ዘመኔን የጨረስኩት ከእናቴ ጋር እየተኛሁ ነው። አድጌና ትዳር ይዤ እንኳን ከሚስቴ ቀጥሎ ከእናቴ ጋር የምተኛ ነኝ። አንድ እህት አለችኝ..ሽንታም እህት። ለእናቴም አንድ ለእህቴም አንድ ስለሆንኩ እናትና እህቴ እኔን መሀል አድርገው ነው የሚተኙት። እህቴ ሽንታም ናት..አልጋ ላይ ሳትሸና ከእንቅልፏ የተነሳችበት ቀን የላትም። እኔም ሆንኩ እናቴ በእህቴ ሽንት ሳንበሰብስ ያሳለፍንው ሌሊት የለም። አልጋው መሀል ላይ ዛሬም ድረስ የማይረሳኝ በእህቴ ሽንት ማዲያት ያበጀ..ማዲያት ብቻ አይደለም የተቦተረፈ ፍራሽ አለ። እናቴ ፍራሹን ከእህቴ ሽንት ለመከላከል ያላደረገችው ጥረት አልነበረም። ወፍራም ጨርቅ፣ ውሀ የማያስገባ ነገር፣ ርጥበት የሚከላከል ላስቲክ በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፎ ግን የእህቴ ሽንት ሁላችንንም ያዳርሰናል። በልጅነቴ እናቴ ሞክራ ያቃተችው የእህቴን ሽንት መቆጣጠር ይመስለኛል። አንዳንድ ጊዜ ጎርፍ የምትሸና ይመስለኛል..።
ጠዋት ከእንቅልፌ የምነቃው በእህቴ ሽንት ግማሽ ጎኔ እርሶ ነው። በእኛ ቤት የእህቴ አለመሽናት እንደ ተዐምር የሚታይ ነበር። ለሽንታሟ እህቴ ብቻ አይደለም ለእኔም ሆነ ለእናቴ የእህቴ ያለሽንት ተኝቶ መንቃት አዲስ ነገራችን ነበር። ግን እህቴ ሳትሸና የነቃችበት ጠዋት የላትም። እናቴ እህቴ ሳትሸና እንድትነቃ የማታደርገው አልነበረም። ማታ ውሃ አትጠጪ ሽንትሽ ይመጣል ሳትላት ቀርታ አታውቅም። በጊዜ ተኝታ ከሆነ ቀስቅሳ ሽንቷን አሸንታ ታስተኛታለች። በዚህ ሁሉ ስጋትና ቁጥጥር ውስጥ ነበር እህቴ ሽንቷን የምትለቅብን።
እናቴ እህቴን ስትሰድባትም ሆነ ስታመናጭቃት ሰምቼ አላውቅም። ሁሌ እንደሸናችብን ነው..ሁሌ እንዳቆሸሸችን ነው። ግን እናቴ ከአፏ ክፉ ሲወጣ አይቻት አላውቅም። ክፉ ብቻ አይደለም በእህቴ ላይ ፊቷን ስታቀጭምባት ተመልክቻት አላውቅም። ‹ይይ እንዳው! በቃ እንዲህ ብቻ ነው የምትለው። የእናቴ ጸዐዳ ፊት እህቴን ያሞላቀቃት..የልብ ልብ የሰጣት ይመስለኛል..አይመስለኝምም።
እውነት ለመናገር በዛ ጠዋት እኔም ሆንኩ እናቴ ከእርጥበት በጸዳ እንቅልፍ በቀር አዲስ ነገር አልነበረንም። ግን ተሳክቶልን አያውቅም..ጠዋት በጣም ጠዋት የእህቴን አልጋ ላይ የመሽናት መርዶ ከእናታችን ነው የምንሰማው። እናቴ ምን እንደምታስብ አላውቅም እንቅልፍ የላትም..አሁን አሁን እጇን ወደ እህቴ መቀመጫ እየሰደደች ፍራሹን ስትፈትሽ እታዘባታለሁ። ገና ሳይነጋ..ገና ለማኝ ሳይጸዳዳ በውርጩ እናቴ ‹ይይ እንዳው! ስትል በእንቅልፍ ልቤ እሰማታለሁ። ያኔ የእህቴን የመሽናት መርዶ፣ የእኔንም መርጠብ አውቀዋለሁ።
ለመኖር ግድ አልነበረኝም፣ በዙሪያዬ ላሉት ነፍሶች የምንበረከክ አልነበርኩም። አይደለም ሽንት ቀርቶ አይነ ምድር ታቅፌ ዓለምን ብዞር እንኳን ግድ የሚሰጠኝ አልነበረኝም። ጠዋት ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ ቁርሴን በልቼ ማታ እህቴ በሸናችብኝ ገላና ጥብቆ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ። ግዴለሽ መሆኔ የአንዳንድ ነውረኛ ነፍሶች ርግማን እንዳይሰማኝ ቢያደርገኝም ከቅጣትና ከመገፋት ግን አላዳነኝም ነበር። በተለይ ሰኞ ሲሆን ተማሪዎችም መምህራንም ነበር በአዲስት ድሀ ነፍሴ ላይ የሚጫወቱት። ሰኞ ሆኖ ሰልፍ ላይ ተማሪ ፊት ያልወጣሁበት ጊዜ የለም። ክፍል ውስጥ በሳይንስ አስተማሪያችን ጆሮ ያልያዝኩበት ጊዜ የለም። በእኔ ምክንያት ብቻ እናቴ በአመት ውስጥ እጅግ ለበረከተ ጊዜ ትምህርት ቤት ተጠርታለች። ሰልፍ ላይ ከዚያም ከዚም እየተጠቋቆሙብኝ ብዙ ፊቶች ይሳለቁብኝ ነበር። ትምህርት ቤታችን ውስጥ እናቴ ካወጣችልኝ ስሜ በላይ ሽንታሙ ተማሪ ሆነ ስሜ። ግን ልበ ሙሉ ነበርኩ። በዛ ሁሉ ወንበዴ ተማሪ ተከብቤ፣ በዛ ሁሉ ነገን በማያስተውሉ መምህራን መሀል ቆሜ ጀብደኛ ነበርኩ። በዛ ጠዋት..በዛ ልጅነቴ ውስጥ የእህቴን ነውር እኔ ነበርኩ የምወስደው። በእህቴ ሀጢአት እኔ ነበርኩ የምገረፈው። የእኩይ ነፍሷ ማረፊያ ነፍሴ ነበረች።
ሰኞን አልወዳትም..ዛሬም ድረስ እጠላታለሁ።
በነጋታው ያው ነኝ.እህቴ ሳትሸናብኝ፣ ዝንቦች ሳይወሩኝ በተፈጥሮ ጠረኔ ትምህርት ቤት ሄጄ አላውቅም። የዛ ሁሉ ተማሪ ነቆራ፣ የነዛ ሁሉ ጓደኞቼ አሽሙር ዘልቆ አይሰማኝም ነበር። አንዳንዴ እኔን በሚያበሽቁኝ ተማሪዎች መሀል ራሴን እየሳኩ አገኘዋለሁ። ብዙ ጊዜ ሽንታሙ ተማሪ እያሉኝ ከሚያበሽቁኝ ተማሪዎች ጋር ወዳጅ ነበርኩ። ኳስ በቡድን እንጫወታለን። ብይ፣ አባሮሽ ሌሎችንም ጨዋታዎች እንጫወት ነበር። በዚያ ሁሉ አብሮነታችን ውስጥ እኔን ለማናደድ፣ እኔን ለማስኮረፍ፣ እኔን ለማስለቀስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አልነበረም ግን በነጋታው አብሬአቸው እስቃለሁ። የሆነ ጊዜ ነውሬን ሰለቹት መሰለኝ..ክብረ አብ ሲሉ እናቴ ባወጣችልኝ ስሜ ይጠሩኝ ጀመር። ሰው አብሮ ካረከሰ በስተቀር እኩዮችን የሚያሸንፍበት አቅም ያጣል ብዬ አላስብም። በልጅነቴ እነዛን በእድሜ የሚበልጡኝን፣ እነዛን በወንድሞቻቸው የሚመኩትን ጓደኞቼን ያሸነፍኩት በመተው ነው እላለሁ። በልጅነቴ እነዛን እልኸኞች፣ እነዛን ትዕቢተኞች፣ እነዛን ጥጋበኞች ዝም ያሰኘሁት በሳቄ ነው እላለሁ። እንጂማ ምን ነበረኝ..ለራሴ የሴት ልጅ።
ቤት ስደርስ እናቴ ገላዬን ታጥበኛለች ግን ማታ በእህቴ ሽንት ሳላድፍ ቀርቼ አላውቅም። ጠዋት የታጠበ ገላዬ፣ በቫዝሊንና እናቴ በአመት አንድ ጊዜ በምታወጣው ሽቶዋ የጠረነ ገላዬ በእህቴ ሽንት ጨቅይቶ አገኘዋለሁ። አብሮ የእናቴ ‹እይይ እንዳው! ይሰማኛል። ቀዝቃዛ ውሃ አልወድም..ቀዝቃዛ ውሀ ከሚነካኝ እድሜ ልክ ሰውነቴን ባልታጠብ የምመርጥ ልጅ ነኝ። ፋሲካ ሲሆን ወይም ደግሞ ራት ሳልበላ የተኛሁ ቀን እናቴ ከእንቅልፌ የምታባንነኝ ቀዝቃዛ ውሃ ፊቴ ላይ በመርጨት ነው። ያኔ አኩርፌ ራት አልበላም ብዬ በግድ አባብላኝ ነበር የምትታረቀኝ። ቀዝቃዛ ውሃ አልወድም። እናቴ እኔን ገላዬን አጥባ ትምህርት ቤት ለመላክ ውሃ ለማሞቅ በጠዋት ትነሳለች። ውሃው እስኪሞቅ ሰዓት ስለሚረፍድ ሳልታጠብ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ። ጠዋት በሞቀልኝ ውሃ ከሰዓት ከትምህርት ቤት መልስ እታጠባለሁ። አንድም ቀን ጠዋት ሰውነቴን ታጥቤ አላውቅም..እናቴ ጠዋት ተነስታ ውሃ ብታሞቅልኝም ሰዓቱ ስለሚረፍድ አልታጠብም..ከምታጠብ ይልቅ አለመታጠቤ ነበር የሚያስደስተኝ..ሙቅ ውሃውም ስለሚቀዘቅዘኝ።
በእህቴ ሽንት ስታጠብ ያደኩ ልጅ ነኝ። እህቴ ሳትሸናብኝ፣ ዝንቦች ሳይወሩኝ ተማሪ ፊት ሳልቆም የቀረሁበት ጊዜ የለም። ከእርጥበት የጸዳ ማለዳ፣ ከነቀፋ የራቀ ጠዋት ብርቄ ነበር። አንድ ጠዋት እህቴን ተቀየምኳት..በልደቴ ዋዜማ እህቴ እንዳትሸናብኝ ያላደረኩት ጥረት አልነበረም። ነግቶ በልደቴ ቀን አዲስ ልብስና ጫማዬን እስክለብስ ቸኩዬ ነበር። ማታ በእኔ ምኞትና ማባበል ይሆን ይመስል ዛሬ እንዳትሸኚብኝ ስል እህቴን በብዙ ለመንኳት። እየሰጋሁ በእናቴና በእህቴ መሀል ተኛሁ። ስለልደቴና ስለምለብሰው አዲስ ልብስና ጫማ እያለምኩ ነበር። ጠዋት በጣም ጠዋት እናቴን ‹እይይ እንዳው! ስትል ሰማኋት። እህቴ እንደሸናችብኝ አመንኩ። ዘመኗን ስትሸናብኝ ያልተቀየምኳትን እህቴን ያን ቀን ተቀየምኳት። አዲስ ልብስና ጫማዬን በእህቴ ሽንት ባደፈ ገላዬ መልበስ ግድ ሆነብኝ።
ቀኑ ቅዳሜ ነበር.. እናቴ በልደቴ ቀን ጠዋት ለእኔ ውሃ ልታሞቅ የተነሳችበት ቅዳሜ። ያን ቀን እናቴንም ሆነ ሙቅ ውሃውን የማመልጥበት ምንም አጋጣሚ አልነበረም። በእለተ ቅዳሜ የሚረፍድ ቀን አልነበረኝም በእናቴ ሙቅ ውሃ ሰውነቴን ታጥቤ አዲስ ልብስና ጫማዬን መልበስ እጣ ፈንታዬ ሆነ። ከሁሉም ቀድማ እንኳን ተወለድክ ስትል ጉንጬን የሳመችኝ ሽንታሟ እህቴ ነበረች።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20 /2014