ሳራ ፍራንሲስኮ በሳይክሎን ከተጠቁ ሞዛምቢካውያን አንዷ ናት:: የደረሰባት አደጋም ከፍ ያለ እንደሆነ ትናገራለች:: እርሷ እንደምትለው ከአደጋው ክስተት በኋላ ባሏ፣ እናቷና ስድስት ወንድምና እህቶቿ የት እንደደረሱ ማወቅ አልቻለችም:: በዚህም በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥና ኀዘን ውስጥ እንዳለች አስረድታለች::
በሞዛምቢክ ከሳይክሎን አደጋ ተርፈው በመጠለያ የሚኖሩ ሰዎች በቤተሰቦቻቸው መጥፋት ብርቱ ኀዘን ውስጥ እንዳሉና ለረሀብና ለኮሌራ በሽታም እየተጋለጡ እንደሆነ አልጀዚራ ዘግቧል:: ሞዛምቢክ በሳይክሎን ከተጠቃች በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደብዛቸው ጠፍቷል:: ጎርፉ ከቀነሰ ከቀናት በኋላ በተለይ በቤይራ ካምፕ የተጠለሉ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውንና ጓደኞቻቸውን በማፈላለግ እየማሰኑ ይገኛሉ::
ሳራ በቤይራ አካባቢ በገጠራማዋ ቡዚ መንደር ነዋሪ ስትሆን ከአውዳሚው የሳይክሎን አደጋ የተረፈችበትን ተአምር እንዲህ ታስረዳለች:: ‹‹ጎርፉ እየተባባሰ ሲመጣና ከፍታውም ሲጨምር ሁለት ሴት ልጆቼን በመያዝ በቤቴ ጣርያ ላይ ወጣሁ:: አብዛኛዎቹ በዙሪያው ያሉ ቤቶች እያየኋቸው በጎርፉ መዋጥ ጀመሩ:: ለሃያ አራት ሰዓት ሁኔታውን በዚህ መልክ እያሳለፍኩ ሳለሁ የነፍስ አድን ሠራተኞች በድንገት ትንሽ ታንኳ ይዘው ደረሱልኝ::
‹‹እኔንና ልጆቼን በቤይራ አካባቢ በተዘ ጋጀው መጠለያ ወሰዱን:: ምንም እንኳን ልጆቼ ቢተርፉልኝም የቀሪ ቤተሰቦቼን መጨረሻ ባለማወቄ አሁን በከፍተኛ ጭንቀትና ድንጋጤ ውስጥ ነው የምገኘው:: ሁኔታው በተከሰተ ጊዜ ከቤተሰቦቼ ጋር አብረን እንደነበርን ትዝ ይለኛል:: ጀልባዋ ትንሽ በመሆኗ ለእኔና ለልጆቼ ቅድሚያ ተሠጥቶን ወደ ካምፑ ተወሰድን::
‹‹ግምቴ እነርሱም እኔን ተከትለው ይመጣሉ የሚል ቢሆንም በካምፑ ውስጥ ላገኛቸው አልቻልኩም:: ስልካቸውም አይሠራም፤ ልክ እንደኔው የተረፉ የአካባቢያችን ሰዎችም ሁኔ ታው ከተረጋጋ በኋላ ወደ መንደሩ ሄደው ለመቃኘት ቢሞክሩም ሊያገኗቸው አልቻሉም:: እንግዲህ የትገቡ ማለት ይቻላል:: ፈጣሪ በሰላም እንዲያገናኘን ጠዋትና ማታ እየጸለይኩ ነው ›› ትላለች::
የ28 ዓመቱ ኤድዋርዶ በበኩሉ እናቱና ሁለት ታናናሽ ወንድሞቹ በሳይክሎን አደጋው እንደሞቱበት ይገልጻል:: ሁኔታውን እንዲህ ይገልጻል:: ‹‹ ቤተሰቦቼ በጎርፍ መወሰዳቸውን ከሰማው ቀን ጀምሮ እስከ አሁን እያለቀስኩ ነው:: አሁን አዕምሮዬ አልታዘዝ እያለኝ ነው:: ወላጅ አልባ ሆኛለሁ፤ ህይወቴ እንዴት እንደሚቀጥል አላውቅም›› ይላል::
የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ፊሊፔ ኒዩሲ ከሰሞኑ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገራቸው የተከሰተው የጎርፍ አደጋ የከፋ እንደነበር በማስታወስ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አቅማቸውን ሁሉ ተጠቅመው የሞቱ ሰዎችን አስክሬን እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል::
ከአደጋው የተረፉና በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦችም ወደ መንደራቸው መመለስ በመፈለጋቸው የሀገሪቱ ብሄራዊ የአደጋ ቁጥጥር ተቋም ወደ ነበሩበት የቀድሞ መንደራቸው ለማስፈር እየሠራ ነው:: የተቋሙ ቃል አቀባይ ቫይቶሪኒ ሞንድሌን እንደሚያስረዱት አንዳንድ ሰዎች በተለይም የቡዚ አካባቢ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞ መንደራቸው በመመለስ የፈራረሱ ቤቶቻ ቸውን በመገንባት ላይ እንዳሉ እና መመለስ ያልፈለጉትም ለተመሳሳይ አደጋ በማያጋልጡ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ እየሰፈሩ እንዳሉ ገልጸዋል::
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያስረዳው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ይሻል:: በአካባቢው የኮሌራ በሽታ መከሰቱም ችግሩን እያባባሰው ይገኛል:: የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠርም የዓለም የጤና ድርጅት 900 ሺህ የሚገመት የክትባት መድኃኒት ለመለገስ ቃል ገብቷል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011
ኢያሱ መሰለ