
ኢትዮጵያና ልጆቿ ፈተናዎችን በማለፍ አሁንም ድል በድል መሆናቸውን ቀጥለዋል፤ አዳዲስ የብስራት ዜናዎች ሲሰሙ የቆዩ ሲሆን፤ ትናንት ደግሞ ሌላ አዲስ ብስራት አዳምጠዋል:: በየካቲት 2014 በዩኒት አስር ብርሃን መስጠት የጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እነሆ ትናንት በወርሃ ነሐሴ ደግሞ ዩኒት ዘጠኝ ሀይል ማመንጨት ጀምሯል:: በእዚህ ግድብ ግንባታ አሻራችሁን ያኖራችሁና እያኖራችሁ ያላችሁ መላ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ!
ኢትዮጵያውያን በቁጭት ሲያነሱት በኖሩት ዓባይ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባት ጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብርሃን ከመስጠት አልፎም ተርፎ ለተለያዩ የልማት ተግባሮች በማዋል ይህን ታላቅ ወንዝ ራት ለማድረግ ተይዞ የነበረው ራእይ እውን ማድረጉ ቀጥሏልና ኢትዮጵያውያንንና መንግስታቸውን ደግሞ ደጋግሞ እንኳን ደስ አላችሁ ቢባል አይበዛምና አሁንም እንኳን ደስ አላችሁ!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ትናንት ሁለተኛው ተርባይን የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት በጀመረበት ሥነሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ በ2014 በጀት ዓመት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተይዘው ከነበሩ ዋና ዋና እቅዶች መካከል የግድቡን ሁለት ተርባይኖች ሀይል ማመንጨት ማስጀመር አንዱ ነበር፤ ይህ እቅድ ሁለተኛውን ዩኒት ሀይል ማመንጨት በማስጀመር በስኬት ተጠናቋል:: ሌሎች በርካታ የግድቡ ስራዎችም እንዲሁ በስኬት ብቻ ሳይሆን አስቀድመውም ተከናውነዋል:: ይህም ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የያዘቻቸው እቅዶች እየተሳኩ ለመሆናቸው ሌላ ታላቅ ማሳያ ነው::
ኢትዮጵያ፤ ለተፋሰሱ ሀገሮች በተለይም ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች ሱዳንና ግብጽ በተደጋጋሚ እንዳስገነዘበችው ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምትገነባው በማገዶ እና በላምባ ጭስ እየተሰቃዩ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ ብርሃን እንዲያዩ ለማድረግ እንዲሁም ልማቷ እየጠየቀ ያለውን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው:: በግድቡ የሚያዘው ውሃ ይህን የኤሌክትሪክ ሀይል አመንጭቶ ጉዞውን ወደነዚሁ ሀገሮች ያደርጋል:: ይህንንም ማድረግ ተጀምሯል:: የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደሚሉት፤ እስከ አሁን ወደ ግብጽና የሱዳን የሚፈሰው ውሃ አልቆምም:: ይህም ጠላቶቻችን ከአስር ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ሲያስወሩት የኖሩትን ውሸት ያጋለጠም ነው::
እነ ግብጽ እንደሚሉት ኢትዮጵያ የትኛውንም ሀገር ለመጉዳት ሃሳቡ የላትም:: በትብብር ማልማት ብትፈልግም ሰሚ አላገኘችም:: ሀገሮቹን ቆማ መጠበቅ አልነበረባትምና ማንንም ሳትጎዳ በራሷ አልምታ ብርሃን ለዜጎቿ ማድረስ ጀምራለች::
ኢትዮጵያ ጥረቷና ርብርቧ መልማት ነው:: ኢንዱስትሪዎቿ፣ የኃይል ያለህ እያሉ በኃይል እጥረት ሳቢያ ከማምረት አቅማቸው ከ50 በመቶ በታች እያመረቱ፣ ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ብርሃን እየናፈቁ፣ ብርሃን ያገኙትም እየተቆራረጠባቸው አንዳንዴም ፈረቃ ውስጥ እየገቡ በመኖር ላይ መሆናቸው የማይካድ እውነታ ነው። በቀጣይ በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማትም ሆነ ዘመናዊ ግብርና እቅድ የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ ግብአት መሆኑ እየታመነበት ምንም አለ አላለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጥያቄ ውስጥ አይገባም:: ስለሆነም ሃገሪቱና ሕዝቦቿ ከ5 ሺ 150 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ከአንድ አስርት ዓመት በላይ የደከሙበት የግድብ ግንባታ ላይ የሚደረግ የትኛውም አይነት ጫናና አፍራሽ ተግባር ቦታ አይኖውም::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የዩኒት ዘጠኝ ኃይል የማመንጨት ሥራን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያን ከጉዞዋ የሚያስቆማት የለም:: ለዚህም አባባል ማሳያዎቹ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የደረሰበት ታላቅ ብርሃን የማመንጨት ምዕራፎች ናቸው::
ከግድቡ እንደሚያመነጭ ከሚጠበቀው የኃይል መጠን አኳያ አሁን ማመንጨት የተቻለው ጥቂቱን ነው:: በሀገራችን እንደ ቡና ያሉ ተክሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ፍሬ ሲያሳዩ የምስራች አሳዩ ይባላል:: የግድባችን አንድ የምስራች በመጀመሪያው ተርባይን በመነጨው ኃይል አይተናል፤ ከግድቡ እንደሚመነጭ ከሚጠበቀው 5 ሺ 150 ሜጋ ዋት አኳያ ሲታይ በሁለተኛው ተርባይን የመነጨውም የምስራች ሊባል የሚችል ነው:: ከዓባይ ወንዝ በግድቡ ማግኘት የታሰበው እስከሚገኝ ድረስ ግንባታው ተጠናክሮ ይቀጥላል:: በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ኢትዮጵያን ከዚህ ሊያቆማት የሚችል ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል አይኖርም::
ኢትዮጵያን ከጉዞዋ የሚያቆማት ምንም አይነት ኃይል ስላለመኖሩ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ቢቻልም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተከናወነ ያለው ተግባር ዋናው ማሳያ ነው:: በእርግጥም ኢትዮጵያን ከጉዞዋ የሚያቆማት ኃይል አይኖርም!
ግድቡ ኃይል ለማመንጨት ምእራፍ ሲደርስ ብዙ ተደክሞበት ነው፤ ብዙ የጠላት ሴራዎች ተበጣጥሰው ነው:: አሁንም ይሄው ነው የሚሆነው:: ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ያላችሁን የፋይናንስና ሌሎች ድጋፎች ማድረጋችሁን አጠናክራችሁ መቀጠል ይኖርባችኋል::
ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ እንደቆየች ሀገር አይደለችም:: ፈተናን እንደ ዕድል በመጠቀም ጣፋጭ ምርቶች የሚገኙባት፣ ውብ አዝመራዎች የሚታዩባት ሀገር ናት:: በቅርቡ የወጡ መረጃዎች የሚያመለክቱትም ይሄንኑ ነው::
በግብርናው ፣ በወጪ ንግዱ፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ ወዘተ ከእቅድ በላይ እድገቶች ተመዝግበዋል:: በፕሮጀክት መጓተት የምትታወቀዋን ኢትዮጵያ ተስፋ የሚያመላክቱ በተያዘላቸው ጊዜና በጀት የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የሚገኙባትም መሆን እየቻለች ነው::
ትናንት ደግሞ ሌላ ታላቅ የምስራች ሰምተናል:: ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀምሯል:: ይህ ደግሞ ለመላ ኢትጵያውያን ታላቅ የምስራች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ስኬት ሌላኛው ማሳያም ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014