ሀገራዊ ለውጡ መላውን የሀገራችንን ህዝቦች ባሳተፈ መልኩ ዕለት ከዕለት ግለቱን እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። ከመከላከያ እስከ ውጭ ጉዳይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኩን አካቶ ፍትሃዊነትን ያረጋገጡ ታላላቅ ሪፎርሞች እየተተገበሩና ውጤትም እየተገኘባቸው ናቸው። ተሸፋፍነው የከረሙ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የዘረፋ ተግባራትም እርቃናቸውን እንዲቀሩ በማድረግ ሀገራችን ከዚህ በኋላ ለእኒህ መሰል እኩይ ተግባራት መደበቂያ ዋሻ እንደማትሆንና ከመጋረጃ ጀርባ የሚፈጸም ምንም ዓይነት በጎም ይሁን እኩይ ተግባር እንደማይኖር ተረጋግጧል።
አሳሪና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደ ጋሻ ሲያገለግሉ ቆይተዋል የተባሉ ህጎችም የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ ለማሻሻል እየተሰራ ይገኛል። የሃሳብ ብዝሃነት በነጻነት እንዲስተጋባም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ነጻ ከማድረግ ጀምሮ የታገዱ ብሎገሮችና ዌብሳይቶች በነጻነት የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታም ተፈጥሯል። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በጋዜጠኝነት ሥራው ምክንያት የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ የለም ብለን ለመናገር የምንችልበት ደረጃም ላይ ደርሰናል።
አሳዳጅና ተሳዳጅ ሆነው የኖሩት መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአንድ አዳራሽ ተሳባስበው መምከርና መሞገትም ይዘዋል። ከእርስ በእርስ መበላላት ወደ አብሮ መብላትም ተሸጋግረው ጠቅላይ ሚኒስትሩና የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች በአንድ ማዕድ አብረው ሲቋደሱም ተመልክተናል።
ከአንድም ይሁን በሌላ አካል በተደረገባቸው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ እጅግ ይፈሩ የነበሩና እንደ አገር በታኝ ይቆጠሩ የነበሩ ፓርቲዎችም በሀገሪቱ የሰፈነውን የነጻነት አየር ተጠቅመውና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ብለው በነጻነት ሲንቀሳቀሱም እየተስተዋለ ነው። በአጠቃላይ በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ እንድንሰንቅና የ2012 ምርጫን ጨምሮ መጪው ጊዜ ይዞልን የሚመጣውን የእኩልነት፣ የነጻነትና የብልጽግና ብርሃንን በተስፋ እንድንጠብቅ አድርጎናል።
ይሁንና በጥባጭ እያለ ማን የጠራ ይጠጣል እንደሚባለው በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ አልዋጥ ያላቸውና እንቅልፍ የነሳቸው ኃይሎች የጥፋት ስልቶቻቸውን እንደ እስስት እየቀያየሩ ሀገራችንን ለማፈራረስና ሰላማችንን ለማናጋት ከምንጊዜውም ይልቅ ተጠናክረው በመስራት ላይ ይገኛሉ። ባለፉት ሳምንታት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እንደ ጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ በመጠቀም ብጥብጥ ለማንገስና ሀገር ለማፍረስ የወጠኑት ውጥን በሰላም ወዳዱ ህዝባችንና በተማሪዎቹ ጥረት ከሽፏል።
ይህም ጠላትን አንገት ሲያስደፋ ለህዝባችንን ደግሞ እፎይታን ለግሷል።
የጥፋት ኃይሎች ተስፋ የሚቆርጡ አይደሉምና ዛሬም ስልቶቻቸውን እየቀያየሩ አንዴ በብሄር ሌላ ጊዜ በሀይማኖት ሽፋን የጥፋት ተልዕኳቸውን ለመፈጸምና ለማስፈጸም እንቅልፍ አጥተው እየባዘኑ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ከሰሞኑ በምስራቅ ወለጋና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አካባቢ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ነው። የዚህ እርኩስ ተግባር ፈጻሚና አስፈጻሚዎች ጥቂቶች ቢሆኑም ዓላማቸው ግን በንጹሃን የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ህዝቦች መካካል ግጭትን በመቀስቀስ ደም ማፋሰስና ሀገርን ወደለየለት ጦርነት ማስገባት መሆኑ ግልጽ ነው።
ይህንን እኩይ ድርጊት አስመልክቶ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ባወጣው መግለጫ የጥፋት ኃይሎች በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ በሰላም የሚኖሩ ኦሮሞዎችን፣ እንዲሁም የሶማሌ ክልል ወሰን አካባቢ በሞያሌ፣ በጭናክሰን እና ባቢሌ ወረዳ በሚኖሩ ሰላማዊ ህዝቦች ላይ አሰቃቂ የሆነ ግድያ እንዲሁም ከቤት ንብረት የማፈናቀል ወንጀል እየፈፀሙ ነው ብሏል። እንዲሁም የተደራጀ ጦርነት በመክፈት በሰላማዊ ህዝብ እንዲሁም የህዝብ ጋሻ በሆነው እና በህዝቡ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ከፊት ሆኖ በሚከላከለው የኦሮሚያ ፖሊስ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑንም ፓርቲው አስታውቋል።
የዚህ የተደራጀ ወንጀል አላማም በጥቅሉ ሲታይ የኦሮሞ ልጆችን ደም ማፍሰስና ኦሮሚያን የጦር አውድማ ማድረግና አንድነታችንን ማፍረስ፤ በህዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር አድርገው የህዝብን ሀብት ለመዝረፍ እንዲሁም ህዝቡ ወደ ነፃነት የሚያደርገው ጉዞ እንዲደናቀፍ በማድረግ ለሌብነት፣ ለዝርፊያ እና ባርነት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው ብሏል። በህዝባችን ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አካላትንም የገቡበት ጉድጓድ በመግባት ለህግ በማቅረብ ተመልሰው ጉዳት ማድረስ እንዳይችሉ እንሰብራቸዋለንም ሲልም ገልጿል።ስለሆነም የፓርቲው አቋም ተገቢና ወቅታዊ በመሆኑ ለህዝቦች ሰላምና ደህንነት ሲባል ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡
ዜጎች ሃይማኖታዊ ሥነ ስርዓቶችን በማካሄድ በደማቅ ሁኔታ የሚያከብሯቸውን በዓላትም ለግጭት መቀስቀሻ ለማዋል የሚደረገው ጥረትም እነዚሁ የጥፋት ኃይሎች ዓላማቸውን እስካሳካላቸው ድረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ያመላክታል። ኢድም ሆነ መስቀል ኢሬቻም ሆነ የህዳር ጽዮን በዓል ምዕመናኑ በታላቅ አክብሮት የሚያከብሯቸው መንፈሳዊ በዓላት ሲሆኑ የጥፋት ኃይሎቹ ደግሞ በሃይማኖት ሽፋን እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም እንደምቹ ሁኔታ ሊጠቀሙባቸው ሲሞክሩ ይታያል። ይህም ነገሮችን በጥንቃቄ እያየን ካልተጓዝን ሀገራችንን የመበተን ተልዕኮን ያነገቡ ኃይሎች የእምነት ተቋማትንም ተጠቅመው እኩይ ተግባራቸውን ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይሉ በግልጽ ያስረዳናል።
አንዴ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በሽፋንነት በመጠቀም በል ሲላቸው በብሄር ሌላ ጊዜ ደግሞ በሃይማኖት መልካቸውን እየቀያየሩ የለውጥ ጉዟችንን ለመቀልበስና እርስ በእርስ ለማባላት የሚደረገው ጥረት የሚከሽፈው ይህን እኩይ ተግባር በሚገባ በመገንዘብና ከዚህ በተቃራኒው ለሰላም በመቆም ነው። ስለሆነም መላ የሀገራችን ህዝቦች የጥፋት ኃይሎችን ሴራችሁ ገብቶናልና የአኩይ ዓላማችሁ ሰለባ አንሆንም ብሎ አደብ ሊያሲዛቸው ይገባል።