የኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች የውሃ ዋና ቻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው። ውድድሩ ትናንት በመኮንኖች የውሃ ዋና ገንዳ የተጀመረ ሲሆን ክለቦችና ክልሎች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።
በተለያዩ ስፖርቶች በሚካሄዱ የታዳጊ ወጣቶች ውድድሮች ላይ ከእድሜ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዚህ የውሃ ዋና ቻምፒዮና ለመቅረፍ አገር አቀፍ ፌዴሬሽኑ ጠንካራ ስራዎችን እንዳከናወነ ተገልጿል። ይህም በቻምፒዮናው በትክክለኛ እድሜ ታዳጊ ወጣቶች የውድድር እድል አግኝተው ራሳቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚን ለመፍጠር ታስቦ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት ደምሱ በቻምፒዮናው የመክፈቻ ስነስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በውድድሩ የሚሳተፉ ታዳጊ ወጣቶች ከዚህ ቀደም በየትኛውም አገር አቀፍ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ እድል ያላገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል። ይህም ውድድሩን የተለየ እንደሚያደርገው ወይዘሮ መሰረት ተናግረዋል።
ቻምፒዮናው ኢትዮጵያ በውሃ ዋና ስፖርት በታዳጊና በወጣቶች ያላትን እምቅ አቅም ለመረዳት እንደሚያስችል የጠቆሙት ወይዘሮ መሰረት፣ በስፖርቱ ወደ ፊት ኦሊምፒክን በመሳሰሉ ታላላቅ መድረኮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተተኪዎችን ለማፍራት መሰል ቻምፒዮናዎች ትልቅ ጥቅም እንዳላቸው አብራርተዋል። ፌዴሬሽኑም በእድሜ ረገድ ዘወትር ለሚፈጠሩ ችግሮች ቀደም ብሎ ከክልሎችና ከክለቦች ጋር ተነጋግሮ መግባባት ላይ በመድረሱ ተወዳዳሪዎች በትክክለኛ እድሜያቸው ወደ ውድድር እንደመጡ ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑም ይህን መልካም ጅምር በማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት በታዳጊ ወጣቶች ላይ ጠንካራ ስራ እንደሚሰራ አክለዋል።
ቻምፒዮናው በሁለት ምድቦች ተከፍሎ ታዳጊ ወጣቶችን የሚያፎካክር ነው። አንደኛው ምድብ ከአስራ አራት አመት በታች የሚገኙ ታዳጊዎችን የሚያፎካክር ሲሆን ሌላኛው ምድብ ከአስራ ሰባት አመት በታች ያሉ ወጣቶች የሚወዳደሩበት ነው።
በዚህም መሰረት በቻምፒዮናው መክፈቻ እለት በበርካታ የውድድር አይነቶች የፍጻሜ ፍልሚያዎች ተስተናግደዋል። ከአስራ ሰባት አመት በታች ምድብ የመቶ ሜትር ነጻ ቀዘፋ በሁለቱም ጾታ፣የሃምሳ ሜትር የጀርባ ቀዘፋ በሁለቱም ጾታ፣ የሁለት መቶ ሜትር የጀርባ ቀዘፋ በሁለቱም ጾታ የፍጻሜ ፉክክር ተካሂዶባቸዋል። ከአስራ አራት አመት በታች በሚገኙ ታዳጊዎች መካከል ደግሞ የመቶ ሜትር ነጻ ቀዘፋ በሁለቱም ጾታ፣ የሃምሳ ሜትር የጀርባና የደረት ቀዘፋ በሁለቱም ጾታ ፍጻሜ ያስተናገዱ ፉክክሮች ናቸው።
ውድድሩ ዛሬም በቢሾፍቱ መኮንኖች ክበብ ቀጥሎ ሲውል በርካታ የፉክክር አይነቶች ፍጻሜ እንደሚያገኙ የሚጠበቅ ሲሆን ቻምፒዮናው የፊታችን ጳጉሜን 2/2014 ይጠናቀቃል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ በቻን ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታውን ዛሬ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል። በቻን ማጣሪያ የመጨረሻው ምእራፍ ላይ የሚገኙት ዋልያዎቹ፣ ያለፉትን ቀናት ቆይታ ያደረጉበትን ታንዛንያን በመልቀቅ ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ አድርገው ወደ ሩዋንዳ ተጉዘዋል።
ኪጋሊ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ ሳደርሱም በስፍራው በሩዋንዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ተወካዮች በመገኘት ለዋልያዎቹ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን፤ በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ከጎናቸው መሆናቸውን እንደገለጹም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።
ዋልያዎቹ ኪጋሊ ከደረሱ በኋላ ጨዋታ ወደ ሚያደርግበት ሁዬ ከተማ የ130 ኪ.ሜ የመኪና ጉዞ በማድረግ 12:00 ሰአት ገደማ ከተማው ደርሰው ማረፊያቸውን ክሬዶ ሆቴል አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት የመጨረሻ ልምምዱን በሁዬ ስታዲየም አከናውኖ ዛሬ ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ 1ለ1 ማጠናቀቁ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከ31 አመታት በኋላ እኤአ 2013 ላይ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ተከትሎ በእግር ኳሱ ከፍተኛ መነቃቃት እንደነበር ይታወሳል። የዚያ ትውልድ ታሪካዊ ተጫዋቾችና የዋልያዎቹ አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ከአፍሪካ ዋንጫው ማግስት በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የቻን ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሳተፉ የመጨረሻውን የማጣሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር ከሜዳቸው ውጪ ተፋልመው ማለፋቸው አይዘነጋም።
ከዘጠኝ አመታት በኋላ ዋልያዎቹ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመሩ በቀጣይ አመት በአልጄሪያ አዘጋጅነት በሚካሄደው የቻን ዋንጫ ለሶስተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ዛሬ ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር የመጨረሻውን የዘጠና ደቂቃ ፍልሚያ ከሜዳቸው ውጪ ያደርጋሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014