የ2015 ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ1ኛ ዙር መርሃ ግብር ይፋ ከተደረገ ሰንብቷል። የፊፋና ካፍ የውድድር ሰሌዳዎችን በማየት፣ ለውድድር ዝግጁ የሆኑ ስታዲየሞችን በመገምገም እና የሊጉን ስፖንሰር አስተያየት አካቶ የተዘጋጀውን የ2015 ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር 1ኛ ዙር(የ15 ሳምንታት) መርሃ ግብር ለፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ተልኳል። መስከረም 20/2015 ዓ.ም በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚጀምረው ውድድር ለአምስት ሳምንታት በባህር ዳር ቆይታ ካደረገ በኋላ በድሬዳዋ ስታዲየም ከ6ኛ እስከ 10ኛ ሳምንት እንዲሁም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከ11ኛ እስከ 15ኛ ሳምንት ሊካሄድ ቀጠሮ እንደተያዘለት ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ በየክልሉ የሚገኙ ክለቦች ባለፉት ዓመታት እንደተለመደው በየአካባቢያቸው እንደ አቋም መፈተሻ የሚጠቀሙበትን የከተማ አቀፍ ውድድር ለማካሄድ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
ከእነዚህ ውድድሮች መካከል ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውና በፕሪሚየርሊጉ የሚሳተፉ በርካታ ጠንካራ ክለቦችን የሚያፎካክረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ነው። ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ(ሲቲ ካፕ) ዋንጫ የፊታችን ቅዳሜ እንደሚጀመር ታውቋል። ውድድሩ ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቻል በሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚከፈትም ተረጋግጧል።
የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትንናት በስቲያ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት በኤልያና ሞል የውድድሩን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት አከናውኗል። በዚህም ውድድሩ በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን የመክፈቻ ተጋጣሚዎቹም ቅዳሜ በ8፡00 ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በ10፡00 ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቻል እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።
ውድድሩ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲጀመርም የተመልካቾች የመግቢያ ዋጋም ይፋ ተደርጓል። በዚህም መሠረት ሚስማር ተራ 20 ብር፣ ካታንጋ 30 ብር፣ ከማን አንሼ 50 ብር፣ ጥላፎቅ 100 ብር እና ክቡር ትሪቡን 200 ብር ሆነዋል።
ውድድሩን በምድብ አንድ ተደልድለው ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ በፕሪሚየርሊጉ የሚሳተፈው ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ያከናውናሉ። በምድብ ሁለት ደግሞ ውድድሩን በርካታ ጊዜ የማሸነፍ ታሪክ ያለውና የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መቻል እንዲሁም ከዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየርሊግ የተመለሰው ኢትዮጵያ መድን መደልደላቸው ታውቋል።
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በገቢ ለማጠናከር ታስቦና ክለቦችም ለቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉ ተሳትፏቸው አቋማቸውን በመለካት በኩል እንዲረዳቸው የተዘጋጀው ይኸው ውድድር ጥሩ ፉክክር እየታየበት ባለፉት በርካታ ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል። በዚህም በየክለቦቹ የውድድር ዕድል ያላገኙ ተስፋ ሰጪ ችሎታ ያላቸው ወጣት ተጫዋቾች ራሳቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚን ፈጥሯል።
የዘንድሮውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሁሉንም ጨዋታዎች አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የሚዲያ አጋር በመሆን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚሰጥ ተገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የከተማውን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋነኛ የገቢ ምንጭ ብቻ ሳይሆን፣ የከተማው የአንድነት መገለጫ ሆኖ እንደሚቀጥል የተናገሩት የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ አረጋ፣ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚደረጉ ጨዋታዎችን የመግቢያ ዋጋም ይፋ አድርገዋል። በዚህም መሠረት የመግቢያ ቲኬቶች ከ20 እስከ 200 ብር በአማራጭ መዘጋጀታቸውንና ለስፖርት ወዳዱ ማኅበረሰብ ሲባል ዋጋው ተመጣጣኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ውድድር በየዓመቱ በስፖርቱ ዘርፍ ለሚያካሂዳቸው የልማት ፕሮግራሞች ራሱን በገቢ እንዲችል እና አቅሙን ለማጎልበት፣ የተሳታፊ ክለቦችም የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከመግባታቸው በፊት የእራሳቸውን አቋም ለመለካት እንዲችሉ ያካሂደዋል። ውድድሩ በየዓመቱ የተለያዩ አዳዲስ ለውጦችን እያመጣም ተሳታፊ ክለቦች ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያገኙበት መሆኑ ይታወቃል።
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለ6 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚው ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ለሦስት ጊዜ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለሁለት ጊዜና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ጊዜ አሸናፊ ሆነው ማጠናቀቅ ችለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2015 ዓ.ም