ከእናቴ ጋር ነው የምተኛው..የምነቃውም አብሬዐት ነው:: እሷ ጓዳ ጎድጓዳውን ስትንጎዳጎድ ቀሚሷን ይዤ በሄደችበት ሁሉ እከተላታለው:: በልጅነቴ የእናቴ ጭራ ነበርኩ:: ከጎኗ፣ ከስሯ፣ ከጉያዋ፣ ከቀሚሷ ስር ማንም ፈልጎ የማያጣኝ:: ስንተኛ እጇን አናቴ ላይ ጥላ ሳትዳብሰኝና ሳታሻሸኝ ቀርታ አታውቅም:: ጭንቅላቴን ሙሉ በእጇ እየዞረች በጎረበጣት ቦታ ላይ ቅማል ያገኘች እየመሰላት በሌባ ጣቷ አናቴን እየቆፈረች በአውራ ጣቷ እገዛ የጎረበጣትን ነገር ከአናቴ ውስጥ መዛ ታወጣለች:: አንዳንዴ ቅማል ይቀናታል አንዳንዴ ደግሞ ፎረፎር እጣፈንታዋ ይሆናል:: እናቴ በጎረበጣት ቁጥር ቅማል ያገኘች እየመሰላት ብዙ ቀን የደረቀ የአናቴን ፎረፎርና እንዴት እንደገባ ያላስተዋልኩትን ብናኝ እድፍ ተጋፍጣ ታውቃለች::
ዳብሳኝ ዳብሳኝ ሁለት ነገሮች ከአፏ አይቀሩም..አንድ..‹እንዳው ከየት አመጣህው ይሄን ከርዳዳ ጸጉር? ድሮ እንዴት ያለ ሉጫ መሰለህ? ስትል ትጠይቀኛለች:: ይሄን ወሬዋን ለዘመናት ሰምቼዋለው:: እናቴ ጸጉሬን በዳበሰችኝ ቁጥር፣ አናቴ ላይ ቅማል ፈልጋ ባጣች ማግስት ከንፈሯ ላይ የሚጸነስ ወሬ ነው:: አልመልሰላትም..እሷም አታብራራልኝም:: ‹እንዳው ከየት አመጣህው ይሄን ከርዳዳ ጸጉር? ድሮ እንዴት ያለ ሉጫ መሰለህ› ብላኝ ዝም:: ለምን እንደምትጠይቀኝ አላውቅም..ግን ትጠይቀኛለች..እጇ አናቴ ላይ ሲያርፍ፣ እንደ ሽቦ የጠነከረ ጸጉሬ መዳፏን ሲፈትነው አፏ ነፍስ ይዘራል::
ሁለተኛው ከእናቴ አፍ ላይ የማይጠፋው ቃል ‹ጸጉርህ አድጓል..ያከሳህ እሱ ነው› የሚለው ቃል ነው:: ጸጉሬን እየዳበሰችኝ ሰንብታ፣ ቅማል ፍለጋ ባዝና ባዝና አልሆን ባላት ሰሞን ‹ጸጉርህ አድጓል..ያከሳህ እሱ ነው› ትለኛለች:: እንዲህ ሳትለኝ ቀርታ አታውቅም:: መክሳቴን የማውቀው ያኔ ነው:: አንድም ቀን ክሳቴን በመስተዋት አይቼው ወይም ደግሞ ከሌላ ሰው ሰምቼው አላውቅም:: እንዲህ ባለችኝ በነጋታው ራሴን እናቴ ጉያ ስር አጎንብሼ አገኘዋለው:: በግራ መዳፏ ወደ መሬት ደፍቃኝ ምላጭ በያዘ ቀኝ እጇ አናቴን እየላጨች:: ለግማሽ ሰዐት ያክል በእናቴ መዳፎች ተጽዕኖ ደርሶብኝ እግሯ ስር ተደፍጥጨ ራሴን አገኘዋለው:: ጫናዋ ሲበረታብኝ ራሴን ለማዝናናት በተደፈቁበት ላመል እላወሳለው::
‹ምን ያቁነጠንጥሀል? ይልቅ እንዳልቆርጥህ አርፈህ ተቀመጥ› ትለኛለች:: በሚያስፈራራና በሚያስጠነቅቅ ድምጽ::
አርፌ መቀመጥ ሳልችል አርፌ ለመቀመጥ እሞክራለው:: ግን አይሆንልኝም የእናቴ ድፍጠጣ ሲበረታብኝ ወዲያው ራሴን ካዘነበለበት ቀና ለማድረግ እሞክራለው::
‹አትሰማም እንዴ! እንዳታስቆርጠኝ አትንቀሳቀስ አልኩህ እኮ!› ስትል ትቆጣኛለች:: በልጅነቱ መላጨት ስቃይ የሆነበት የመጀመሪያው ሰው እኔ ሳልሆን አልቀርም እላለው:: መላጣነቴ ምኑ እንደሚያስደስታት አላውቅም ገና ጸጉሬ ባቆጠቆጠ በሰልስቱ ነበር እናቴ ጸጉሬን መላጨት እንዳለብኝ የምታረዳኝ:: ደሞ ውጣ ውረዱ..ዝም ብላ ጉያዋ አድርጋ የምትላጨኝ መሰላችሁ? አይደለም:: መጀመሪያ አረፋ ባለው ሳሙና ጸጉሬን ታጥበኛለች:: አጥባ አትተወኝም..ድጋሚ ሳሙና ትመታኝና ሳሙናውን ጸጉሬ ላይ እንዳለ ወደ ጉያዋ ታስጠጋኛለች:: የሳሙናው መኖር ለምን እንዳስፈለገ ቆይቼ ነው የገባኝ:: አንድ ቀን ሳሙናው እያለ አልላጭም ብዬ ሳምጽባት ሳሙናው እኮ ጥሩ ነው..እንዳትቆረጥ፣ ጥሩ ሆኖ እንድትላጭ ያደርግሀል አለችኝ:: ያኔ ነበር ብልሀቷ የተገለጠልኝ:: ተላጭቶ ለሚወድቅ ጸጉር ያ ሁሉ እንክብካቤና ሽር ጉድ ይገርመኝ ነበር::
አረፋው አይኔ ውስጥ እየተማገደ ስቃይ ፈጠረብኝ:: ለነገሩ ለምጄዋለው..ስላጭ ከነአረፋዬ ስለሆነ አይኖቼ በሳሙናው መለብለባቸው ግድ ነበር:: የሳሙናውን ቁጥቋጤ ሰበብ አድርጌ እናቴ ላይ እንደፈለኩ አርጎመጉማለው..እቁነጠነጣለው..ለማልቀስ ይቃጣኛል::
በዚህ መሀል ‹ጨርሻለው..ትንሽ ብቻ ነው የቀረኝ› የሚል የእናቴን ድምጽ እሰማዋለው::
በቃሏ ላይ ተስፋን ጥዬ እረጋጋለው:: ወዲያው በሳሙናው፣ በድፈቃው ባጎነበስኩበት እንደ ስንኩል ወዲያ ወዲህ እንፏቀቃለው..
‹አይዞህ..ጨርሻለው በቃ! ስትል ልታባብለኝ ትሞክራለች::
ለለቅሶ የቀረበ ሲቃ የሚመስል ድምጽ እያወጣሁ ባጎነበስኩበት ዝም እላለው..
‹ቁንጮ ላድርግልህ ወይስ ጋሜ? ስትል ትጠይቀኛለች::
አኩርፌ ዝም እላለው..
‹አትናገርም እንዴ?
ማኩረፌን የሚነግራት ዝምታዬ ነው:: ዝምታዬ የእናቴን ልብ የሚያራራልኝ ሞገሴ ነው:: እናቴ ስትላጨኝ ሳላኮርፍ ቀርቼ አላውቅም:: እያኮረፍኩም ቢሆን ላጭታ ትጨርሰኛለች:: ቁንጮም ጋሜም ሳታደርገኝ ራሴን ርቃኑን ታስቀረዋለች:: አንዳንዴ በእኔ ይሁንታ ቁንጮ አድርጋልኝ ታውቃለች:: ጋሜ ምን እንደሆነ አላውቅም:: ግን በላጨችኝ ቁጥር ‹ቁንጮ ላድርግልህ ጋሜ? ብላ ትጠይቀኛለች:: የቱን መምረጥ እንዳለብኝ ለአፍታ ዝም እላለው:: የማላውቀውን ጋሜ መርጨ እዝራ እንዳያበሽቀኝ ስል ብቻ ቁንጮ አድርጊልኝ እላታለው::
ከተላጨሁ በኋላ የእናቴ ተቀዳሚ ስራ ጸጉሮቼን ከሜዳ ላይ መሰብሰብ ነው:: ‹ጸጉርና ጥፍር የትም አይጣልም› ብላ ጸጉሮቼን ሰብስባ አንድ ጥግ ላይ ትወሽቃቸዋለች:: ቀጥላ ወደ ጓዳ ነው የምትገባው..እሳት በገል ጭራ ተመጣና ከለቃቀመችው ጸጉሬ ጥቂት ታስቀርና እሳቱ ላይ ትጨምራቸዋለች:: ከዛም ‹ምቺ እንዳይመታህ ታጠን› ስትል አንገቴን ይዛ ወደ ጭሱ ትደፍቀኛለች::
ከተላጨሁ በኋላም ከመከራ አላርፍም:: እናቴ እጇን አናቴ መሀል እያርመሰመሰች ‹ጸጉርህ አድጓል..ያከሳህ እሱ ነው ካለችኝ ሰዐት ጀምሮ ባለመከራ ነኝ:: በመዳፏ ተደፍቄ፣ በአረፋ እየተለበለብኩ ተላጭቼ እንደጨረስኩ ከሁሉም የሚከፋ መከራ ይጠብቀኛል:: ወደ ቤት ታስገባኝና ከቅባት እቃው ውስጥ መጠነኛ ቅባት በሌባ ጣቷ ዝቃ መዳፏ ላይ እያሳረፈች በሁለት እጆቿ ታርመጠምጠዋለች:: ከዛ መላጣ ራሴን ትቀባዋለች:: አቤት ያኔ የምሆነው መሆን..ገና ቅባት ልትቀባኝ እንደሆነ ሳስብ ነበር ልቤ የሚርደው:: እናቴ ሳትቆርጠኝ ላጭታኝ አታውቅም:: ቅባቱን መላጣዬ ላይ ስትለቀልቀው በጣም ያቃጥለኛል:: ያኔ ነፍሴ ከልቤ ውስጥ መሹለክ ያቃጣታል:: ያኔ ምን ያክል እንደገበጠችኝ አውቃለው::
ከመላጣነቴ በኋላ እናቴ ጸጉር ያለኝ እየመሰላት እጇን ወደ አናቴ ስትሰድ ከመላጣ አናቴ ጋር ትገናኛለች:: በእናቴ መሳሳት በውስጤ እስቃለው:: እሷም ጣቶቿን ለመላጣ ራሴ ሳትነፍግ ወዲያ ወዲህ ታርመሰመሳቸዋለች::
ከእናቴ ጋር ያለኝ ቁርኝት ሞቼም የሚከተለኝ ይመስለኛል:: በወዲያኛውም አለም ከእናቴ ነፍስ ጋር ዳግም የምጫወት ይመስለኛል:: የትም ይሁን መቼም እናቴ አጠገቤ ካለች እጇ ጭንቅላቴ ላይ ነው:: ሲዳብሰኝ..ሲያሻሸኝ የማገኘው ደስታ ዛሬም ውስጤ ይላወሳል:: ነፍሴ በዚህ ሁሉ የዘመን እንደናቴ መዳፍ ደስታ ጎብኟት አያውቅም:: ከነፍሷ ያጋራችኝ ዛሬም ድረስ የሚከተለኝ ስውር ዳና አለ::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27 /2014