በመገባደድ ላይ በሚገኘው ዓመት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እጅግ ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል። በዚሁ ዓመት በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያ ስም በብርቅዬ አትሌቶቿ አማካኝነት በተደጋጋሚ በክብር ተነስቷል። ከወራት በፊት በሰርቢያ ቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በተመዘገበው አስደማሚ ድል ከአለም ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀው የአትሌቲክስ ቡድን፤ ከወራት በኋላ ደግም በኦሪገኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ፈጽሟል።
በሳምንት ልዩነትም በ20ዓመት በታች የአለም አትሌቲክስ ኢትዮጵያ አስደናቂና ከዚህ ቀደም ከነበረው የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ከዓለም ሶስተኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች። ይህም ሲጠቃለል ኢትዮጵያ በዓመቱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ቁንጮ ሆና ማሳለፏን የሚያሳይ ነው። ይህም ስኬት በፌዴሬሽኑ ውስጥ ከአመራር ጋር ተያይዞ አንዳች የተለወጠና ጥሩ መስመር የያዘ ነገር እንዳለ አመላካች ሆኗል።
ወደ ኮሎምቢያ ካሊ ያቀናው የኢትዮጵያ ወጣት አትሌቲክስ ቡድን በውድድሩ ላይ እጅግ አበረታችና በቅርቡ ሁነኛ ተተኪ ሆኖ በዋና ዋና የውድድር መድረኮች ትልቅ ተስፍ እንዳለው የሚያረጋግጥ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። ከውጤቱ ባለፈም ኢትዮጵያ በታሪክ በየትኛውም የውድድር መድረክ አስመዝግባ የማታውቀውን ከፍተኛ የወርቅ ሜዳሊያ ቁጥር ማሳካት ችሏል። ከዚህ በበለጠ ግን ተስፋ ሰጪ የሆነው በውድድሩ ላይ ተካፋይ ከሆኑት 19 አትሌቶች መካከል 11 የሚሆኑት አትሌቶች የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ሲካተቱ 6 የሚሆኑ አትሌቶች የዲፕሎማ ደረጃ ማግኘት መቻላቸው ነው። ይህም በውድድሩ ከተሳተፉ አትሌቶች ብዛት አኳያ የተገኘው ውጤት ምን ያህል ስኬታማ ወጣት አትሌቶች እየፈሩ መሆኑን በግልጽ አመላካች ነው።
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችን እንደ ኬንያ ካሉ የዘወትር ተቀናቃኞቻቸው በላይ ሆነው ማጠናቀቃቸው አሊያም በሜዳሊያ ሰንጠረዡ አሜሪካ እና ጃማይካን የመሳሰሉ አገራት ተገዳዳሪ በመሆናቸው ብቻም አይደለም። ሩጫና የሜዳ ተግባራትን በመሳሰሉ በርካታ የውድድር አማራጮችን ይዘው የሚፎካከሩ የዓለም አገራትን በጥቂት የውድድር ዓይነቶች (በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫዎች ብቻ) ይህንን ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸው ትልቅ ስኬት ነው። በተመሳሳይ ከተሳታፊዎቹ ቁጥር አኳያ በሚያገኙት የሜዳሊያ እንዲሁም የዲፕሎማዎች ቁጥር እጅግ ስኬታማ አትሌቶች መሆናቸው ሳይደነቅ አይታለፍም።
ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ ኢትዮጵያ በመሰል ትልልቅ ውድድሮች ላይ በሚኖራት ተሳትፎ ከአትሌቶችና አሰልጣኞች አመራረጥ ጋር በተያያዘ ውዝግቦች ከዝግጅቱ አስቀድሞ ነበር የሚታዩት። በዝግጅት ወቅትም ከአትሌቶች ስነ-ምግባር ጋር በተያያዘ ቅሬታ የሚታይ ሲሆን፤ በውድድር ወቅት የሚመዘገበው ውጤት እንደ አትሌቶች ምንጭነቷ ኢትዮጵያን የሚመጥን አልነበረም ለማለት ያስደፍራል። በዚህም ምክንያት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በተደጋጋሚ ቅያሜ ተፈጥሯል።
ከዚህ አንጻር በዓመቱ እየታየ የሚገኘው ስኬት ውዝግብና አለመግባባትን በአንጻራዊነት ያስወገደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተገኘ መሆኑ እሙን ነው። ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከመነሻውም የሚታወቁበት የአብሮነትና በጋራ የመስራት መንፈስ ተመልሶ አትሌቶች በግል ከሚያገኙት ድል ይልቅ የአገራቸውን ክብር ሲያስቀድሙ ታይቷል። ይህም በቡድን ውስጥ ከፍተኛ መከባበር፣ መተሳሰብ እንዲሁም መመካከር እንዳለ አንጸባራቂ ነው። ይህ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ደግሞ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም አመራሮቹ በጥምረት እየሰሩ ባሉት መልካም ተግባር መሆኑ አያጠያይቅም።
ይህ ይበል የሚያሰኝና አርዓያነት ያለው ተግባር ይሁን እንጂ ይበልጥ ሊተኮርባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ግን አሁንም መስራት አስፈላጊ ነው። ቀዳሚ ሊሆን የሚገባው ደግሞ በአብዛኛዎቹ አፍሪካዊያን አገራት ዘንድ የተለመደው የዕድሜ ጉዳይ ነው። በእድሜ እርከን በሚደረጉ መሰል ውድድሮች ላይ ተካፋይ የሚሆኑ አትሌቶች እድሜ አሁንም አጠራጣሪ ሁኔታ የሚታይበት ነው። ከማሰልጠኛ ተቋማት የሚወጡ ታዳጊዎችን በየጊዜው እግር በእግር በመተካት እንዲሁም እንደየእድሜ እርከናቸው በማሳተፍ ከተጠያቂነት መውጣት ብቻም ሳይሆን ለሌሎች ጀማሪ አትሌቶችም እድል መስጠት አስፈላጊ ነው።
ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ እነዚህ ወጣት አትሌቶች አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ውጤታማ እንደመሆኗ እንዲሁም ወጣት አትሌቶቹ ቀጣይ የመም ተረካቢዎች እንደመሆናቸው ከውድድር አስቀድሞም ሆነ ከውድድር በኋላ የሚደረግላቸው ድጋፍና ክትትል ዝነኞቹ አትሌቶች ውጤታማ ሲሆኑ እንደሚደረግላቸውም ባይሆን እንኳን ተመጣጣኝ ሊሆን ይገባል። ወጣቶቹን ጀግኖች ዛሬ ማክበር ካልተቻለ አገርን ማስጠራት የሚችሉ ተተኪዎችን ማግኘት አዳጋች እንደሚሆንም ሊዘነጋ አይገባውም።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 4 /2014