የካፍ ኤሊት ኢንስራትክተር አብርሃም መብራቱ የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሆነው መሾማቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ:: አሰልጣኙ በዚህ ዘርፍ በመመረጥ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊም ሆነዋል::
የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) አሰልጣኝ እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሆነው መሾማቸው ተረጋግጣል:: በአሁኑ ወቅት የፕሪምየር ሊግ ክለብ የሆነውን ባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ የሆኑት ኢንስትራክተር አብርሃም ፊፋ ለቴክኒክ ኤክስፐርትነት ያቀረባቸውን መመዘኛዎች ማለፍ ችለዋል:: በመሆኑም እንደ ሁኔታው በሚታደስ የሁለት ዓመት ኮንትራት የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሊሆኑ እንደቻሉ የአትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረገጹ ያስነበበው::
የካፍ መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ እንደቀዳሚነቷ በእግር ኳሱ ያለችበት ደረጃ አርኪ ባይሆንም በተለያዩ ባለሙያዎች ግን መወከሏ አልቀረም:: ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የካፍ ኤሊት ኢንስራትክተር አብርሃም መብራቱ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት በሚመራው ተቋም የማገልገል ዕድል አግኝተዋል:: ይህ ደግሞ በፊፋ በዚህ ዘርፍ የተመረጡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢንስትራክተር አድርጓቸዋል::
ኢንስትራክተር አብርሃም ለቦታው ተመራጭ ያደረጋቸውም በአፍሪካ በኤሊት ኢንስራክተርነት፣ በአፍሪካ ዋንጫ እና መሰል ትልልቅ ውድድሮች በቴክኒክ ጥናት ቡድን አባልነት በሚያደርጉት ተሳትፎ ነው:: በተጨማሪም በአሰልጣኝነት በኤዥያ እና የመን እግር ኳስ ላይ ያላቸው የስራ ልምድ እንደሆነም ነው የተጠቀሰው:: አሰልጣኙ የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት በመሆናቸው ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል፤ በኤሊት የእግር ኳስ አሰልጣኝነት፣ በወጣቶች እግር ኳስ፣ በታዳጊዎች እግር ኳስ፣ ለቴክኒክ ዳይሬክተሮች፣ ለኢንስትራክተሮች እና ከእግር ኳስ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ጉዳዮች ዙርያ ስልጠናዎች(ኮርሶችን) ማዘጋጀት ይገኝበታል::
በተጨማሪም ለአባል ሀገራት እና አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽኖች በእግር ኳስ ልማት ዙርያ የቴክኒክ ማማከር፤ የአባል ሀገራት የእግር ኳስ ልማት ፕሮግራሞች እና ተግባራትን መከታተል፤ አዲሱ የፊፋ ቴክኒክ ልማት ፕሮግራም ዝግጅት እና አስፈላጊ ሰነዶችን በማዘጋጀት ላይ መሳተፍ እንዲሁም ሌሎች በፊፋ የቴክኒክ ልማት መምሪያ ስር የሚሰጣቸው ተግባራትን መከወንም ይጠቀሳሉ።
ኢንስትራክተር አብርሃም የቀድሞው የወንጂ ስኳር እና ጉምሩክ አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል:: ከኢትዮጵያ ባለፈም በየመን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነትና ስኬታቸው ይታወቃሉ:: ከ22 እና 23 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝ እና የየመን እግር ኳስ ማህበር የቴክኒክ ዳይሬክተር በመሆንም ሰርተዋል:: ዋናውን የየመን ብሄራዊ ቡድን በመምራትም እአአ በ2019 በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ አዘጋጅነት ለ17ኛ ጊዜ በተካሄደው የእስያ ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተሳትፎ እንዲበቃ በማድረግ የቻሉ ሲሆን፤ በዚህም ከፍተኛ አድናቆት አግኝተዋል:: ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሄራዊ ቡድኑን (ዋሊያዎቹን) እንዲያሰለጥኑ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ይታወቃል::
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በማሰልጠን በቆዩበት ወቅትም ዋልያዎቹ ላለፈው የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ከስምንት ዓመት በኋላ ተሳታፊ እንዲሆኑ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል:: ይህም በአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ ዋልያዎቹን እየመሩ ባህርዳር ስቴድየም ላይ ኮትዲቫርን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ያስመዘገቡት ሦስት ነጥብ ከሚጠቀሱ ስኬቶቻው አንዱ ሆኖ ይታወሳል:: ይሁንና አሰልጣኙ ከኢትዮጵያ እግር ካስ ፌዴሬሽን ጋር ዋልያዎቹን ለማሰልጠን ከተስማሙበት ከሁለት ዓመት በላይ ቡድኑን ይዘው መቆየት አልቻሉም:: ከብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ከተነሱ በኋላም የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆነውን ክለብ ሰበታ ከነማን በማሰልጠን ውጤታማ መሆናቸውም ይታወሳል:: አሰልጣኙ በርካታ ክለቦች የሚፈልጓቸው የነበረ ቢሆንም ከሰበታ ከተማ በመልቀቅ የባህርዳር ከተማን ለማሰልጠን በመስማማት አሁንም ድረስ ክለቡን እየመሩ ይገኛሉ::
አሰልጣኙ አሁን ላይ ሀገራቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስጠራት የሚችሉበት እድል አግኝተዋል:: ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተሰማውን ደስታ ገልጿል:: ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በፊፋ በተሰጣቸው አዲሱ ስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑም ልባዊ ምኞቱን አስተላልፏል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2015 ዓ.ም