ነጻ የንግድ ቀጠና ማለት ምንም ዓይነት የንግድ እንቅፋት የሌለበት አካባቢ ማለት መሆኑን የኢኮኖሚ ተንታኞች ያስረዳሉ። ከሌሎች አገሮችና አካባቢዎች ያነሰ ታሪፍ ያለባቸውና አነስተኛ ታክስ የሚከፈልባቸው ናቸው፡፡ በተጨማሪ ታክስ ለመክፈል ቀላል የሆነበት አካባቢ ነው፡፡ አነስተኛ ታክስ በመከፈሉ የምርቶቹ ታሪፍ ዋጋ ቅናሽ መሆኑ መለያ ባህሪው ሲሆን፤ ንግዱን የሚያዛቡ ፖሊሲዎች ካለመኖራቸው በተጨማሪ ገበያዎቹ ጠንካራ ቁጥጥር አይደረግባቸውም፡፡
ነፃ የንግድ ቀጠና ጥቅም ሲነሳ በዋናነት የሚጠቀሰው የውጭ ኢንቨስትመንት የሚያስፋፋ ስለመሆኑ ነው። መከፈል ያለበት ታክስ እና ታሪፍ ስለሚቀነስና በዚህ መንገድ ኢንቨስት ለማድረግ ብዙ ካፒታል ስለሚገኝ የውጭ ኢንቨስተሮች ይሳቡበታል፡፡ በዚህ ምክንያት አዳዲስ ስራዎችን ለመፍጠርና የቢሮክራሲያዊ ሂደቶችን የሚቀንስ ከመሆኑም በተጨማሪ ፈጣን አገልግሎት እና ግብይት ለመፈፀም የሚያግዝ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታሪፍ ነፃ የሆነ አዲስ ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር ዕድል ከመስጠት ባሻገር፤ በአገራት መካከል የበለጠ የንግድ ትስስር እንዲፈጠር ይረዳል። በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ምክትል ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን እንደገለፁት፤ ነጻ የንግድ ቀጠና በአገሪቱ ያሉ ወይም ደግሞ ከዚህ ቀደም ሲሰራባቸው የነበሩ የንግድ ህጎች የማይመለከተው ሆኖ ለብቻው የተለየ አሰራርና የንግድ ማዕቀፍ ተበጅቶለት በአንድ ቦታ የሚከወን የንግድ ሥርዓት ነው፡፡ ነጻ የንግድ ቀጠና ዓለም አቀፍ የንግድ ህጎችም የሚደግፉትና አገራትም ተግባራዊ ሲያደርጉት የነበረና አሁንም እየተገበሩት ያለ አሰራር ነው፡፡
ነፃ የንግድ ቀጠና ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳትም እንዳለው ይጠቀሳል፡፡ ከሚነገሩት ጉዳቶች መካከል የበለጠ ኃይልና አቅም ያላቸውን ሰዎች የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል። ሠራተኞችን የሚፈለገውን ያህል ብዙም የማይጠቅምና ወደ ሌሎች አካባቢዎች የስራ ፍልሰት እንዲኖር ማድረጉም ከጉዳቶቹ መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
ነፃ የንግድ ቀጠና ሃሳብን ተግባር ላይ በማዋል ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል ስዊዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ አይስላንድን የመሳሰሉት አገሮች በዓለም ታዋቂነትን ያተረፉ ናቸው፡፡ ሜክሲኮ፣ አሜሪካ እና ካናዳን የመሳሰሉ አገራት የሰሜን አሜሪካ ነጻ የንግድ ስምምነት በማድረግ ግብይቱን ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡ የደቡብ ምስራቅ እስያ ነፃ የንግድ ስምምነትም እነቻይናን ይዞ ሲሰራበት መቆየቱን ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ወደ አፍሪካ ሲመጣ የአፍሪካ አገራት እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት መደበኛ ንግድ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት አጠቃላይ የአገራቱ የወጪና ገቢ ንግድ ድርሻ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑን በማንሳት፤ የአፍሪካ አህጉራዊ የነጻ ገበያ ቀጠና ስምምነት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ያግዛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የፀደቀው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና አፍሪካን በገበያ ማስተሳሰር፣ በአገራቱ መካከል ንግድን ማሳደግ እና ቀጠናዊ ውሕደትን ማበረታታትና ማጠናከርን ግብ ስለማድረጉ በነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ላይ ተመላክቷል፡፡
የአፍሪካ ነጻ ገበያ ቀጠና እንደ ነጻ ንግድ ስምምነት የጸደቀው እ.አ.አ በግንቦት 30 ቀን 2019 ቢሆንም በቀጠናው ነጻ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲጀመር የተቀጠረው እ.አ.አ ሰኔ 1 ቀን 2020 ነበር፡፡ ነገር ግን የታሪፍ ድንጋጌዎች ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው በመሆኑ፤ አገልግሎቶችን በተመለከተ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶችና ኢንቨስትመንትም ሙሉ ለሙሉ ቁርጥ ውሳኔ ላይ ያልተደረሰባቸው በመሆኑ በድርድር ተጨማሪ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ከቢቢሲ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያን ጨምሮ 44 የአፍሪካ አገራት መሪዎችና የአገራት ተወካዮች አህጉሪቱን በነፃ የንግድ ልውውጥ ሊያስተሳስር የሚችል ስምምነት ቀደም ሲል የፈረሙ ቢሆንም ሳይተገበር ቆይቷል፡፡ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን አፍሪካውያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ለአገራት ኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ እንዳለው የተጠቀሰለት ይኸው ስምምነት በአፍሪካ አገራት መካከል ድንበር የማያግዳቸው የንግድ ልውውጦች እንዲካሄዱ እንደሚያግዝ፤ አስመጭዎች ላይ የሚጫነውን ቀረጥ በማስቀረት በአህጉሪቱ አገራት መካከል ያለውን ነፃ ዝውውር እንደሚያበረታታ ተገልጿል፡፡
ምንም እንኳ ኢትዮጵያን ጨምሮ 44 የአፍሪካ አገራት ስምምነቱ ይጠቅመናል ብለው ፈርመዋል ቢባልም፤ ጥር 2013 ዓ.ም /እ.አ.አ.ጥር 1 ቀን 2021 / ወደ ሥራ ሲገባ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ከኤርትራ በቀር 54 አባል አገሮች መፈረማቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የአፍሪካ አገራት በእኩል የዕድገት ደረጃ ላይ አለመሆናቸው ለማዕቀፉ ተፈፃሚነት ትልቅ እንቅፋት እንደሚሆን በመጥቀስ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ቢሞግቱም ቀድሞ ስምምነቱ በሒደት ላይ እያለ አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የአፍሪካ አገራትን የንግድ ልውውጥ በማሳደግ ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር ይጨምራል ተብሎ ተገምቷል፡፡ አሁን 54 አገራት ፈርመው የተቀበሉት በመሆኑ የሚያስገኘው ትርፍ እና የአገራት ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል እየተተነበየ ነው፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፤ አፍሪካን በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም የማዋሃድ ተልዕኮ ያነገበው አህጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ወደ ሥራ መግባት፤ ነጻ የንግድ ቀጠናው በአፍሪካ አገራት መካከል ተመጋጋቢ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር፣ በአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዲመጣ፣ የግል ባለሃብቱ ተሳትፎ እንዲያድግ፣ ለስራ ፈጠራ እና ሚዛናዊ የንግድ ስርዓትን ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ እና በሌሎችም የተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊነቱ ዘግይቶ የነበረው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተግባራዊ መሆን መጀመር ለአህጉሪቱ ትልቅ ጥቅም እንደሚያስገኝ በቀጣይ በተግባር ይረጋገጣል የሚል ተስፋ ተይዟል፡፡
ኢትዮጵያ በአየር መንገዷ በኩል በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚጓጓዘውን የመጀመሪያ ጭነት ከእስዋቲኒ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ጀምራለች፡፡ በንግድ ሚኒስቴር የባለብዙ ወገን ንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳዬ ነጻ የንግድ ቀጠናው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ አምራቾች ተገማችና ሰፊ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡
‘አጎአ’ን በማስታወስ ለአፍሪካ የተሰጡ የንግድ አማራጮች ቢኖሩም ዘላቂ አለመሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህ የንግድ ስምምነት ግን ዘላቂና አስተማማኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ብዙ እንደምትጠቀም ያነሱት ዳይሬክተሩ በአግባቡ ከተጠቀመች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የምትችል መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር አለማየሁ ገዳ እንደሚናገሩት፤ ነጻ የንግድ ቀጠናው በአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ በ20 በመቶ ወይም በ14 ቢሊዮን ዶላር ይጨምረዋል፡፡
እንደምጣኔ ሃብት ባለሙያው ገለፃ፤ ነፃ የንግድ ቀጠና ምንም ችግር አያጋጥመውም ወይም ምንም ችግር የለበትም ለማለት አዳጋች ነው፡፡ አቶ ሙሴ ምንዳዬ በአፍሪካ ያለው የመሰረተ ልማት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ቦታዎች እየተሠሩ ያሉ የባቡር መሰረተ ልማቶች መኖራቸው ችግሩን ያቀለዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
አገራት ከሌሎች አገራት ጋር ወይም በአህጉር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥም ነፃ የንግድ ቀጠና ይተገበራል፡፡ በኢትዮጵያ ከሰሞኑ በድሬዳዋ ከተማ በሙከራ የተጀመረው ነጻ የንግድ ቀጠና ራሱን የቻለ የህግ ማዕቀፍ፤ ከአዋጅ ጀምሮ መመሪያና ፖሊሲ፤ እንዲሁም ራሱን የቻለ ቀጠናውን የሚቆጣጠር ተቆጣጣሪ ያለው ሆኖ የሚደራጅ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአንድ ቦታ የተከለለና የንግድ ሥርዓቱ ከተለመደው የንግድ ሥርዓት በተለየ መልኩ የሚከወነው ንግድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ነገር ግን የተለየ ዞን እንዳለ ተደርጎ የሚወሰድ የንግድ ቦታና ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መሆኑን በመጥቀስ፤ በነፃ ቀጣናው የአገሪቱ የጉምሩክ ሥርዓትና አጠቃላይ ሕጎች ልማቱን ለማፋጠን በሚያስችል ሁኔታ ላልተው የሚተገበሩበት እንደሆነ በመጠቆም፤ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች በዚህ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ገብተው ሲሠሩ የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ በማለት ለማበረታታት ጥሪ ሲቀርብ ሰነባብቷል፡፡
ከኢትዮጵያ አንፃር በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ምክትል ዴኤታ አቶ እንዳለው መንግሥት በሚፈልገው ቦታ ላይ በተለይም ከትራንስፖርትና ከሎጅስቲክስ እንዲሁም ከደረቅ ወደብ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ቦታው የሚመረጥበት የራሱ መስፈርት አንዳለው ይናገራሉ፡፡ ይህን መስፈርት መሰረት በማድረግም የራሱ አጥር ኖሮት የተከለለ ቦታ ይኖረዋል፡፡ በዛ ቦታ ላይ የሚስተናገደው ንግድ ማንኛውም በአገሪቱ ያሉ የንግድ ህጎች የማይገዙትና ቀለል ባለ ሁኔታ የሚስተናገድ የንግድ አሰራር መሆኑን አንስተው፤ በምሳሌነትም የሰሞኗን ድሬዳዋን ገልጸዋል፡፡
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ሲነሳ በቀጠናው ውስጥ የሚገቡ አምራቾች ከነፃ የንግድ ቀጠናው ሳይወጡ የምርት ግብአቶችን የሚያገኙበት ከመሆኑ ባሻገር፣ ከነፃ የንግድ ቀጠና ውጭ የሚያመርቱ ኩባንያዎች በግብዓትነት የሚጠቀሟቸውን ያላለቁ ምርቶች ከውጭ ሲያስገቡ እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸው ቀረጥና ታክስ በነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ ተግባራዊ የማይደረግ በመሆኑ የምርት ወጪ የሚቀነስ ስለመሆኑም ተጠቁሟል።
ይህም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና እንዲገቡ ትልቅ ብርታት የሚሰጥ እንደሚሆን ይታሰባል። በመሆኑም ነፃ የንግድ ቀጣና መቋቋም የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ከዚያው ጎን ለጎንም የውጭ ምንዛሬ፣ የኤክስፖርት ዕድገት፣ የኤክስፖርት ምርት ስብጥር ከማሳደግ ባሻገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ፡
የመንግሥት ገቢ በማሳደግ ረገድ የራሱን ጉልህ ሚና የሚጫወት ይሆናል የሚባለው የነፃ ንግድ ቀጣና እንቅስቃሴ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና የሠራተኞች ክህሎትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ይነገራል። በተጨማሪ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚመሠረትበት አካባቢን ወይም ቀጣናን በማልማትና በማሳደግ ረገድ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ ስለመሆኑም ይገለጻል፡፡
በ60ዎቹ አካባቢ ሰዎች ማውራት የጀመሩለት ነጻ የንግድ ዞን፤ በእነዚህ የመጀመሪያ ዓመታት ውስጥ የአየር ማረፊያዎች እና ወደቦች አካባቢ በአጎራባች አገሮች መካከል የሁሉም ዓይነት ዕቃዎች ልውውጥ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ታስቦ የተነሳ ፅንሰ ሃሳብ ነበር። በ80ዎቹ ግን የነፃ ንግድ ዞን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ማግኘት የጀመረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከአምስት ሺህ በላይ ዞኖች በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች እንደ ልዩ ዞኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።
እንደምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ገለፃ፤ ነጻ የንግድ ቀጠና በአፍሪካ አገራት መካከል ተመጋጋቢ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር፣ በአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዲመጣ ለማስቻል፣ የግል ባለሃብቱ ተሳትፎ እንዲያድግ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሚዛናዊ የንግድ ስርዓትን ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በልዩ ትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አያጠራጥርም፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17 /2014