ከአስር ቀናት በኋላ በጎንደር ከተማ የሚካሄደው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ፌዴሬሽኑን ለቀጣይ አራት አመታት የሚመሩ የፕሬዚዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ በታቀደው ቀን እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የምርጫ አስፈጻሚና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች ከትናንት በስቲያ በጋራ በሰጡት መግለጫ እስካሁን ያከናወኑትን ስራ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ምርጫውም በታቀደው መሰረት እንደሚከናወን አስረድተዋል። ግንቦት 7/2014 ተመርጦ ባለፉት 55 ቀናት የተለያዩ ስራዎቾን እየሰራ የነበረው የአስመራጭ ኮሚቴው “ 3 ለፕሬዚዳንትነትና 26 ለስራ አስፈጻሚነት ዕጩ ሆነው የቀረቡትን ግለሰቦች ቀደም ሲል ይፋ ማድረጉን አስታውሶ፣ የዕጩዎችን ዝርዝር ከተቻለ ከነሀሴ 12 በፊት ካልተቻለ ደግሞ በነሀሴ 22 ምርጫው በሚከናወንበት ዕለት ለጉባኤተኞች ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁሟል። የቀረው ነገር የጉባኤው መካሄድ ብቻ እንደሆነም የኮሚቴው በሰብሳቢ በአቶ ሀይሉ ሞላ አስረድቷል።
በቀረበው የተገቢነት ጥያቄ ዙሪያም “ ከጉባኤተኛውም ሆነ ከፊፋ የቀረበ ተቃውሞም ይሁን ቅሬታ የለም ሼር ካምፓኒው የጉባኤው አባል ባለመሆኑ የምንለው ነገር የለም በእኛ በኩል የፌዴሬሽን አካላት ናቸው መሳተፍ አይችሉም ብሎ ካፍ በዝርዝር የከለከለው የኦዲት ኮሚቴ ፣ የስነምግባር ኮሚቴ፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላትን ነው ከዚያ ውጪ ማንንም አይከለክልም” ያሉት አቶ ሃይሉ “የዛሬ አራት አመት ምርጫ ኮሚቴና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ መሃል ጸብ ተነስቶ መሰነጣጠቅ በመኖሩ ምክንያት ፊፋና ካፍ መጥተው ሁለቱን ወገኖች አሰናብተው ሌላ አስመራጭ ኮሚቴ ተመርጧል አሁንም እንዳለፈው አራት አመት ለመሰነጣጠቅና ለማጣላት ተሞክሮ ከሽፏል አሁንም አይደገምም አይሳካም” ሲሉ ተናግረዋል።
“ካፍና ፊፋ ሊመጡ ነው ብለን አንሰጋም ከመጡና ልክ አይደሉም ከተባለ ይቆማል ነገር ግን የሚያስቆም ነገር ሰርተናል ብለን አናምንም ያሉት የኮሚቴው ጸሀፊ አቶ መንግስቱ መሃሩ “በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደንብና ተሻሽሎ የቀረበ አዲስ የምርጫ ደንብ መሠረት የቀረቡ ዕጩዎች ህጋዊ ናቸው የሚለውን አይተን የመጨረሻውን ወስነናል የተነሳው የተገቢነት ጥያቄ ግን አያሳስበንም” ሲሉ ያለውን ሂደት አስረድተዋል።
በሂደቱ ዙሪያ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በአቶ ብርሃኑ ከበደ አማካይነት በሰጠው ምላሽ “ የህግ ሰው በሌለበት ሰዓት አንሰራም ልቀቁን ስንል ባላችሁበት ቀጥሉ ብለውን ሰርተናል በኮሚቴው ውስጥ የህግ ሰው ይኑር ይላል ነገር ግን የተቀመጠ ከልካይ ህግ ባለመኖሩ ስራውን ሰርተናል አጠቃላይ ሂደቱን ለጠቅላላ ጉባኤው የምናሳውቅ ይሆናል “ ሲሉ መልሰዋል።
ለፕሬዚዳንትነት ከቀረቡ ዕጩዎች መካከል አንዱ በነበሩት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የምርጫ ክልከላ ዙሪያ ኮሚቴው በተሰጠው ምላሽ “አቶ ገዛኸኝ የሉበትም ብሎ ምርጫ ኮሚቴ ያስቀረውን ጉዳይ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ተቀብሎ ማየት አልቻልም ደንቡም ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚያየው አስመራጭ ኮሚቴ የወሰነውን ጉዳይ ብቻ ነው ስለሚል የአቶ ገዛኸኝ ይግባኝን ለማየት አልቻልንም፣ በተገቢነት ጉዳይ የተነሳው ጥያቄ ግን የኮሚቴውን አባላት አይመለከትንም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በአቶ ገዛኸኝ ዙሪያ አስመራጭ ኮሚቴው በሰጠው ምላሽ “የሀረሪ ክልል የወከለውን ውክልና አንስቻለሁ ብሎ ደብዳቤ ላከ በህጉ መሠረት ተቀባይነት ያለው ጥያቄ በመሆኑ ውክልናው ተነሳ። እንደ ኮሚቴው በቀጥታ የተነጋገርነው ከክልሉ እንጂ ከአቶ ገዛኸኝ ጋር አይደለም ክልሉ በግልባጭ ለላከላቸው ሁሉ ውሳኔያችንን በግልባጭ አሳውቀናል፣ ኮሚቴው የዘጋውን ጉዳይ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ያላየውም ለዚህ ነው” ሲል ሂደቱን አስረድቷል።
ሁለቱም ኮሚቴዎች የተጣመራችሁ መሆኑ ፍትህ አያዛባም ወይ ለአንድ ወገን የማድላት ሂደትንስ አይፈጥርም ወይ? ለተባለው ጥያቄ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሀይሉ በሰጡት ምላሽ “ሁለቱም ኮሚቴዎች ተያያዥነት የላቸውም ግልጽነቱን ለማስፈን ብለን ነው አብረን የቀረብነው፣ ውስጣችን ምንም አይነት ሸፍጥ የለም ተለያይታችሁ መቅረብ ነበረባችሁ ካላችሁ ለወደፊቱ እንማራለን” ሲሉ ተናግረዋል።
“ፍቅር አያስፈራም መጣላት ነው የሚፈራው የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔን እንኳን የሰማነው ከመግለጫው 5 ደቂቃ በፊት ነው” ያሉት አቶ መንግስቱ “የፌዴሬሽኑ ደንብን ተመልከቱ በጣም መሻሻል ያለባቸው ህጎች አሉ የሀገር እግርኳስ የሚያሳድጉ ሰዎች ወደ ፌዴሬሽኑ የሚመጡበት መንገድ ጠንክረን መስራት አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።
ፊፋ ከ6 ወር በፊት አሳውቁ እያለ እናንተ በ4 ወር ውስጥ ማሳወቃችሁ ፊፋ ሊቀጣን አይችልም ወይ ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሃይሉ “ፊፋ ከ6 ወር በፊት የሚል ህግ ባለበት በ4 ወር ውስጥ ሲካሄድም ያውቃል፣ ከጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ አንስቶ እያንዳንዱን ጉዳይ ያውቃል ጸጉር ስንጠቃ አያስፈልግም፣ እናም መቼ ይካሄድ መቼ ይጨረስ የሚለውን ሁሉ ፊፋ ያውቃል፣ በዚህ አንሰጋም እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ ስጋት የለብንም ፊፋ ጥቃቅን ነገር እየሰነጠቀ የሚሄድ ተቋም አይደለም፣ ህግ እንዳለ አይተረጎምም የሚታዩ ጉዳዮች ከግምት የሚገቡ ነገሮችም አሉ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 /2014