የሰው ልጅ ለመኖር በርካታ ጥረቶችን ያደርጋል። ለመኖር ብሎም ጥሪት ለማፍራት ጥሮ ግሮ ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ ይፈልጋል። አንዳንዱ ተምሮ ስራ ሲይዝ የመማር እድል ያላገኘው ደግሞ በትንንሽ ስራዎች ላይ ይሰማራል፤ በንግድና በግብርናው አለሁ ብሎ ወደ ስራ ይገባል። በዛም አነሰ ሁሉም ኑሮውን ለማሸነፍ ይታትራል። ተምሮ ስራ ያገኘውም ሆነ በተለያየ ስራ የተሰማራው ለነገ ለውጥ ለማየት ተስፋ አድርጎ ይሮጣል።
በአብዛኛው ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ የተወለዱ ወጣቶችም የተሻለ የስራ እድል ለማግኘት ሲሉ የትውልድ ቀያቸውን ለቀው ወደ የሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ በመምጣት ስራ መፈለጋቸው የተለመደ ነው። በተለይም ከደቡቡ የሀገሪቱ አካባቢ የሚመጡ ልጆች ከህፃንነታቸው ጀምሮ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ይታያሉ። በመንገድ ዳር አነስተኛ ሚዛን አስቀምጠው “ተመዘን”‹‹ተመዘኚ›› የሚል ጣፋጭ ቃል ከሚያወጡት ህፃናት አንስቶ በጉልበት ስራ ላይ የተሰማሩት ወጣቶችም በብዛት ከዛው አካባቢ ነው የመጡት። ከይርጋለም አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ለስራ በሚል ምክንያት ከሚመጡት ወጣቶች መካከልም ወጣት ወሰን ለማ አንዷ ናት።
ታታሪዋ ወጣት
ወጣት ወሰን አዲስ አበባ በመጣችበት ጊዜ የመጀመሪያ ስራዋ በሰው ቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ መስራት ነበር። ለተወሰኑ አመታት በዚሁ ስራ ላይ ተሰማርታ ስትሰራ ከቆየች በኋላ ትንሽ ሳንቲም ሲጠራቀምላት የእራሴን ስራ መጀመር አለብኝ ብላ ትወስናለች። እቅዷን በፍጥነት ወደ ተግባር የቀየረችው ወጣት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሸለሞ ግቢ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ የጀበና ቡና ለመሸጥ ቦታውን ተከራይታ የሚያስፈልጋትን ግብአት አሟልታ ስራዋን ትጀምራለች። ቀን ቀንን እየወለደ በቡና ጠጡ የተጀመረው ስራ ቁርስም፤ የተቀቀለ ድንችም ሌሎችንም ፈጣን ምግቦች እያስከተለ ስራዋ እየሰፋላት ሄደ። ተወዳጅም ሆነና ደንበሾች እሷን ብለው መምጣት አበዙ።
ከእለት ጉርስና ከቤት ኪራይ የተረፋትን እቁብ እየጣለች አነስተኛ ሽሮ ቤት ለመክፈት ያቀደችው ይች ወጣት በጠዋት ተነስታ ሻይ፤ ቡናና ቁርስ ለማዘጋጀት ትጣደፋለች። ደንበኞቿ የሚረኩበት ጣእም ለማምጣት ተፍ ተፍ ስትል ነው የምታረፍደው። የቁርስ መስተንግዶ እንዳበቃ ምሳቸውን በልተው ቡና ለመጠጣት የሚመጡ ደንበኞቿ ቡና አጥተው እንዳይመለሱ እሱን በማዘጋጀት ስራ ላይ ትጠመዳለች። የምሳ ሰአቱ ግርግርና መስተንግዶ ከበቃ በኋላ ደግሞ ማምሻቸውን ትኩስ ድንች በሚጥሚጣ ለሚመገቡ ደንበኞቿ ድንች ጥዳ መምጣታቸውን በጉጉት ትጠባበቃለች።
በስራዋ ቀልድ የማታውቀው ወጣት ከፊቷ የማይጠፋ ፈገግታዋን ይዛ ሙሉ ቀን ስትደክም ትውላለች። በዚህ መካከል ነው እንግዲህ ህይወቷን ያስከፈላት አጋጣሚ የተፈጠረው።
የድካሟ ማረፊያ ክፉ ገጠመኝ
ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ ነበር። የምሳ ሰአት የቡና ደንበኞቿን ሸኝታ አረፍ ወደ ማለቱ ነበረች። ቀኑን ሙሉ ሲለፋ የዋለ ጎኗ ረሃብ ስለተሰማው የሚበላ ነገር ለመቅመስ ዙሪያ ገባዋን ብታይ ከተጣደው ድንች በስተቀር ምንም መመልከት አልቻለችም ነበር። የዛሬ ገበያ ጥሩ ነበር፤ አንድም የሰራችው ምግብ አልተረፈም። ተጥዶ በመንተክተክ ላይ ካለው ድስት ውስጥ አንድ ትኩስ ድንች ከድስቱ አውጥታ እንዲቀዘቅዝ ሰሀን ላይ አድርጋው ቀና ስትል አንድ ሰው ወደ ምትሰራበት በመሄድ “ቡና ስጭኝ” በማለት ተቀመጠ። እጅግ በጣም የተጣደፈ ይመስላል። “እሽ ቆይ ላሙቅልህ” በማለት ቡናውን በተያያዘ ከሰል የተሞላው ማንደጃ ላይ ጥዳ የራበውን ሆዷን ለማስታገስ ድንች ወደመላጡ ተመለሰች። ድንች እየላጠች ሳለ ”ለምን ቡናውን ቶሎ አትሰጭኝም” ብሎ ስድብ ጀመረ። “ አንዴ ይሙቅ አልኩህ” አለችው ትእግስት ማጣቱ እያበሳጫት። በመጮህና በመሳደብ ከተቀመጠበት ተነስቶ ድንች እየላጠችበት የነበረውን ቢላዋ እጇን ጠምዝዞ በመያዝ እና ጣቷን በመንከስ አስለቀቃት።
ቢላውን ከእጇ ላይ ካስለቀቃት በኋላ ቢላውን ጨብጦ በመያዝ ደረቷ ላይ ለመውጋት ይሞክራል፤ ወሰንም የስውየው ንዴት አስደንግጧት ዞራ ለማምለጥ ስትሮጥ ተከትሏት ከጀርባዋ ሲሰነዝር ላለመወጋት የአቅሟን ያህል ትታገላለች። ምን ብትውተረተር ረሀብና ስራ ያደከመው ሰውነቷን ግን በቀትር ከመጠባት ውርጅብኝ ማዳን አልቻለችም። ብዙ ታግላ የወደቀችውን የሃያ ስድስት አመት ወጣት ወሰን በወደቀችበት በተደጋጋሚ በሰነዘረው ቢላ የእግር ታፋዋ ላይ ወግቶ ለማምለጥ ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ተይዟል። ወሰንም በግርግር መካከል ወደ ህክምና መስጫ ቦታ በፍጥነት መድረስ አልቻለችም ነበር። ፖሊስ በአካባቢው ደርሶ ወጣቷ ወደ ህክምና ቦታ ስትደርስ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ብዙ ደም ስለፈሰሳት ህይወቷን ማትረፍ ሳይቻል ቀረ።
አሰራለሁ እለወጣለሁ ብላ ከቤቷ የወጣችው ወጣት የስራ ቦታዋ መጥፊያዋ ሆነ። የእራሷንም ሆነ የቤተሰቧን ህይወት ለማሻሻል ስትታር የነበረችው የጀበና ቡና የምትሰራው ወጣት ከህልሟ ሳትደርስ በአጭር ተቀጨች። ዛሬን እንደምንም ኖራ ነገን የተሻለ ለማድረግ ያቀደችው ዕቅድ በማይረባ ምክንያት በተራ ግለፍተኛ የተነሳ ለማንም ሳትተርፍ ቀረች። ምኞቷና ተስፋዋ ሁሉ እንደ ሀምሌ ደመና በኖ ቀረ።
ቡና ያሰከረው ነፍሰ ገዳይ
በመካከለኛ እድሜ ያለ ሰው ነው አቶ ገንዘብ ታምሩ። በኮንስትራክሽን የስራ ዘርፍ ተሰማርቶ ግንበኝነቱንም፤ ቀለም ቀቢነቱንም ሁሉንም ስራ የሚሞካክር ሁለገብ ባለሙያ ነው። ለወትሮው ማለዳ ተነስቶ ቡናውን ጠጥቶ ነበር ወደ ስራው የሚሄደው። ሰሞኑን ግን ስራ ጠፍቶ ቤት ከዋለ ሰነባብቷል። ጠዋት መነሳቱ ቀርቶ አልጋ ላይ ማርፈድን ልማድ እያደረገው ነው። ያች የቡና ሱሱ ብቻ ስትቀሰቅሰው ከመኝታው ተነስቶና ቡና ጠጣጥቶ ስራም ጠያይቆ ተመልሶ አልጋ ውስጥ ይገባል።
እጁ ላይ ያለው ገንዘብ እያለቀ ስራም ከጠፋ መሰነባበቱ እያበሳጨው ባለበት ወቅት ነበር ቡና በአይኑ ላይ ውል ያለው። ከአልጋው ብድግ ብሎ ወደ ቡና ደንበኛው ጋር ሄደ። የሃሳቡ መብዛት ይሁን ሱሱ ጥድፍድፍ ችኩልኩል ብሏል። ሰሞኑን ያለ አመሉም መበሰጫጨትን እያበዛም ነበር። ልክ ቡናው ስኒ ጋር እንደደረሰ ወዲያው እጁ ላይ ሲኒ እንዲቀመጥለት የተመኘው ሰው ቡና የምታፈላውን ሴት በትእግስት ማጣት ያጣድፋት ጀመር። ቡናውን አሙቃ እስክትሰጠው ትእግስት ያጣው ገንዘብ ምሳዋን ልትበላው ድንች እየላጠችበት የነበረችበትን ቢላዋ ተቀብሎ ነፍስ ሊያጠፋ በቃ።
ሰው አጠፋለሁ ብሎ ባላሰበበት በአጋጣሚ የደቂቃዎች ትእግስት ማጣት የተነሳ የአንዲት ምስኪን ነፍስ በእጁ አለፈ ። አስቦትም ይሁን ሳያስብ የአንዲት ተስፈኛ ወጣት ህይወት በእጁ በማለፉ የተነሳ ህግ ፊት መቅረብ ግድ ነው።
የፖሊስ ምርመራ
ተከሳሽ አቶ ገንዘብ ታምሩ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሸለሞ ግቢ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ የጀበና ቡና በመሸጥ ነበር የምትተዳደርን የ26 ዓመት ወጣት ወሰን ለማ ‹‹ቡና ቶሎ አልሰጠሽኝም›› በሚል ምክንያት ታፋዋ ላይ በመውጋት ጉዳት ማድረሱንና በዚህም ጉዳት መነሻነት ህይወቷ ሊያልፍ መቻሉን በሰነድ ማስረጃና ከአይን ምስክሮች ያገኘው ማስረጃ አጥናክሮ ለአቃቤ ህግ በመላክ ክስ እንዲመሰረት አድርጓል።
የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ከሆነ ገንዘብ ታምሩ የተባለው ተከሳሽ ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ሲሆን ሟች ወደ ምትሰራበት በመሄድ “ቡና ስጭኝ” በማለት ሲቀመጥ “እሽ ቆይ ላሙቅልህ በማለት” ቡናውን ማንደጃ ላይ ጥዳ ድንች እየላጠች ሳለ “ለምን ቡናውን ቶሎ አትሰጭኝም” ብሎ ስድብ በመሳደብ ተነሰቶ ድንች እየላጠችበት የነበረውን ቢላ እጇን ጠምዝዞ በመያዝ እና ጣቷን በመንከስ ካስለቀቃት በኋላ በቢላዋ ደረቷ ላይ ለመውጋት ይሞክራል፤ ሟች ዞራ ለማምለጥ ስትሮጥ ተከትሏት ከጀርባዋ ሲሰነዝር ሟችም ላለመወጋት ትታገላለች ፤ በዚህን ጊዜ በተደጋጋሚ በተሰነዘረው ቢላዋ የሟችን የእግር ታፋዋ ላይ ወግቶ ለማምለጥ ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ተይዟል። ሟችም ህክምና መስጫ ቦታ ስትደርስ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ብዙ ደም ስለፈሰሳት ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል። ዐቃቤ ህግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ተገቢውን የወንጀል ምርመራ ካከናወነ በኋላ ተከሳሽ ላይ የሰው መግደል ወንጀል ክስ መስርቶበታል።
ውሳኔ
ተከሳሹም ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ “ድርጊቱን ፈፅሜአለሁ ነገር ግን እራሴን ለመከላከል ነው” በማለት የተከራከረ ሲሆን ዐቃቤ ህግ ደግሞ ያሰባሰባቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ተከራክሯል። ፍርድ ቤቱ መረጃዎችን ሲመረምር ቆይቶ በተከሳሹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀነ ቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ተከሳሹ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጦ የክስ መከላከያውን እንዲያቀርብ ዕድል ሰጥቷል ። ድርጊቱን መፈፀሙን አምኖ እራሴን ለመከላከል ስል ነው ከማለት ያለፈ ተከሳሹ ወንጀል መፈጸሙን አላስተባበለም።
ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ግድያ እና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም ተከሳሹ በተከሰሰበት አንቀፅ ጥፋተኛ ነው በማለት በዋለው ችሎት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት አንደኛ ተከሳሽ አቶ ገንዘብ ታምሩ እጁ ከተያዘበት ቀን አንስቶ በሚቆጠር በአስራ ሶስት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል። ይግባኝ መብት ሆኖ መዝገቡም ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ የሚል ውሳኔ በመስጠት የተሰየመው ችሎት ተበትኗል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም