ሱፐር ሞዴል አና ጌታነህ መሰረቷን አሜሪካና ፈረንሳይ አድርጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነችበትን የሞዴሊንግ ስራን ለበጎ አድራጎት ያዋለች የአገር ልጅ ናት ። አና የተወለደችው በስዊድን ሲሆን በአባቷ ዲፕሎማትነት ምክንያት አብዛኛው እድገቷ በውጭ አገራት ቢሆንም የኢትዮጵያ አገሯን ቋንቋዋንና ባህሏን እያስተማሩ አሳድገዋት ከወላጆቿ ጋር በተለያዩ አገራት በመዘዋወር የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች ። በቤልጀየም በማርኬቲንግ የትምህርት ዘርፍ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ተከታትላም ተመርቃለች ። የስዊድን ቋንቋ አፍ መፍቻዋ ቢሆንም አማርኛ ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛን አቀላጥፋ ትናገራለች ።
አና በፈረንሳይ እና አሜሪካ የሞዴሊንግ ጥበብን ተምራለች፤ ሰርታለችም ። በመቀጠልም ወደ ደቡብ አፍሪካ ተዛውራ ለ10 ዓመት በሞዴሊንግ ስራ በርካታ ተግባራትን ፈጽማለች ። በዚህ ወቅት አፍሪካን ሞዛይክ የተሰኘውን ተቋም መስርታ በርካታ አፍሪካውያን በአንድነት የአፍሪካን የፋሽን ጥበብ ለዓለም እንዲያሳዩ አድርጋለች ። እንደ ውጭ አገሩ ሁሉ ይህን የፋሽን ትርኢት በኢትዮጵያም አካሂዳለች ። የአና አፍሪካን ሞዛይክ በአሜሪካን በግብረ ሰናይ ድርጅትነት የተመዘገበ ነው። በሞዴሊንግ ሙያ ያገኘችውን ዓለም አቀፍ እውቅናና ሀብት ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት አውላዋለች ።
ገና በልጅነቷ ፍርቱናዋን ያወቀችው እና በዚህም የተሳካላት አና ሞዴሊንግ አንድ ወጥ የሆነ ፎርሙላ የለውም ትላለች ። ሞዴሎችም ራሳቸውን ከሌላው ጋር ማወዳደር እንደሌለባቸው ትናገራለች ። ስለዚህም ሞዴሊንግ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች በተለይም ሴቶች እድሉን ካገኙ መጠቀም እንዳለባቸው ነገር ግን ብቸኛ ተስፋዬ እሱ ነው ብለው መቀመጥ እንደሌለባቸው ትመክራለች ። ብዙ ሰዎች ‹‹ፊቴን መቀየር አለብኝ፣ በጣም መክሳት አለብኝ፣ ምግብ አበላሌን መቀየር አለብኝ፣…›› በማለት በመልካችን ላይ ብቻ መጠመድ ሌላ አይነት ችግር ሊፈጥር ይችላልም ትላለች ።
አና ከውጫዊ ገጽታዋ በላይ በውስጣዊ ማንነቷ ላይ አትኩራ እንደምትሰራ ትናገራለች ። ለሃይማኖቷ ትኩረት እንደምትሰጥ እንዲሁም ለስኬቷ ባለቤቷ አቶ አድማሱ እንደሚያግዛት ትናገራለች ። ለቤተሰብ ጊዜ መስጠት፣ ከመጠን በላይ ራስ ላይ ጫና አለመፍጠር እና ነገሮችን ተረጋግቶ ማስኬድ ከህይወቷ ያገኘችው ተሞክሮ ነው ። የእናቷ ከፍተኛ የሆነ በጎ ተጽእኖ እንዳለባት የምታነሳው አና እናቷ ጀግናዋ እንደሆኑ ትናገራለች። በሞዴሊንግ ዙሪያ አባቷ እና እናቷ የተለያየ አቋም ነበራቸው ። አባቷ የምዕራቡን ዓለም የሚያውቁ ዲፕሎማት ቢሆኑም እንደ ብዙው ኢትዮጵያዊ አባት ቆጠብ ያሉ ሰው ናቸው ። በዚህም የተነሳ የልጃቸውን የሙያ ምርጫ በቀላሉ አልተቀበሉትም ። እናቷ በበኩላቸው ዲዛይነር በመሆናቸው የልጃቸውን ምርጫ ለመቀበል አልከበዳቸውም ። በዚህም የተነሳ እናትና አባት በዚህ ዙሪያ ለመስማማት ጊዜ የወሰደባቸው ሲሆን በኋላ ግን አባት የሚስትን ሀሳብ ተቀብለው ልጃቸውን መደገፍ ጀምረዋል ። በወቅቱ በነበሩት ጥቂት እድሎችም ተጠቅማ ከነበሩት ጥቂት ጥቁር ሞዴሎች መካከል አንዷ ሆና በስኬት መጓዝ ችላለች ።
ገና በልጅነቴ በቂ ገንዘብ አግኝቻለሁ ስኬታማም ነበርኩ የምትለው አና በወቅቱ የነፍሴ ጥሪ ምን እንደሆነ ራሴን እጠይቅ ነበር በማለት ልቧ ገና ያኔ ተመልሳ አገሯ መኖር እና ህዝቧን ማገዝ ትመኝ እንደነበር ትናገራለች ። ተመኝታም አልቀረች ሁኔታዎች ሲመቻቹላት ወደ አገሯ ለመመለስ እና ህዝቧን ለማገዝ አላመነታችም ።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አለልቱ ከተማ ከ22 ዓመት በፊት በመሰረተችው ትምህርት ቤት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የእውቀት ብርሃንን አብርታለች ። አና ትኩረቷን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ለአካባቢው ወጣቶች በነጻ ማዳረስ መሆኑን ትናገራለች ። በአለልቱ ከተማ በከፈተችው ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በነጻ ያገኛሉ፤ ምግብ በቀን ሶስት ጊዜ ይመገባሉ ። ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱም ምግብ በቤታቸው ለማግኘት የሚቸገሩ ከሆነ ይዘው የመሄድ መብት አላቸው ።ተማሪዎቹ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሻገሩም ድጋፉ አይለያቸውም ።
አና ከ25 ዓመታት በፊት ያቋቋመችው የኢትዮጵያ ህጻናት ፈንድ የተሰኘው የበጎ አድራጎት ተቋም ከላይ በተገለጸው ትምህርት ቤት ከ800 በላይ ተማሪዎችን ያስተምራል ። ከዚህ ትምህርት ቤት ተነስተው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ራሳቸውን የቻሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን አሉ ። የአካባቢው ማህበረሰብ በምጣኔ ሀብት ራሱን የሚችልበት በርካታ የራስ አገዝ ስራዎችን ያከናውናል። ከዚህ ባለፈ በሙያዋ አዳዲስ ዲዛይነሮችን ለመፍጠር የግሏን ጥረት እያደረገች ሲሆን አንደኛው በጎ ተጽእኖዋ ይህ እንዲሆን እንደምትፈልግ ትናገራለች ። ጥጡም ቆዳውም ሌላውም እኛ ጋር አለ ስለዚህ እኛ ሌሎችን ለመምሰል ከመሞከር ይልቅ የራሳችን አዲስ መንገድ መፈለግ አለብን ስትልም ለዲዛይነሮች ትመክራለች ።
አና በበጎ ስራዋ በዘንድሮው የ10ኛው የበጎ ሰው ሽልማት በጎ ባደረጉ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ዘርፍ ከሶስት የመጨረሻ ተሸላሚዎች አንዷ ሆናለች። ባለፈው ዓመትም የጣሊያን መንግስት አና የኢትዮጵያ እና የጣሊያንን ወዳጅነት ለማጠናከር ባደረገችው ተግባር የኢጣሊያ ከፍተኛው ሽልማት የሆነውን ኦፊሰር ኦፍ ኦርደር ኦፍ ዘ ስታር ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ተበርክቶላታል ።
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም