በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በሜዳቸው ያከናወኑት ፋሲል ከነማና ቅዱስጊዮርጊስ የአፍሪካ መድረክ ጉዟቸውን በድል ጀም ረዋል።
ከአዲስ አመት ዋዜማ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ባለፈው አርብ በባህርዳር ስቴድየም የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት አጼዎቹ የቡሩንዲውን ክለብ ቡማሙሩን 3ለ0 በማሸነፍ ጣፋጭ ድል አስመዝግበዋል። አለምብርሃን ይግዛው፣ፍቃዱ አለሙ፣ታፈሰ ሰለሞን አጼዎቹን ለድል ያበቁ ግቦችን ከመረብ ያሳረፉ ተጫዋቾች ናቸው። ባለ ድሉ አሰልጣኝ ሃይሉ ነጋሽ አጼዎቹ በጨዋታው የነበራቸው የበላይነት የጠበቁትና ቡድናቸው ከዚህም የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ አቅም እንዳለው ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት ሰጥተዋል።
አፄዎቹ ከቡማሙሩ ጋር ላለባቸው የመልስ ጨዋታ በአዲስ አበባ ሲዘጋጁ እንደሚቆዩ ትናንት የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል። የመልሱ ጨዋታ የፊታችን ዓርብ እንደሚከናወን ይጠበቃል። አጼዎቹ በአዲሱ አመት ምክንያት የሁለት ቀን እረፍት ካደረጉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ።ቡሩንዲ የመልሱን ጨዋታ ለማስተናገድ በካፍ ፍቃድ የተሰጠው ስታድየም የሌላት በመሆኑ ቡማሙሩ ክለብ አጼዎቹን በገለልተኛ ሜዳ ለመግጠም ተገደዋል። የመልሱን ጨዋታ የሚካሄደው ደግሞ በታንዛኒያ አዛም ኮምፕሌክስ ሜዳ ላይ ሲሆን የመጫወቻ ሜዳውም ሰው ሰራሽ መሆኑ ተዘግቧል። በዚህም ምክንያት አጼዎቹ ወደ ታንዛኒያ እስከሚያቀኑበት ጊዜ ደረስ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ዝግጅታቸውን ለማድረግ እንደፈለጉ ታውቋል። አፄዎቹ ይህንን ጨዋታ በድምር ውጤት የሚያሸንፉ ከሆነ በቀጣይ የቱኒዚያውን ሴፋክሲየንን እንደሚገጥሙ አስቀድሞ የወጣው መርሐ ግብር ይጠቁማል።
በተመሳሳይ ከትናንት በስቲያ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በባህርዳር ስቴድየም ያደረጉት ፈረሰኞቹ አዲሱን አመት በጣፋጭ ድል ጀምረዋል። ፈረሰኞቹ የሱዳኑን ሃያል ክለብ አል ሂላልን ቸርነት ጉግሳ በመጀመሪያው የጨዋታ ጊዜ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች 2ለ1 አሸንፈዋል።
የፈረሰኞቹ አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ “በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጥሩ ነበርን ፤ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ቀላል ስህተት ሠርተን ሁለት ለአንድ አሸንፈናል። ከሞላ ጎደል በጣም ጥሩ ነው ተጫዋቾቼ የሠሩት።” በማለት ከድላቸው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት ሰጥተዋል።
ፈረሰኞቹ በመጨረሻ ሰአት ግብ ማስተናገዳቸው በመልሱ ጨዋታ ጫና ውስጥ እንዳይገቡ ስጋት ቢፈጥርም ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ እድል አላቸው። አሰልጣኝ ዘሪሁን ወደ ጨዋታው ሲገቡ ቡድናቸው ግብ እንዳያስተናግድ አስበው እንደነበር ተናግረዋል። ነገር ግን ባለቀ ሰአት ላይ በትንሽ የመከላከል ቅንጅት በሰሩት ስህተት ግብ አስተናግደዋል። ይህም በመልሱ ጨዋታ ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል አስተያየት ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ይህን ስጋት ለማስቀረት ፈረሰኞቹ ከባህርዳሩ ጨዋታ የተሻለ ነገር ሠርተው በድምር ውጤት ለማሸነፍ እንደሚዘጋጁ አስረድተዋል። ፈረሰኞቹ የመልስ ጨዋታቸውን የፊታችን መስከረም 8 ቀን 2015 ዓ.ም በአል-ሂላል ስታዲየም ያደርጋሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚውን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈም በቀጣዩ ዙር ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስና ከደቡብ ሱዳኑ ዛላን ኤፍሲ ሩምቤክ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2015 ዓ.ም