መላ የኢትዮጵያውያን ህዝብ በዚህ ዓመት በሄድኩበት ስፍራ ሁሉ በፍቅር፣ በደስታ፣ ከጎንህ ነን በሚል ስሜት የደገፋችሁኝ ወገኖቼ እንዲሁም ሰኔ 16 የተሰነቀልኝን የሞት ድግስ የሞታችሁልኝ፣ የቆሰላችሁልኝ፣ የደማችሁልኝ ወገኖቼ፤ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሎሳንጀለስ፣ በሜኒሶታ፣ ከመላ አውሮፓ የተውጣጣችሁ፤ በፍራንክፈርት በዚያ ብርድ ሙሉ ቀን መሪያችን ይመጣል እናደምጠዋለን ብላችሁ ለዘመናት ተለያይታችሁ ከነበራችሁበት ያ አስፈሪ የተራራቀ ስፍራ ድልድይ በመገንባት በአንድ ላይ ኢትዮጵያ እያላችሁ ያዜማችሁ ዲያስፖራ ወገኖቼ በሙሉ ያለ እኔ ኢትዮጵያ፤ ያለ እኔ ኢትዮጵያውያን መኖር ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ያለ እናንተ ምንምና የማልረባ ነኝ።
ኢትዮጵያዊነት ዘመም ካለበት ቀና እናድርገው የሚለውን ፕሮጀክት አብረን ስንጀምር ኢትዮጵያዊነት ታክቲክ ወይም ቴክኒክ መሆን አይችልም። ኢትዮጵያዊነት የማይቆራረጥ ፏፏቴ፤ የማይፈረካከስ አለት፤ የነበረ የሚኖር ድንቅ ምስጢር መሆኑን በመገንዘብ ጭምር ነው። የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለውጡ እንደ ውሃ ፈሳሽ፤ እንደ እንግዳም ደራሽ የመጣ አልነበረም።
ብዙዎች የሞቱለት፤ የተገረፉለት፣ የታሰሩለት፣ የተሰደዱበት፣ ያለቀሱበት፣ የፀለዩበት፣ የሁላችን ድምር እንጂ የጥቂት ግለሰቦችም አልነበረም። ይህ በብዙዎቹ ዋጋ የመጣውን ለውጥ በተባበረ ክንድ ፤ በመደመር ሀሳብ መጠበቅና ማስቀጠል ከመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚጠበቅ አደራ ይሆናል። ባሳለፍነው አንድ ዓመት ሺዎች ተፈቱ ከቂሊንጦም ከካይሮም፤ የተለያዩ ተገናኙ፤ እንዳይወጡ የታገዱ፣ እንዳይገቡም የታገዱ እገዳው ተነሳላቸው።
የሚታኮሱ አፈሙዝ አዘቅዝቀው ለሰላም ወደ ሀገራቸው ገቡ፤ የሚሰጉም እፎይ አሉ። አምና በዚህ ጊዜ የሀገሪቱ ቀጣይነት ልጡ የተራሰ፤ ጉድጓዱም የተማሰ ይመስል ነበር። ተንሸራተን እንዳንወድቅ፤ ገብተንም እንዳንቀበር በሰጋንበት ጊዜ በኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድና በፈጣሪም እርዳታ ያ ክፉ ጊዜ፣ ያ ጨለማ ተገፎ ለሁላችንም የፌሽታ፣ የደስታ ብርሃን እንደመጣ መዘንጋት አለማመስገንም ተገቢ አይሆንም።
ቀደም ሲል የጥበብ ሰዎች በግጥም፣ በመነባነብ እንዳሉት ፖለቲካችን ባልተሟሸ ጀበና እንደተጣደ ቡና በረባ ባልረባ ቱግ ቱግ የማለት ባህሪይ አለው። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ ህዝብ ዝምታው እንደ ሬሳ፤ ቁጣው እንደ አንበሳ፤ ሲታገስ እንደ እግዜር፤ ሲነሳበትም እንደነብር መሆኑን ማሰብ ይኖርብናል። ዝም ሲል የሞተ እንዳይመስለን፤ ሲቆጣም ይቅርታን የማያውቅ እንዳይመስለን።
በዚህ በዝምታና በቁጣ መካከል ባሉ ህዝቦች ለውጥ ሲታከልበት የሚገጥመውን ፈተና በጋራ አይተነዋልና ልተርከው አልሻም። ተርቦ የከረመ ሰው መጀመሪያ ያገኘውን ዳቦ በተለየ ፍቅርና አድናቆት እንደሚጎርሰው ሁሉ ለውጡን በአንድ ልብ ከጎረስን በኋላ ርሀባችንን አስታግሰን የዳቦ ከለር ጣዕምና ማጣቀሻ እንደሚመርጥ ርሀብተኛ አሁንም ግራ ቀኝ መማተራችንና መፈለጋችን ሰዋዊ ባህሪ ነውና እንደ እንግዳ ባህሪ የማናየው ነው።
ነገር ግን የጠገበን ሰው ደረቅ ዳቦ ብቻ ሳይሆን ጣፋጭ ከጎኑ ማስቀመጥ ግዴታችን መሆኑን ተገንዝበን ለህዝባችን የባለፈውን ድል በመናገር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ድሎችን በማስመዝገብ ኢትዮጵያውያንን ዳግም እንደምናኮራ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ውድ ኢትዮጵያውያን፤ ለውጡ እንደ ጤዛ ነው። ታይተው የሚጠፉ ችግር ፈጣሪዎች ያመጣል። ነገር ግን ዝናቡን ፈርተን ክረምቱን ማስቀረት አይሆንልንም። ዝናቡ አፈር ይወስዳል፤ ያጓራል፣ ይረብሻል። የዛሬውን ዝናብ ማለቴ አይደለም።
የዛሬው ዝናብ የአንደኛውን ዓመት ድል አብሳሪ ሆኖ ለአዲስ አበቤዎች የተረጋገጠ መሆኑን ስለማውቅ። ለውጥ የሚያከብደው ባልተለወጠ ባህል ሲሆን ነው። ለውጥ የሚያስቸግረው ባልታደሰ ተቋም ሲጀመር ነው። ለውጡን ስንጀምር ሀሳብ፣ ለውጡን ስንጀምር የሚያሻግር የመደመር ፍልስፍናን ብናበስርም ባልተለወጠ ባህልና ባልተለወጠ ተቋም ነውና መንገራገጩ አይቀሬ ነው።
ለዚህም ሲባል ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችን አይተኬ ሚና የሚጫወተውን የምርጫ ቦርድ ስናደራጅ ከአንዴም ሁለቴ ታስራ ለፍትህ በጀግንነት ለመላው ኢትዮጵያ አርዓያ የሆነችውን ብርቱካን ሚዴቅሳን ያመጣነው። የፍትህ እጦት ኢትዮጵያውያንን እንዳንገሸገሸ ስለምናውቅ እናት፣ እህት፣ ሚስት ሆና ፍትህ የሚሸቅጡትን በመለየት፣ በማስተማር ለማንም ዝቅ ሳትል በህግና ህግ ብቻ ፍትህን ለኢትዮጵያ እንድታመጣ ወይዘሮ መአዛን ለፍትህ ሥርዓት እንዳመጣን ይታወቃል።
የጸጥታ ተቋሞቻችን ላለፉት ዓመታት በጀግንነት የፈጸሙት ገድሎች እንደተጠበቁ ሆነው የሚነሳባቸውን ስሞታዎች ለመቅረፍ በተለየ ትኩረት ከሠራንባቸው የሪፎርም ሥራዎች አንዱ ኤስ ኤስ አር የሚባለው በሴክዩሪቲ ሰርቪስ ላይ አተኩሮ የሠራው መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ደህንነትን የሚጨምረው ነው። እንዲሁም የኢትዮጵያ ግማሽ አካል የሆነውና ኢትዮጵያውያንን የሚሸከሙ ሴቶች በዋናው የሥልጣን ጥግ የካቢኔ ግማሽ ሆነው ለኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም አስተማሪ የሆነ ድርጊትም የፈጸምነው በዚሁ ዓመት ነው።
ኢኮኖሚን በሚመለከት በተለያዩ ምክንያቶች በዝርዝር ሳንገልጽላችሁ የቆየን ቢሆንም ዛሬ አንደኛ ዓመታችንን ስናከብር ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በኩራት ለመግለጽ የምፈልገው ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ወደ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ በብድር፣ በእርዳታ በሪሚተንስና በሰርቪስ 13 ቢሊዮን ዶላር ማምጣት ችለናል።
ውድ ኢትዮጵያውያን እንድትገነዘቡ የምፈለገው ላለፉት መቶ ዓመታት በሰባት ወር 13 ቢሊዮን ዶላር አምጥታ አታውቅም። ይህን ማድረግ ባንችል ኖሮ የነበርንበት አዘቅት በቀላሉ መሻገር የምንችለው አልነበረም። በርካታ ኤሊሲዎች ተከፍተው የግሉ ዘርፍ ከውጭ ሊያስገባ የሚፈልጋቸውን እቃዎች በምንዛሪ ችግር የነበረበትን ተግዳሮት ለመፍታት 8 ቢሊዮን ዶላር ለግሉ ዘርፍ በዚህ ሰባት ወር ያወጣን መሆኑን በኩራት ልገልጥላችሁ እወዳለሁ።
በዚሁ የኢኮኖሚ ግስጋሴያችን የዕዳ ጫናን ለመቀነስ ተጨማሪ እርዳታን ለማምጣት በጅምር የቀሩ ፕሮጀክቶቻችንን ለማስቀጠል በተለይ ዛሬ ስምንተኛ ዓመቱን ያከበረው የህዳሴ ፕሮጀክት የነበረበትን አደገኛ አደጋ ለመከላከልና ፕሮጀክቱን ለመጨረስ የሚያስችል ቁርጠኛ አመራር እንደሰጠንም በኩራት ልገልጥላችሁ እወዳለሁ።
ኢትዮጵያውያን ሰይፍ ያስፈልገናል። በአማራና በትግራይ ህዝቦች መካከል ሰይፍ ያስፈልገናል። ያ የሚያስፈልገን ሰይፍ ሰላም ይቅርታና ፍቅር ነው። በሶማሌና በአፋር ህዝቦች መካከል እንዲሁ ሰይፍ ያስፈልገናል። ሰላም ይቅርታና ፍቅር። በጌዲዮና በጉጂ ህዝቦች መካከል ሰይፍ ያስፈልገናል። ሰላም ይቅርታና ፍቅር። መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የለመድነውን አንገት የሚቀላውን ሰይፍ ሳይሆን የሰላሙን የይቅርታውንና የፍቅሩን ሰይፍ በመምዘዝ ኢትዮጵያን እንደጥንቱ ታላቅ የማድረግ ፕሮጀክት ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ እንጂ ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የማይጠበቅ መሆኑን እንዲሁ ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ።
ኢትዮጵያ ጤና እንድታድር ጎረቤትህ ጤና ይደር ይላሉ። ጎረቤትህ ብቻ ሳይሆን ወንድም የሆነው የኤርትራ ህዝብ ጥርስና ከንፈር መሆን ሲገባው ላለፉት 20 ዓመታት ዓይንና ቅንድብ ሆኖ መቆየቱ የማይዘነጋ ጉዳይ ነው። ለኢትዮጵያና ለኤርትራውያን እንደጥርስና ከንፈር በደስታ ጊዜ የሚከፈት በር በኀዘን ጊዜ የሚሸፈንና ውስጣዊ ማንነት እንጂ ጎን ለጎን እንደዓይንና ቅንድብ ተቀምጦ የማይተያይና የማይነካካ መሆኑ ተገቢ አልነበረም። ኢትዮጵያዊን ባለፈው ዓመት በርካታ ሰበር ዜናዎች በርካታ ድሎች ማግኘታችን መላው ዓለም የመሰከረው በመሆኑ እኔ እሱን በመደጋገም ጊዜያችሁን ላባክን አልፈልግም።
ያለፈው ዓመት ለውጥ ወይም ድሉ በለውጥ ብቻ የታጀበ አይደለም። ያ ሀሳብ ብዝሃነት ባለመዳበሩ ነጭ ወይም ጥቁር፤ ጥሩ ወይም መጥፎ በሚል ሁለት ጽንፍ የተከፈለው ፖለቲካችን ጠዋት ያ ሞገሰ እንደሁ ከሰዓት ፈጥፍጦ ይጥላል። ይህንን ክፉ ባህል በንግግርና በስድብ ታገል ሰይፉ እንዳለው በፌስቡክ ብቻ ብናበቃው መልካም ነበር። ነገር ግን ወገን ወገኑን እንዲሰደድ እንዲገደል እንዲቸገርም ጭምር አሳፋሪ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያውያን ሊያዩት፤ ሊሰሙት የማይፈልጉት ችግርም እንዲሁ ተስተናግዷል። ድሉን በጋራ እንዳመጣነው ሽንፈቱንም በጋራ ልንቀበለው ይገባል።
ከሁሉም የከፋው ደግሞ የወረስነው የሴራ ፖለቲካና መጠራጠር ነው። አቅፎ ማለፍ ሳይሆን ጥሎ ማለፍ የለመደው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በረባ ባረባው በሚቆሰቁሱ ነገሮች የራሱን ወገን ከማፈናቀል፣ ከጅምላ ጥላቻ፣ ስድብ፣ መገፋፋትና ተስፋ አስቆራጭ ዜናዎችን መስማት የቅርብ ጊዜ ዜናዎቻችን መሆናቸውንም ኢትዮጵያውያን ማስታወስ ይኖርብናል።
የሀገሬ ሰው ‹‹ባጭር ታጥቆ ጋሻ ነጥቆ ዘገር ነቅንቆ ይዋጋል አጥብቆ›› እንደሚለው ታላቅ ሀገር ይዘን ታናሽ እንዳንሆን፤ ጀግና ህዝብም ይዘን ሰነፍ እንዳንሆን። በአንድ ማዕድ ማብላትና መብላት ለዓለም ያስተማረ ህዝብ ጥላቻና ስድድብን፣ መፈናቀልና መገዳደልን ሌላው ዓለም በተረጋጋ ሁኔታ ወደመኖር የመጣውን አፍሪካ የሚያስተምር እንዳይሆንም ኢትዮጵያውያን በአንክሮ ልንመለከተው ይገባል።
ውድ ወገኖቼ የሚያኮራ፣ የሚነገርና የሚዘከር ታሪክ አለን። ነገር ግን በማይታወቅ ጊዜ የተወጋነው አንስቴዢያ እንድናንቀላፋ አድርጎናል። ሌሎች የአፍሪካ ወንድሞቻችን በቅኝ ገዢዎች ያሳብባሉ። እኛ በማን ማሳበብ እንደምንችል ባላውቅም ውድ ኢትዮጵያውያን እንንቃ ልላችሁ ግን እፈልጋለሁ። በኢትዮጵያ ወላጆች ልጆቻቸው ሙሉ ሰው እስኪሆኑ ማስተማርና ማሳደግ ወጋቸው ነው። ልጆች ሙሉ ሰው ሲሆኑ ደግሞ ወላጆቻቸውን በተራ መጦርም እንዲሁ ባህላቸው ነው። ዛሬ ግን ኃላፊነት በተሳነው በዚህ ትውልድ የሚፈጠሩ ልጆች ሲያድጉም ሲያረጁም የሚጦሩ እንዳይሆኑና የሚጦር ትውልድ እንዳንፈጥር እያንዳንዱ ዜጋ በማስተዋልና በአንክሮ እየሆነ ያለውን እንዲያስብ እፈልጋለሁ።
የልጆቻችን አብሮነት ዋጋ እንዳለው፣ በጋራ መኖር ክብር እንደሆነ፣ ኢትዮጵያን ያቆየናት በጋራ እንደሆነ፣ የወደፊት እጣ ፈንታዋም የልጆቿ መደመርና መሰባሰብ እንደሆነ ደጋግመን መናገርንና ደጋግመን ማስተማርን መሰልቸት የለብንም። የምንሰራውና የምንናገረው ሁሉ ኢትዮጵያችንን ትልቅ የሚያደርግና የሚያኮራ እንዲሆን ከአደራ ጭምር ልለምናችሁ እፈልጋለሁ።
እውቀታችን ጉልበታችን፣ ሀብታችን፣ ጊዜያችን ለኢትዮጵያ እድገት እንጂ ኢትዮጵያውያንን ለማፈናቀል እንዳይውል እንዲሁ አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ። የጀመርነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንጭጭ በመሆኑ እንጨቃጨቅ፣ እንነጋገር፣ እንወያይ ነገር ግን ንግግራችንና ውይይታችንን ከአደባባይ ወደ አዳራሽ እንመልስ። ንግግራችን የኢትዮጵያን ልማት፣ የኢትዮጵያን እድገት፣ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያቆይ እንዳይሆን እያለማን እንጨቃጨቅ፤ አንድ መሆናችንን ጥያቄ ውስጥ ሳናስገባ እንጨቃጨቅ።
መላው የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል፣ የጋምቤላና የሐረሪ ህዝብ እንዲገነዘብ የምፈልገው እኔ ዐብይ እባላለሁ አህመድ ካልተጨመረ ግን እኔን መለየት ያስቸግራል። ኦሮሞ ብሎ ኢትዮጵያ ካልተባለ፤ አማራ ብሎ ኢትዮጵያ ካልተባለ፤ ትግራይ ብሎ ኢትዮጵያ ካልተባለ፤ ሶማሌ ብሎ ኢትዮጵያ ካልተባለ፤ ያስቸግራል። ኦሮሞ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ኬንያም ስላለ ትግራይ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ኤርትራም ስላለ፤ አፋር ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ጅቡቲም ኤርትራም ሰላለ የአባታችንን ስም ጥለን ብቻችንን አንታወቅምና ኢትዮጵያ ሁሌም ኩራታችን ትሁን።
እጅግ የምወዳችሁና የማከብራችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ኢትዮጵያ ለማኝ ሀገር መሆኗን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ ድንቅ አርቲስት ፈጥረን እንደሆነ የለማኝ ሀገር አርቲስት መሆኑን መቀየር አይችልም። ድንቅ ሳይንቲስት ፈጥረን እንደሆነ የለማኝ ሀገር ሳይንቲስት መሆኑን መካድ አይችልም ። ጥበበኞች አሉን ባለሀብቶች አሉን ባለእውቀቶች አሉን ኢትዮጵያ ካልተለወጠች ግን የደሀ ሀገር ባለጥበብና ባለ እውቀት ስለሚያስብል ኢትዮጵያን ያልቀየረ በግል በዝርፊያም ይሁን በስራ የመጣ ማንኛውም ሀብት ከንቱ መሆኑን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ።
እየለመኑ ፉከራ እየለመኑም ቀረርቶ ሰለማያዋጣ በሰከነ መንፈስ ኢትዮጵያን እያሳድግንና እየቀየርን ከአደባባይ ወደ አዳራሽ የተቀየረውን ንግግርና ውይይት ብናመጣ ለስልጣኔ ለእድገት ወደፊት ለምናደርገው ጉዞ ጠቃሚ እንደሚሆን በዚሁ አጋጣሚ ላሳስብ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ ኢትዮጵያ ምትክ የሌላት ብቸኛ ሀገራችን ናት። እቺን ብቸኛ እናት አባቶቻችን እምዩ ብለው ይጠሯት ነበር ። እምዩ ኢትዮጵያን ከሚያፈርስና ከሚያጠፋ ከሚያደኸይና ከሚቆረቁዝ ተግባር ተቆጥበን በሰከነ በተደመረ በሚያዘልቅና በሚያልቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት እቺን ሀገር በጋራ እንድንገነባ ጥሪዩን አስተላልፋለሁ።
አንድ ዓመት የመጣንበት ጉዞ የሚያስደምም የሚያስደንቅ ባለ ብዙ ድል እንደሆነ ሁሉ ያሉበት ችግሮችም እንዲሁ ዘርፈ ብዙ ናቸው። በሚቀጥለው አንድ ዓመት ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ አተኩረን ብንሠራ ብዬ ጥሪ ላቀርብላችሁ የምፈልገው የመጀመሪያው በይቅርታ በትዕግስት ጎንደርና መቀሌ፤ ባህርዳርና አዲግራት፤ ጅግጅጋና አዳማ፤ አሶሳና ጋምቤላ፤ እንደ ወንድማማች በጋራ እየዘመርን በማንግባባበት እየተወያየን ኢትዮጵያዊነትን የምናደምቅበት ዓመት እንዲሆንልን በታላቅ ትህትና ጥሪዬን አቀርባለሁ።
የጀመርነው ተቋማዊ ለውጥ ሁሉን አሟልቶ መሬት ረግጦ የኢትዮጵያውያንን ፍላጎት ሊያሟላ ባለመቻሉ መንግሥት ከሁሉ ነገር ቅድሚያ ሰጥቶ የጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም አጠናክሮ ገለልተኛ ነፃ ሁሉን ኢትዮጵያዊ በእኩል ዓይን የሚያገለግሉ ተቋማት የመገንባት ሥራውም ከሰላም ከይቅርታና ከፍቅር ቀጥሎ ግምት ሰጥተን ጊዜ ሰጥተን የምንሠራው ሥራ እንደሆነ ከወዲሁ ልገልፅላችሁ እፈልጋለሁ።
በኢኮኖሚ መስክ በርካታ የሚሠሩ ሥራዎች ያሉ ቢሆንም በተለይ ቱሪዝምን በሚመለከት በዚህ መስከረም በመጪው መስከረም የብሄራዊ ቤተ መንግሥት በሙዚየምነት መልክ ለመላው ኢትዮጵያ ከአስደሳች ሥራዎቹ ጋር ክፍት ይደረጋል።
ከመስከረም እስከ እዚያኛው መስከረም አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ እናደርጋለን የሚለው ፕሮጀክት ቢያንስ አንድ አራተኛውን ጨርሰን ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን። እነዚህን ሥራዎች ስንሠራ ከየክፍለ አገሩ ክልሉና ከተማው ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ቱሪስትነት ከመላው አፍሪካ፤ ከአፍሪካ ወንድሞቻችን በቱሪስትነት ከሌላውም ዓለም በርካታ ዜጎች እየመጡ በአዲስ አበባ ውስጥ ለወጣቶች የሥራ እድል ታሪካችንን ማንንታችንና ባህላችንን እና ባህላችንን በማወቅ በቱሪዝም ሴክተር ከፍተኛ እድገት እንደምናመጣ ተስፋ ተጥሏል። በግብርናው ዘርፍ ከሁሉ በላይ በትናንሽና በመካከለኛ መስኖ በዚህ ዓመት የጀመርናቸውን ሥራዎችና ጥናቶች አጠናክረን ፍሬያማ ሥራ እንደምንሠራ ከወዲሁ ልገልፅላችሁ እፈልጋለሁ።
ሌላው የትኩረት መስክ ማዕድን ዘርፍ ማጎልበትና የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት ሲሆን፣ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትብብር በአገራችን በምናረጋግጠው ሰላም የተቋማት ገለልተኛና ጠንካራ መንግሥት በመፍጠር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ወይም ባለሀብቶች ብዙ መስክ ውስጥ በመሰማራት ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩም ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ከወዲሁ ልገልፅላችሁ እፈልጋለሁ፡
የህግ የበላይነትን በሚመለከት የጀመርነው ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚያስፈልግ መሆኑን በፅኑ የምናምን ቢሆንም የህግ የበላይነት ማረጋገጥ የጀመርነውን ለመጨረስ የፍፃሜውንም ፍሬ ለመቋደስ ስለሚያግዝ ሁሉም ህግ የሚያስክብሩና ህግ የሚተረጉሙ አካላት ዘንድሮ ያሻሻልናቸው ህጎች እንደተጠበቁ ሆነው እያንዳንዱን ዜጋ ከጥቃት የሚከላከሉና ፍትህን በገንዘብ ሳይሆን ከፍርድ ቤት ደጅ ማግኘት የሚያስችሉ ሥራዎች በጠንካራ መሰረት ላይ የሚጣሉበት ጊዜ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። የተፈናቁ ዜጎች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ብቻም ሳይሆን ባሉበት እንዲጠናከሩም በከፍተኛ ጥረት መንግሥት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን ይሠራል።
በሚቀጥለው ዓመት በምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሚኖረን ምርጫ ፍፁም ነፃና ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ ዳግም ለአፍሪካ አዲስ ትምህርት ለመስጠት አርዓያ የምንሆንበት እንደሚሆን የላቀ ተስፋዬን ኢትዮጵያንም በዚያው ስሜት እንዲጠባበቁ ልናገር እፈልጋለሁ። ባለፈው ዓመት ስትጠብቁ ቢሆን ስትሉ የጎደለ ያልተሟላ ካለ ቆሜ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ትህትና ኢትዮጵያውያንን ዝቅ ብዬ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ።
ቁጣችሁ ተግሳፃችሁ ለእኔ ሽልማቴ ነበር። ኢትዮጵያውያን ካልጠበቁ እንደማይቆጡ ስለማውቅ። በእኔ ተስፋ ጥላችሁና ቢያደርግ ብላችሁ ፈቅዳችሁና ወዳችሁ የጎደለ ነገር ካለ በዳተኝነትና በእንዝላልነት ሳይሆን ምናልባት ክእውቀት ማነስና ከሁኔታዎች አለመመቸት እንጂ ያለኝን ጊዜ ሁሉ በታማኝነት ያገለገልኳችሁ መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ ልገልፅላችሁ እፈልጋለሁ።
የእኛ ሩጫ ሁሉም የአገራችን ህዝቦች ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስክ ምዕራብ እኩል ሆነው በነፃነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መፍጠር ነው። ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ትውልዷን ማንቃት ዘመም ያለችውን አገሬን ማቅናት እንጂ ከዚያ የተለየ ሸፍጥም ሃሳብም ተግባርም አልነበረንም።
ይህ ኢትዮጵያን ዘመም ካለችበት ቀጥ የማድረጉ ፕሮጀክት እናቶች ባትፅልዩ፤ ምሁራን ባትፅፉ፤ ወጣቶች ባታበረታቱ ፤አርሶ አደሮች ባትተጉ፤ ዲፕሎማቶች ተግታችህ ባትስሩ፤ ወታደሮች ድንበራችሁን ባትጠብቁ እንደማይሳካ አውቃለሁ። ላደረጋችሁት ሁሉ ወሮታውን ፈጣሪ ይክፈላችሁ።
ሁሌም እንደምለው አሁንም ኢትዮጵያ የነበራትን ታሪክ እድሳ ለአፍሪካና ለዓለም ምሳሌ ሆና ያበበ ፍሬዋን አፍሪካውያንን በመመገብ አርዓያ መሆኗን እንደምትቀጥል በታላቅ ኩራት ልገፅላችሁ እፈልጋለሁ። ዲያስፖራዎች የጀመራችሁት አገራችሁን የመርዳት ለአገራችሁ የመቆም በአንድ አዳራሽና እስታዲየም መሰባሰብ በሁኔታዎች እንዳይቀያየር ስሜታችሁን ገዝታችሁ ኢትዮጵያን አግዝፋችሁ ተደምረን በውጭና በአገር ውስጥ ያለን ዜጎች ይህችን ታላቅ አገር መልሰን ታላቅ እንድናደርግ በትህትና እለምናችኋለሁ። ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ።
አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011