ጉዳዩ
አቶ ዘመረ ጀማነህ ይባላሉ። የ80 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ በፍርድ ሂደት ውስጥ የተዛባ ውሳኔ ተላልፎብኝ በስተእርጅና ስለ ፍትህ እያልኩኝ ነው ይላሉ። ነዋሪነታቸውም ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ቤት ቁጥር 405 የራሳቸው መኖሪያ ቪላ ነበር። 1965 ዓ.ም ጀምሮ አብሯቸው ጋብቻ የፈፀሙት ባለቤታቸው ወይዘሮ አልማዝ አስፋው እና አራተኛ ልጃቸው ዳዊት ዘመረ በዚህ ቤት ውስጥ ነበሩ። ዳሩ ግን በሂደት የህይወት ምህዋሯ ተቀይሮ ሰለማዊ የነበረው ህይወት ተናጋ፤ አምቧጓሮ ተበራከተ።
አቶ ዘመረ እንደሚሉት፤ ያልጠበቁት የቤተሰብ ግጭት በመፈጠሩ ከቤት ለመውጣት ተገደዋል። በተለይም ደግሞ ለዚህ ሁሉ ግጭት ትልቁን ሚና ይወስዳል የሚሉት የገዛ አብራካቸውን ክፋይ ልጃቸውን ነው። በዚህም የተነሳ እርሳቸው ሻንጣቸውን ሸክፈው 1997 ዓ.ም ከቤት ወጡ። በዚህ ሁኔታ አብሮ መቀጠል ለህይወቴም ስጋት የፈጠረብኝ ስለነበር ነው ቤቱን ጥዬ የወጣሁት ይላሉ።
አቶ ዘመረ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ቤት ቁጥር 405 ከባለቤታቸው ጋር ከነበሩበት ቤት ወጥተው ወደ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጎተራ አካባቢ ካራሶሪያ አስመራ የሚባለው ፖሊስ መምሪያው አካባቢ ሌላ ቤት መኖር ጀመሩ። ምንም እንኳን ከባለቤታቸው ቢርቁም 1997 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም ድረስም የቤት ወጪ እየሸፈኑ የብቸኝነት ኑሯቸውን ቀጠሉ። ነገር ግን ከመከሰስ አልዳኑም።
ልደታ ችሎትና ፍቺ
ባለቤታቸው ወይዘሮ አልማዝ አስፋው እና የአብራካቸው ክፋይ የሆነው የጋራ ልጃቸው ዳዊት ዘመረ በጋራ ሆነው የፍቺ ጥያቄ ለልደታ ክፍለ ከተማ ማቅረባቸውን ይናገራሉ። በዚህም 1965 ዓ.ም የተፈፀመው አቶ ዘመረ ጀማነህ እና ወይዘሮ አልማዝ አስፋው ጋብቻ ሐምሌ 1ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ እንዲፈርስ ተወሰነ። በልደታ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት የ1965 ዓ.ም ጋብቻ መፍረስ ከውሳኔ ደረሰ። በዚሁ ክርክሩ ቀጥሎ በ2002 ዓ.ም ከፊል የንብረት ክፍፍል ውሳኔ ተደረገ። በፍርድ አፈፃፀሙም 24 ቀን ቆጠራ ተካሂዶ የከባድ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫ ክፍፍል ተደረገ። አቶ ዘመረ ቀደም ሲል የከባድ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫዎችን ይነግዱም ነበር። ታዲያ በክፍፍሉ ወቅት የትዳር አጋራቸው የነበሩት ወይዘሮ አልማዝ የሚገባቸውን ድርሻቸውን ወስደው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወደ ነበረ ቤታቸው አመሩ፤ በዚያው መኖርም ጀመሩ።
በ2003 ዓ.ም ደግሞ የመጨረሻው የንብረት ክፍፍል ውሳኔ ተሰጠ። በዚህም የሦስተኛ ወገን ንብረት ነው ተብሎ የነበረው ጉዳይ ላይ ወይዘሮ አልማዝ ቅር ተሰኝተው ስለነበር ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቅሬታ አቀረቡ። የሦስተኛ ወገን ንብረት ተብሎ የነበሩት ካዛንቺዝ አካባቢ የነበረ መሬትና ቤት ነበር። ይሁንና ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ሲያጣራ ከቆየ በኋላ ንብረቱ የሚመለከተው ካርታውም ሆነ ግዥው የተካሄደው በጋራ ሴት ልጃቸው መሆኑ ተረጋገጠ። ንብረቱም ሁለቱንም የማይመለከትና የሦስተኛ ወገን መሆኑን ተረጋገጠ። በዚህም ላይ የነበረው ክርክር መቋጫውን አገኘ።
አሁንም የትዳር አጋራቸው የነበሩት ወይዘሮ አልማዝ ቅሬታቸውን ይዘው ወደ ልደታ ምድብ ችሎት ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤት አሉ። እስከ 2004 ዓ.ም ክርክሩ ቀጠለ። በዚህ መሃል ግን የአራት የቤተሰብ አባላትን ግጭት በውል የተረዱ አካላት ይህን በሠላማዊ መንገድ ብትፈቱስ ብለው መከሯቸው። አቶ ዘመረም ከቤተሰብ በላይ ምን አለ፤ እርቅንስ ማን ይጠላል ሲሉ እሽታቸውን ገለፁ። በዚህም ጊዜ ሽማግሌዎች ተመርጠው ወደ እርቅ መንገድ ለመሄድ ከሥምምነት ተደረሰ።
የእርቅ ሥምምነት
ይህ ቤተሰብ መበተን የለበትም የሚሉ አካላት ወደ እርቅ እንዲያመሩ የሚጠበቅባቸውን ሥራ ጀመሩ። የዕርቅ ስምምነት መግቢያውም እንዲህ ይላል። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ፍትሃብሄር ችሎት በአንድ በኩል በወይዘሮ አልማዝ አስፋው እና በአቶ ዘመረ ጀማነህ እንዲሁም በጣልቃ ገብ ወይዘሮ ዕፀሕይወት ዘመረ መካከል ያለው የቤተሰብ ጉዳይ በሌላ በኩል በአቶ ዘመረ ጀማነህ እና በአቶ ዳዊት ዘመረ መካከል ያለው የፍትሀብሔር ክርክር በአስታራቂ የሸምጋዮች ጉባኤ ዓማካኝነት በዕርቅ እንዲጠናቀቅ ባዘዘው መሠረት ጉባኤው ባደረገው ከፍተኛ ጥረት የፈጣሪም ኃይል ተጨምሮበት ቤተሰቡ ጉዳያቸውን በዕርቅ ጨርሰው ልዩነታቸውን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ እንደሚከተለው የዕርቅ ስምምነታቸውን አድርገዋል።
አንደኛ ወይዘሮ አልማዝ አስፋው እና አቶ ዘመረ ጀማነህ ቀደም ሲል የነበራቸው ትዳር (ጋብቻ) በፍርድ ቤት የፍቺ ውሣኔ ፈርሶ የነበረ በመሆኑ እንደገና በአዲስ መልክ ሕጋዊ ጋብቻ በማድረግ በሰላም አብረው ለመኖር በሙሉ ፈቃደኝነት ስምምነት አድርገዋል። ሆኖም የቀድሞው ትዳር በፍርድ ቤት የፍቺ ውሣኔ ከፈረሰ በኋላ የባልና ሚስት የጋራ ንብረት እና ሀብት ክፍፍል አስመልክቶ የመጨረሻ የፍርድ ቤት ውሣኔ በማግኘት ክፍፍል ያልተደረገ በመሆኑ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ፍትሃብሔር ችሎት በኮድ መለያ ቁጥር 142607 በ28/11/03 በዋለው ችሎት የባልና ሚስት የጋራ ሀብትን አስመልክቶ በሰጠው ፍርድ የተጋቢዎቹ የጋራ ሀብት ናቸው ያላቸውን ንብረቶች በአንድ ላይ በማጣመር አዲስ ጋብቻ በመፈፀም አብረው ለመኖር ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የ3ኛ ወገኖች ንብረትን አስመልክቶ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሣኔ ሁለቱም ወገኖች በዚህ የዕርቅ ስምምነት በሙሉ ፈቃደኝነት መቀበላቸውን አረጋግጠዋል።
በመሆኑም የጋራ ንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ 115327 ያለው የይግባኝ ክርክር በዚህ የዕርቅ ስምምነት መሠረት እንዲዘጋ ስምምት ላይ ተደርሷል።
ሁለተኛ በአቶ ዘመረ ጀማነህ እና በአቶ ዳዊት ዘመረ መካከል ያሉት የፍትሃብሔር ክርክሮች አቶ ዳዊት ዘመረ በወላጅ አባቱ ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ላደረሰባቸው ጉዳት በማልቀስና እግራቸው ላይ ወድቆ ይቅርታ በመጠየቁ ወላጅ አባቱ ይቅርታውን ተቀብለዋል። አቶ ዘመረ ጀማነህ እና ወይዘሮ አልማዝ አስፋው ልጃቸው አቶ ዳዊት ዘመረ ከእስር በሚፈታበት ወቅት ራሱን ችሎ ከወላጆቹ ተለይቶ እንዲኖር ተስማምተዋል። አቶ ዳዊት ዘመረም እራሱን ችሎ እንዲኖር ያስችለው ዘንድ በሱ ሥም ተመዝግቦ የሚታወቀው 548ሺ500 ብር የሚያወጣ የአዋሽ ኢንሹራንስ ኢንሹራንስ እና ከሼሩ የተገኘ ዲቪደንድ h250ሺ ብር በላይ ክፍያ የተጠራቀመለት ገንዘብ በበቂ ሁኔታ ሊያቋቁመው እንደሚችል ተስማምተዋል።
በተጨማሪ አቶ ዘመረ ጀማነህ በአቶ ዳዊት ዘመረ ላይ የመሠረትዋቸው በመ/ቁ 01595 እና በመለያ ቁጥር 71986 የፍትሃብሔር ክርክሮች በዚህ የዕርቅ ስምምነት በራሳቸው ተነሳሽነት እንደሚያቋርጡ ፈቃደኛነታቸውን አረጋግጠዋል። አቶ ዳዊት ዘመረም ከቤተሰቡ እራሱን ለማስቻል የተደረገለትን ስጦታ በመቀበል የራሱን ሕይወት ከወላጆቹ ቤት በመውጣት እንደሚመራ ስምምነቱን በዚህ የዕርቅ ስምምነት አረጋግጧል።
ሦስተኛው ሁሉም የቤተሰብ አባላት ባሉበት ከልብ የመነጨ ይቅር ባይነት ባለበት ሁናቴ በሙሉ ፈቃደኝነት እና ቅንነት ይህ የዕርቅ ስምምነት የተደረገ ሲሆን ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትም የቤተሰቡ አባላት በሚገኙበት አንድ የጋራ ጉባኤ የቤተሰቡን ሕይወት ወደነበረበት የሚመልስ አንድ አጋጣሚ ለመፍጠር ጉባኤው እና ታራቂዎቹ ተስማምተዋል ይልና አምስት አስታራቂዎችና አራት ታራቂዎች ፊርማ ያለበት ሰነድ ያስረዳል። በዚህ የእርቅ ሥምምነት በርካታ የንብረትና እና ቤተሰባዊ ጉዳዮች የተገለፁ ቢሆንም ለእርቁ ስኬታማ መሆንና ቀጣይ መሆን በቅድመ ሁኔታ የተቀመጡ ነበሩ።
ያልተፈፀመው ቅድመ ሁኔታ
ከሁሉም በላይ ግን ለዕርቁ ተፈፃሚነት የሚከተሉት ነጥቦች በግልጽ ተቀምጠው ነበር ይላሉ አቶ ዘመረ። እነዚህም ቀደም ሲል ክፍፍል ተደርጎበት የነበረው ንብረት ወደቦታው ተመልሶ የጋራ እንዲሆን፤ የሦስተኛ ወገን ተብሎ የተወሰነ ዳግም ተመልሶ ጥያቄ እንዳይነሳበትና የሌላ አካል ንብረት ስለመሆኑ፤ የ1965 ዓ.ም ጋብቻ በፍርድ ውሳኔ የፈረሰ በመሆኑ በድጋሚ ጋብቻ ለማድረግ፣ አቶ ዳዊት ዘመረ እድሜው ከ40 ዓመት በላይ ስለሆነ እና ባሕሪው ለጋብቻው ዳግም መከናወን ሆነ ሌሎች የባልና ሚስት ሁለትዮሽ ጉዳዮች አስቸጋሪ በመሆኑ ተመልሶ ወደ ወላጆች እንዳይመለስ፣ እንደ አዲስ ለሚመሰረተው ጋብቻ እንቅፋት ስለሚሆን ሁኔታዎች እንዲመቻቹ የሚሉ ናቸው።
ዳዊትም የራሱን ሕይወት ይመራበት ዘንድ 550ሺ ብር የሚያወጣ ከአዋሽ ኢንሹራንስ አክሲዮን መርቀው መስጠታቸውን ይናገራሉ። እንዲሁም 250ሺ ዲቪደንድም ስለነበረው ይህን እያንቀሳቀሰ መኖር ይችላል የሚል ነው። ይሁንና እነዚህ ጉዳዮች በሙሉ ተፈፃሚ ባለመሆናቸው አቶ ዘመረ ከባለቤታቸው ጋር መቀጠል አልቻሉም። በዚህም የተነሳ ቅድመ ሁኔታዎቹ ዋጋ ቢስ ሆነዋል ይላሉ።
ታዲያ ይህ ቅድመ ሁኔታ ባለመሟላቱ በ2003 ዓ.ም ቀደም ሲል በተሰጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ንብረት ክፍፍል ለማድረግ ተስማሙ። ለዚህም ዳግም ወደ ልደታ መጀመሪያ ደረጃ ቤተሰብ ችሎት አመሩ። ችሎቱም በንብረት ላይ እግድ ጥለው ለነበሩ ድርጅቶች ትዕዛዝ እንዲሰጥና እንዲከፋፈል ደብዳቤ ፃፈ። በዚህ መሰረትም ወይዘሮ አልማዝና አቶ ዘመረ በጋራ ፊርማ ለእያንዳንዱ ተቋማት ደብዳቤ ፃፉ። የሁለቱን አመልካቾችን ሃሳብና ፍላጎት መሰረት በማድረግም የንብረት ክፍፍሉን በዓደባባይ አከናወኑ። ይህን ያደረጉ ድርጅቶችም በፊርማ እና ማህተም አረጋግጠው ለሁለቱም ወገኖች ማስረጃ ሰጥተዋል። ይህንንም ማስረጃም ለፍርድ ቤት አቅርበዋል-አቶ ዘመረ ጀማነህ። ቦሌ ከፍለ ከተማ ከሚገኘው ቤት በስተቀር ሁሉም ክፍፍል ተደረገ።
በክፍፍሉም መሰረት ወይዘሮ አልማዝ አስፋው ኮድ2-08823 ቮልስዋገን እና ኒሳን የጭነት መኪና የሆነና ሰሌዳ ቁጥሩ 2-12568 ወስደዋል። ዳሩ ግን አቶ ዘመረ የቦሌውን ቪላ ቤት ሊካፈሉ አልፈለጉም። ምክንያቱ ደግሞ የልጆቼ እናት ማረፊያ የት ይሆናል የሚለውን የሞራል ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት ስለመሆኑም ይናገራሉ። ሚያዚያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም የተፈፀመው ዕርቅ ሥምምነት ገቢራዊ ባለመሆኑም ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ግንቦት 2 ቀን 2004 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጠ። ትዕዛዙም በእርቁ ስምምነት መሰረት ይፈፀም የሚል ነበር። በዚህም ሃምሌ 2004 ዓ.ም ክፍፍል ተጀመረ። በዚህ ወቅትም በሁለቱም ጎን ንብረት ቆጠራ ተካሂዶ ክፍፍሉ ተጠናቀቀ። በዚህ ወቅትም ያረካከቡ ምስክሮች ነበሩ። ከፊል ክፍፍል ቀርቶ ወደ ሙሉ ክፍፍል አመራ።
ክስ እንደገና
አቶ ዘመረ እንደሚሉት፤ 1965 ዓ.ም ጋብቻ በ2001 ዓ.ም ፈርሶ፤ ንብረት ክፍፍሉ ደግሞ በ2004 ፍፃሜውን አገኘ። ሁለታችንም የራሳችን ሕይወት ጀመርን። ሆኖም ከ10 ዓመታት ቆይታ በኋላ አቶ ዘመረ እንደገና በወይዘሮ አልማዝ አስፋው ክስ ቀረበባቸውና ችሎት ፊት ቀረቡ። በዚህም ቦሌ የመጀመሪ ደረጃ ፍርድ ቤት ችሎት ቀርበው ክሱን አዳመጡት።
የክሱ ጭብጥም በ2004 ዓ.ም የተፈራረምነው የዕርቅ ሥምምነት ትዳራችንን ወደነበረበት መልሶታል። በመሆኑም አልተለያየንም፤ ንብረትም አልተከፋፈልንም፤ አብረንም ንብረት አፍርተናል የሚል ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን አብረን መኖር ባለመቻላችን የ1965 ዓ.ም ጋብቻ ይፍረስ የሚል ነበር።
ዳሩ ግን ይላሉ አቶ ዘመረ፤ ጋብቻችን ፈርሶ ንብረትም ተከፋፍለን ነበር። በዚህ አካሄድ የፈረሰው ጋብቻ እንዲፈርስ የሚል ነው። በዚህም የተነሳ እንዲህ ብለው ለችሎቱ አስረዱ። 1965 ዓ.ም የተፈፀመው ጋብቻ ቀደም ሲል በ2001 ዓ.ም መፍረሱንና ንብረት ስለመከፋፈላቸውም 17 መረጃዎችን አቀረቡ። እነዚህ መረጃዎችም ምስክሮች ቆመው ያከፋፈሉትና የተረካከቡበትና የተፈራረሙትን ሰነድ፤ የባንክ ቤት የክፍፍል ሰነዶችና የመሳሰሉትን ያካትታል። ይህም ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ያላገባ ሰርተፍኬት ማውጣታቸውን አስረዱ። ባለቤታቸው የነበሩት ወይዘሮ አልማዝም ቀደም ብለው ከኩነት ምዝገባ ጽህፈት ቤት ያላገባ ሰርተፍኬት ስለማውጣታቸውም ፍርድ ቤት ጭምር ቃላቸውን ሰጥተዋል፤ በሰነድም የተደገፈ ሆኖ ተገኘ።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ንብረት ሸጠዋል፤ ለውጠዋል። በእነዚህ አስር ዓመታት ውስጥ አቶ ዘመረ በርካታ የግል ንብረት ማፍራታቸውንና በሌላ የህይወት መስመር እየተጓዙ እንደነበርም ይናገራሉ። ወይዘሮ አልማዝም በክፍፍሉ የደረሳቸውን የአዋሽ ባንክ አክሲዮን ሸጠው ዕዳ መክፈያ ስለማድረጋቸውም ዋቢ አድርገው ለችሎቱ አቀርበው ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ከንብ ባንክም አክሲዮን እያንዳንዳቸውም አንድ ሚሊዮን ስለመከፋፈላቸውም አስገነዘቡ። ከንብ ኢንሹራንስም የሚገባቸውን መከፋፈላቸውን አስረዱ። ይህ በቃል የሆነ ነገር ሳይሆን በሰነድ የተደገፈ ሆኖ ተገኘ።
በዚህ የክርክር ሂደት የቦሌ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም፤ የ1965 ዓ.ም ጋብቻ ስለመፍረሱ እና የእርቅ ስምምነቱ ወደነበረበት እንደማይመልሰው አረጋገጠ። ሆኖም እርቅ ሥምምነት ሲፈረም አዲስ ጋብቻ እንደተፈፀመ ይቆጠራል ይልና፤ ስለዚህ 2004 ዓ.ም ህጋዊ ጋብቻ ከዛሬ ጀምሮ እንዲፈርስ ወስኛለሁ ሲል የ2004 ዓ.ም የተከናወነውን እርቅ ጋብቻ እያለ በመጥራት ብያኔ ሰጠ።
በዚህ ጊዜ አቶ ዘመረ ለቦሌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አሉ። የይግባኙ ፍሬ ነገርም ፍርድ ቤቱ ያልተጠየቀ ጥያቄ ላይ ምላሽ መስጠቱ አግባብ አይደለም የሚል ነው። እየተጠየቀ ያለው በ2001 ዓ.ም ስለፈረሰ ጋብቻ እና በይፋ ስለተከናወነ፤ በሰነድ ስለተደገፈ ንብረት ክፍፍል ሆኖ እያለ 2004 ዓ.ም የተደረገን የእርቅ ስምምነት እንደ ጋብቻ መቁጠሩ አግባብ አይደለም የሚል ነው።
ዳሩ ግን ወይዘሮ አልማዝም የቦሌ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተመሳሳይ ይግባኝ አሉ። እነርሱ ደግሞ ያልጠየቅነውን ጉዳይ ተፈረደልን የሚል ነበር። ጥያቄያችን 2004 ዓ.ም ጋብቻ ሳይሆን 1965 ዓ.ም ጋብቻ ይፍረስ ብለን ነው ሲሉ ነበር ይግባኝ ያሉት። ጉዳዩ ግን በዚህ ችሎት አላበቃም። ወደ ሌላ የክርክር ሂደት ተሸጋገረ።
ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት
የሁለቱ ክርክር አልበቃ በማለቱ እየተራዘመ በመሄዱ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረሰ። ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበኩሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰነውን ሽሮ እና የሥር ፍርድ ቤትን ፍርድ አሻሽሎ 1965 ዓ.ም ጋብቻ ይፍረስ ሲል ወሰነ።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጋብቻ ስላልተመሰረተ ብሎ የፈረደው ፍርድ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ደግሞ በሰበር ውሳኔ መዝገብ ቁጥር 23021 መሰረት ሁለት ባልና ሚስት ከተፋቱ በኋላ አብረው እንደባልና ሚስት ከሆኑ እንደ ጋብቻ ይቆጠራል ብሎ የወሰነው አመክንዮ አድርጎ አቀረበ።
ይሁንና ይላሉ አቶ ዘመረ መዝገብ ቁጥር ‹‹23021›› ከእኔ ጉዳይ ጋር አንዳችም አይገናኝም። የተጣመመ ትርጉምና ሂደት ነው። በዚህ መዝገብ የተወሰነው ውሳኔ ንብረት ባልተከፋፈሉ ሁለት ግለሰቦች መካከል ስለላው ጉዳይ የሚያወራ እንጂ ለዚያውም ደግሞ ለአራት ወራት ስለተለያዩ ግለሰቦች እንጂ የእኔን ጉዳይ የሚዳስስ አይደለም ሲሉም ያስረዳሉ። ‹‹እኔ ጋብቻችን ስለመፍረሱ ማስረጃ ያለኝ፤ ንብረት በገሃድ የተከፋፈልኩ፣ ሁለታችንም ያላገባ ሰርተፍኬት ያወጣን›› ሆኖ ሳለ የማይገናኝ የውሳኔ መዝገብ መጠራቱ ፍርድ ስለመጣመሙ ሁነኛ ማስረጃ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ታዲያ በዚህ ሂደትና ፍርድ አመኔታ ያጡት አቶ ዘመረ ጀማነህ ወደ ሰበር ችሎት ለማምራት ወሰኑ።
የሰበር ችሎት
የክርክር ሂደቱ ከሥር ፍርድ ቤት ጀምሮ ጠቅላይ ፍርድ ቤትንም አልፎ ወደ ሰበር ችሎት ደረሰ። አቶ ዘመረም ሰበር አጣሪ ችሎት ያቀረቡት ቅሬታና አቤቱታ ወደ ሰበር የሚያስኬድ ነው በማለት ሦስት ዳኞች ጉዳዩን መርምረው ወደሚመለከተው አካል አሳለፉት። በዚህ ክርክር ሂደት የፍትሃብሄር ህግ ከ1731 እስከ 1733 በጋብቻ ውል መሰረት ታይቶ መፈረድ አለመፈረዱ ይታይ የሚለውንም መርምሯል። በዚህ የክርክር ሂደት የአቶ ዘመረ ጉዳይ ሰበር መቅረቡ ግድ ሆነ።
በሰበር ችሎት አምስት ዳኞች ተሰይመው ጉዳዩን ግራ ቀኝ መርምረናል ሲሉ አሳወቁ። ፍርዱን አፅንተናል ሲሉም ደመደሙ ይላሉ። በዚህም የሰበር ውሳኔ ከታች ጀምረው የተበላሹ ውሳኔዎች ጠልቀው ምርምር ሳይደረግባቸው ተወሰነ ይላሉ። ተስፋ ያደረኩበት ሰበር ቅስሜን ሰብሮኛል፤ አግባብም ያልሆነ ፍርድ ፈርዶብኛል ሲሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፈረደኝ ሲሉ አቤት ይላሉ።
አቶ ዘመረ እንደሚሉት፤ ህግ ስለመጣሱ ባመለከትም፤ ፍርድ ስለመጣመሙም ማስረጃ ጭምር ባቀርብም ምንም ሰሚ ማጣቴ ያሳዝናል ባይ ናቸው። በሁሉም ክርክሮችና ችሎቶች ብሎም የፍርድ ሂደት ውስጥም ቢሆን ጋብቻችን ስለመፍረሱ የሚያስረዱ በርካታ ሰነዶች ቀርበው ሳለ፤ የንብረት ክፍፍል ስለመደረጉም ህጋዊ ማስረጃዎች ቀርበው እያለ የተሰጠው ፍርድ ከምን መረጃ የመነጨ ነው ሲሉም ይጠይቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ በፍርድ ቤት ሲቀርቡ የነበሩ ምስክሮች ጥቅም ፈላጊ የሆነው ዳዊት ዘመረ የተባለ ልጃቸውና ሌላኛው ደግሞ ስለ ጉዳዩ ምንም መረጃ የሌለውና አሜሪካን አገር 30 ዓመት በላይ የኖረ ግለሰብ ሲሆን በእነዚህ ላይም ተቃውሞ ባሰማም ሰሚ አጣሁ ባይ ናቸው። ሌላው ደግሞ የእኔን አምስት ምስክሮች ለመስማትም ፈቃደኛ አለመሆኑ ፍትህ ወደየት እየሄደ ነው ስል እንድጠይቅ፤ በአገሬም የፍትህ ሥርዓት ላይ ትልቅ ጥያቄ እንዳነሳ ያደርገኛል ይላሉ። በተለይም የማስረጃ ምዘና በአግባቡ ከማየት አኳያ ትልቅ በደል እንደተፈፀመብኝ አገርና መንግስት ይወቅልኝ ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰማሉ።
የአቶ ዘመረ ጥያቄዎች
ንብረት በውል ስለመከፋፈላችን በሁለታችን ወገን ሽማግሌዎች በፊርማቸው አረጋግጠዋል። በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት ቦሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ቤት ቁጥር 405 ውጪ ሁሉንም ስለመከፋፈላችን በፊርማችን አረጋግጠን ሳለን እንደምን ዳግም ንብረት ተከፋፈሉ ይባላል፤ ለመሆኑ የእኔን ድርሻ ለሁለተኛ ጊዜ ሳካፍል ለህሊናስ እንደምን መፍረድ ይቻላል የሚለውን ጥያቄ ያነሳሉ። ሌላኛው ጥያቄያቸው ሁለታችንም ያላገባ ሰርተፍኬት ለፍርድ ቤት አቅርበን አልተፋታችሁም ሲባል ግራ አያጋባም ሲሉም ይጠይቃሉ። በባንክ ያለውን ገንዘብም ባንኮች ራሳቸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት ማከፋፈላቸውን እየተገለፀ እንዴት ድጋሚ የንብረት ክፍል ይደረግ ይባላል ሲሉም በአግራሞት ይጠይቃሉ። በዚህ የፍርድ ሂደት ሀቄን አጥቻለሁ፤ ፍርድ ተዛብቶብኛል፤ ሰበርም ቅስሜን ሰብሮኛል ሲሉ ሂደቱ የሚያሳምም ፍርዱም ሚዛን ያልጠበቀ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
ከአዘጋጁ
የዝግጅት ክፍላችን ከዚህ የፍርድ ሂደት ጉዳይ ጋር ተያይዞ ለሚመጡና በመረጃና ማስረጃ የተደገፉ የሌላ ወገን ሐሳቦችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 4 /2014