የሐመር ብሔረሰብ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን በዋናነት በዞኑ ውስጥ በሐመር ወረዳ ይኖራል። ሐመሮች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ‹‹ሐመር አፎ›› በማለት የሚጠሩ ሲሆን፣ ሌሎች ግን ‹‹ ሐመርኛ›› ይሉታል። ሀመር በኦሞአዊ የቋንቋ ቤተሰብ ሥር የሚመደበው ሲሆን የብሔረሰቡ አባላት ከራሳቸው ቋንቋ በተጨማሪ የ1በና፣ የአርቦሬ፣ የካራ እና የዳሰነች ብሔረሰቦች ቋንቋዎችን በሁለተኛ ደረጃ ይናገራሉ።
የሐመር ቋንቋ ከንግግር ወይንም ከመግባቢያነት አልፎ የትምህርት ወይም የሥራ ቋንቋ ለመሆን አልበቃም።በ1999 ዓ.ም በተደረገ የሕዝብና ቤቶች የቆጠራ ውጤት መሠረትም የብሔረሰቡ ሕዝብ ብዛት 46ሺ532 መድረሱ ይታወቃል። ‹‹ሐመር›› የሚለው ቃል የብሐረሰቡ መጠሪያ ቃል በብሔረሰቡ ቋንቋ ‹‹በተራራ እና በድንጋይ መካከል የሚኖሩ፣ የተዋሃዱና የተቀላቀሉ ሕዝቦች›› የሚል ፍቺ እንዳለውና ይህም ትርጉም ታሪካዊ መሠረት እንደያዘ ከብሔረሰቡ አዛውንቶች የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሞ ዊኪፒዲያ የተሰኘ ድረ ገጽ አስነብቧል።
ይህ ትውፊት ሐመሮች ከጥንት ዘመን አንስቶ በትላልቅና ሰንሰለታማ ተራሮች መካከል የሚገኙ የተቦረቦሩ ቋጥኞች ውስጥ ይኖሩ እንደነበር የሚያመላክት እንደሆነ የመረጃ ምንጩ አትቷል።
የብሔረሰቡ አባላት ዋነኛ መተዳደሪያ ከብት እርባታ ሲሆን፣ ከዚህ ጐን ለጐን ንብ በማነብ እና በዝቅተኛ ደረጃ ደግሞ በቆሎና ማሽላ ለዕለት ፍጆታ በማምረት ኑሮአቸውን ይመራሉ። የብሔረሰቡ ታሪካዊ አመጣጥ ጥንት ከ ‹‹ካራ››፣ ከ‹‹ኦሪ›› እና ከ‹‹መርሲ›› በመጡ የተለያዩ ማህበራዊ ቡድኖች ውህደት የዛሬው የሐመር ብሔረሰብ እንደተገኘ ከብሔረሰቡ ታዋቂ ግለሰቦችና የሀገር ሽማግሌዎች የተገኘ አፍአዊ መረጃ ያስረዳል። ከእዚህ የትውፊት መረጃ እና ከላይ የተጠቀሱትን አራት መነሻ ሥፍራዎች መሠረት በማድረግ ብሔረሰቡ ውስጥ ስድስት ማኀበራዊ ቡድኖች መኖራቸውን ይናገራል።
‹‹ቶርቶሮ›› የሐመር ብሔረሰብ አባላት በአመት አንድ ጊዜ አደባባይ በመውጣት የሚያከብሩት ባህላዊ በዓላቸው ነው። የሚከበረውም በሰኔ ወር መባቻ በእሸት ወቅት ነው። በዓሉም በድግስና በጭፈራ ይከበራል። የጭፈራው ዋነኛ ተዋናዮችም ያገቡ ወጣቶች ጎልማሶችና አዛውንቶች ሲሆኑ ፣ ያላገቡ ወጣቶችና ኮረዶች ሚና ደግሞ ድግሱን በማዘጋጀትና በማስተናገድ ላይ የተወሰነ ነው። ‹‹ኢቫንጋዲ ›› የሐመር ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ብቻ የሚሳትፉበት ባህላዊ ጭፈራ ነው። ጭፈራውም በየሦስት ቀን አንዴ እያሰለሰ በሐመር መንደሮች በምሽት ጨረቃ ይካሄዳል።
‹‹ኢቫንጋዲ›› በአዝመራ ወቅት በሥራ የደከመን አእምሮና አካል ለማዝናናት ሲባል የሚደረግ ባህላዊ ጭፈራ ነው።የሐመር ወጣቶች ከማህበራዊ ሕይወት ጋር የሚተዋወቁበት አዳዲስ ባህላዊ ዘፈኖችና የአጨፋፈር ስልቶችን የሚቀስሙበት አጋጣሚ ነው። ከእነዚህ በተጨማሪ ሐመሮች የተለያዩ አጋጣሚዎችን ምክንያት በማድረግ የሚጫወቱት ‹‹ኤሬ›› የተባለ ባህላዊ ጨዋታ አላቸው።
ኤሬ ወደ ሌላ አካባቢ ወይም ወደ ዘመቻ ለመሄድ ሲታሰብ በፉከራ መልክ የሚከወን ባህላዊ ጨዋታ ነው። የሐመሮች ባህላዊ ቤት ከእንጨት የሚሠራ ሲሆን፣ ጣሪያው በሣር ይከደናል።ነብሳት በግድግዳ ላይ እንዳይራቡ ለመከላከል በሚል ግድግዳው በምንም አይመረግም። ባህላዊ ቤቱ የውስጥ ክፍሎች የሌሉት ልቅ በመሆኑ የቤት ውስጥ የመገልገያ ቁሳቁስ ከቆጥ ላይ ይሰቀላል።
በቤት ግንባታው ሂደት ዋነኛውን ሚና የሚጫወቱት ወንዶች ሲሆኑ፣ ሴቶች ደግሞ በሣር አቅርቦት ይሳተፋሉ።
የአመጋገብ ስርዓት
‹‹ሙና መቱቆ›› ወይም ኩርኩፋ፣ ‹‹ በላሽ›› ወይም በማሽላ ቂጣ፣ ‹‹ዳንጵደ›› ወይም ፎሰሴ እና ዝጉ ወይም ከማሽላና ከበቆሎ የሚዘጋጅ ቂጣ ዋነኛ የሐመሮች ባህላዊ ምግቦች ናቸው። ‹‹ፐርሴ›› (ቦርዴ) እና ‹‹አላ›› (የማር ብርዝ) ደግሞ ባህላዊ መጠጦቻቸው ናቸው። የአመጋገብ ሥርዓታቸውን በተመለከተ የቤቱ አባወራ ከሁሉም ቀድሞ ይመገባል ።
እናት በመጨረሻ ለብቻዋ የምትመገብ ሲሆን፣ አንዳንዴም ከልጆቿ ጋር ትመገባለች። ሆኖም ግን አባወራው በምንም አጋጣሚ ከመጀመሪያ ወንድ ልጁ ጋር አይመገብም፤ ይህን እንዳይፈጽም ባህላዊ ሥርዓቱ እንደሚከለክለው የብሔረሰቡ አዛውንቶች ይናገራሉ። የዚህ ብሔረሰብ አብሮ የመኖር ጥበብ ባህልን እንደ አገር ብንጠቀምበት፤ተቻችሎ ለመኖር፣ ለመከባበር፣ ለአንድነት እና ለሰላም እንዲሁም ፍትሃዊነትን ለማምጣት ይጠቅማል። አገራችን ኢትዮጵያ ከሰማንያ በላይ የሆኑ ብሔር ብሔረሶች የሚኖሩባት እንዲሁም ህዝቦቿ ያለ ምንም የዘርና የቋንቋ ልዩነት ተጋብተው እና ተዋልደው ያቆሟት ውህድ የብሔረሰቦች ስብስብ አገር ናት።
አሁን ባለንበት ወቅት እዚህም እዚያም ጊዜ እየጠበቁ የሚነሱ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ ዋልታ ረገጥ የሆኑ አስተሳሰቦች እንዲሁም «እኔ እና የእኔ ብቻ» ከሚል ግለኝነት ለመውጣት ከሐመሮች ባህል ብዙ ልንማር ይገባናል። አንደኛው የሌላውን መብት እያከበረ፣ እየተቻቻለ እና የወንድማማች መንፈስን እያዳበረ በፍቅር ለፍቅር መኖር እንደሚቻል ካሉን ወርቃማ ባህል እና እሴት ካላቸው ብሔረሰብ የሐመር ባህል አንዱ ማሳያ ነው። እኛም ያሉንን ባህላዊ እሴቶቻችንን በመጠቀም ለአገር አንድነት እና ሰላም ልንሰራ ይገባል እንላለን።
ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011