ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ የቀረቡ የመጨረሻ እጩዎች ዝርዝር ይፋ ተደርጓል።ምርጫውን ተከትሎ በፌዴሬሽኑ ላይ እየተነሱ ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተም ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያ መግለጫ ሰጥቷል።
የአራት ዓመት የስራ ዘመኑን ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቀጣይ ሳምንት መጨረሻ በሚካሄደው ምርጫ እንደሚተካ ይታወቃል።ይህንን ተከትሎም የተቋቋመው የምርጫ አስፈጻሚ እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ከየክልሉ በደረሱት ተወካዮች የመጨረሻዎቹን የፕሬዚዳንታዊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እጩዎች አሳውቋል።በዚህም መሰረት ለፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ሶስት እጩዎች የቀረቡ ሲሆን፤ ያለፉትን አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን ሲመሩት የቆዩት አቶ ኢሳያስ ጂራ ኦሮሚያ ክልልን በመወከል በእጩነት ቀርበዋል።የአማራ ክልላዊ መንግስትን በመወከል አቶ መላኩ ፈንታ የቀረቡ ሲሆን፤ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ደግሞ አቶ ቶኩቻ አለማየሁ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው እጩ ሆነዋል።በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ምርጫውም 32 የሚሆኑ እጩዎች የተለያዩ ክልሎችን በመወከል ለውድድር ቀርበዋል።
በመጪው ሳምንት መጨረሻ ነሃሴ 21 እና 22/2014ዓም ከሚደረገው የፌዴሬሽኑን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አክሲዮን ማህበር አስመራጭ ኮሚቴው ትችቶችን ሲያስተናግድ መቆየቱ የሚታወስ ነው።ይህንን ተከትሎም ፌዴሬሽኑ ያለአግባብ የስም ማጥፋት ደርሶብኛል ባላቸው ርዕሶች ላይ በፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጂራ አማካይነት በጋዜጣዊ መግለጫ ማብራሪያ ተሰጥቷል።ፕሬዚዳንቱ ካነሷቸው ነጥቦች መካከልም ከገንዘብ አወጣጥ ጋር የተያያዘው አንዱ ሲሆን፤ እርሳቸው ወደ ስልጣን በመጡበት ዓመት ፌዴሬሽኑ 16 ሚሊየን ብር እዳ የነበረበት መሆኑን ጠቁመዋል።በዚህም ምክንያት ቡድኖች አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ እስከማይችሉበት ሁኔታ ላይ ተደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።ነገር ግን አቅም በማደራጀትና የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን በመስራት በዚህ ወቅት ፌዴሬሽኑ በአካውንቱ ከ45 ሚሊየን ብር በላይ እንዳለው ጠቁመዋል።
ይህም ፌዴሬሽኑ በተለያዩ የዕድሜ እርከን ከሚመራቸው ብሔራዊ ቡድኖች፣ የወዳጅነት ጨዋታዎች፣ የስፖርት ልማት ስራዎች፣ ሌሎች ወጪዎች እንዲሁም ለየክልል ፌዴሬሽኖች ከተሰጠው 12 ሚሊየን ብር ውጪ ነው።ከዚህ ጋር በተያያዘ ስማቸው የተነሳ ግለሰቦች ለፌዴሬሽኑ ከሚያስገኙት ገቢ ጋር ሊያገኙት የሚገባቸውን ገንዘብ ለልማት ስራዎች እንዲውሉ በማድረግ ጭምር በመሆኑ ሊመሰገኑ እንጂ ሊወቀሱ እንደማይገባ ገልጸዋል።
ከፌዴሬሽኑ ህንጻ ግዢ እና ስም ማዘዋወር ሂደት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ትችትም ፕሬዚዳንቱ ምላሽ ሰጥተዋል።በዚህም በፊፋ ድጋፍ በ95 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዛውና ፌዴሬሽኑ እየተገለገለበት ያለው ህንጻ፤ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር እንዲሁም የኮንስትራክሽን ቢሮ ባለሙያዎችን አካቶ በወጣ ጨረታ የተገዛ መሆኑን አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል። ከስም ዝውውሩ ጋር በተያያዘም የተለያዩ ሂደቶችን ያለፈ ሲሆን፤ ፌዴሬሽኑን የማያሳምን ጉዳይ በመፈጠሩ ምክንያት በህግ እንዲያዝ ተደርጓል።በመሆኑም ህንጻው የፌዴሬሽኑ አይደለም የሚባለው ስህተት መሆኑ እንዲሁም ካርታ፣ ሙሉ ውክልና ያለው እና መሸጥ ቢፈልግም የሚችል መሆኑን አብራርተዋል።
ከትጥቅ አቅራቢው ድርጅት ጋር በተያያዘም በቅድሚያ በነጻ የቀረበ መሆኑን በመጠቆም፣ በወቅቱ በተነሳው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት አንዴ የቀረበውን ትጥቅ ለሶስት ዓመት ለመጠቀም ተገዷል።በቀጣይም ፌዴሬሽኑ 12ሺ500 ትጥቆችን በመግዛትና 10ሺ የሚሆኑትን በመሸጥ 10 ሚሊየን ብር እንዳገኘ ገልጸዋል። ይህም ፌዴሬሽኑ ራሱን ለማቋቋም ካደረጋቸው ጥረቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
ከምርጫው ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የተወሰነው የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ በጎንደር ከተማ እንዲካሄድ ነበር።ይሁንና ከተማው ለዚሁ የሚሆነውን ዝግጅት እያደረገ ባለበት ሁኔታ ውዝግቦች መነሳታቸው አልቀረም። በፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ኮሚቴም ጠቅላላ ጉባኤው የሚካሄድበት የቦታ ለውጥ መደረጉን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል። ይህም የሆነው ከአማራ ክልል የስፖርት ቢሮ ምክትል ኋላፊ ወደ ፌዴሬሽኑ በተደረገ የስልክ ጥሪ ምክኒያት መሆኑ ተገልጿል። እንደፌዴሬሽኑ ገለጻ፣ የክልሉ ምክትል ቢሮ ኋላፊው ‹‹ከክልሉ ክለቦች የተላኩ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ወኪሎች ስሞች መቀየር እንዳለባቸው እና ይህንን እንዲያደርጉ፤ ካላደረጉ ግን ጉባኤው እንዲስተጓጎል እንደሚያደርጉ በማስፈራራት ጭምር ስሜታቸውን መግለጻቸው ኮሚቴው ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል››።በመሆኑም ኮሚቴው የጉባኤው ውጤታማነት ላይ ስጋት ስላደረበት ምርጫው ቀድሞ ከተያዘው ጎንደር ከተማ ወደ አዲስ አበባ እንዲዘዋወር ውሳኔ ያሳለፈ መሆኑን አስታውቋል።
ፌዱሬሽኑን የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ ቦታ እንዲቀየር ያሳለፈውን ውሳኔም ተገቢነት እንደሌለው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ገልጿል። የከተማው ኮሚኒኬሽን ትናንት የመምሪያው ኃላፊ አቶ አበበ ላቀውን ጠቅሶ በማህበራዊ ገጹ ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው፣
ፌደሬሽኑ በከተማዋ ጉባኤውን እንዲካሂድ ካሳወቀ በኃላ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ከፌዴሬሽኑ አብይ ኮሚቴ ጋር በቅንጅት በተሳካ ሁኔታ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል።
ይሁን እንጅ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው ከተማዋ ጉባኤውን ለማስተናገድ በመጠባበቅ ላይ ባለችበት ወቅት አሳማኝ ባልሆነ ምክኒያት ፌደሬሽኑ ጉባኤው የሚካሄድበትን ቦታ መቀየሩን በቀን 12/12/2014 ዓ.ም አሳውቋል። ስለሆነም ፌዴሬሽኑ የወሰነው ውሳኔ ተገቢነት የሌለው መሆኑን የመምሪያ ኃላፊው ገልፀው፣ ፌደሬሽኑ የወሰነው ውሳኔው ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ውሳኔውን በድጋሜ ሊጤን እንደሚገባው መምሪያ ኃላፊው ገልፀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2014