የአዳራሹ በተለያዩ ምርቶች ተሞልቷል፤ ሚሊኒየም አዳራሽ። ጤፉ፣ ጥራጥሬው፣ የቅባት እህሉ፣ አትክልትና ፍራፍሬው፣ የማርና ሰም ምርቱ፣ በፋብሪካ ከተቀነባበሩት ፓስታና መካሮኒ፣ ዱቄት፣የተለያዩ ብስኩቶች፣ወተትና የወተት ተዋጽኦ፣ ከአልኮል መጠጦችም ወይንን ጨምሮ በርካታ ምርቶች በስፋት ቀርበዋል።
ከግብርና ምርቶች በተጨማሪ አልባሳትና ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶች በአንድ ቦታ መቅረባቸው አምራቹንና ሸማቹን ማገናኘት የተቻለበት አጋጣሚ ማለት ያስችላል። አጋጣሚው ለበዓል ወቅት ብቻ የሚጠቅም አልነበረም፤ የአንድን ተቋም አገልግሎት ወይንም ጥራት ያለው ምርት ፈልጎ ግን ደግሞ ለማግኘት ለተቸገረ ሸማች ሁሉንም አይነት አገልግሎቶች በአንድ ስፍራ ማግኘት ያስቻለም ነው።
ለግብርናው ስራው ግብአት የሚሆኑ አነስተኛና ከፍተኛ መጠን ያላቸው ማሽነሪዎች፣ ማቀነባበሪያዎች፣ ፀረተባይ ኬሚካሎችም እንዲሁ ለሽያጭ ቀርበዋል።
ቀኑ ጳጉሜን 2 ቀን 2014 አም ነው። ይህ ቀን የአምራችነት ቀን በሚል ተሰይሞ አምራችነት በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረበት ነው። በአዳራሹ ከክልሎች፣ ከአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ የመጡ አምራቾችና አልሚዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ቀርበዋል። ሸማቾችም የመድረኩ ተቋዳሾች ነበሩ፤ አምራቾቹ ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን በማስተዋወቅ ደንበኛ ለማፍራት የሰሩበት፣ ሸማቾችም የተለያዩ ምርቶችን ጥራታቸውን እያረጋገጡ የገበዩበት። ወቅቱ የበዓል መዳረሻም ስለነበር አምራችና ሸማቹ የተገናኙበትት መልካም አጋጣሚ መሆን ችሏል።
በዚህ የአምራቾች ቀን መድረክ አምራችና ሸማቹ ብቻ አይደለም የተገናኙት፤ መርሃ ግብሩን ያዘጋጁት ስድስት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተገኝተዋል፤ እነሱም እንደ ቡናና የመሳሰሉትን ምርትና አገልግሎታቸውን አስተዋውቀዋል። ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ዝግጅቱን በመጎብኘት፣ እዛው መቅመስ የሚቻለውን በመቅመስ አምራቾችንና አገልግሎት ሰጪዎችን አ በረታትተዋል።
በዚህ የአምራችነት ቀን ላይ ለሥራ በተገኘንበት ወቅት በተለያየ የኪሎ መጠን ታሽጎና የምርት መለያ ተለጥፎበት (ሌብል ተደርጎ) ከገጠር ተጓጉዞ በስፍራው የቀረበ ማር ተመለከትን፤ እንዲህ ያለው አቅርቦት አልፎ አልፎ እንደ ሱፐርማርኬት ባሉት የግብይት ማእከላት ውስጥ እየተለመደ መጥቷል። የማር ምርቱ በዚህ አይነት መልኩ ለሽያጭ መቅረቡ የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለሸማቾች የማቅረብ ባህል እየዳበረ መምጣቱንም ያመለክታል።
ከከተማ ወጣ ባለ የገጠር አካባቢ ከሰፈፉ የተለየ ወይም የተጣራ ማር ታሽጎና የምርት መለያና ስያሜ ይዞ አንዲቀርብ መደረጉ የማሩ ሰፈፍ/ሰም/ ም ለብቻው ተዘጋጅቶ ለገበያ ምቹ በሆነ መልክ መቅረቡ ትኩረታችንን ሳበው። በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ማር ከነሰፈፉ ሲሸጥ የተመለከተ በአዳራሹ የቀረበው የማር እና ሰፈፍ ግብይት በማርና ሰፈፉ ምርት ግብይት ላይ ለውጥ እየመጣ መሆኑን እንዲገነዘብ ያስችለዋል።
ማሩ እና ሰሙ የተመረተው በአማራ ክልል አዊ ዞን ጓጉሳሽኩዳድ ወረዳ ሽንኩርታ ቀበሌ ናንታ ጎጥ ነው፤ አምራቾቹ ደግሞ በንብ ማነብ ወይንም በማር ልማት በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ነው። የማምረት ስራው 13 ሴቶችና ሁለት ወንዶች በመሆን ትግሥት፣ላወይ፣መሰለችና ጓደኞቻቸው ብለው በሰየሙት ማህበር ነው የሚከናወነው።
የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ትግሥት ተስፋሁን እንደነገረችን፤ በአዲስ አበባ በተዘጋጀው መድረክ የሚቆዩት ለአጭር በመሆኑ መጠኑ አነስተኛ የሆነ ምርት ነው ይዘው የቀረቡት። ማህበሩ ምርቱን እንዲያስተዋውቅ የተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ በቀጣይም ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚያስገኝለት ተስፋ አድርጓል። አባላቱ ባቀረቡት የማር ምርት ሸማቹ መርጧቸው ባለበት ቦታ ሆኖ ምርታቸውን ለማዘዝ እንዲችል የሚያደርግ በጥራት የታሸገ ማር ይዘው ነው የቀረቡት።
አካባቢያቸው ለማር ልማት ምቹ እንደሆነ የምትናገረው ወጣት ትግስት፣ ከተሰራ በስፋት ማቅረብ የሚቻልበት ዕድል መኖሩንም ትገልጻለች። የማህበሩ አባላትም የሥራ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሳ፣ የሚመጣውን የገበያ ፍላጎት ለማሟላት ዝግጁ እንደሆኑም ገልጻለች።
እርሷ እንዳለችው፤ አባላቱ በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡ ሁለተኛ አመታቸውን ይዘዋል፤ ውጤታቸውን ለማየት ጓጉተዋል። እስካሁን ባለው ተሞክሮ የማር ልማቱ በአመት ሁለቴ ነው የሚከናወነው። እነሱም በህዳርና በግንቦት ወራት ሶስት መቶ ኪሎ ግራም ማር አምርተዋል። ይሄን ሥራ በማሳደግ ከዚህ በላይ በማምረት ገበያውን ለመያዝ እየሰሩ ናቸው። ምርቱን ለማሳደግና ጥራት ያለው ማር ለማምረት ንቦችን በተገቢው መንገድ መንከባከብ፣ የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ፣ የሚቀስሟቸውን እጽዋት በስፋት መትከል ይጠበቃል። ይህን ማሟላት ከተቻለ ንቦች ከፍተኛ የማር ምርት መስጠት እንደሚችሉ በአንድ አመት የንብ ማነብ ሥራ ተሞክሮ አግኝተዋል።
ወጣቶቹ በዘመናዊ የማር ማቀነባበሪያ ተጠቅመው ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የማር ምርት ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። ከከተማ ወጣ ባለ አካባቢ የሚኖሩ በመሆናቸውና በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡም ገና አጭር ቆይታ ያላቸው እንደመሆናቸው ምርቱን የሚያቀነባብሩበትን ቴክኖሎጂ እንዴት ማግኘት እንደቻሉ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ወጣት ትግስት ስታብራራ እንዳለችው፤ የሥነ ነፍሳት ምርምር ማዕከል ሞይሽ ፕሮጀክት(ኢሲፔ) በቅድሚያ ስለንብ ማነብ፣ ማር ቆረጣና ዘመናዊ አስተሻሸግ፣ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ሰጥቷቸዋል።
በዚህም ክህሎት መጨበጥ እንዲችሉ ከተደረገ በኋላ ዘመናዊና የተሻሻሉ ቀፎዎችን እና በማር ቆረጣ ወቅት የሚያስፈልጉ አልባሳትን በማቅረብ ፣ማሩን ከሰፈፉ ለይቶ የሚያጣራና የተጣራውንም ማር በማሸጊያ እቃ ውስጥ ለመጨመር የሚያስችል መሳሪያ እንዲሁም ለማሩ ማሸጊያ ዕቃ በማቅረብ ለማር ልማቱ አስፈላጊ የሆነ ቁሳቁስ ከተሟላላቸው በኋላ ነው ወደ ልማቱ የገቡት። ያሉበት ወረዳም ንቦች የሚቀስሙትን እጽዋት የሚያለሙበትን ቦታ አመቻችቶላቸዋል፤ ይህን ድጋፍ በጋራ ተጠቅመው ለውጤት በቅተዋል።
እንዲህ ያለው የፕሮጀክት ድጋፍ ለተወሰነ አመት ብቻ የሚዘልቅ እንደሆነ ይታወቃል።ባለው ተሞክሮ ፕሮጀክቶች ውስን ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ እንቅስቃሴው ባለበት የማይቀጥልበት ሁኔታ ይስተዋላል። ወጣት ትግስት የፕሮጀክቱ ድጋፍ ለአምስት አመት ብቻ እንደሚቆይ አባላቱ ግንዛቤው አላቸው ትላለች። ፕሮጀክቱ ክህሎት እንዲጨብጡ በመደረጉም ለማር ልማቱ የሚውል የተለያዩ የመሥሪያ ግብአቶችን ስላሟላላቸውና የመስሪያና የመሸጫ ቦታም ገንብቶ ስለሰጠላቸው፣ ለንብ ማነቢያ የሚሆን መሬትም በወረዳው ትብብር ተደርጎላቸው ስለተሟላላቸው ከዚህ በኃላ ወደኃላ የሚመለሱበት ሁኔታ እንደሌለ ተናግራለች። በእነዚህ ድጋፎች የበለጠ አቅም ፈጥረው የማር ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ጭምር መዘጋጀታቸውን ነው የጠቆመችው።
እነ ትግስት የገበያ ዕድላቸውን አስፍተው አካባቢያቸውን በማር ምርት ለማስተዋወቅ ጭምር አቅደዋል። ፕሮጀክቱ የጊዜ ገደቡን አጠናቅቆ ሳይወጣ ውጤቱን ለማሳየት ተግተው እየሰሩ እንደሆነም ነው ወጣት ትግሥት የተናገረችው። ከማር ልማቱ ጎን ለጎንም ለእድገት የሚያበቁ ሥራዎችን ለመሥራትም አቅደዋል። ለእዚህም የሥራ ተነሳሽነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው ከወጣት ትግስት አገላለጽ መረዳት የቻልነው።፡
በምርት መጠን ማነስ፣በጥራት መጓደል፣በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘ የተጣራ ማር ለገበያ ለማቅረብ የክህሎትና የአቅም ውስንነት፣ የማር ምርቱ ለውጭ ለገበያ ቀርቦ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኝ ቀርቶ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን እንኳን ያሟላ እንዳልነበር ምርቱን አስመልክቶ በተካሄዱ የተለያዩ መድረኮች ሲነሳ ይታወሳል። እሴት የተጨመረበት የማር ምርት ለሸማቹ ምቹ ከመሆኑ በተጨማሪ አልሚው ወይንም አምራቹ በገቢ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያደርግ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ችግሮቹን ብቻ ከማውሳት ባለፈ የማር ልማቱን በማሳደግና የገበያ ፍላጎትን በሚያሟላ መልኩ ለማቅረብ ጥረቶች አልተቋረጡም።
ትግሥት፣ላወይ፣መሰለችና ጓደኞቻቸው ማህበር አባላት ከእጅ ንኪኪ ነፃ የሆነ የጣራ ማር እንዲያመርቱና የገበያ ትስስርም እንዲፈጠርላቸው በማድረግ የማር ምርት በቀጣይም ለውጭ ገበያ ጭምር በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖረው በመንግሥት፣በማስተርካርድ ፋውንዴሽንና የሥነ ነፍሳት ምርምር ማዕከል (ኢሲፒኤ) ትብብር እየተሰራ ይገኛል። መንግሥት ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን በማደራጀትና የሥራ ቦታን ምቹ በማድረግ፣ ኢሲፔ ደግሞ ክህሎት፣ለማር ልማት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስን በማሟላትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ማር ለማምረት የተደራጁ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለውጤት እያበቋቸው ይገኛሉ።
የሥነ ነፍሳት ምርምር ማዕከል ሞይሽ ፕሮግራም(ኢሲፔ) ዋና አስተባባሪ ዶክተር ወርቅነህ አያሌው እንደተናገሩት፤ ማር እንደሌላው የግብርና ውጤት ሰፊ ገበያ ኖሮት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ቢችልም፣ እየተመረተ ያለው ግን በአርሶ አደሮች ደረጃ መጠኑ አነስተኛ የሆነ ማር ነው፤ ምርቱም የጥራት ጥያቄ በስፋት እየተነሳበት ያለና የገበያ አዋጭነቱም ዝቅተኛ ሆኖም ይገኛል። በዚህ የተነሳ አልሚውም ሀገርም ከዘርፉ ይህ ነው የሚባል ገቢ እያገኙ አይደለም። ሸማቹም ቢሆን የተጣራ ማር ስለማይቀርብለት ፍላጎቱ አልተሟላለትም።
እንደ ዶክተር ወርቅነህ ገለጻ፤ አሁን ላይ የማር ልማቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተደራጁ ወጣቶች በስፋት እየተካሄደ ይገኛል። ወጣቱም በአካባቢው ላይ በዘመናዊ የማር ልማት መሳሪያ በመጠቀም ጥራት ያለው ማር አሽጎና ስምም ለጥፎበት ማቅረብ በመጀመሩ በማር ገበያው ላይ ለውጦች መመዝገብ ጀምረዋል። ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚችል ከማሩ የተለየ ሰምም በወጣቶቹ እየተመረተም ይገኛል።
እና ምርት ሲባል በትልቅ ግብርና ወይንም በከፍተኛ የኢንዱስትሪ ውጤት ደረጃ ብቻ መጠበቅ የለበትም የሚሉት ዶክተር ወርቅነህ፣ ማርን በአካባቢ ላይ በስፋት አምርቶና እሴት ጨምሮ ከትላልቅ ኢንዱስትሪ ውጤቶች እኩል ለገበያ በማቅረብ ገበያውን መያዝ እንደሚቻል ወጣቶችን በማደራጀት ባለፉት ጥቂት አመታት የተከናወኑት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩ አመልክተዋል።
ማር በቀላሉ ማቀነባበር የሚያስችል ቴክኖሎጂ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል መፍጠር መቻሉን፣ የንብ ማነብ ሥራውም በዘመናዊ መንገድ እንዲታገዝ መደረጉን፣ ለንብ ማነብ የሚያስፈልጉ ከአልባሳት አቅርቦት ጀምሮ መሟላታቸውን ዶክተር ወርቅነህ ጠቅሰው፣ ከዚህ በኃላ የሚያስፈልገው የንብ ማነብ ፍላጎት ያለው የሰው ኃይል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። ለማር ማጣሪያ ከሚውለው ማሽን በስተቀር የተቀሩት ለንብ ማነብ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስም በአካባቢው ተዘጋጅተው ሊቀርቡ እንደሚችሉም ይጠቁማሉ። ቁሳቁሱን ንብ አናቢዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያገኙ እንደሚችሉም ተናግረው፣ ሁሉንም በገበያ በማስተሳሰር ከማር ልማቱ ተጠቃሚ የሚሆነውን የሰው ኃይል ማስፋት መቻሉንም ነው ያመለከቱት።
ዶክተር ወርቅነህ በወጣቶቹ እየተመረተ ለገበያ እየቀረበ ያለው የማር ምርት በኤሌክትሮኒክስ ወይንም ኢ ኮሜርስ በሚባለው የገበያ ሥርአት ውስጥ መግባቱንም ይጠቁማሉ። በዚህ መንገድ የገበያ ትእዛዝ ለሚያቀርቡ ደንበኞች ቤታቸው ድረስ ተደራሽ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋቱንም ነው የጠቆሙት።
እንደ ዶክተር ወርቅነህ ገለጻ፤ ሸጋ ዶትኮም በሚባለው የገበያ ዘዴ የማር ግብይቱ ተጀምሯል። የማር ምርቱም በዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንዲያልፍ እየተደረገ ይገኛል። ወጣቶቹ በቀጥታ ለውጭ ባይልኩም፣ ምርቶቻቸውን ተቀብለው በሚልኩ ለዓለም ገበያ መድረስ ችሏል።
ይህ በራሱ ተስፋ ሰጪ መሆኑንና ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻፀር ከፍተኛ የሚባል ለውጥ መኖሩን እንደሚያመለክት ተናግረው፣ መሬቱ፣ ሀብቱና የሰው ኃይሉ ሁሉም በመኖሩ በፖሊሲ በመደገፍ በስፋት ተሰርቶ ለገበያ የሚቀርብበትን ሁኔታ ማጠናከር እንደ ሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ።
በማህበር በመደራጀት በንብ ማነብ ሥራ ላይ ተሰማርተው ማር በማልማትም ሆነ የገበያ ዕድል በመጠቀም የሚያደርጉት እንቅስቀሴ፣ በግላቸው ንብ የሚያንቡ አርሶ አደሮችንም ማነቃቃት መቻሉን ዶክተር ወርቅነህ ይገልጻሉ። ይሄ ደግሞ ጥራት ያለው ማር ለገበያ እንዲቀርብ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው የሚሉት።
ከኤሲፒ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢሲፔ በሀገር አቀፍ ደረጃ በማህበር ለተደራጁ ንብ አናቢ ወጣቶች ድጋፍ ያደርጋል፤ በየሽ ፕሮጀክት 10ሺ፣በሞይሽ ፕሮጀክት ድግሞ 60ሺ ወጣቶች በንብ ማነብ ሥራ ላይ ተደራጅተው ተሰማርተዋል፡፡ በትግራይ ክልል የሚካሄደው ተመሳሳይ ፕሮጀክት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ቢቋረጥም፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሚደረጉ የተለያዩ ድጋፎች ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2015 ዓ.ም