ስፖርት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ያደገና በስፋት መዘውተር የጀመረ ዘርፍ መሆኑን የታሪክ ማህደሮች ይነግሩናል። ከዚያ ቀደም በነበረው ጊዜ ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች እንዲሁም የሰራተኛው መደብ የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ነበር ስፖርታዊ ውድድሮችን የሚከውኑት። ከጊዜ በኋላ ግን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እየተጠናከሩና ውድድሮችም ሽልማት ማዘጋጀት መጀመራቸውን ተከትሎ የስፖርት ዘርፍን በነጻ የሚያገለግሉና በስፖርተኝነት ሙያ ሕይወታቸውን የሚመሩ በሚል ተለዩ።
መደበኛ ስራቸው ስፖርት ያልሆነ ነገር ግን ለስፖርት ባላቸው ፍቅር የተነሳ ከሜዳ፣ ከመምና ከጂምናዚየም የማይጠፉ ሰዎችም አማተር ስፖርተኞች በሚል ይጠራሉ። ‹‹አማተሪዝም›› የሚለው ቃል ሲተረጎምም በስፖርት፣ በኪነጥበብ አሊያም በሳይንስ ዘርፎች ውስጥ ባለሙያ የነበረ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ እንደ ባለሙያ ምንም ዓይነት ገቢና ጥቅማ ጥቅም ሳያገኝ ማገልገልን ያመላክታል። ይህም በስፖርት ዘርፍ ከተለመዱ አሰራሮች መካከል ሲሆን፤ በተለያዩ ስፖርቶች መደበኛ ልምምድና ዝግጅት በማድረግ እንዲሁም በመወዳደርም ጭምር ተካፋይ ናቸው። ተሳትፏቸውም አገርን ወክለው በኦሊምፒክ እስከመወዳደር ይደርሳል።
ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ የተለመደ ባይሆንም በሌላ መልክ መተግበሩ አልቀረም። የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ ዘርፉ በመንግስትና ህዝባዊ አካል እንደሚመራ ያመላክታል። ይህም ማለት መንግስት በበላይነት ቁጥጥር ከማድረግና አቅም የሌላቸውን ማህበራት በበጀት የመደገፍ ኃላፊነት ሲኖርበት ህዝባዊው አካል (የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት) ደግሞ ስፖርቱን ይመራል። ይኸውም ከህብረተሰቡ መካከል የተመረጡ፣ በስፖርቱ ውስጥ ያለፉ ወይም ስለ ስፖርቱ የሚያውቁ ነጻ አገልጋዮች በእውቀታቸው፣ ገንዘባቸውና በጊዜያቸው ስፖርቱንና ህዝባቸውን ያገለግላሉ። በሌላ በኩል ያለ ምንም ገቢ በገዛ ፈቃዳቸው ታዳጊ ስፖርተኞችን በማሰልጠንና በማብቃት ለክለቦች እንዲሁም ብሄራዊ ቡድኖች ግብዓት የሚሆኑ ስፖርተኞችን የሚያፈሩ በርካታ አገልጋዮችም አሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ስፖርት የመልካም ገጽታቸው ምክንያት ሆኗል። ኢትዮጵያ በተለይ የታወቀችበት አትሌቲክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋወቃት ከመሆኑም ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር፣ ከስፖርቱ በሚገኘው ገቢም ለሌሎች እንጀራ ሆኖ ያገለግላል። አትሌቶችና አሰልጣኞችም ታዳጊዎችን በማፍራት እንዲሁም በስፖርቱ ስር ያሉ ማህበራትን በማደራጀትና በመምራትም ያልተቆጠበ አገልጋይነታቸውን ያሳያሉ።
ለዚህ ግልጽ ማሳያ የምትሆነው ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት በማገልገል ላይ የምትገኘው ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ናት። በርካቶች ‹‹አገር›› እያሉ የሚጠሯት ደራርቱ ከአገሯ አልፏ አፍሪካንም በማስጠራት ነበር የስፖርቱን ዓለም ስኬቷን የተቀዳጀችው። ለዓመታት በአትሌትነት ስታሳልፍም ላቧንም እንባዋንም ለአገሯ ያለስስት በማፍሰስ ነበር። በኦሊምፒክ፣ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተካፍላ በማሸነፍና የአገርን ስም እንዲሁም ባንዲራ በበጎ በማስነሳት አገሯን ስታገለግል ኖራለች።
ከስፖርቱ ከራቀች በኋላም ወደ ፌዴሬሽኑ በመምጣት ስፖርቱንና አገሯን በአመራርነት በማገልገል ላይ ትገኛለች። በቅድሚያ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ቀጥሎም በፕሬዚዳንትነት ፌዴሬሽኑን በመምራት ላይ የምትገኘው ፍልቅልቋ ደራርቱ አትሌቶችን፣ አሰልጣኞችን፣ ዳኞችን፣ የጽህፈት ቤቱን ሰራተኞች እንዲሁም በስፖርቱ ዙሪያ ያሉ ባለሙያዎችን በልምዷ እንዲሁም በገንዘቧ ስታገለግል ሙሉ ጊዜዋንና ልቧን በመስጠት መሆኑን በርካቶች ይመሰክራሉ። ከአመራርነት ይልቅ እንደ አገልጋይ በልምምድና ውድድር ሜዳዎች አትሌቶችን ከማበረታታትና ከማጽናናት አልፋ እንደ እናት በመንከባከብም ጭምር ወደር የማይገኝላት አገልጋይነቷን አሳይታለች።
ከስፖርቱ ባለፈ በኢንቨስትመንት፣ በበጎ ፈቃደኝነት፣ በአስታራቂነት እንዲሁም ሰላምንና አንድነትን በማስፈን ህዝቧን እስካሁንም በማገልገል ላይ ትገኛለች። ለበርካቶች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ በኢንቨስትመንት ተሳታፊ በመሆን ላይ ትገኛለች። ልበ ሩህሩህ በመሆኗም ካዘኑት ጋር ከማዘንና የተሰበሩትን ከማጽናናት ባለፈ የቁሳቁስ እርዳታን በማድረግ በጎ ፈቃደኝነቷንም በተለያዩ ጊዜያት አሳታለች። ሰላምና አንድነትን በመስበክና በማስታረቅ የምትተጋው እንቁ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በአመራርነት በማገልገል እጅግ አስመስጋኝ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል።
በዚህም ምክንያት በርካታ እውቅናዎችን ያገኘች ሲሆን፤ በቅርቡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተሰጣትን የክብር ዶክትሬት እንዲሁም ከቀናት በፊት በበጎ ሰው ሽልማት ላይ ልዩ ተሸላሚ ሆና ካባ ለብሳለች።
ብሔራዊ የስፖርት ፌዴሬሽኖችን መምራት አገርና ህዝብን ለማገልገል ሳይሆን አንዳች ጥቅም የሚገኝበት ስልጣን አድርገው የሚቆጥሩ በርካታ ግለሰቦች ባሉባት አገር ደራርቱ ብዙ ሽኩቻና ሴራዎችን እየታገለች የአገልጋይነት ተምሳሌት ሆናለች። ደራርቱ በፌዴሬሽን አመራርነት ዘመኗ ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጣለች። በስፖርቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ሴራዎችን ተመልክታ በዝምታ አላለፈችም። ከአገር ውጤት ይልቅ ለገዛ ጥቅማቸው ቅድሚያ የሚሰጡ ግለሰቦችን ፊት ለፊት ተጋፍጣለች። በጉባኤ ፊት አልቅሳለች። አገርና ህዝብን ለማገልገል የገባችውን ቃል በሴራና በደባዎች ተሸንፋ ምን አገባኝ ብላ አልሸሸችም። ታግላ ትክክል የመሰላትን ነገር አድርጋለች። በዚህም ውጤታማ መሆኗን ሊጠናቀቅ አንድ ቀን በቀረው በዚህ አመት ብቻ በስፖርቱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዓለም አቀፍ ስኬቶችን በማስመዝገብ በተግባር አሳይታለች። ለዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ለእሷ ትልቅ ክብርና ፍቅር አለው። ዛሬ የአገልጋይነት ቀን እንደመሆኑ ስፖርትና አገልጋይነት ስናስብ ከደራርቱ የተሻለ የአገልጋይነት ተምሳሌት ማንን ማስቀመጥ ይቻላል?
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2014