በሳምንቱ መጨረሻ ሊካሄድ በታቀደው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ስፖርቱን ለቀጣይ አራት አመታት የሚመሩ ግለሰቦች ለፕሬዚዳንትነትና ለስራ አስፈጻሚነት የሚያደርጉት የምርጫ ፉክክር ይጠበቃል።
የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴውም ባለፈው ሳምንት ለፕሬዚዳንትነት የሚፎካከሩ ሶስት የመጨረሻ እጩዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በዚህም ባለፉት አራት አመታት ፌዴሬሽኑን ሲመሩ የቆዩት አቶ ኢሳያስ ጂራ ከኦሮሚያ ክልል ተወክለው ለፕሬዚዳንትነት የሚፎካከሩ ሲሆን፣ አቶ መላኩ ፈንታ ከአማራ ክልል እንዲሁም አቶ ቶኩቻ አለማየሁ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው እጩ ሆነው መቅረባቸው ይታወሳል። ከፕሬዚዳንታዊ እጩዎች መካከል የአገልግሎት ዘመናቸውን አጠናቀው ዳግም ለመመረጥ እየተፎካከሩ የሚገኙት አቶ ኢሳያስ ባለፈው ሳምንት በእሳቸው የአስተዳደር ዘመን ፌዴሬሽኑ ላይ እየቀረቡ ለሚገኙ ትችቶች ምላሽ የሰጡ ሲሆን ሌላኛው ተፎካካሪ አቶ መላኩ ፈንታ ደግሞ ትናንት ምርጫውን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ መላኩ ፋንታ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ካሸነፉ ሊሰሯቸው ያሰቧቸውን የትኩረት አቅጣጫዎችን በመግለጫው ላይ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የተደረጉ ምርጫዎችን በተመለከተ ብዙ ብልሹ አሠራሮች መኖራቸውን በሰነድና በሰው ማስረጃ አረጋግጫለሁ ብለዋል። ይህ ነገር ለእግር ኳሱ እድገት ስለማይበጅም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊታገሉት እንደሚገባ አሳስበዋል። “ሃሳብ እንጂ ኔትወርክ፣ ገንዘብ፣ አካባቢና ዘር ተኮር ምርጫ መቆም አለበት” ያሉት አቶ መላኩ በተለይም በምርጫው ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው የጉባኤ አባላት በገንዘብ ከመገዛት መውጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ያላቸውን እምነት የገለፁት አቶ መላኩ፣ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ካሸነፉ ሊሰሯቸው ያሰቧቸውን የትኩረት አቅጣጫዎችን በሰፊው አንስተዋል። እግር ኳስ በጠንካራ ቢዝነስ ሞዴል ከተመራ ትልቅ አገራዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር የዓለም አቀፍ ተሞክሮን አንስተውም ሃሳብ ሰጥተዋል።
“ኢትዮጵያ የካፍ መስራች ብትሆንም ዓለም እየተጠቀመበት ካለው ትልቅ የእግር ኳስ አቅም መጠቀም አልተቻለም” የሚሉት አቶ መላኩ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የእግር ኳስ አቅም፣ ወጣቶችን፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ሌሎችንም በቅንጅትና በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ዓለም ወደ ደረሰበት ደረጃ በቀላሉ መድረስ እንደሚቻል አስረድተዋል።
“የኢትዮጵያን እግር ኳስ ትንሣኤ እውን ለማድረግ ሁላችንም ለለውጥ ዝግጁ መሆን አለብን፤ እኔም፣ አንተም፣ አንቺም፣ እናንተም፣ ሁላችንም ይህን የለውጥ ሃሳብና ተነሳሽነት በአመራርነት ለማቀጣጠል፣ ከፊት ሆኖ ለምራትና በለውጥ ለለወጥ እንነሳ” ያሉት አቶ መላኩ ፋንታ ቻይ በሥራ አመራር ቦርድ መሪነትና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ በርካታ ስኬቶችን እና ተጠቃሽ ውጤቶችን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ አሻራቸውን ባሳረፉባቸው ተቋማት ሁሉ አዳዲስ የለውጥና ማሻሻያ ሃሳቦችን በማመንጨትና በመተግበር ይታወቃሉ። በአሁኑ ሰዓት የአማራ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ መላኩ ፋንታ መንግስት በተሰጣቸው የሥራ ኃላፊነት በርካታ ተቋማትን መርተዋል። ከነዚህ መካከል በኢትዮጵያ የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።
አቶ መላኩ ፈንታ በሥራ አመራር ቦርድ መሪነትና አባልነት በርካታ ተቋማትን ያገለገሉና በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው አማራ ባንክ ከምሥረታው ጀምሮ የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን እያገለግሉ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ እግር ኳሱ ከቅርብ አመታት ወዲህ ስኬታማ መሆኑን ያስመሰከረው የፋሲል ከነማ የስፖርት ክለብም የሥራ አመራር ቦርድ አባል ናቸው። ይህን ከፍተኛ ልምድና ውጤታማ ተሞክሮ በእግር ኳሱ መድረክ ለመጠቀምና በለውጥ ሃሳብ ትግበራ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ጠንካራ ተፎካካሪ ያደርጋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
“ስፖርት በተለይም እግር ኳስ የሕዝብ፣ ለሕዝና በሕዝብ የሚከወን እንደመሆኑ በተቋማዊ ለውጥ ትግበራ የሚፈለገው ተጨባጭ ውጤት እንዲገኝ ለውጡ ባለድርሻዎችን ሁሉ ያካተቱ የሚከተሉት መሠረታዊ መርሆዎች ይኖሩታል” ብለው ወደ ምርጫው ፉክክር የገቡት አቶ መላኩ በአዝጋሚ ሂደቶች በተገኙና በሚገኙ አንዳንድ ውጤቶች በመርካት ሳይሆን ሁለንተናዊ የሆነ ተቋማዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
አቶ መላኩ ምርጫውን ካሸነፉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚሳተፉበትና በተለይ መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና ሕዝቡ ለእግር ኳሱ ትንሣኤ በጋራ እንዲሰሩ የማስቻል አላማ እንዳላቸው ገልጸዋል። የመልካም አስተዳደር እጦት፣ በተለይም የሙስና ችግር የስፖርቱ ውድቀት ዐብይ ምክንያት በመሆኑ መልካም አስተዳደርንና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ለስፖርቱ እድገት ቀጣይነት አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንዲኖር ስፖርቱን በቢዝነስ መርህ መምራት፣ ስፖርቱ ከሁሉም፥ ለሁሉም እንዲሆን ተደራሽነትን ማስፋት፣ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ለማስቻልም እንደሚሰሩ አብራርተዋል።
ስፖርቱ በእውቀት እንዲመራ እያንዳንዱ ተግባር ብቃት ባለው ባለሙያ እንዲመራ በዘርፉ በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ የማከናወን ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። ተቋማዊ አቅሙ የዳበረ፣ በኢትዮጵያውያን ሁሉ ቅቡል የሆነና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቱ ከፍ ያለ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የመገንባት ራእይና አላማ እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17 /2014