊም ናት። ይኸውም ብርቱዋን አትሌት በማራቶንም ውጤታማ ትሆናለች በሚል እንድትጠበቅ አድርጓታል።
ሌላኛዋ በሪዮ ኦሊምፒክ 1ሺ500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችውና በርቀቱ የዓለም ክብረወሰን በእጇ ያለው ኢትዮጵያዊት አትሌት ገንዘቤ ዲባባም ለመጀመሪያ ጊዜ በዘንድሮው አምስተርዳም ማራቶን እንደምትሳተፍ ታውቋል። የ31 ዓመቷ የመካከለኛና ረጅም ርቀት ውድድሮች ኮከብ አትሌት ገንዘቤ እ.አ.አ በ2015 የቤጂንግ ዓለም ቻምፒዮና በምትታወቅበት ርቀት የዓለም ክብረወሰንን በመስበር ብቃቷን ስታስመሰክር በዓለም አትሌቲክስ ምርጥ አትሌትነት ምርጫም አሸናፊ መሆን ችላለች። ፈጣኗ አትሌት ለረጅም ጊዜ ከውድድር ርቃ የቆየች ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ከምትታወቅበት የመካከለኛ ርቀት ሩጫ ወጥታ በአምስተርዳም ማራቶን ረጅሙን የጎዳና ላይ ሩጫ ‹‹ሀ›› ብላ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ትገኛለች። አልማዝና ገንዘቤ በአስደናቂ ብቃት ላይ በነበሩበት ወቅት በተለይም በ5ሺ ሜትር ብርቱ ተፎካካሪና ተቀናቃኝ እንደነበሩ አይዘነጋም። ሁለቱ አትሌቶች አሁንም በሌላ የውድድር መስክ የሚያደርጉት ፉክክር የዘንድሮውን የአምስተርዳም ማራቶን ከወዲሁ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።
ከሁለቱ ከዋክብት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተጨማሪ በግማሽ ማራቶን የተሻለ ልምድ ያላት አትሌት ፀሐይ ገመቹም በዚህ ውድድር ላይ ተፎካካሪ መሆኗን ያረጋገጠች አትሌት ናት። ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ከመግባቷ አስቀድሞ በረጅም ርቀት የመም ውድድሮች ላይ ተፎካካሪ የነበረችው ፀሐይ፤ እ.አ.አ በ2019ኙ የዶሃ ዓለም ቻምፒዮና አገሯን በ5ሺ ሜትር በመወከል አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። በዚያው ዓመት በተካሄደ የአገር አቋራጭ ውድድር ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ በቶኪዮ ኦሊምፒክም በ10ሺ ሜትር ተካፋይ ነበረች። በግማሽ ማራቶን ውድድሮች ተሳትፎዋም 65.01 የሆነ ፈጣን ሰዓት አላት። በአምስተርዳም ማራቶን ደግሞ ከአገሯ እንቁ አትሌቶች ጋር ማራቶንን የምትሮጥ ይሆናል።
በወንዶች በኩል በሚካሄደው ውድድር ደግሞ በርቀቱ ከፍተኛ ልምድ ያለው ኢትዮጵያዊ አትሌት ለሚ ብርሃኑ እንደሚሮጥ አወዳዳሪው አካል አስታውቋል። ከ10 ዓመት በላይ ማራቶንን የሮጠው ይህ አትሌት ትልቅ ትኩረት አግኝቷል። ኬንያዊው አትሌት ቲተስ ኪፕሩቶ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ሁለቱ አትሌቶች እርስ በእርሳቸው ለአሸናፊነት ከሚያደርጉት ፉክክር ባለፈ ክብረወሰን ሊያሻሽሉ እንደሚችሉም ከወዲሁ ተገምቷል። የቦታው ክብረወሰን 2.03.39 ሲሆን፤ እ.አ.አ በ2021 በኢትዮጵያዊው የዓለም ቻምፒዮን ታምራት ቶላ ባለፈው ዓመት የተያዘ ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2015 ዓ.ም