ክብርት ፕሬዚዳንት ፣ ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የተከበራችሁ ሚኒስትሮች ፣ ከሁሉ በላይ በዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ላይ የተሳተፋችሁ ሰራተኞች እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዛሬው ዕለት በምናስጀምረው ሁለተኛው ዩኒት እና አጠቃላይ ግድቡ የስራ ውጤት እንኳን ለእድልም ፤ እንኳን ለድልም አበቃን አበቃችሁ!፡፡
በታሪክ ውስጥ ማለፍ እና ታሪክ መስራት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው ። በታሪክ ውስጥ ማለፍ እድል ነው። በታሪክ ውስጥ ማለፍ አንድ ሁነት ሲከወን ነበርኩ፤ አይቻለሁ፤ ሰምቻለሁ ፤ ብሎ መመስከር መቻል ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ታሪክ መስራት ግን እድል ብቻ ሳይሆን ድልም ነው። በመገኘት እውቀትን ፣ ገንዘብን ፣ ሃሳብን ጉልበትን በመስጠት አንድ ሁነት እንዲከወን ማድረግ ከእድል ያለፈ ድል ስለሆነ እኛ የዛሬ የኢትዮጵያ ትውልዶች አሁን በሕይወት ያለን የኢትዮጵያ ዜጎች በሙሉ የዚህ እድልም ፤ የዚህ ድልም ተቋዳሽ ስለሆንን እንኳን ደስ ያለን እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ይህንን ትውልድ ባለ እድል እና ባለድል የሚያደርገው ለአንድ ሺህ ዓመታት ሲታሰብ፤ ሲተለም ብዙዎች ሲመኙት የነበረውን ይህንን ግድብ፤ ይህንን ውሃ የመገደብ እና መጠቀም መሻት በአይኑ ያየ በእጁ የዳሰሰ እንዲሁም በእግሩ መርገጥ የቻለ ባለእድል ትውልድ ስለሚያደርገው ነው ። አባቶቻችን ተመኝተዋል ፤ አስበዋል ፤ አቅደዋል፡፡ እኛ ዛሬ ያየነውን ግን ማየት አልቻሉም፡፡ እኛ የቆምንበትም መቆም አልቻሉም፡፡ ሁሉ ቀርቶ የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ በዚህ ስፍራ አስረኛውን እና ዘጠነኛውን ዩኒት ጎን ለጎን ማየት የቻሉ ብዙ ሰዎች አልነበሩም፡፡ እና ዛሬ እዚህ የተገኛችሁ ሰዎችም በሚዲያ የሚከታተሉ ሌሎች ሰዎችም ኢትዮጵያውያን በሙሉ ባለ እድልም ፤ ባለ ድልም መሆናቸውን እንዲያስቡ እና በዚህም እርካታ እንዲሰማቸው መፈለጌን በዚህ አጋጣሚ መግለጥ እፈልጋለሁ፡፡
ሁላችሁም እንደምታውቁት ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን ከዚያም አልፎ ሕይወታቸውን የገበሩለት ፕሮጀክት ነው፡፡ ብዙ ንጹሃን ዜጎች ከጥፋታቸው ውጭ ይህ ጉዳይ ተከውኖ በዚህ መንገድ እንድናየው ሕይወታቸውን ገብረዋል። ከዚህም ባሻገር በየመንገዱ የእለት ስራቸውን ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች ስራው በዚህ ደረጃ እንዳይከናወን ከፍተኛ ተግዳሮቶች ገጥመውን ያውቃሉ ፤ መስዋዕትነት ተከፍሎ ያውቃል። የጸጥታ ተቋማት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ ዛሬ በእድል እና በድል እዚህ ስፍራ መቆማችንን አቅልለን ሳንመለከት ለላቀው ድል ደግሞ እንድንነሳ ማሳሰብ እወዳለሁ።
አባቶቻችን ይህንን ግድብ አስበዋል ፤ አልመዋል፤ ዘፍነዋል፤ ገጥመዋል ፤ ብዙ ቁጭት አስደምጠዋል። ነገር ግን እኛ ያ የታሰበውን ግድብ ከሃሳብ ወደ ተግባር ፤ ከመገድብ እና በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ከማለፍ አልፎ ዛሬ ሁለተኛውን ዩኒት ኢነርጂ ጄኔሬት ማድረግ ወደ ምንችልበት ማድረስ በመቻላችን ከተረት፣ ከዘፈን፣ ከቁጭት ፣ ከሃሳብ ፣ ከምኞት፣ ከራዕይ ተሻግሮ ሃሳቡን በተግባር ማየት እና መዳሰስ በመቻላችን ፤ ተረት የነበረውን ታሪክ ማድረግ በመቻላችን ፤ አይቻልም የተባለውን ተችሎ በማየታችን እንደዜጎች የምንኮራ ስንሆን ከዚህም በላይ ግን የአባቶቻችንን ትልም እና ፍላጎት በማሳካት ሀገራችንን በጸና መሰረት ላይ የማቆም የዚህ ትውልድ ዋነኛ ሃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ብዙ ሰዎች ለልጆቻቸው ቤት ማውረስ ይፈልጋሉ፤ ሀብት ማውረስ ይፈልጋሉ ፤ ንብረት ማውረስ ይፈልጋሉ ፤ ነገር ግን ቤት ሳይኖር ሳሎን ማውረስ አይቻልም፡፡ መጀመሪያ ስለሳሎን ለማውራት ቤት ያስፈልጋል ፡፡ ቤት ለማውረስ ደግሞ ሀገር ያስፈልጋል፡፡ ሀገር የሌለው ሰው ቤት ማውረስ አይችልም ።
እኛ ኢትዮጵያውያን የጸናች፤ የበለጸገች ሀገር ማቆየት ከቻልን በዚያ ውስጥ ያለ ሀብት ፣ ቤት ፣ ንብረት ልጆቻችን በቀላሉ ሊወርሱ እንደሚችሉ ማሰብ ያስፈልጋል። በእኛ አጥር ውስጥ ፤ በእኛ ቤት ውስጥ ፤ በእኛ ሳሎን ውስጥ የአማረ ነገር ኖሮ በሀገራችን የተመቸ ነገር ከሌለ ሙሉ ስለማይሆን ሀገርን ማጽናት ማስቀጠል፤ ሀገርን ለማበለጽግ እና ለማስቀጠል በሚደረግ ጥረት ውስጥ አቅም በፈቀደ መጠን ተሳታፊ መሆን ከሁሉም ዜጎች የሚጠበቅ ይሆናል።
ይህ በእንዲህ እያለ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ሱዳን እና ግብጽ በተደጋጋሚ እኛ ሃይል በማመንጨት ኢኮኖሚያችንን የማሻሻል ፤ በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቻችን ብርሃን እንዲያገኙ ከመፈለግ ውጭ እነሱን የመግፋት ፤ የመጉዳት ዓላማ እንደሌለን በተደጋጋሚ ገልጸናል።
ዘንድሮ ሶስተኛው ሙሊት ያረጋገጠው 22 ቢሊዮን ሜትር ኪውቢክ ገደማ ውሃ መያዝ የሚያስችል ስራ ፤ እንዲሁም ሁለት ዩኒት ጄኔሬት ማድረግ የሚያስችል ስራ ቢሰራም በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት የውሃ እጥረት እንዳያጋጥም ፤ ኢነርጂ ጄኔሬት እያደርግን ከዚያ ባሻገር ቦተም አውትሌት የሚባለው ከውጭ የሚታየው በከፍተኛ ግፊት የሚሄደው ውሃ አንድም ቀን ሳይቋረጥ እንዲሄድ የተደረገበት ዋነኛው ዓላማ ሌሎች ወንድሞቻችን መጉዳት ሳይሆን እኛ የመጠቀም ፤ የማደግ ፍላጎት ስላለን ያንን በተግባር ለማሳየት ነው።
ይህ እየፈሰሰ ያለው ውሃ ቢገደብ በአጠረ ጊዜ ውስጥ ግድቡ ውሃ ሊይዝ ይችላል፡፡ ለእነሱ የሚገባቸውን እየለቀቅን እኛ በረጅም ጊዜ ውስጥ ውሃ የምንይዘው እነሱም ሳይጎዱ እኛም ሳንጎዳ በጋራ ለመበልጸግ ፤ ለማደግ ካለን ፍላጎት መሆኑን ተገንዝበው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በንግግር፣ በድርድር ፣ በስምምነት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ከልብ አምነው ለዚያ እንዲተጉ፤ ከዚያ ውጪ ያለው ማንኛውም አማራጭ የጀመርነውን ነገር የማያስቆም እንዲሁ በከንቱ የሚያደክም መሆኑን ተገንዝበው ወደ ሰላም ፤ ወደ ድርድር ፤ በጋራ ለማደግ እንዲመጡ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ ፡፡
በዚህ ስራ ውስጥ በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸው፣ እንዲሁም በሚዲያ ባላቸው የቋንቋ ብቃት ከዚያም ባሻገር እዚህ ቦታው ላይ በመገኘት ይህንን ስራ በታቀደለት እቅድ መሰረት እንዲከወን ጥረት ያደረጉ ሰራተኞች ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ ! እንዲሁም እጅግ አድርገን እናመሰግናለን ፡፡ በእናንተ ጥረት ፤ በእናንተ ልፋት፣ በእናንተ እውቀት፣ በእናንተ ድካም ሀገራዊ ትልሞቻችን ተሳክተው ለዛሬ ስለበቃን እናመሰግናለን ! እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈለጋለሁ፡፡
በመጨረሻም የህዳሴ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን የሚሆን ፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማንም ሊያቆመው እንደማይችል ፤ ይህ የኢትዮጵያ ሲዝን በመከወን በኢክሰለንስ በመጨረስ ወደ ሚቀጥለው ሌየር የሚያድግ መሆኑን ማሳያ ነው።
በዚህ ሰዓት ሁላችሁም እንደምታውቁት ውሃ የሚፈስብትን የመጨረሻውን ወለል ስድስት መቶ ለማድረስ እንዲሁም ግራ እና ቀኝ ያለውን ስድስት መቶ አስራ አንድ ለማድረስ ታቅዶ ሲሰራ የነበረ ቢያንስ ከአስር ቀን በፊት ተጠናቋል። ባለፈው ዓመት የነበረነው ችግር እየሰራን ውሃው የቀደመን ሲሆን ዘንድሮ ግን በነበረው እርብርብ ውሃውን ቀድመን ከአስር ቀናት በላይ ቀድመን የዓመት እቅዳችን ማሳካት የቻልነው በብዙ የኢትዮጵያ ወንድ እና ሴት ልጆች ጥረት በመሆኑ ያሰብነውን ማሳካት ብቻ ሳይሆን ቀድመን ማሳካት በመቻላችን ፣በግሪን ሌጋሲም ፣ በስንዴውም ፣ በኤክስፖርቱም በጀመርነው ስራ ሁሉ የምናየው የኢትዮጵያ ብልጽግና የማይቋረጥ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም የምናየው መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑን የተገነዘብንበት፣ የተማርንበት ስለሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ብልጽግና ለሚደረገው ጉዞ የእራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥ ፤ ከአቧራ እራሱን እንዲጠብቅ አደራ እያልኩ ይህ ሁሉ እንዲከወን ፤ እንዲጨረስ ለረዳን የኢትዮጵያ አምላክ ፣ የኢትዮጵያ ፈጣሪ፣ እጅግ ከፍተኛ ምስጋና እያቀረብኩ ለሚቀጥለው ጊዜም ፈጣሪ ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿን እንዲባርክ ኢትዮጵያ ህልሟን እንዲያሳካ ፣ የኢትዮጵያን የእጅ ስራ እንዲከናውን የሁላችን ጸሎት እና ልመና እንዲሁም ምስጋና እንዲሆን እያሳሰብኩ እንኳን ደስ ያለን ፤ እንኳን ደስ ያላችሁ!
በህዳሴ የተጀመረው ድል በሁሉም ይቀጥላል፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና በጋራ እናያለን ! ብልጽግና ከተግዳሮት ውጭ አይደለም ተግዳሮቶች ይበልጥ እንድንማር ፣ እንድንበረታ፣ እንድንጠነክር የሚያደርጉ መሆናቸውን ተገንዝበን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለትልቁ ድል እና ብልጽግና እንድንቆም አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ ፤ እንኳን ደስ ያላችሁ ! እንኳን ደስ ያለን !
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014