ህይወት በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ ስትሰነብት ትሰለቻለች። አንዳንዴ የተለየ ጣዕም መስጠት ይገባል። ለዚህ ደግሞ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እራስን ለየት ባለ ሁኔታ ላይ ማግኘት ጥሩ ነው። በሚገጥሙን አሉታዊ ነገሮች ደጋግመን የምንቆርጠው ተስፋ ይለመልም ዘንድ፤ ተበድረንም ቢሆን አንዳንዴ ቁርጥ መቁረጥ ጥሩ ነው። ወገን እውነቴ ነው ከሌላችሁ ተበድራችሁም ቢሆን ቁረጡ፡፡ሁሌ ተስፋ ብቻ መቁረጥ አይገባም።
ሰሞኑን “ዓለም ዘጠኝ ነው፤ አስር አይሞላ” የሚለውን መፈክር ተደግፌ፤ ምን አባቱ! የሚለውን ፉከራ ራሴን አስታጥቄ ለመቁረጥ ቆርጬ ተነሳሁ። ደጋግሜ የምቆርጠው ተስፋ እስኪ አንድ ቀን እራሱን ልቁረጠው ብዬ ወሰንኩ። ቁርጥ መቁረጥ አምሮኝ፤ መቁረጥ አሰኝቶኝ ልቆርጥ አሰብኩ። እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ የኑሮ መወደድ የደቆሰኝ ደሞዝተኛ ነኝና ውሳኔውን መወሰን ቀላል አልነበረም። ጊዜ ወስጄ መከርኩ፤ ከራሴ ጋር ብዙ ታገልኩ። ላድርገው፤ አላድርገው የሚል ሙግት ገጥሜ ለመቁረጥ ወሰንኩ። እና ወደ ቁርጥ ቤት ለመሄድ ተዘጋጀሁ፡፡
ወገን ‹‹ምግብ ብቻ ሲበሉት አይጥምም›› ይባል የለ! እውነት ነው። አብረውኝ የሚቆርጡ ወዳጆቼ ትውስ አሉኝ፤ ከሰው ጋር መቁረጥን አሰብኩ። ብቻዬን ከምሆን ብዬ በዚያውም ጨዋታውም ይደምቃል። በማቀርበው ተስፋ የተሞላበት ሀሳብ ደጋግመው ተስፋ የሚያስቆርጡኝ ጓደኞቼ ሀሳቤን ነገርኳቸውና ተስማሙ፤ እናም የመቁረጥ ምኞቴን ሙሉ አደረጉት። የደሞዝ ሰሞን ነበርና ከመካከላችን ብዙም ያንገራገረ አልነበረም። በወቅቱ የፆም መግቢያ ነበርና አጋጣሚውን ልንጠቀምበት ፈልገናል።
እየተጨዋወትን ስለ ቁርጥ እያወራን አራት ኪሎ አካባቢ ከሚገኙ ቁርጥ ቤቶች አንዱ ጋር ሳናስበው ደረስን። ከመካከላችን አንዱ ጓደኛችን ቤቱን በደንብ ያውቀው ነበርና “ኧረ ጎበዝ የዚህ ቤት ዋጋ ወገብ ይቆርጣል፤ ሌላ ቤት ይሻለናል” የሚል ሀሳብ ሲያነሳ በስንት ጊዜያችን ልንቆርጥ አስበን ክፈሉ በሚሉት ገንዘብ ወሽመጣችን ከሚቆረጥ ብለን እርምጃችንን ገታ አድርገን ተያየን። በነገራች ላይ አንድ አይነት ምግብ እያቀረቡ፣ ተመሳሳይ አገልግሎት እየሰጡ ዋጋቸው የምድርና ሰማይ ያህል የሚራራቀው ንግድ ቤቶቻችን ይገርሙኛል። ያለ ምክንያት ይቆልሉታል። የሚገርመው ደግሞ እዚያ እየተጋፋ የሚጠቀም ሰው መብዛቱ። እኛ ግን የመጋፋት አቅም የሌለን ነንና ቤቱን ትተነው ወደ ሌላ ለመሄድ ወሰን፡፡
እዚያው በአጋጣሚ በቆምንበት ምን ያህል እንደምናዋጣ ተነጋገርን። ልናዋጣ ያቀድነውና ልንገባበት ያሰብንበት ቤት ዋጋ የማይቀራረብ መሆኑ ግልፅ ነበር። ወይ የእኛ ነገር፤ በሆነ አጋጣሚ እንቁረጥ ብለንም ቅናሽ ፍለጋ መንገላታት። እንዲህ ነው ኑሮ፤ ይሄ ነው መልካችን።
ትንሽ በእግር ከተጓዝን በኋላ በዋጋው መካከለኛ ነው የተባለው ቤት ደጃፍ ደረስን። ቤቱ ከሩቅ ይጣራል። ዋጋቸው በአንፃራዊነት ጥሩ ነው፤ አገልግሎታቸውም መልካም የተባለበት ቤት ነው። ፆም መያዣ ነው አላልኳችሁም? ቤቱ ገበያ ሆኗል። ሰው ይተራመሳል። አዲስ አበቤ እዚህ ነው እንዴ የተሰበሰበው ያስብላል፡፡
የቤቱ መግቢያ ላይ ‹‹ከዚህ ቁረጥ ከዚያ ጨምር›› እያለ ቀዩን ከጮማ እየመረጠ የሚያስቆርጥ ተራ እስኪደርሰው በሰልፍ መልክ ተደርድሯል። ወደ ውስጥ ዘልቀን ስንገባ በዚያ በተንጣለለ ሰፊ አዳራሽ ውስጥ እያሽካኩ የሚቆርጡ፣ ጠረጴዛቸውን በመጠጥ ጠርሙሶች ሞልተው ከስጋ ጋር የሚታገሉ ሰዎች እዚያም እዚህም ተመለከትን።
ኑሮ ተወደደ የሚለው ሰው ተደብቆ እዚህ ሊቆርጥ ነው እንዴ የመጣው ያስብላል። ልብ አድርጉ እንግዲህ ቤቱ የፍየል ቁርጥ ብቻ የሚሸጥበት ቤት ነው። የበሬ ቁርጥ ቤትማ ስፍር ቁጥር የለውም።
አንዱ ጥግ ወንበር ስበን አረፍ አንዳልን እጅግ አጭር ቀሚስ የለበሰች ቆንጆ ወጣት ሴት ቀርባን “ምን ልታዘዝ” አለችን በትህትና። ያሻንን ታዘዝን። ቆርጠን አጥቅሰን አጣጥመንም በላን። በመጨረሻም ያ ክፉ ሰዓት ደረሰ። የክፍያ ሰዓት። ለአስተናጋጅዋ ሂሳብ ሰርታ እንድታቀርብልን ምልክት ሰጠናት፤ ይዛ ስትመጣ ሁላችንም ስንት እንደሆነ ለማየት ጓጓን፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድቡ ውሀ ሲሞላና ከላዩ ላይ ሲፈስ የነበረን ጉጉት አስታወሳችሁ? የሱን ያህል ነበር ስሜቱ። በእርግጥ ሁለቱ ጉጉቶች ይለያሉ። ያኛው የደስታ ጉጉት፤ ይሄኛው ደግሞ ስጋት የሞላበት፤ ምን ያህል ይሆን የመጣብን ጉድ የሚያስብል፡፡
ገለጥ አድርጌ አይቼው ፈገግ አልኩ። በደስታ አይደለም ፈገግታዬ በአግራሞት እንጂ። መካከለኛ ክፍያው ነው ለአገልግሎቱ የተባለው ቤት ጣራውን የነካ የሂሳብ ቁልል አቀረበልን። ጎኔ ላለው ጓደኛዬ አቀበልኩትና የሚደርስብንን ማስላት ቀጠልኩ። ሂሳቡ አንድ ኪሎ የፍየል ቁርጥ 1200 ብር ይላል። አራት ጎረምሶች ነን። ጠግበን በላን ነው ያልኩት ወገን። መቼም የበላነው አንድ ኪሎ አይሆን አይደል፡። የኪሎው ብዛት ገምቱና ሂሳቡን አስሉ። ክፍያው ጥሞን የበላነው ቁርጥ ለዛ አሳጣብን፡፡
ምነው ቀድመን በነገሩንና ቀስ እያልን እያጣጣምን በበላነው ያስብላል። ወይ ጉድ! እንዲህ ኪሳችንን እንገልብጥ። እንደምንም ኪሳችን ፈታትሸን ከፍለን ወጣን። በነገራችን ላይ ቁርጥ ቤቶች ኪሎ ታዘው ሙሉ ኪሎው አይደለም ለተጠቃሚ የሚያቀርቡት። ይህንን መታዘብ ችያለሁ። ስጠይቅ የእንጀራ እና የሚሰጠው አገልግሎት የሚካካሰው በዚያ መሆኑ በጥቆማ መልክ አንዷ አስተናጋጅ ነግራኛለች። ይሄም ህገወጥነት ነው። ቁርጥ ቤቶቹ ካልተጠየቁ በስተቀር ደረሰኝ ቆርጠውም ለተጠቃሚ አይሰጡም። አንድ ኪሎ 1200 ብር የሆነው፤ ፍየልዋን ስንት ቢገዝዋት ነው? ኧረ ተዉ ነጋዴዎች። ደግሞ የምትቀሻሽቡት ነገርስ አግባብ ነው? ስንቱን አላግባብ ሰብስባችሁ ትዘልቃላችሁ ጎበዝ? አንዳንዴ በምንቀርበው ቁርጥም ተስፋ ካስቆረጣችሁን ደንበኛ ከየት ልታገኙ ነው? በልክ አድርጉት እንጂ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 /2014