በሰሜን ኢትዮጵያ በአሸባሪው ትህነግ የተጀመረው ጦርነት እነሆ ሁለት ዓመታት ሊሆነው ነው:: በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ብዙ ሕይወት ጠፍቷል፤ ብዙ ንብረት ወድሟል:: የጦርነቱ ዳፋ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ተርፏል::
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሰላም ድምጾች መስማት የተቻለ ቢሆንም ከብድኑ ጸረ ሰላም ባህሪ አንጻር አሁንም የጥይት ድምጾች ይሰማሉ:: ዜጎች ከጦርነትና ከጦርነት ድምጾች የተነሳ ለሞት እና ለመፈናቀል እየተዳረጉ ነው። በውድመት ላይ ውድመትም እየተፈጠረ ነው::
አሸባሪው ትህነግ በለኮሰው ጦርነት የትግራይ ሕዝብ ሰርቶና አርሶ እንዳይበላ በማድረግ ለከፋ የምግብ እጥረትና ጠባቂነት ተዳርጓል፤ በህዝቡ ስም የሚገቡ የእርዳታ ድጋፎችን ከህዝቡ ጉሮሮ እየተናጠቀ ለጦርነት እያዋለም ይገኛል። ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ለትግራይ ህዝብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል።
ቡድኑ የትግራይ ወጣቶችን ‹‹በክንዳችን፣ በጀግንነታችን…›› በሚል ርካሽ ፕሮፓጋንዳ እያሰከረ ለከፋ እልቂት ከመዳረግ ባለፈ ፤ጤነኛ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖረው በክልሉ ህዝብ ላይ ግፍ እየሰራ ይገኛል።
ለመሆኑ ግን ጀግንነት ማለት ምን ማለት ይሆን?
ጀግና ማለት ለራሱ የሚኖር ማለት አይደለም:: ጀግና ማለት ለሌሎች የሚኖር ነው:: ራሱ ተጎድቶ፣ የግሉን ቂምና በቀል ይቅር ብሎ ለሌሎች ሰላም የሚኖር ነው:: ራሱን ሰውቶ ሌሎችን ማዳን እንጂ ራሱን አድኖ ሌሎችን ማሰዋት ማለት አይደለም:: ሌሎችን እያስገደሉ ራስን ማዳን ራስ ወዳድነት ነው:: ለጅግንነት ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ደግሞ የወታደሮች መስዋዕትነት ነው::
ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ‹‹የማይጻፍ ገድል›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ለጀግንነት ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አንድ ታሪክ ጽፈዋል:: ይህ ታሪክ ዶክተር በድሉ በደርግ ዘመነ መንግሥት ወታደር ሆነው ያጋጠማቸው ነው:: ታሪኩን በጥቂቱ እንጥቀስ::
‹‹…ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን፣ 1976 ዓ.ም፣ ከጠዋቱ ልክ በሶስት ሰዓት…›› ብሎ ይጀምራል ታሪኩ::
ሥልጠና ላይ እያሉ አንድ ወታደር ለምልምል ወታደሮች የቦምብ አወራወር እያሳያቸው ነው:: በማሳየት ሂደት ውስጥ በተፈጠረ ቴክኒካል ስህተት ቦምቡ የሚፈነዳበት ደረጃ ላይ ደርሷል::
‹‹..‹ዞር በሉ! ዞር በሉ!› በግራ እጁ ቀለበቱ የተነቀለለትን ቦንብ እንደያዘ፣ እንድንሸሽ ምልክት እያሳየን፣ በከፍተኛ ድምጽ ጮኸ:: ‹እባካችሁ ዞር በሉ! . . . ባላችሁበት ተኙ!› እየጮኸ ምልምሎች እንደጉንዳን የሚርመሰመሱበትን ሜዳ ቃኘ::
የተወሰኑት ግን በምክትል መቶ አለቃው ተደጋጋሚ ጩኸት ግራ ተጋብተው፣ ለመሸሽ፣ ለመቀመጥ፣ ለመተኛት እየሞከሩ ነው:: ቀለበቱ በወለቀ ቦምብ ፊት የሕይወት ጊዜ የሚለካው በሰከንድ ሽርፍራፊ ነው::
ምክትል መቶ አለቃ ላቀው በዛብህ ቦንቡን እንደጨበጠ ለሶስተኛ ጊዜ፣ ‹ዞር በሉ! ባላችሁበት ተኙ!› አለና ጮኸ:: ጩኸቱ ተስፋ መቁረጥም የተቀላቀለበት ነበር:: የሚናገረው ለእኛ … አጠገቡ ላለነው ይሁን እንጂ፣ አሻግሮ የሚመለከተው በሜዳው ላይ እንደአሸን የፈሰሱትን ምልምሎች ነው::
ቦምቡን በየትኛውም አቅጣጫ ቢወረውረው ምልምሎችን ይገድላል:: ቦምቡን የቱንም ያህል ርቀት ቢወረውረው ሰው ሳይገድል ማረፍ አይችልም::
ጀግናው ወታደር፣ ቆራጡ፣ ከራሱ ይልቅ ለሌላው አሳቢው፣ የራሱን ሕይወት ከማዳን ይልቅ የነገ አገር ተረካቢዎችን ማዳን የፈለገው ጀግና ግን ይህን የቆራጥ ጀግና ውሳኔ ወሰነ!
ቀለበቱ የወለቀውን ቦምብ በሁለት እጆቹ ጭብጥ አድርጎ ይዞ ሆዱ ላይ በማስደገፍ ለጥ ብሎ ተኛበት፤ ቦምቡ ፈነዳ!
ምልምል ወታደሮች ወደፈነዳበት ዘወር ሲሉ ምክትል መቶ አለቃ ላቀው በዛብህ የለም:: ቦምቡ የፈነዳበት ቦታ ላይ የሚታየው የተቃጠለ ልብስ እና የተቆራረጠ የተጠበሰ ብጥስጣሽ የሰውነት ክፍል ብቻ ነው:: መቶዎችን ምናልባትም ሺዎችን ሊያወድም የነበረ ቦምብ በአንድ ጀግና ሰው መስዋዕትነት ተጠናቀቀ::
እነሆ ዛሬ ድረስ ምክትል መቶ አለቃ ላቀው በዛብህ በየጋዜጦችና መጽሔቶች፣ በየመድረኮች የጀግንነት ምሳሌ ተደርጎ ይጠቀሳል:: ጀግንነት እንዲህ ነው፤ ከራስ በላይ ለሌሎች ማሰብ:: ወታደሩ ቦምቡን አርቆ ቢጥለው ራሱ ይተርፍ ነበር፤ ዳሩ ግን ሌሎች ብዙ ሰዎች ይሞቱ ነበር:: የአንድ ሰው መሞት ሺዎችን እንደሚያድን የወሰነው በዚያች ሽርፍራፊ ሰከንድ ውስጥ ነው::
ስለጀግንነት የሚፎክሩ ተፋላሚ ኃይሎች እንዲህ አይነት ሌሎችን የማዳን ጀግንነቶችን ልብ ሊሉ ይገባል:: ከራስ በላይ ለሌሎች ማሰብ:: ዛሬ በሀገር ውስጥ ሆነ ከሀገር ውጪ ያሉ የቡድኑ አመራሮች የጦርነቱ ዋነኛ ተጠቂዎች አይደሉም ። ‹‹በክንዳችን፣ በጀግንነታችን…›› እያሉ የሚያስፈጁት የድሃውን የትግራይ ታዳጊ እና ወጣት ነው::
ከፍ ባለ እብሪት የተነጠቁትን ስልጣን ለማስመለስ ላለፉት አራት አመታት የሄዱባቸው መንገዶች ብዙዎችን የትግራይ ታዳጊዎች ቀጠፈ፣ ንብረት አወደመ:: ይሄ የጥቂቶችን ስልጣን ለማራዘም የሚካሄድ ጦርነት ውስጥ ያለው የጀግንነት ትርክት ምንድን ነው? የትርክቱ መነሻና መድረሻስ?
ለሕዝብ ማሰብ ማለት የራስን የግል ፍላጎትና ምቾት ትቶ ለሚቆረቆሩለት ሕዝብ ዋጋ መክፈል ነው::ይህንን እውን ለማድረግ የሚደረግ ትግል ነው ጀግናና ጀግንነትን የሚጠይቀው:: ከዚህም በላይ ጀግንነት ገዳይነት ብቻ አይደለም:: ጀግንነት ለሚቆረቆሩለት ሕዝብ ፈቅዶ መሞትንም ይጠይቃል። ከእብሪት ወጥቶ ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ መስጠት ጀግንነት ነው::
በነገራችን ላይ ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ ለመስጠት የተፋላሚዎች ብቻ ሳይሆን የሕዝቡም ሚና ቀላል አይደለም:: ልክ ለጦርነቱ ‹‹ደጀን›› እንደሚባለው ሁሉ የሰላምም ደጀን ያስፈልጋል:: የሰላም ደጀን ማለት ሰላም ፈላጊውን አካል መደገፍና ጦርነት ፈላጊውን አካል መውቀስና መገሰፅ ማለት ነው:: ሰላምን ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ብቻ መጠበቅ የለብንም:: ከእኛ ከሕዝቦች የሚጠበቀው ጀግንነት መግደል ብቻ ሳይሆን ጥፋትን አምኖ መሸነፍን መቀበልም ጀግንነት መሆኑን መቀበል ነው::
የትግራይ ሕዝብም ጀግንነት ማለት ለጦርነት ብቻ መፎከር አለመሆኑን ለቡድኑ ሊነግረው ይገባል:: ጥፋተኝነቱንና ፀብ አጫሪነቱን ሊነግረው ይገባል:: ጀግንነት ማለት ለሕዝቡ ሲል ጥፋተኞችን አሳልፎ መስጠት መሆኑን ሊነግረው ይገባል:: የራስን ጥቅምና የራስን ፍላጎት ወደ ጎን ትቶ ለሌሎች መኖርና ማሰብ ከተጀመረ ሰላም ይመጣል፤ ጀግንነት የምንለውም ይህንን ነው!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2015