አገርን የሚያስጠሩና ህዝባቸውን የሚያኮሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት፤ ስልጠና በዘመናዊና ሳይንሳዊ መንገድ ሊቃኝ ይገባዋል። ኢትዮጵያም ይህንኑ መንገድ በመከተልና የስፖርት ማሰልጠኛ አካዳሚዎችን በማቋቋም ከቅርብ ዓመት ወዲህ ጥረት ማድረግ ጀምራለች። በዚህ ረገድ ለአገራችን በርካታ ስፖርቶች ተተኪዎችን በብዛት እያፈራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተጠቃሽ ነው። የዛሬው እለት ‹‹የአምራችነት ቀን›› በሚል የተሰየመ እንደመሆኑ ይህን የአገሪቱን ትልቅ የስፖርት አካዳሚ ባለፉት ዓመታት ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ጉዞና በአገር ስፖርት ያመጣውን ተጨባጭ ለውጥ እንዳስሳለን።
አካዳሚው ከመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮዎች ለመወጣት ተተኪዎችን በማፍራት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። እስካሁን ስልጠና መስጠት ከጀመረበት ከ2006 ዓ.ም አንስቶ 669 ሰልጣኞች በተለያዩ ስፖርቶች አስመርቆ ወደተለያዩ ክለቦች አሸጋግራል። 259 ሰልጣኞችን ደግሞ ለብሄራዊ ቡድን ማስመረጥ ችሏል። በዚህም የአካዳሚው ፍሬዎች 33 ሜዳሊያዎች በአህጉር አቀፍ ውድድሮች፣17 ሜዳሊያዎችን ደግሞ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ማስመዝገብ ችለዋል።
አካዳሚው ታዳጊዎችን ከማሰልጠን ባለፈ የአካዳሚ ቆይታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት በተለያዩ አገርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በማሳተፍም ውጤታማ ሆኗል። የአካዳሚው ፍሬዎች አትሌቲክስን ጨምሮ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች (ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌት፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቅርጫት ኳስ እና ቦክስ) ውጤታማ መሆን ችለዋል። በዚህም የታዳጊዎች የኦሊምፒክ ውድድሮችን ጨምሮ በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች በሜዳሊያ ሰንጠረዥ የገቡ ብዛት ያላቸው ሰልጣኞችን ለአገር ማበርከት ችሏል። ይህም አካዳሚው ምርጥ ስፖርተኞችን በማፍራት ተልዕኮው በርካታ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አንዱ ማሳያ ሆኗል።
አካዳሚው ባለፉት ዓመታት አሰልጥኗቸው ስኬታማ መሆን ከቻሉ ታዳጊ ሰልጣኞች መካከል ስማቸው ነጥሮ የወጣ በርካቶች ናቸው። በአትሌቲክስ ስፖርት በዓለም ወጣቶች ቻምፒዮና የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ፣ በሪዮ እና ቶኪዮ ኦሊምፒኮች እንዲሁም በኳታር የዓለም ቻምፒዮና ተሳታፊ፣ በ3ሺ ሜትር መሰናክል እአአ የ2020 የዳይመንድ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ እና የኢትዮጵያ የርቀቱን ክብረ ወሰንን ለአምስት ዓመታት ይዞ የቆየው አትሌት ጌትነት ዋለ አካዳሚው ካፈራቸው ስመ ጥርና ስኬታማ ስፖርተኞች ግንባር ቀደሙ ነው።
የአካዳሚውን የአራት ዓመታት ቆይታ ከማጠናቀቁ አስቀድሞ አገሩን በተለያዩ መድረኮች እስከመወከል የደረሰው የዘንድሮው ተመራቂ ኤርሚያስ ግርማም በቅርቡ ትልቅ ስም እያተረፉ ከመጡ የአካዳሚው ፍሬዎች አንዱ ነው። ወጣቱ አትሌት ኤርሚያስ ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በ800 ሜትር እስከ መጨረሻው ማጣሪያ የተጓዘ ሲሆን፤ በኦሪጎን የዓለም ቻምፒዮናም አገሩን ወክሏል። በቅርቡ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ቻምፒዮና የወርቅ እና የነሃስ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብም አካዳሚው ከሚኮራባቸው ውጤታማ አትሌቶች አንዱ መሆን ችሏል።
በዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድሮች ላይ ውጤታማ የሆነች አትሌት የአለምዘርፍ የኃላው፣ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የዲፕሎማ ተሸላሚ በዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤት እንዲሁም የዳይመንድ ሊግ ተሳታፊዋ አትሌት ዘርፌ ወንድምአገኝም ከአካዳሚው ውጤታማ ፍሬዎች መካከል ይካተታሉ።
በእግር ኳስ ዘርፍም የዋናው ብሄራዊ ቡድን የመጀመሪያ ተሰላፊ ሱሌማን ሃሚድ፤ በሴቶች አረጋሽ ካልሳ፣ ንግስት በቀለ፣ መሳይ ተመስገን፣ ፎዚያ መሀመድ እንዲሁም አርያት ሁዶንግን የመሳሰሉ በርካታ ውጤታማ ተጫዋቾችን ባለፉት ዓመታት ማፍራት ችሏል። በርካታ የአካዳሚው ፍሬዎች ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች እና ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ተመርጠው በመጫወት ውጤታማ ሰልጣኞችን በሁለቱም ጾታ ማፍራት ተችሏል።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ ከምትታወቅባቸው ስፖርቶች ባሻገር በወርልድ ቴኳንዶም ለመጀመሪያ ጊዜ ስሟ የተጠራው አካዳሚው ባፈራው ሰልጣኝ ነው። ይኸውም በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በብቸኝነት የተካፈለውና በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ የሆነው ሰለሞን ቱፋ ነው። በተመሳሳይ ስፖርት በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አሸናፊዋና ሌላኛዋ ሰልጣኝ ናርዶስ ሲሳይም ስሟ ሳይነሳ አይታለፍም። ሃና ደረጀ እና እንዳሻው አላዩ ደግሞ በቦክስ ስፖርት የአፍሪካ ቻምፒዮና ወርቅ በማምጣት ውጤታማ መሆን የቻሉ የአካዳሚው ተተኪ ስፖርተኞች ናቸው።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ስር የተቋቋመውና አሰላ ከተማ የሚገኘው ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በርካታ ውጤታማ አትሌቶችን በማፍራት ሳይጠቀስ አይታለፍም። የአገር ውስጥ ክለቦችን ከማጠናከር ባሻገር በኦሊምፒክ፣ በዓለም ቻምፒዮና፣ በአፍሪካ እና የዓለም ታዳጊ ወጣቶች እና ሲኒየር ቻምፒዮናዎች ውጤታማ የሆኑ አትሌቶችን አፍርቷል። ለአብነትም በ3000 ሜትር መሰናክል ሃይለማርያም አማረ፣ ለሜቻ ግርማ፣ ታደሰ ታከለ፣ ሳሙኤል ፍሬው፣ ተስፋዬ አምሳሉ፣ አስማረች ነጋ፤ በ5000/1500/800 ሜትር ሳሙኤል አባተ፣ ወገኔ አዲሱ፣ አዲሱ ይሁኔ፣ ሰንደል ሙሳ፣ ድሪባ ግርማ፣ ደሳለኝ ግርማ፣ አህዛ በርሄ፤ በአጭር ርቀት፤ አደም ሙሳ፣ አህመድ ሙሳ፣ ደረሰ ተስፋዬ፣ ምህረት አሻሞ፣ ዮሀንስ ተፈራ፣ ፅጌ ድጉማ፣ ኤቢሴ ከበደ፤ በዝላይ ደግሞ ኡመድ ኡኩኝ፣ ድሪባ ግርማ፣ ብርሃኑ ሞሲሳ፣ አርያት ዲቦ፤ በውርወራ ብዙነሽ ኡተጌ ፣ ማሙሽ ታዬ ከዚሁ አካዳሚ የተገኙ ፍሬዎች ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2/2014