ስልክን ለፈለሰፈው ምስጋና ይግባውና ዛሬ በስልክ የማይቀለጥፍ ስራ፣ የማይሰራ ሴራ፣ የማይዋሽ ውሸት፣ የማይቀመር ሂሳብ፣ የማይጎለጎል መረጃ ኧረ የማይገኝ ትዳርም የለም። ምን ያህሉ በአዳር፤ ምን ያህሉ በውጤታማና በተሳካ ትዳር መጠናቀቅ አለመጠናቀቁን የሚያረጋግጥ ጥናት ይፋ አልሆነም እንጂ፤ ብዙዎቻችን ለአዳርም ይሁን ለትዳር የእጅ ስልኮቻችንን ተጠቅመናል። ከማህበራዊ ሚዲያም የተለያዩ ማዕዶችን ተቋድሰናል። ታዲያ፤ ለዚህ አይመስላችሁም እኛና የእጅ ስልካችን ክፉኛ ተዋድደን፣ ተፋቅረንና ሳንለያይ ተነፋፍቀን “ብለቅህ ወገቤ ይላቀቅ” በሚል ጠንካራ ስሜት ተጠባብቀን ያለነው!?
ታዲያ ይህን ሁሉ ለምናደርግበት ስልክ ምንስ ብንሆን ይገርማል እንዴ” በእውነት አይገርምም። ይሁንና ልጆቻችን ሳይቀሩ ለእጅ ስልኮቻችን ያላቸው ፍቅር ከእኛ በብዙ እጥፍ ልቆ፤ መጥቆና ጠልቆ ስመለከት ግን በጣም ይገርመኛል። ስልክ ስላችሁ ሕፃናቱ የሚፈልጉት ሃሎ… አቤት… ብሎ መልዕክት ለመለዋወጥ ብቻ የሚያገለግለውን ዓይነት ስልክ አይደለም። የዘመኑን… ዓይነት ስልክ ነው የምላችሁ፤ ገባችሁ አይደል? አዎ… እንደሱ ዓይነት ዘመናዊ ስልክ (ተች ስክሪን) አዎ… ሕፃናቱ እሱን ነው የሚወዱት፤ ይህን ስል አንድ የስራ ባልደረባዬ ያለው ነገር ትዝ አለኝ “እኔ ሕፃናትን እወዳለሁ፤ ነገር ግን ሕፃናቱ አይቀርቡኝም የገዛ የእህትና የወንድሜ ልጆች እንኳን ብዙም አይቀርቡኝም ምክንያቱ ደግሞ የእጅ ስልኬ እነሱ የሚፈልጉት አይነት አይደለም” ሲል አጫውቶኛል።
አሁን አሁን አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች በዘመናዊ የእጅ ስልኮቻቸው ምክንያት ልጆቻቸው ከነርሱ ሲርቁ፤ ከፋ ሲልም ወላጆች ራሳቸው በስልኮቻቸው አማካኝነት በሚያገኙት መረጃም ይሁን መዝናኛ ጭልጥ ብለው በመጓዝ ልጆቻቸውን ሲረሱ ይስተዋላል። አንዳንድ ስራ ውሎ ሲገባ ለልጆቹ የረባ ሰላምታ እንኳን ሳያቀርብ ስልኩ ላይ የሚጣድ ወላጅ እንዳለ ሁሉ፤ ከወላጆቻቸው ፍቅር በላይ ስልኮቻቸውን በብዙ እጥፍ ጓጉተውና ናፍቀው የሚጠባበቁ ልጆችም አሉ። ወላጆች በስልኩ ያልተጠቀሙትን ያህል ሕፃናቱ ከ“ሀ እስከ ፐ” እያንዳንዷን ነገር ሲጠቀሙ ይስተዋላል። እነዚህ ልጆች ታዲያ ከዕድሜያቸው በላይ ለሆኑ በርካታ ጉዳዮች ተጋላጭ በመሆን መስመር ሊስቱ ይችላሉና ሁሉንም ነገር በገደብና በጥንቃቄ ማስኬድ ተገቢ ነው።
እስኪ ደግሞ የልጆቹን የስልክ ፍቅር ተወት እናድርግና ወደራሳችን እንመለስ፤ ስንቶቻችን ነን ለእጅ ስልኮቻችን ግድ የማይሰጠንና ካልጠራ በስተቀር ስልክ እንዳለን እንኳን የማናስታውስ? ስንቶቻችንስ ነን የእጅ ስልካችንን በየደቂቃው ካለየነው ቅር ቅር የሚለንና ዓይናችንን ከስልኩ እስክሪን ላይ አፍጥጠን የምንውል? ከዚያም በላይ ደግሞ አንዳንዶቻችን ስልካችንን ከመቆለፍም አልፈን ማንም ይሁን ማን፤ የቤተሰብን አባል ጨምሮ እንዲነካብን አይደለም እንዳያይብን ከፍተኛና ልዩ ጥንቃቄ በማድረጋችን ምክንያት “ኧረ የሱን ስልክ…የሷን ስልክ…ማን ሊነካ! የማይሆነውን” የምንባልም ብዙዎች አለን።
ይሄኔ ታዲያ “ጠርጥር ከገንፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር” ነውና ተረቱ መጠርጠር ደግ ነው። በተለይም ቤተሰብ መስርቶ ስልኬን አትዩብኝ፤ አትንኩብኝ ማለት ወፍጮ ቤት ገብቶ ዱቄት አይንካኝ እንደማለት ነውና ጤናማነቱ ያጠያይቃል። ምክንያቱም ከላይ ለመግለፅ
እንደሞከርኩት በእጅ ስልኮቻችን የማንሰራው ስራም ሆነ ሴራ የለምና ነው። በመሆኑም፤ በርካታ ትዳሮችና ጓደኝነቶች ሳይሰምሩ ቀርተው ቤተሰብ የሚበተንበት አጋጣሚም ሲፈጠር አስተውለናል። እንግዲህ አንተም፤ አንቺም፤ እሷም፤ እነርሱም፤ እኛም፤ ሁላችንም ከመጠን ያለፈ ጥንቃቄና ፍቅር ለእጅ ስልክ ሲሰጥ ካስተዋልን ጤናማ አይደለምና ብንጠረጥር መልካም ነው እላለሁ።
ይህን ካልኩ ወዲያ፤ ከእጅ ስልኳ ጋር ክፉኛ የተቆራኘች አንዲት ወጣት የገጠማትን ላካፍላችሁ። በመኝታ ሰዓታችን ብዙዎቻችን እንደምናደርገው የእጅ ስልካችንን ከራስጌያችን እናስቀምጣለን። ወጣቷም ከእንቅልፏ በቅጡ ሳትነቃ ስልኳን ካስቀመጠችበት ራስጌዋ ለማንሳት አንድ እጇን ሰንዝራ ትዳስሳለች፤ ዳሰሳዋ እየጨመረ ስልኳ እየራቀ በመሄዱ አልጋዋን ለቅቃ መሬት ትወርዳለች። መሬት ወርዳም አላበቃችም ዳሰሳዋን ትቀጥላለች።
ወጣቷ፤ ስልኳን ለማግኘት ያላት ጉጉት ጨምሯል። አንድ እጇ ዳሰሳውን፤ ሌላው አካሏ ደግሞ በአንሶላዋ እየተጠቀለለ ዙሪያዋን በመዳሰስ መሬት ለመሬት መንከባለሏን ቀጥላለች። በእንቅልፍ ሰመመን ውስጥ እንዳለች ነውና አይኖቿ አልተገለጡም። የመኝታ ቤቷን ለቃ ሳሎኑንም አልፋ ከቤቷ ውጭ ድረስ አይኖቿን ሳትገልጥ የእጅ ስልኳን ፍለጋ እየዳሰሰች ነጎደች።
በመጨረሻም ከደጅ አልፋ በግቢው የአትክልት ስፍራ እየተንከባለለች በዳሰሳ የፍለጋ ዙሩን አከረረችው። ሄዳ ሄዳም ውሃ ዳር ደረሰች ደርሳም አልቀረች ውሃ ውስጥ ገብታ መንፈራገጥ ጀመረች። ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ማወቅ ብዙም አያጓጓም ቢያጓጓም እንኳ ላካፍላችሁ አልችልም። ምክንያቱም ይህን መልዕክት ያስተላለፈው ቪዲዮ ጫወታውን እዚህ ላይ አብቅቷል።
የሆነ ሆነና ይህ ድርጊት የተፈፀመው በውጪው ዓለም ይሁን እንጂ፤ በእኛም ሀገር አይደረግም ማለት አይቻልም። እንዲያውም ወጣቷን ከገጠማት አጋጣሚ በላይ ቢገጥመንም ይገባናል ባይ ነኝ። ምክንያቱም እኛ ከውጭው ዓለም ይልቅ የመዝናኛም ሆነ የመረጃ ድርቅ ተጠቂዎች በመሆናችን በርካታ ነገሮችን ከእጅ ስልኮቻችን የምንጠብቅ በመሆናችን ሲያንሰን ነው እላለሁ። እናንተስ በእጅ ስልኮቻችን አጠቃቀም ዙሪያ ምን አስተያየት ይኖራችሁ ይሆን?…
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011
በፍሬህይወት አወቀ