በኮሎምቢያ መዲና ካሊ ለስድስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው እሁድ በተጠናቀቀው የዓለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳትፎ አንጸባራቂ ድል ያስመዘገበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልኡካን ቡድን ከትናንት በስቲያ ወደ አገር ቤት ተመልሷል። ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች የጀግና አቀባበል ተደርጎለታል።
በአቀባበል ስነስርአቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ፣ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም ሌሎች የስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ለልኡካን ቡድኑ የአበባ ጉንጉን አበርክተዋል።
በትናንትናው እለትም ቡድኑ በክፍት አውቶብስ በተለያዩ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየተዘዋወረ ከሕዝብ ጋር ደስታውን ተጋርቷል። በስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀ መርሃ ግብርም የእውቅናና የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶለታል። በዚህም በቻምፒዮናው በ8 መቶ ሜትር የወርቅና በ1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ በማጥለቅ የጎላ ስኬት የተጎናጸፈው አትሌት ኤርሚያስ ግርማ በልዩ ሁኔታ ከመንግስት 5 መቶ ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል። በተመሳሳይ የወርቅ ሜዳሊያ ላስመዘገቡ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው መንግስት የ3 መቶ ሺ ብር ሽልማት አበርክቷል። የብር ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች የ2 መቶ ሺ ብር፣ የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ ደግሞ የመቶ ሺ ብር ተሸላሚ ሆነዋል። በቻምፒዮናው የዲፕሎማ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶች የ50 ሺ ብር ሽልማት ሲሰጣቸው በውድድሮች ተሳትፈው ምንም ውጤት ያላስመዘገቡ አትሌቶች ለተሳትፏቸው የ30 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ቡድን መሪና ሌሎች ከቡድኑ ጋር የተጓዙ የስራ ሃላፊዎች ከ75 ሺ እስከ 30 ሺ ብር ድረስ ሽልማት አግኝተዋል።
ከፌደራል መንግስት በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አ ስ ተ ዳ ደ ር ም ለስኬታማው የወጣቶች አትሌቲክስ ቡድን የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል። በዚህም የወርቅና የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው አትሌት ኤርሚያስ ግርማ የ250 ሺ ብር ተሸላሚ ሆኗል። የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች የ150 ሺ ብር ሽልማት ከከተማ አስተዳደሩ ሲበረከትላቸው የብር ሜዳሊያ ያጠለቁ የመቶ ሺ ብር፣ የነሐስ ሜዳሊያ ላሸነፉ ደግሞ የ75 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቷል።
በሽልማትና እውቅና መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ስፖርት ቀደሞ ከነበረው መቀዛቀዝ ወጥቶ በዘንድሮው አመት ውጤታማ የሆነ አንጸባራቂ ድል እየተመዘገበበት እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያ ገጽታ ከፍ ያለበትና ሕዝብንም ያኮራ ድል መመዝገቡን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ የታላላቆቻቸውን ፈለግ ተከትለው ወጣቶቹ አትሌቶች 12 ሜዳሊያዎችን አስመዝግበው በመመለሳቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። መንግስት ብቁ፣ አሸናፊና ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ረገድ ያስቀመጠው የትኩረት አቅጣጫ ስኬታማ በመሆኑ ውጤቱ እንደተመዘገበም ሚኒስትሩ አክለዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር በበኩላቸው “ኢትዮጵያና አትሌቲክስ የማይነጣጠሉና የተጋመዱ ናቸው” በማለት ይህ የውጤታማነት ጉዞ ከቀጠለ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ገልጸዋል። ለዚህም መንግስት ከአትሌቶች ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
ኮማንደር ደራርቱ ባደረገችው ንግግርም፣ እንዳለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ፌዴሬሽኑ ጣልቃ ገብነት ሳይኖርበት በመናበብ መስራቱ ለአንጸባራቂው ውጤት መመዝገብ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ተናግራለች። የአትሌቶች ተወካይ የሆነችው አትሌት መሰለች መልካሙ ለተደረገው ደማቅ አቀባበል ምስጋና በማቅረብ፣ ወጣቶቹ ያስመዘገቡት ድል በቻምፒዮናው ታሪክ ለኢትዮጵያ ትልቁ ውጤት መሆኑን አስታውሳለች። ወጣቶቹ አትሌቶች በውድድር ወቅት ከአሰልጣኞቻቸው የሚሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ በማድረግና እንደ ታላላቆቻቸው በመተባበር ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተው ስኬታማ መሆን እንደቻሉ ተናግራለች። ይህም ታዳጊዎች ላይ መሰራት እንዳለበት ማሳያ መሆኑን ጠቁማ ለወጣቶቹ አትሌቶች በቀጣይ ድጋፍና ክትትል እንዲደረግ ጠይቃለች።
የወጣት አትሌቲክስ ቡድኑ በውድድሩ ታሪክ 6 ወርቅ፣5 ብርና 1 የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብም ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል። በ19 አትሌቶች በሁለቱም ፆታ በ10 የውድድር ተግባራት ብቻ የተሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን በድምሩ በ12 ሜዳልያዎች ያስመዘገበ ሲሆን ከአንድ አትሌት በስተቀር ሜዳሊያ ያላገኙ አትሌቶች የዲፕሎማ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። ይህም ቡድኑ ከዓለም አገራት አሜሪካንንና ጃማይካን ተከትሎ 3ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ አስችሎታል።
በዚሁ ቻምፒዮና በ1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለው ወጣቱ አትሌት ኤርሚያስ ግርማ በ800 ሜትር ተጨማሪ ወርቅ በማጥለቅ በቻምፒዮናው የጎላ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆኗል። በ3ሺ ሜትር መሰናክል ወንዶች ሳሙኤል ዱጉና የወርቅ ሜዳሊያውን ሲያጠልቅ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት አትሌት ሳሙኤል ፍሬው በድንቅ ብቃት የብር ሜዳሊያውን ወስዷል።
ከባድ ፉክክር ባስተናገደው በ5ሺ ሜትር ሴቶች ውድድር መዲና ኢሳና መልክናት ውዱ በተመሳሳይ ወርቅና ብር ሜዳሊያ ሲያጠልቁ፣ በ1500ሜ ሴቶች ደግሞ በአትሌት ብርቄ ሀየሎም (4:04.27) የቻምፒዮናውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ ችላለች።
በ5ና 3ሺ ሜትር ወንዶች በአዲሱ ይሁኔና መልኬነህ አዘዝ የወርቅ፣ በ3ሺ ሜትር መሠናክል ሴቶች በሲምቦ አለማየሁ፣ በ1500 ሜትር ወንዶች በኤርሚያስ ግርማ እና በ3ሺ ሜትር ሴቶች በፅዮን አበበ የብር ሜዳሊያዎችን ያሸነፈች ሲሆን፣ በተጨማሪም በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል በአትሌት መሰረት የሻነህ የነሀስ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2014