ኢትዮጵያዊው ነፃነታቸውን ጠብቀው የኖሩ ኩሩ ህዝቦች ምድር ናት። ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ ትቆይ ዘንድ ምክንያት የሆኑት ደግሞ ከራሳቸው በላይ አገሬን ባሉ ጀግኖቿ ነው። ኢትዮጵያን አትንኩብኝ! አገሬን አትዳፈሩ! ብለው፤ ብዙዎች በዱር በገደሉ ተዋድቀዋል። በዚህም አገራቸውን በክብር አቆይተዋል።
በዛሬ ሳምንቱን በታሪክ አምዳችን ስለኢትዮጵያ ከተዋደቁ ጀግኖች መካከል አንዱን እናስታውስ።
አላስኬድም አለኝ ጣልያን በመንገዱ
ያ ሻቃ በቀለ ና ወንዱ ና ወንዱ !
ተብሎ የተቀኘላቸው ጀግናው የጦር ሜዳ ትንታግ ደጃዝማች በቀለ ወያ ናቸው። በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳዋ ጎጌቲ ሲብስቶ መንደር፤ ነሐሴ 21 ቀን 1902 ዓ.ም አንድ ዜና ተሰማ። ወይዘሮ ብርቄ ጂሎ የተባሉ ኩሩ ሴት አንድ ልጅ መውለዳቸው ተነገረ። አባት አቶ ወያ ኦብሴና የተወለደው ልጅ ወንድ መሆኑን ሰምተው ደስ ተሰኙ። በዚህ ቀን ኢትዮጵያ አንድ ጀግና ተፈጠረላት። ስለኢትዮጵያ አገሩ የሚዋደቅ፣ ስለ እናት ምድሩ ስምና ክብር ዘብ የሚሆን ትንታግ ተወለደ። አባት የልጃቸውን ስም በቀለ አሉት።
ይህ ህፃን እዚያው የትውልድ መንደሩ ጎጌቲ ሲብስቶ ላይ በእንክብካቤ የልጅነት ጊዜውን አሳለፈ። ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር አፈር ፈጭተው፣ ጭቃ አቡክተውና ቦርቀው ሰነበቱ። በቤተሰብ ፍቅር ተኮትኩተው በስስት አደጉ። የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ደጃዝማች በቀለ ወያ። የአማርኛ ፊደል መለየትና የቋንቋ ትምህርትን እቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው ተማሩ።
ደጃዝማች በቀለ ዕድሜያቸው 16 ሲሞላ እናታቸው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ወደሆኑት አጎታቸው ገ/ማርያም ዘንድ ላኳቸው። ከሰው ጋር ተግባቢ እና ታዛዥ የነበሩት በቀለ ከአጎታቸው ጋር አድገው ኋላ ላይ እልፍኝ አስከልካይ ሆኑ። አጎትየው ደጃዝማች ገብረማርያም ከ1923 እስከ 1926 ዓ.ም ድረስ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሆነው አግልግለዋል። በዚያን ወቅት በቀለ ወያ ሻቃ የሚል የማዕረግ ስም ተሰጣቸው።
ጉዳዮችን ቶሎ የመቀበል ችሎታና ቀልጣፋ የነበሩት ደጃዝማች በቀለ፤ አጎታቸው ጋር በነበሩበት ጊዜ በረዳት ወታደርነትና በአስተዳደር ሥራ ላይ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ቆዩ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ አንድ አዲስ ክስተት ተፈጠረ። ይህም ከሚኖሩበት ሀረርጌ ግዛት ወደ አዲስ አበባ የሚያመጣቸው ነበር። የደጃዝማች በቀለ አጎት ደጃዝማች ገ/ማርያም የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር ተብለው በ1927 ዓ.ም ተሾሙ።
ደጃዝማች በቀለ ከአጎታቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የታንክ መስበሪያ መሣሪያ አጠቃቀምን አጠኑ። ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ታላቅ ጠላት ገጠማት። በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረር መጀመሩ ተሰማ። ደጃዝማች በቀለም መጀመሪያ ወደ ሰሜን፣ ቀጥሎ ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ ወደ ሲዳሞ በመሄድ በአጎታቸው ሥር ያለውን ጦር በመምራት ከጠላት ጋር ተፋልመዋል። በዚህም ከፍተኛ ጀብዱ መፈፀማቸው የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ።
የደጃዝማች በቀለ ወያ ገድል በተመለከተ፤ ደራሲ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ቀሪን ገረመው በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ያወሱታል
“የጠላት ታንክ ወገንን በማጥቃቱ ደጃዝማች ገ/ ማርያም ጋሪ በጣም ያዝኑ ነበር። አንድ ቀን አምስት ታንኮች በመደዳ ሆነው ጦሩን እያጠቁ ሲመጡ “በቀለ፤ ያንተ ብልኀት ለመቼ ሊሆነን ነው ! አትለውም ወይ ! ወይኔ !” እያሉ ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ ሲያዝኑ በቀለ ዝም ብሎ ይመለከት ነበር። ታንኮቹ ጠጋ ብለው በደንብ ሲታዩት በመድፍ የመጀመሪያውን አኮማተረው፤ ደግሞም የኋለኛውን ደገመው። እንደዚሁ በ5 ደቂቃ አምስቱንም ታንክ አቃጥሎ ሲነድዱ፤ “ደጃዝማች ! ሄደው እሳት ይሙቁ” አላቸው።”
በወቅቱ ግንቦት 9 እና 11 ቀን 1928 ዓ.ም በሲዳሞ የጦር ግንባር የደጃዝማች ገ/ማርያምን ጦር ለመውጋት የመጣውን ወራሪ ሀይል ተፋልመዋል። ደጃዝማች በቀለ የአጎታቸው ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ ጦር የመድፍ ክፍል ኃላፊ ሆነው ተዋግተዋል። የጠላትን ጦር መሣሪያ ማከማቻንም አውድመዋል።
በዚያ የጦር ሜዳ ውሎ ላይ በእህታቸው ልጅ ጀግንነት አጎታቸው ገ/ማርያም እጅጉን ተደሰቱ። ከባልደረቦቻቸው ምስጋና አቀረቡላቸው። በጦርነቱ ስምንት ባለ ውሃ ከባድ መትረየስ፣ 14 ቀላል ድግን አልቤን መትረየስ ሲማረኩ 30 የጣሊያን የጦር መኰንኖችና በርካታ ወታደሮች ተገለዋል።
የደጃዝማች በቀለ የጦር ሜዳ ጀግንነት በዚህ አላበቃም። ከሰኔ 1 ቀን 1928 ዓ.ም እስከ መስከረም 23 ቀን 1929 ዓ.ም የበዙ ጦርነቶች የተካሄዱባቸው ጊዜያት ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከባድ የነበረው የደባ ስሬ ጦርነት ነበር። ደጃዝማች በቀለ ደግሞ ከ12 በላይ ታንኮችን በመድፋቸው በማውደም የማይረሳ ታሪክ በዚያ ጦርነት ሰርተዋል። በውጊያው ጦሩን ይመሩት የነበሩት የበቀለ አጎት ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ ቆሰሉ።
ጀግናው የጦር ሜዳው ነበልባል ደጃዝማች በቀለ በኅዳር ወር ከ13 እስከ 19 ቀን 1929 ዓ.ም ድረስ በአለታ ወንዶ አካባቢ ተፈሪ ኬላ፣ ጥር 12 1929 ዓ.ም ደግሞ አርቤጎና፣ ጥር 15 ቀን 1929 ዓ.ም በደኤላ ጭሪ፣ ጥር 19 ቀን 1929 ዓ.ም በሂበኖ አሩሲ፣ የካቲት 5፣ 10 ና 11 ቀን 1929 ዓ.ም በላቂ ደንበል የፈጸሙት ገድል ታሪክ የማይረሳው ለአገር የተከፈለ ትልቅ ዋጋ ነበር።
የካቲት ወር ለደጃዝማች በቀለ ወይ ጥሩ አልነበረም። ከጎናቸው ሆነው ለአመታት ለወግ ማዕረግ ያበቋቸውና በጦር ሜዳ ውሎ አጋርና አዛዣቸው የነበሩት አጎታቸው ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ አረፉ። በየካቲት 13 ቀን 1929 ዓ.ም ጎጌቲ በተባለ ቦታ በነበረው ከባድ ጦርነት ነው ደጃዝማች ገ/ማርያም የተሰውት።
ያኔ ምክትል የነበሩት ደጃዝማች በቀለ ሙሉውን ጦር መምራቱን ተረከቡ። ደጃዝማች በቀለ ከአክስታቸው ልጅ ከነበሩት በዳኔ ጉደታና ከሌሎች አርበኞች በመመካከር ወታደራዊ ትጥቃቸውን አጥብቀው በትውልድ ሀገራቸው ሶዶ ጠላትን ተፋልመዋል። ጦራቸውን በማደርጀት በየካቲት ወር 1930 ዓ.ም በሶዶና ሜጫ አውራጃ ወሰን ላይ ሁለት ባታልዮን የጠላት ጦር ገጥመው አኩሪ ገድል ፈፅመዋል።
ጀግናውና የጦር ሜዳው ትንታግ በቀለ በአገምጃ ያካሄዱት ጦርነት ላይም የፈፀሙት ጀግንነት የማይረሳ ነበር። ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ድረስ ለ10 ሰዓታት ድረስ ዘመናዊ ትጥቅ ታጥቆ በምድር በመድፍና በሰማይ በአይሮፕላን የመጣውን ጠላት በጀግነት ገጥመዋል።
በዚያ ጦርነት የበዙ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተሰው። ነገር ግን የጦር መሪው ጀግናው ደጃዝማች በቀለ ነበሩና ድሉ የኢትዮጵያዊያን ሆነ። ይህን ጀግንነታቸውን የሰማ የሶዶ ሕዝብ በጅምላ ይጎርፍ ጀመር። በሶዶ ቶሌና በረጲ ጦርነትም የደጃዝማች በቀለ ጦር የጠላትን ጦር ድል ማድረግ ልማዱ ሆነ። በዚህም ጣልያን አፈግፍጎ ለቀጣይ ለ6 ወራት ከአካባቢው ርቆ ቆየ።
የዚህ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጀግና የጦር ሜዳ ገድል ይህ ብቻ አይደለም። በሶዶ አጨበር፥ ቁሻትና ኢቲኒ ለ8 ሰዓት ያህል በተደረገው ፍልሚያ ደጃዝማች በቀለ ድል ማድረግ ቻሉ። በሶዶ ጫከ ደራራ፣ አገምጃ፣ በሶዶና በወለኔ ወሰን ላይ የሲ፣ ኦሞ፣ ጎደብ በተባሉ ቦታዎች አንጸባራቂ ድል ተጎናጽፈዋል። በወርሃ መስከረም 10 ቀን 1932 ዓ.ም ሶዶ ባንቱ በተባለ ቦታ ለ7 ሰዓታት ያህል ተዋግተው ድል አደረጉ።
ደጃዝማች በቀለ ከሌሎች አርበኞች ጋር ኅብረት በመፍጠር ጠላትን በጋራ ተዋግተዋል። በተለይም ከዘመዳቸው ገረሱ ዱኪ ጋር ተባብረው ጠላትን የመደምሰስ ዕቅድ በማውጣት ብዙ መክረዋል። በጋራም የጠላትን ጦር ይደመስሱ ነበር። ከገረሱ ዱኪ ጋር በበዳና አቄሮና ሶዶ ከፍተኛ ጦርነቶች ተዋግተዋል። በውጊያውም ከፍተኛ ጀብዱ ፈፅመዋል።
ለዚህ ጦርነት ምክንያቱ ሙሴ ቀስተኛ የተባለ የጣልያን መልእክተኛ ገረሱን ለማጥመድ የተላከ መሆኑ በገረሱ ተደርሶበት የሞት ውሳኔ ተፈረደበት። ሄን የሰማው የጣሊያን ጦር የሙሴ ቀስተኛን ደም ለመበቀል ሀይሉን አሰባሰበ። ከጅማ፣ ከሲዳሞ፣ ከሐረር፣ ከአርሲና ከሸዋ ጦር ሰበሰበ። በዚህም የገረሱን ጦር በመውጋት ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ። ብዙ ኢትዮጵያን ተሰው።
በውጊያው ጦራቸው የተጎዳባቸው ገረሱ ሸሽተው ከደጃዝማች በቀለ ጋር በመገናኘት ለሦስት ቀንና ሌሊት 44 ባታልዮን ይገመት ከነበረ ጦር ጋር በጣም ዘግናኝ የሆነ ጦርነት አካሄዱ። ጣሊያኖች በዘመናዊ የጦር መሳሪያና በአይሮፕላን ተደግፈው ይዋጉ ስለነበር ከኢትዮጵያ ወገን ሠራዊት አለቀ። ደጃዝማች በቀለ ቀኝ እጃቸው ቆሰለ። በዚህም ምክንያት መድፍ እንደልብ ባለመተኮሳቸው ጦርነቱ ተገታ። በዚህ ምክንያት ጦሩ ተበተነ።
ደጃዝማች በቀለም እስኪያገግሙ ድረስ ሸዋ ቡልጋ አቀኑ። እዚያም ከጦሩ ጀግና አበበ አረጋይ ጋር የጦር ስልት ነደፉ፤ መክረውም በኋላ ላይ ወደ ሶዶ ተመለሱ። ከጠላት ለደጃዝማች በቀለ መጋቢት 17 ቀን 1932 ዓ.ም አንድ መልዕክት ደረሳቸው። በወቅቱ አብረዋቸው ከነበሩት ቀኛዝማች በየነ ጉደታ ጋር ሳሉ “እጅ ብትሰጡ ይሻላችኋልና አስቡበት” የሚል ደብዳቤ ደረሳቸው።
ነገር ግን እነኚህ ቆራጥ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ጠላት እንዲህ ማለቱ አስቆጣቸው። በድፍረት እጅ ስጡ በመባላቸው ተናደዱ። እንቢኝ ለአገሬ አሉ። መስከረም 22 ቀን 1932 ዓ.ም ጦር ተከፈተ። ሶዶ ውስጥ ረጲ የተባለ ቦታ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ከባድ ጦርነት ተፋፋመ። ብዙ የደጃዝማች በቀለ ጦር እየፎከረ በጀግንነት አለቀ። ቀኛዝማች በየነ ጉደታም ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ሶዶ እንዲሄዱ ተደረገ።
ቀኛዝማች በየነ ጉደታ እዚያ ሳሉ የመግደል ሙከራ ገጠማቸው። ሸሽተውም ገረሱ ዱኪ ጋር ተመለሱ። ቁስላቸውም ሲድን ወደ በቀለ ወያ ለመሄድ መንገድ ላይ ሳሉ የጣሊያን ወራሪ ሀይል ከበባቸው። በዚህም ውጊያ ተከፈተ። ከጠላት 20 የጦር መኮንኖችና ከ30 በላይ ወታደር ገድለው በመጨረሻ በክብር ተሰው። እዚያው የነበሩ ስድስት አርበኞችም አብረው ተሰው።
ደጃዝማች በቀለ በሰሙት ነገር ልባቸው ክፉኛ አዘነ። በዚህም የወንድሞቻቸውን ደም ለመመለስ ቆረጡ። ሚያዝያ 23 ቀን 1932 ዓ.ም ዝቋላ ላይ በተለየ የጦርነት ስልት የወራሪው ጠላት በመረፍረፍ ቁጭታቸውን ተወጡ። ቀጥሎም ግንቦት 27 ቀን 1932 ዓ.ም ዝቋላ ወንበራ ሌላ ጦርነት አድርገው አስደናቂ ድል ተቀዳጁ። በዚህም “በኮሎኔል አቡ” የተባለውን ከባድ ጦር ገጥመው 26 የጠላት መኮንኖችና 60 ወታደሮች ገድለዋል።
በዚህም የጠላት ጦር እጅግ ተረበሸ ፍርሀትም አደረበት። ጠላት ጎጃም ላይ ጀግናው በላይ ዘለቀ የፈጠረበት ድንጋጤ ሶዶ ላይ በበቀለ ወያ ተደገመ። ጣልያንም የደጃዝማች በቀለን ሠራዊት ለመደምሰስ ባንዳና የራሱን ወታደሮች ከጅማ፣ ከሲዳሞ፣ ከናዝሬት፣ ከወሊሶ፣ ከአዲስ አበባና ከአርሲ ሰብስቦ ያለመቋረጥ 12 ሰዓት የፈጀ ውጊያ አደረገ። ነገር ግን ወራሪው ተስፋ ያደረገበት ውጊያ በጀግናው በቀለ ወያ በሚመራው ድባቅ ተመታ። የጀግናው በቀለ ወያ ጦር ከገረሱ ዱኪ ጋር በመተባበር ጠላትን እያርበደበደና እየወጋው ብዙዎችን ገደለ፤ ማረከም፤ በዚህም ድል ተቀዳጀ።
በዚህም ደጃዝማች በቀለ ወያ አገሬን አላስደፍር ካሉ ኢትዮጵያዊያን ጋር አምስቱን አመት በዱር በገደሉ ተዋድቀው አገራቸውን ዳግም ድል አጎናፀፉ። ከጣሊያን መባረር በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት እንደተመለሱ በቀለ ወያ የተለያዩ ማዕረጎች አግኝተው በሀላፊነት ህዝባቸውን አገልግለዋል።
በዚህም በ1933 ዓ.ም በፊታውራሪነት ማዕረግ የሲዳሞ ጥብቅ አስተዳዳሪና የክብረ መንግሥት የወርቅ ማዕድን ኃላፊ፣ በ1933 ዓ.ም የሁለተኛ ሬዥማን አዛዥ፣ በ1934 ዓ.ም በወለጋ የሶዩ አውራጃ ገዥ፣ በ1935 ዓ.ም በደጃዝማችነት ማዕረግ የጨቦና ጉራጌ አውራጃ ገዥ፤ በ1936 ዓ.ም የወላይታ አገረ ገዥ፣ በ1938 ዓ.ም በሐረር የጨርጨርና ኢሳ አውራጃ ገዥ በመሆን ለአገራቸው ታላቅ አገልግሎትን ሰጥተዋል።
በመጨረሻም እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጀግና ባደረባቸው ጽኑ ሕመም ምክንያት ለሕክምና ወደ ስዊዘርላንድ በጉዞ ላይ ሳሉ ሚያዝያ 6 ቀን 1946 ዓ.ም አርፈዋል። ይህንን ፅሁፍ ስናዘጋጅ ፣ በሽፈራው መንገሻ በ1993 ዓ.ም የታተመው የሻቃ በቀለ ወያ ታሪክ “የትውልድ አርአያ ” የተሰኘ መፅሐፍና ልዩ ልዩ ድህረ ገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22 /2014