ልጆች እንዴት አላችሁ፤ አዲስ ዓመት እንዴት አለፈ? እርግጠና ነኝ ጥሩ ነው ብላችሁኛል። ምክንያቱም በዓሉን ቤተሰብ በመጠየቅ፤ የእንቁጣጣሽ ጭፈራዎችን በመጨፈርና ይህንን እድል ያላገኛችሁ ደግሞ ስዕሎችን በመስራት ለጎረቤት በመስጠት አሳልፋችሁታል። ይህ ደግሞ ሁለት አይነት ገጸ በረከትን ይዞላችሁ ይመጣል። የመጀመሪያው ምርቃትን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ገንዘብ አስገኝቷችኋል። ለመሆኑ ልጆች ያገኛችሁትን ገንዘብ ምን ልታደርጉበት አሰባችሁ? መቼም ከረሜላ በላንበት አትሉኝም። ይህን ካደረጋችሁ ትክክል አይደለም። ገንዘቡ ለብዙ ነገር ይጠቅማችኋል። በተለይም አሁን የአዲሱን ዓመት ትምህርት የምትጀምሩበት ጊዜ ላይ ናችሁና እስኪሪብቶ፣ ደብተር ሊገዛላችሁ ይችላል። ይህንን አደረጋችሁ ማለት ደግሞ በትንሹም ቢሆን ቤተሰባችሁን አገዛችሁ ማለት ነው። ስለዚህም ማድረግ ያለባችሁ ይህንን ብቻ ነው።
ልጆች ቤተሰብ ለእናንተ ብዙ ነገሩን የሚሰጥ ነው። አዲሱን የትምህርት ዘመን ስትጀምሩ ከሌሎች ጓደኞቻችሁ እንዳታንሱባቸው የቻሉትን ሁሉ ያደርጉላችኋል። በዚህም ይህ ወር ብዙ ወጪ የሚያስወጣቸው ነው። እናም እናንተ በትንሹም ሆነ በትልቁ ነገር ካላገዛችኋቸው ይቸገሩባችኋል። ስለሆነም ገንዘብ አጥፊ ሳይሆን ቤተሰቦቻችሁን ደጋፊ መሆን አለባችሁ። ከዚያም በተጨማሪ ይህ ካልተገዛልኝ እያላችሁ እንዳትጨቀጭቋቸው። ምክንያቱም ካላችው ለእናንተ የማይሰጡት ነገር የለም።
ሌላው ልጆች በዚህ አዲስ የትምህር,ት ዘመን ማድረግ ያለባችሁ ነገር ጎበዝ ተማሪ መሆን ነው። ያለፈው ዓመት ውጤታችሁ ደስተኛ ያላደረጋችሁ ከሆነ እርሱን ለማሻሻል የተለየ ጥረት ማድረግ አለባችሁ። ለዚህ ደግሞ ገና ትምህር ስትጀምሩ ጀምሮ ማንበብ መጀመር ነው። ነገ ደግሞ እንደአገር አቀፍ ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ ነው። ስለዚህም በአዕምሮም ዝግጁ ሆናችሁ በትምህር ገበታችሁ ላይ መገኘት ይኖርባችኋል። በእርግጥ ደስተኛ ሆናችሁ ወደ ትምህርትቤት እንደምትሄዱ አስባለሁ። ምክንያቱም ብዙ የናፈቃችኋቸው ነገሮች አሉ። አንዱ የትምህርትቤት ጓደኞቻችሁ ናቸው። ሌላው መምህራንና የትምህርትቤቱ ቅጥር ግቢ ሲሆን፤ ይህንን ሁሉ ናፍቆታችሁን ለመወጣት ወደዚያ ታመራላችሁ።
ልጆች መናፈቃችሁ ትምህርታችሁም ላይ መኖር አለበት። ‹‹ኤጭ›› ትምህርት ተጀመረ እንግዲህ ማለት የለባችሁም። ልክ የውጪውን አየርና የምድሪቱን ልምላሜ እንዲሁም የጓደኞቻችሁን ማግኘት እንደምትናፍቁት ሁሉ የትምህርትንም መጀመር በዚያው ልክ ጓጉታችሁለት መግባት አለባችሁ። ያን ጊዜ ውጤታማና ጎበዝ ተማሪ ትሆናላችሁ። የሚበልጣችሁም አይኖርም። ምክንያቱም ለውጤቱ ሲባል ማንበብን፣ ትምህርትን በአግባቡ መከታተልን፣ የቤት ሥራ መስራትን ታዘወትራላችሁ።
ልጆች ሌላው ማድረግ ያለባችሁ ነገር ምን መሰላችሁ ? ከክረምት ልምዳችሁ መላቀቅ ነው። ክረምቱ ብርድ በመሆኑ ከአልጋችሁ ቶሎ አትነሱም። ይህ ደግሞ ማንበብ፣ የቤት ሥራ መስራትና ሌሎች ተግባራትን እንዳትከውኑ ያደርጋችኋል። በተለይም በሰዓቱ ትምህርትቤት ለመድረስ እንድትቸገሩ የሚያደርግ ነው። ከዚያም ውጪ ሰዓቱ ደረሰ በሚል ስትፋጠኑ የምትረሷቸው ነገሮች እንዲበራከቱ ያደርጋል፤ ንጽህናችሁን ጠብቃችሁ እንዳትወጡ እንቅፋት ይሆናል።
ሌላው ከክረምት ባህሪ መተው ያለበት ነገር በጨዋታ ረጅም ጊዜን ማሳለፍ ነው። እረፍት በመሆናችሁ የተነሳ ብዙ ሰዓታችሁን በጨዋታ ታሳልፋላችሁ። የሚቆጣችሁም አይኖርም። ስለሆነም ይህንን ልምድ መተው ካልቻላችሁ ትምህርታችሁ ላይ በብዙ መልኩ እንቅፋት ይፈጠራል። ምክንያቱም በጊዜ ገብታችሁ የምታደርጓቸው ነገሮች በሙሉ ያቆማሉ።
ልጆች ይህንን ስል ግንየክረምት ልምዶች በሙሉ እርግፍ ተደርገው መተው አለባቸው ለማለት አይደለም። መቀጠል ያለባቸውም ልምዶች ይኖራሉ። ለምሳሌ፡- በክረምት እውቀታችሁን ሊያዳብሩና ተሰጥኦዋችሁን ሊያወጡ የሚችሉ ተግባራትን ስትከውኑ ከቆያችሁ መቆም የለባቸውም። ከትምህርታችሁ ጋር በማይጣረስ መልኩ ማስኬድ አለባችሁ። በተጨማሪም ትምህርቱ እንዲደግፈው አድርጋችሁ ልታስቀጥሉት ትችላላችሁ። ይህ ሲባል ለአብነት የሳይንስ ክህሎታቸውን ለማዳበር ሲሉ ኤሌክትሮኒክሶችን ፈታቶ በመገጣጠም፣ የተለዩ የፈጠራ ሥራዎችን መስራት አይነት ተግባራት በትምህርት የመደገፍ አቅም አላቸው።
በትምህርትቤት ውስጥ ስትሆኑ ደግሞ በእጅጉ ልታጎሏቸው የምትችሉበት አጋጣሚን ይፈጥርላችኋል። ምክንያቱም ደጋፊያችሁ ብዙ ነው። መምህራን ነገሮችን እንዴት እንደምትከውኗቸው ያሳዩዋችኋል። በክበባት ውስጥ ያሉ ጓደኞቻችሁም እንዲሁ በእውቀትና በልምድ ልውውጥ ይደግፏችኋል። ስለሆነም እነዚህን ልምዶቻችሁን ሁልጊዜ ይዛችሁ መዝለቅ አለባችሁ።
ይህንን ልምዳችሁን እያጎላችሁት ከሄዳችሁ በምንም አትጨናነቁም። በእውቀትም በገንዘብም ኃያል ትሆናላችሁ። ለልጆች አርኣያ የምትሆኑበትን እድልም ይሰጣችኋልም። ከሁሉም በላይ የራሳችሁ ጌታ ያደርጋችኋል። ማለትም በገቢ ማንም የማይደርስበት ልጅ ትሆናላችሁ። ምክንያቱም መሰረት የሆናችሁ የፈጠራ ባለቤት ናችሁና። ይህ ደግሞ ገጸ በረከቱ ከእናንተ አልፎ ለቤተሰባችሁና ለአገራችሁ ይደርሳል። ስለዚህም እነዚህን ሁሉ ለመያዝና ደስተኛ ሆናችሁ ለመቀጠል ካሰባችሁ መልካሙን ማጎላት፤ ተው የተባላችሁትን ማቆምና በትምህርታችሁ ጠንካራ ተማሪ መሆን ይኖርባችኋል።
አዲሱን የትምህርት ዘመን ስትጀምሩም ሌላ ብታደርጉት የምለው ነገር አለኝ። ይህም ያላችሁን ለተቸገሩት ማካፈል ነው። ለምሳሌ፡- አዲስ የደንብ ልብስ የተገዛላችሁ ልጆች የቆየውን ለሌላቸው መስጠት፤ ትርፍ እስኪርብቶና እርሳስ እንዲሁም ደብተር ያላችሁም እንዲሁ ለተቸገሩት ማካፈል የእናንተ ድርሻ ይሆናል። ይህንን ስታደርጉ ግን አንድ ነገር አትርሱ ለቤተሰብ ማሳወቅን። ምክንያቱም ሊቆጧችሁ ይችላሉ። ነግራችኋቸው ካደረጉት ግን ምንም አይሏችሁም። ይልቁንም ተጨማሪ ያላያችሁትን ነገር ሊያደርጉላችሁ ይችላሉ። እናም አዲሱ የትምህርት ዓመት አዲስ እንዲሆንላችሁ በለጋስነት፤ በናፍቆትና በደስታ ግቡበት። መልካም የትምህርት ዘመን በመመኘት በቀጣይ በሌላ ጉዳይ ላይ እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2015