በችግራችን ወቅት ስለሚደርስልን ብቻ ሳይሆን፤ ሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነው ስለተባለም ሳይሆን፤ የራሳችን አገር በቀል እውቀታችን ውጤት ስለሆነም ሳይሆን …፤ ሁላችንም፣ እዚህም እዛም (ዲያስፖራ) ያለነው እንደምናውቀው እቁብ ከእኛው፤ ለእኛው፤ የእኛው …. የሆነ ማህበራዊ ተቋም ነው።
ምናልባት «የአካባቢ ፀበል ልጥ መንከሪያ ነው» እንደሚባለው ሆኖ እንደሆነም እንጃ ብዙውን ጊዜ ዕቁብ ሲባል እንደ ቀላል፤ እንደ ዋዛ የምንመለከት ቁጥራችን ብዙ ነው። ይህ ጸሐፊ እስከሚያውቀው ድረስ ለማህበራዊ ተቋማቶቻችን ልዩ ትኩረትን ሰጥተው የሠሩ አንድ ሰው ቢኖሩ ደራሲ፣ ተርጓሚና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ናቸው።
ማሞ ውድነህ እነዚህን አገር በቀል እውቀት አፈራሽ (ወይም አገርኛ) የሆኑ ተቋማትን ራሳቸውን አስችለው፤ በርእሰ ጉዳይነት አንስተው ለወግ ለማዕረግ አብቅተዋቸዋል። «እድርተኞቹ»፤ «ዕቁብተኞቹ»፤ «ማህበርተኞቹ» ሲሉም ተጠብበውባቸዋል። በእነዚሁ ሥራዎቻቸው አማካኝነትም የእነዚህኑ ተቋማት አስፈላጊነ ታቸውን፤አላማቸውን፤አተገባበርና ተግባሪያቸውን በዘመናዊ አስተሳሰብ የተረኳቸው ሲሆን፤ በተገቢው መንገድ አሽተውና ገርተው በእሴትነታቸው ይቆዩ ዘንድ አሳስበዋል። (እነዚህን «ልቦለድ» ሥራዎች፣ በተለይ ቀደም ያለው ትውልድ አሳምሮ ያውቃቸዋል ብለን በማሰብ ማሞን እያመሰገንን ማለፍን መርጠናል።) ወደ ባህር ማዶ እንዝለቅ።
ዕቁብ ሲያትል በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድም ተጉዞ ከላይ ያልንለትን፣ «ሰውን ሰው ያደረገው …» ብለን ያፀደቅንለትን ሥራ እየሠራ ይገኛል። ለጊዜው ሲያትልን እንጥቀስ እንጂ በሌሎቹ ዘንድ የለም እያልን አይደለም። «አበሻ ባለበት ሁሉ …» እስኪባል ድረስ ሁሉም አለ።
በሲያትል እቁብተኞች ድረ-ገፅ ላይ ሰፍሮ እንደሚነበበው ዕቁብ የእንግሊዝኛ አቻው ወይም በፈረንጆቹ እይታ ”Rotating Savings and Credit Association (ROSCA)” የሚል ብያኔ ተሰጥቶታል። ትክክል ነው። ምክንያቱ ደግሞ ዕቁብ ዙር መሆኑ፤ በዙር (እጣ) የሚደርስ መሆኑ፤ ሌላው የቁጠባ ዓይነት መሆኑና እንደየዕቁቡ ባህርይ (እንደየ ቤቱ) ብድር ወይም ቅድሚያ የሚሰጥበት ሁኔታ የመኖሩ ጉዳይ ነው።
ወደ ኢ-መደበኛ ፋይናንሳዊ ተቋምነቱ ዝርዝር ጉዳይ ከመሄዳችን በፊት የእቁብን ሌላ ገፅታ አስመልክተን አንድ ነገር እንበል።
ዕቁብ፣ ልክ እንደ እድር እና ማህበር ሁሉ ከዋና አላማው ባሻገር ሌሎች ተጓዳኝ አላማና ፋይዳዎችም አሉት። እነዚህ ፋይዳዎች በአንድ ማህበረሰበ ውስጥ ሊኖሩና ያ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ ይቀጥል ዘንድ እጅግ አስፈላጊ ከመሆናቸው አኳያ ዕቁብም ሆነ ማህበር እና እድር የሚጫወቱት ሚና በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም።
መቸም «እከሌ እኮ ዕቁብተኛዬ ነው፤ እከሌ እኮ ማህበርተኛዬ ነው፤ እከሌስ? እሱማ እድርተኛዬ ነው እኮ፤ አታውቅ(ቂ)ም እንዴ? …» የመሳሰሉ አገላለፆችን የማናውቅ የለንም። እነዚህ አገላለፆች ደግሞ በማህፀናቸው ውስጥ የያዙት ማህበራዊ እሴት እንዲህ በቀላሉ ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም። መተማመን አለ፤ አንዱ ላንዱ ዋስ መኳኳን አለ፤ በመገናኘት ወቅት ሃሳብ ለሃሳብ መለዋወጥ አለ፤ ስለ ሥራ፤ ስለ አገር፣ ፖለቲካ፣ መንግሥትን ማማት (ያለ ምንም መፈራራትና ፍፁም መተማመን) …. ሁሉ አለ። ስለ ቤተሰብ፣ ትዳር፣ ልጆች …. ስለ ራስ፣ ጎረቤት፣ ጓደኛ … ጤንነት ሁሉ መነጋገር አለ፤ አሳልፎ መሰጣጣት ሁሉ የለም። ይህ ደግሞ በመንግሥት የውይይት (ስብሰባም እንበለው) ደረጃ እንኳን የማይገኝ እሴት (ዲሞክራሲ) ነውና እድርም ሆነ፣ ማህበርና ዕቁብ ያላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበረ-ባህላዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በመሆኑም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ወደ ተነሳንበት፤ ወደ ዕቁብ ኢ-መደበኛ ተቋምነት እንሂድ።
እቁብ ኢ-መደበኛ (በመንግሥታዊ አወቃቀርና መዋቅር ያልተደገፈ) ማህበራዊ የቢስነስ ተቋም ነው ብለናል:: ብዙዎች ዕድሜ ጠገብ ነው ቢሉትም፤ ከገንዘብ ሥሪት ጋር የተጣመረ በመሆኑ እንደ ዕድር ተቋማቶቻችን አንጋፋ አይመስልም::
በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሰፋ አድርገው የሄዱት የቺካጐ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ዕቁብ በ1930ዎቹ በጉራጌ ሕዝብ አማካኝነት እንደተጀመረ ጽፈዋል:: የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቢስዝነስና ምጣኔ ሀብት መምህር አዲሱ ካራፎ «በኮንሶ ጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ማዕከላትን በመደገፍ ዕቁብ ያለው ሚና» (2017) በሚል ርእስ ባካሄዱት ጥናት፤ ዕቁብን አፍሪካ በቀል የፋይናንስ ተቋም መሆኑን ያስረዳሉ:: ዕቁብ በጋና ሱሱ፣ በናይጄሪያ ኢሱሱ፣ በማላዊ ቺፐረጋኒ፣ በታንዛኒያ ምቸዞ፣ እና በፈረንሳይኛ ተናጋሪ አፍሪካ አገሮች ደግሞ ቶንቲነርስ በመባል እንደሚታወቅም ያብራራሉ።
የደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት ቃሉን ሲፈታው ዕቁብ የተጠበቀ፤ ጥብቅ፤ የመዋጮ ገንዘብ ባንድ ሰው እጅ ተጠብቆ በዕጣ ለዕቁብተኛው የሚታደል ይለዋል:: ቁብ የሚለው ቃልም ዐቀበ፤ዕቁብ ከሚለው ቃል ጋር ይመሳሰላል፤ ቁብ ፍቺው ዐሰበ፤ ግድ ይለዋል:: ቁብ የለሽ ሲልም ሀሳብ የለሽ፤ ግድ የለሽ ማለት መሆኑን ያስረዳል:: በግእዝ ዕቁብ የተጠበቀ፣ የተጠነቀቀ፣ ጥብቅ፣ ጥንቁቅ፣ የተቀመጠ፣ ያለ ማለት ነው:: በግእዝ ዕቀቡ ሕግየ ሲል ሕጌን ጠብቁ ማለት ነው:: (ዘሌ 19፡20) በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም አቁብ፤ ዕቁብ፣ አቃቢ፣ ጠበቀ፣ ከለከለ እንደማለት ነው በሚል ይፈታዋል:: መቆጠብ የሚለውም ቃልም ሲጠብቅ ገንዘብን ከማባከን መራቅ መጠንቀቅ ማለት ሲሆን፤ ሲላላ እየቀነሱ ማስቀመጥ ማለት መሆኑ ተፅፏል::
ፕሮፌሰር አየለ በከሬ የአፍሪካ አያዎ (Paradox) የሆነው ድህነት በአፍሪካ በቀል ዕውቀት፣ ባህላዊ ኩነቶችና በቀበሌያዊ ተቋማት ሚና እንደሚፈታ ይገልፃሉ:: ዕቁብ በጥቂት ሰዎች፣ በተዘዋዋሪ ብር አኗኗራቸውንና ሕይወታቸውን ለማሻሻል እንደሚቋቋም ጽፈዋል:: ይህም እንደ አባላቱ ፍላጎት በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት ነው፤ እንደ ዕድር ግን ዘለቄታዊ ዕድሜ የለውም ይላሉ::
ዕቁብ ብዙውን ጊዜ የሚሰበሰበው በአንድ አካባቢ በሚኖሩ፣ በሚሠሩ በሚተዋወቁ እና በሚተማመኑ፤ እንዲሁም በብዛት ተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ ባላቸው ሰዎች ነው:: የዘመናችን ዲጂታል ዕቁብ ግን በየትኛውም ቦታ ያሉ ሰዎች ገንዘብ እንዲጥሉ እያደረገ ነው። (100ሺህ ሰዎች ዕቁብ የሚጥሉበት «በ30 ወራት የሚያልቅ» የሚል መረጃ አይቻለሁ።) በኪስ ስልክና በመረጃ መረብ የሚታገዝ፤ የዲጂታል ዕቁብ አስተማማኝነቱስ? የሚለውን ግን ከስልጣኔ፣ ዝማኔና እምነት ጋር የሚያያዝ ስለሆነ እዚህ አስፍተን የምናየው ሳይሆን ጊዜ የሚመልሰው ይሆናል (በተለይ የእኛን በመሳሰሉ አገራት)።
ሰዎች የገንዘብ እጥረት በሚያጋጥማቸው ጊዜ ዕቁብን እንደ አንድ መውጫ መንገድ ይጠቀሙበታል:: የዕቁብ ተጠቃሚዎች፣ ሌኒን እንዳይሰማቸው እንጂ፣ ‹‹ሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነው›› ሲሉ ይሰማል:: በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ እና በአረብ ሀገራት፤ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጭምር ዕቁብ እየሰበሰቡ ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን እንደሚፈቱ እራሳቸው ሲናገሩ ይሰማሉ:: በደርግ ውድቀት ከሀገር የወጡት ፈላሻዎችም በእሥራኤል ዕቁብን እንደችግር መፍቻ አማራጭ ይጠቀሙበታል:: ጌታቸው መኳንንት የኢመደበኛ ተቋማት (ዕቁብ፣ ዕድርና ማኅበራት) ሚና የስደተኛ ዜጎችን ሕይወት በማስተካከል፤ በሚል ባቀረቡት ጥናት በካናዳ ቶሮንቶ ኢትዮጵያውያን ዕቁብ እየሰበሰቡ ችግሮቻቸውን ይቀርፋሉ፤ መኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪ …. የመሳሰሉትን በመግዛት፤ የተሻሉ ሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ራሳቸውን ያጠናክራሉ ይላሉ::
በጋራ ዕቃ ለመግዛት የሚጠቀሙበትም አሉ:: መጽሐፍ የሚገዙ (የመጽሐፍ ዕቁብ)፤ ቴሌቪዥን፣ ማቀዝቀዣ ወይም ሶፋ ከአንድ ንግድ ቦታ ለመግዛት ዕቁብ የሚጥሉ አሉ:: ሰብሳቢው አስቀድመው ዕቃውን ከሚገዙት ድርጅት ተስማምተው ዕጣ ለወጣለት እየሄደ ከንግድ ቦታው ዕቃውን እንዲወስድ ያደርጋሉ:: ገንዘቡን ቢፈልግ አይሰጠውም:: የተስማማው ዕቃውን ለመግዛት ስለሆነ ማለት ነው:: ሰብሳቢው በቀዳሚው ዕጣ ዕቃውን ወይም ብሩን ሲወስድ፤ ከንግዱ ተቋሙ ደግሞ የተወሰነ ጥቅም እንደ ውለታ ይሰጠዋል::
የዕቁብን የአባላቱ ብዛት ገንዘቡ የሚሰበስብበት ቦታ እና ጊዜ፣ መጠን፣ በምን ያህል ጊዜ እንደሚወጣ የሚወሰነው በሰብሳቢው ነው:: አንዳንዴ ሰብሳቢውና ተሰብሳቢው ሊወስኑ ይችላሉ::
በብዙ ቦታዎች በዕቁብ አሰባሰብ፣ አሠራርና ውስጣዊ ደንብ መሠረት ዳኛውና ሰብሳቢው የመጀመሪያውን ዕጣ መውሰዳቸው የተለመደ ነው:: የመጀመሪያው የዳኛው፤ ሁለተኛውን ደግሞ የሰብሳቢው።
የዕቁብ አባላት፣ እቁብተኞች (በተለይ አንድ ቤተሰብ ከሆኑ) ገንዘቡን ለጋራ ዕድገት ይሠሩበታል:: አንዳንዴ ዳኛውም ሰብሳቢውም አንድ ሰው ይሆንና ቀዳሚውን ዕጣ በመውሰድ ለቀጣዮቹ በየጊዜው ዕጣ እያወጣ ወይም አንዴ ሁሉንም አውጥቶ በየጊዜው በተራ ይሰጣል:: ዕቁቡን በልቶ ቀጣዩን ለመጣል ደግሞ የሚያስቸግር የሚያስቀርም ካላ ጣጣው የዳኛው ይሆናል:: ቅድሚያ ይበላ ዘንድም ውስጠ ደንቡ ከሚፈቅድባቸው ምክንያቶች አንዱም ይሄው ነው።
እንደምናውቀው በኢትዮጵያ ብር ከብድር ተቋማት ማግኘቱ እንዲህ ቀላል አይደለም፤ ሲበዛ ውስብስብ ነው። ተገኘ ቢባል እንኳን ለተደቀነ ችግር አፋጣኝ መፍቻ አይሆንም፤ አይደርስም። ባንኮች ገንዘብ በመጠበቅና በማስቀመጥ ሁሉን ቢያስተናግዱም በማበደር ረገድ ድሃውን ዘንግተውታል:: ዜጋው ግን ዕቁብን በመሰብሰብ ችግሩን ይፈታል:: የሚፈልገውን ያሟላል:: ለኅብረተሰብ ቁልፍ ችግር መፍቻው አገር በቀል እውቀት ሆነ ማለት ነው፤ ሀገርኛ ማለትም ይሄው ነው።
በብዛት በልምድ የሚካሄደው ዕቁብ፤ ገንዘቡ ከፍ ያለ ከሆነ ተዘጋጅቶ በአባላቱ በፀደቀ መተዳደሪያ ደንብ ይመራል:: የዕቁብ መተዳደሪያ ሕግና ደንብ የሚተላለፉ ይቀጡበታል:: ዎልፍ ሌስላውና ቶማስ ኤል.ካኔ ባወጡት አንድ መጽሐፍ የነጋዴዎች፣ የመንደርተኞችን ጨምሮ የሠራተኞች፤ ማለትም የተቀጣሪዎችና የደመዝተኞች የተባሉ የዕቁብ ዓይነቶች እንዳሉ ይገልፃሉ::
የነጋዴዎች ዕቁብ በንግድ ቦታዎች በብዛት ዘወትር ከሰዓት በኋላ እየሰበሰቡ በተወሰኑ ቀናት የሚወጣበት ነው:: እንዲሁም በየዕለቱ ዕቁብ የሚሰበስቡ ግሮሰሪዎች ቡና ቤቶች አሉ፤ ይህም ከነጋዴዎች የሚሰበሰብና ዕጣ የሚወጣበት አሠራር ነው:: የደረሰው ዕጣ ቁጥሩ በአነስተኛ ጥቁር ሰሌዳ ላይ ተጽፎ መጠጥ ቤቶች ግድግዳ ላይ ሲሰቀል አሁንም ይታያል:: የሠፈር ዕቁብ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በሳምንት ገንዘብ ሰብስበው ዕጣ የሚያወጡበት ነው:: በተለይ በመንደር ዕቁብተኞች፤ ወይዛዝርት ከሆኑ ቡና አፍልተው የቡና ቁርስ ቀማምሰው ተጨዋውተው ዕጣውን አውጥተው ይለያያሉ::
ጎልማሶች ከሆኑም ዕቁባቸውን ሰብስበው ዕጣ አውጥተው፤ ቢራ፣ ለስላሳ ጠጥተው ሳምንት ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ:: ለዚህ ነው ሰዎች ሲናገሩ ከእነርሱ ጋር እኮ ዕቁብ እጠጣለሁ የሚሉት:: ዕጣ የሚደርሰውም የ«ፍንጥር» ብሎ አባላቱን የሚጋብዝ አለ። ይህም ተገዶ ሳይሆን ወዶ፣ በፍቅር የሚያደርገው ነው:: በእንደዚህ ዓይነት ዕቁብ ዕጣው ሲወጣ፣ ዕጣው የደረሰው ባለ ዕጣ ገንዘብ በአስቸኳይ እፈልጋለሁ፣ ቸግሮኛል የሚል አባል (ዕቁብተኛ) ካለ ዕጣውን በተወሰነ ገንዘብ ይሸጥለታል:: ዕጣውን ያሳለፈው ዕቁብተኛ ደግሞ የሸጠለትን ሰው ዕጣ ጠብቆ በደረሰው ጊዜ ይወስዳል:: በደሞዝተኞች (ቢሮዎች አካባቢ) ገንዘብ የቸገረው ካለ ዕጣውን ከሚወስደው ሰው ጋር በመነጋገርና በመመካከር ነው የሚያልቀው። ሁለቱ ብቻ የሚጨርሱት ይሆናል።
ሁሉም ደርሶት ሲጠናቀቅ አንዳንድ ዕቁቦች፤ በግ ወይም በሬ አርደው ጠጅ፣ ቢራ አወራርደው፤ ለቀጣይ ያገናኘን ብለው ያሰነባበታሉ:: ይህም ከፊሎቹ ከየዕቁብተኛው በትርፍ መዋጮ እየተሰበሰበ ሲጠናቀቅ የሚደረግ ነው:: ዳኛው በፈቃዱ የሚያደርገውም ግብዣ አለ:: (ይህ ሁሉ፣ እያንዳንዱ ተግባር እራሱን የቻለ ማህበራዊ እሴት መሆኑን ልብ ማለት ያሻል።)
ትልልቅ ዕቁብ ሲሆን ጠበቃ ያዘጋጃሉ:: ባለ ዕጣው ተያዥ ማምጣቱ ግድ ይሆናል:: ከአባላቱ ሁለት ሦስት ዋስ ማለት ነው:: ዕቁብ የበላው ቀጣይ ክፍያ ቢያቋርጥ ዋስ የሆነለት ሰውዬ ዕጣው ሲደርሰው ገንዘቡ ይያዝበታል::
በመንግሥት ሠራተኞች ያለው ዕቁብ አሰባበሰብ በየወራቱ ሆኖ ብዙ ጊዜ መንፈቅና ዓመት የሚቆይ ነው:: ሰብሳቢው የመጀመሪያውን ዕቁብ ወስዶ ገንዘቡን በተራው በየወሩ ይጥላል:: ከንግድ ቦታዎች የሚለየው ሰብሳቢው የመጀመሪያውን ዕጣ መውሰዱ ብቻ ነው:: ቀሪዎቹን ጊዜያት እሱም ከዕቁብ አባላቱ ዕኩል ገንዘብ በየወሩ ይጥላል:: ሰብሳቢው ዕቁብ ከሚጥሉት መካከል አንዱ ቢክደው (ብዙ ጊዜ አይከሰትም) ወይም ዕቁብ መጣሉን ቢያቆም አግባብቶ እንዲጥል ማድረግ አልያም ዕዳውን ሰብሳቢው መወጣት ይጠበቅበታል::
ሌላው የዕቁብ ፀጋ ዕቁብተኛ ለመሆን ፆታ፣ ጎሳና እምነት የሚጠይቅ አለመሆኑ ነው:: ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። የአባላቱ የኑሮ ደረጃ መመጣጠን ግን ግድ ነው፤ ዋናው የሚጣለውን የዕቁብ መዋጮ ይችለዋል ወይ? የሚለው ጉዳይ መሠረታዊ ነው ማለት ነው::
በአጠቃላይ፣ ወንዝ አፈራሽ የሆነው ዕቁብ ጥሪት ለመሰብሰብ፣ ችግርን ለመቅረፍ፣ እንዳስፈላጊነቱ ደረጃ በደረጃ የቤት ቁሳቁስ ለማሟላት፣ ሦስት ጉልቻ ለመመሥረት፤ ቤት ለመሥራት በነጋዴዎች ደግሞ የንግድ ደረጃቸውንና ዐቅማቸውን ለማሻሻል (ለአራት ዓመት ከ30 ነጋዴዎች ዕቁብ እሰበስብለት የነበረ ግለሰብ፤ ሁለት ተሽከርካሪዎች መግዛቱን ስመለከት ዕቁብ ፋይዳ ያለው መሆኑን በውል ተገንዝቤያለሁ) ወ.ዘ.ተ የሚረዳ ኢ-መደበኛ የገንዘብ ተቋም ነው:: ማኅበራዊ ሕይወትን ለመጋራት (ሳይቸግረው ዕቁብ የሚሰበስበውን ሰው ለማበረታታት) ለፍጆታ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ወዳጅ ዘመድን ለመርዳት፣ አስቸኳይ የገንዘብ ፍላጎትን ለማሟላት ይረዳል:: አንዳንዶችም ገንዘባቸውን ከብክነት ቆጥበው የተሻለ ነገር ያደርጉበት ዘንድ ያነሳሳቸዋል:: በመሆኑም፣ ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ ነውና «እቁብ ለዘላለም ይኑር!!!» እንላለን።
የነጋዴዎች ዕቁብ በንግድ ቦታዎች በብዛት ዘወትር ከሰዓት በኋላ እየሰበሰቡ በተወሰኑ ቀናት የሚወጣበት ነው:: እንዲሁም በየዕለቱ ዕቁብ የሚሰበስቡ ግሮሰሪዎች ቡና ቤቶች አሉ፤ ይህም ከነጋዴዎች የሚሰበሰብና ዕጣ የሚወጣበት አሠራር ነው
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27 /2014