በመጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት አጋማሽ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ይከናወናሉ። ሶስት ዙር ባለው በዚህ የማጣሪያ ፍልሚያ ላይም 38 ሀገራት ተካፋይ ናቸው። በዚህ ውድድር የሚሳተፉትም ስምንት አገራት ናቸው። በአፍሪካ ዋንጫው ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ አገራትም እአአ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ተካፋይ ይሆናሉ።
በአፍሪካ ዋንጫው ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ ከሚገኙ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን፤ የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታም ከ10 ቀን በኋላ በሜዳዋ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ታከናውናለች። ለዚህ የማጣርያ ጨዋታ የቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት አጥናፉ ዓለሙ እና ረዳቶቻቸው ለ36 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ከነሐሴ 24/2014ዓም ጀምሮ በካፍ የልህቀት ማዕከል ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚም ከመቻል ስፖርት ክለብ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርገዋል። ይሁንና በዋናው ብሄራዊ ቡድን ለቻን ማጣርያ ጨዋታ የተካተቱ፣ በክለቦች አህጉራዊ ተሳትፎ ዝግጅት እና ክለቦች ተጫዋቾች ባለመልቀቃቸው ምክንያት ስብስቡ የተሟላ አልነበረም።
አሁን ግን ጨዋታው ቀናት ብቻ የቀሩት በመሆኑ አሰልጣኙ ለኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ተጫዋቾች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል። እነርሱም ኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ ጫላ ተሺታ፣ ብሩክ በየነ እና መሃመድ ኑር ናስር መሆናቸውን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ሌላኛው የክለቡ ተጫዋች አማኑኤል ዮሐንስ እና የወላይታ ድቻ የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ሳሙኤል ተስፋዬ በአዲስ መልክ ጥሪ የቀረበላቸው ተጫዋቾች ሆነዋል።
ከክለቦች ተጫዋቾችን አለመልቀቅ ጋር በተያያዘም አሰልጣኝ አጥናፉ በሰጡት አስተያየት፤ ክለቦች ሀገራዊ ገጽታውን መመልከት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ባለችበት ነባራዊ የእግር ኳስ ደረጃ ሰፊ የዝግጅት ጊዜ መውሰድና ጨዋታውም በቅርብ ሚደረግ እንደመሆኑ ሀገራዊ ጉዳይን ማስቀደም ተገቢ ነው። ውድድሩ የኦሊምፒክ ውድድር እንደመሆኑ ወጣት ተጫዋቾች በእግር ኳስ ወኪሎች (ኤጀንቶች) የመታየት ዕድላቸው የሰፋ በመሆኑ ራሳቸውን መመልከት እንዳለባቸውም አሰልጣኙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ቡድኑን በተቀላቀሉና ከተለያዩ ክለቦች ከተሰባሰቡ ተጫዋቾች ጋር በመሆንም ክፍተታቸውን ለመሙላት ዝግጅቱ አተኩሮ እየተሰራ ነው። የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን በተመለከተ ቡድኑ ከሀገር ውስጥ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎች እያደረገ ሲሆን፤ ከካሜሩን ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጋር ለመጫወት የሚያስችለውን ሙከራ እየተደረገ መሆኑንም አሰልጣኙ ገልጸዋል። የሚሳካ ከሆነም የተጫዋቾችን ወቅታዊ አቋም እንዲሁም የውድድሩን መንፈስ ለመመልከት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን አስረድተዋል።
እስካሁን ቡድኑን ካልተቀላቀሉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ በደቡብ አፍሪካው ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውስ በመጫወት ላይ የሚገኘው አቡበከር ናስር ሲሆን፤ በቅርቡ ተመልሶ ከቡድኑ ጋር ዝግጅቱን ይቀጥላል በሚልም ይጠበቃል። ተጫዋቹ ካለው ልምድና ብቃት አንጻር ውጤቱን የተሻለ ለማድረግ እንዲሁም ለሌሎች ተጫዋቾች ተምሳሌት እንደሚሆንም አሰልጣኙ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ፍልሚያ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ከ23 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በሜዳው የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ የፊታችን መስከረም 12 ይካሄዳል።
ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታውን በሜዳው እንዲያደርግ በእጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱ መርሐ-ግብር ተይዞ የነበረ ሲሆን በሀገራችን በካፍ ፍቃድ ያገኘ ሜዳ አለመኖሩን ተከትሎ ጨዋታውን የሚያደርግበት ስታዲየም ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከቀናት በፊት የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ብሔራዊ ቡድኑ የሜዳ ላይ ጨዋታውን በመዲናችን አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲያደርግ ፍቃድ አግኝቷል። በዚህም የመጀመሪያ ጨዋታውን መስከረም 12 በደጋፊው ፊት ሲያከናውን የመልስ ጨዋታውን ደግሞ መስከረም 17 ኮንጎ ላይ የሚከውን ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 2 / 2015 ዓ.ም