የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው፤ ስፖርትና ሰላም። ስፖርት ያለ ሰላም ሊከወን አይችልም፤ ሰላምም በስፖርት አውድ ይሰበካል። ከማዝናናት፣ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነትን ከመጠበቅ ባለፈ ከተፈጥሮ እና ከሰላም ጋር ባለው ጥብቅ ቁርኝት ምክንያት የተለያዩ መልእክቶችን ለማስተላለፍ ጭምር እጅግ ተመራጭ ዘርፍ ነው። ለዚህም ነው ከአሸናፊነት ፉክክሩ ተመጣጣኝ የሆነ ዋንጫ (ሽልማት) ለስፖርታዊ ጨዋነት የሚበረከተው። ይኸውም ተደጋጋሚ ጥፋት ላላደረሰ፣ ተፎካካሪውን በወዳጅነት ስሜት ለሚያስተናግድ እንዲሁም ሰላማዊ ስፖርትን ለሚተገብር ስፖርተኛ ወይም ቡድን እውቅና የሚሰጥ ነው።
ስፖርት ዓለምን የመለወጥ ኃይል አለው፤ ማህበረሰባዊነትን በማጠናከር እና አብሮነትን በማጎልበት ሰላምን ለማስፈን ይተጋል። ለዚህም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እአአ በ2013 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው፤ ዓለም አቀፍ የስፖርት ቀን ለሰላም ግንባታ በሚል እንዲከበር የወሰነው። ዘመናዊው ኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ እአአ በ1896 በሚያዝያ ወር መጀመሩን ተንተርሶም የስፖርት ለሰላም ግንባታ ዕለት በመላው ዓለም ታስቦ ይውላል። ይህም ብቻም ሳይሆን ተቋሙ ሰላምን ለማስፈንና ለመስበክ ከሚጠቀማቸው መሳሪያዎች መካከል አንዱ ስፖርት ነው። በመገባደድ ላይ ባለው ዓመትም ስፖርት በአካባቢያዊ የአየር ለውጥ ላይ ያለውን በጎ ሚና በማመላከት ተከብሯል።
ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ከመርሆዎቹ ሁሉ አንኳር የሆነው ሃሳቡ ሰላም ሲሆን፤ ሰላምን ባላከበሩና በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ያነጣጠሩና አደገኛ ትኩሳቶች ያሉባቸውን አገራት እስከማገድና ከአባልነትም እስከማሰናበት ይደርሳል። ከዚህ ባለፈ ኮሚቴው በተለያዩ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች አገራቸውን ጥለው ለስደት የተዳረጉ ሰዎችን በራሱ ባንዲራ በመወከል በታላቁ የውድድር መድረክ ላይ አገራቸውን እንደወከሉት ሌሎች ስፖርተኞች ሁሉ እንዲወዳደሩ በማድረግም አስመስጋኝ ተግባርን ይከውናል።
የዓለም ቋንቋ የሚል ስያሜ የተሰጠው እግር ኳስም ከትኩረት አቅጣጫዎቹ መካከል አንዱ ሰላማዊ የውድድር መድረክ ነው። የእግር ኳስ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ ተጋጣሚዎቹ ቡድኖች እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት ሰላምታ እንዲሁም አስቀድሞ ሰላማዊነትን የሚያንጸባርቁ ማስታወቂያዎችን ይዞ መገኘትም የስፖርቱን ዓላማ በግልጽ የሚያመላክት ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በሚደረጉ የእግር ኳስ ውድድሮች የጸባይ ዋንጫን ማበርከትም የተለመደ ነው። ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው ፊፋም ሰላማዊነትን በወርቃማ ደንቦቹ ላይ በግልጽ አመላክቷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቀመጠውን አቅጣጫ እአአ ከ2016 ጀምሮ በመተግበር እንዲሁም ብሄራዊ ፌዴሬሽኖችን፣ ክለቦችንና ተጫዋቾችንም በማስተባበር ይታወቃል። በቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የተመሰረተና ለትርፍ ያልተቋቋመው እግር ኳስ ለሰላም የሚል ድርጅትም ከፊፋ ጋር በጋራ ይሰራል። ይህ ተቋም እግር ኳስ ለዲፕሎማሲ መሳሪያ እንዲሁም መግባቢያ እንዲሆንም ይሰራል። የሰላም ዋንጫ የሚል ስያሜ የያዘው ሌላኛው ተቋምም በየሁለት ዓመት የወዳጅነት ጨዋታን መሰረት ያደረገ የእግር ኳስ ውድድርም እአአ እስከ 2012 ሲደረግ ቆይቷል።
በአንጻራዊነት ሰላማዊና ከንክኪ የጸዳ እንደሆነ የሚነገርለት የአትሌቲክስ ስፖርትም መተሳሰብና አንድነትን ከአሸናፊነትም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። በውድድሮች ላይ ከራሳቸው አሸናፊነት ይልቅ ለተፎካካሪያቸው መልካምነትን ያሳዩና የአንድነትን ዋጋ ያንጸባረቁ ምስጉን አትሌቶችም በየጊዜው ታይተዋል። ዓለም አቀፉ ተቋም ሰላምን በሚመለከቱ ጉዳዮች ከሌሎች አካላት ጋር ከመስራት ባለፈ ለሰላም መስፈን ከፍተኛ ሚና ያላቸው ውድድሮችንም በመደገፍ ይታወቃል። ተፈጥሮን በመንከባከብ እንዲሁም ማህበራዊነትን ማስፋፋት ላይም ይሰራል።
የስፖርት ማህበራትና ሌሎች ተቋማትም ሰላምን ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ሲሆን፤ መቀመጫውን በሞናኮ ያደረገ ‹‹ስፖርትና ሰላም›› የሚልና አላማውም እንደመጠሪያው የሆነ ተቋምም ዓመታትን በስራ ላይ አስቆጥሯል። የዓለም ዋንጫ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን በአገሩ ለዓመታት የነበረውን የእርስ በእርስ ግጭት እንዲቆም በመማጸን ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ስሙ ከታሪካዊ የእግር ኳስ ከዋክብት መካከል የሰፈረው ኮትዲቯራዊው ዲድየር ድሮግባ ደግሞ ተቋሙን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ያገለግላል።
ተቋሙ በየአገራቱ ዓላማውን ለማስረጽ የሚሰራ ሲሆን፤ ስፖርተኞችንም ይሸልማል። እንደሚታወቀው ተገዳዳሪ በሆኑ አካላት መካከል የበላይነትን አሊያም አሸናፊነትን ለመቀዳጀት ሲባል በሚካሄድ ፍልሚያ ለሚሰሩ ጥፋቶች ቢጫ እና ቀይ ካርዶች መመዘዛቸው አይቀሬ ነው። ይሁንና ነጭ ካርድም የስፖርትን ሰላማዊነት የሚያንጸባርቅ እንዲሆን አስተዋውቋል።
የኢትዮጵያን የሰላም ሁኔታ ለመመለስ መንግስት የተለያዩ ስልቶችን እየተከተለ የሚገኝ ቢሆንም ፤ የሰላም ማዕከል በሆነው የስፖርት ዘርፍ ግን ብዙ አልተሰራበትም። በኢትዮጵያ እየገነገነ የመጣው የዘውግ ፖለቲካ ክልሎች በጎሪጥ እንዲተያዩ፤ የኔ ብሔር፣ ያንተ ጎሳ በሚል የጠበበ አስተሳሰብ መገፋፋቱ እየጎላ ሄዷል። ይህን ለአገር ጠንቅ የሆነ እንቅፋት ለመቅረፍ የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር የተለያዩ የሰላም መድረኮችን በማዘጋጀት ጥረት ማድረጉ ይታወቃል። የሚኒስቴሩ ጥረት የስፖርቱን ዘርፍን በተለየ መልኩ መሰረት ማድረግ በጥራትና በፍጥነት ፍሬያማ ማድረግ ላይ ግን የማይካዱ ውስንነቶች አሉ።
በተለይ ደግሞ በአገሪቱ ህዝቦች መካከል መቻቻልን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን…የሚሰብኩ የውድድር መድረኮችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ቀርጾ ወደ ተግባር በመግባት ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው አልቀጠሉም። ለምሳሌ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ«ኢትዮጵያችን እንሩጥ» የሚል ሀሳብ የያዘ ውድድር አዘጋጅቶ፤ አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ ብሄራዊ ስሜት፣ ባጠቃላይ ኢትዮጵያዊነት የሚያንጸባረቁባቸውን መልዕክቶች በማስተላለፍ የልዩነቱን ግንብ የመናድ አጋጣሚ መፍጠር ይቻላል። እንደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሁሉ በሌሎች የስፖርት አይነቶችም አንድነትን፣ ሰላምን የሚያጎሉ ስፖርታዊ ክንውኖች ማዘጋጀት ቢቻል ትርፉ የጎላ እንደሚሆን ይታመናል። ምክንያቱም ስፖርት ሰላምን ለማስፈን ያለውን አቅምና ውጤታማነት በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ለመመልከት ተችሏልና። የዘርፉ የሰላም አለኝታነት ደግሞ በትላልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር ቅቡልነቱ ያለው መሆኑን በዛሬው የሰላም ቀን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2014