ከሻሻመኔ ከተማ ወደ ሐዋሳ በሚወስደው መንገድ ላይ በግምት ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንገኛለን። ወደ አንድ ሰፊ ግቢም አመራን። በሥፍራው እንደደረስን የመጣንበትን ጉዳይ አስረድተን እንድንጨዋወት ብንጠይቃቸው የግቢው ባለቤት በቀላሉ በጀ የሚሉ አልነበሩም።
«ከዚህ በፊት በርካታ ሰዎች እየመጡ ካሜራቸውን ደቅነው ይሄዳሉ እንጂ ምንም ሲሠሩ አላየሁም፤ እኔም ተጠቃሚ አልሆንኩም» የሚለው ደግሞ ዋንኛ ምክንያታቸው ነው። ከበርካታ መለማመጥ በኋላ ተግባብተን ቃለምልልስ ማድረግ ጀመርን። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው አመራን። አቶ ገመዳ ባይሶ ይባላሉ። ለ40 ዓመታት ያለመታከት ዋሻ ቆፍረዋል።
ዋሻውን ለመቆፈር የአንዲት ቀን ህልም መነሻ ሆናቸዋለች። ለስድስት ወራት በተከታታይ በየ15 ቀኑ ህልም ይመላለስባቸው እንደነበር ያስታወሳሉ። ከዚያም ለአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ። ግማሹ ግራ በመጋባት ያዳምጣቸው እንጂ ነገሩ ገዝፎ አልታያቸውም። ጥር 21 ቀን 1971 ዓ.ም ግን የቁርጥ ቀን ሆነች።
በእርሳቸው እምነት ያቺ ውድቅት እርሳቸውን ታሪክ እንዲሠሩ፤ ሌሎችም በታሪካቸው እንዲደመሙ በልዩ ሁኔታ የተቸረቻቸው ቀን ናት። ያኔ ‹‹ሀ›› ብለው ዋሻ መቆፈር ሲጀምሩ 22 ዓመታቸው ነበር። በዚህ ዕድሜያቸው ሁለት ልጆች ነበራቸው።
በእርግጥ አሁንም ቢሆን ጥር 20 ቀን 1971 ዓ.ም ምሽት በተለይም የዕኩለ ሌሊቷ መልሳ መላልሳ በአዕምሯቸው ሽው እልም፤ በምናባቸው ድቅን ትላለች። የዋሻው ባለቤትና ቆፋሪው አቶ ገመዳ ባይሶ የቆፈሩትን ዋሻ ስያሜ ‹‹ደነባ ዋሻ›› ብለውታል። ለ15 ተከታታይ ዓመታትም ብቻቸውን ቆፍረዋል።
«ለምን ትደክማለህ?»ብሎ ከመጠየቅ ውጪ አንድም ሰው ላግዝህ የሚላቸው አላገኙም ነበር። እርሳቸው ግን ተስፋ አልቆረጡም፤ ዋሻውን መቆፈሩን ተያያዙት። ከ15 ዓመታት በኋላ ግን ገንዘብ ሲያገኙ እቅድ እያወጡና ከአጠገባቸው ሆነው እያሳዩ፤ የጉልበት ሠራተኛ ቀጥረው አሠርተዋል።
በወቅቱ በአካባቢው ለእንስሳትም ሆነ ለሰዎች የመጠጥ ውሃ እጥረት ስለነበርም ውሃ አፍልቀው የአካባቢውን ሰው ጥም ቆርጠዋል። በሁለት አህዮቻቸው ውሃውን እያዞሩ ሸጠው ጉድጓድ ለሚያስቆፍሩበት ይከፍሉ ነበር። ዋሻ ቆፋሪው አቶ ገመዳ ዛሬ 62 ዓመት ሆኗቸዋል።
በሻሸመኔ ባህል እና ቱሪዝም ልኬት መሠረት፤ ዋሻው በአጠቃላይ ውስጣዊ ስፋቱ 250 ካሬ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ ዋሻው የተቆፈረው ውስጡ መሬት ለመሬት 155 ሜትር ነው። በውስጡ አልጋ፣ መኝታ ክፍሎች፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ እርቅና ሠላም የሚካሄድባቸው ስፍራዎች፣ የአባ ገዳ መቀመጫ፣ መዝገብ ቤት፣ ፀሎት ቤትና የመሳሰሉ ክፍሎችን ያካተተ ነው።
ዋሻው ፊልም ለመሥራት፣ የዘፈን ክሊፖችን ለመቅረፅ ምቹ ሥፍራ ቢሆንም የሚመጡት አካላት በጣም ጥቂቶች ናቸው። ወደ ሐዋሳ የሚወስደውን የአስፋልት መንገድም ውስጥ ለውስጥ አቋርጠው ዋሻ ለመሥራት ቢያስቡም ለመንገድ ደህንነት ሲባል ተከልክለዋል። ዋሻ ቆፋሪው በበኩላቸው፤ እስከአሁን የቆፈርኩት ዋሻ አንድ ሄክታር ተኩል ይሸፍናል ይላሉ።
አቶ ገመዳ ትዳራቸው እንደ ጉድጓድ ቁፋሮው ውጣ ውረድ የበዛበት ሆኗል። ከሁለት ሚስቶቻቸው 22 ልጆች አሏቸው። የሚገርመው ደግሞ ከአንደኛው ሚስታቸው ከወለዷቸው መካካል አራት ልጆች ሞተዋል፤ ከሁለተኛ ሚስታቸው ከወለዱት ውስጥም አንዲሁ አራቱ ሞተዋል። የልጅ ልጆቻቸውን ጨምረው ከአስፋልት ማዶ ለማዶ በግራ እና ቀኝ የሚኖሩ 50 ቤተሰቦች አሏቸው። በሹፍርና፣ በንግድና ግብርና ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ልጆች አሏቸው።
የተወሰኑት የቤተሰባቸው አባላት በሥራው ደስተኛ ቢሆኑም የተወሰኑት ግን ሰፊ መሬት በዋሻ ቁፋሮ ስለዋለ ከእርሻ ነፃ መሆኑ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል። ኑሮ በተወደደበት፤ ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት ዘመን ይህን ያክል መሬት ማረሻ ሣይነካው ፆም ማደሩ አልተዋጠላቸውም። እናም ይህ ዋሻ መቆፈር ይቅር ሲሉ አባታቸውን ተማፀኑ። አባታቸው አሻፈረኝ አሉ።
ኋላ እሰጣ ገባው እየጦዘ የክስ ዶሴ ተመዘዘባቸው። አቶ ገመዳ ተናደዱ። ወዲህ ግን የልጆቻቸው አቤቱታ እውነታውን ሲሩዱ ጋብ አሉ። ለጊዜውም ዋሻ መቆፈሩንም ጋብ አደረጉት። ታዲያ ፍርድ ቤትም «ቤተሰብዎን መንከባከብ ይገባል» ሲል ወሰነባቸው። በአገሬው ደንብ መሰረት በሽማግሌ እርቅ ፈፀሙ። ከዋሻ ጉብኚዎች የተገኘችውን ገንዘብ ተካፍለው እንዲጠቀሙ ተወሰነ። አሁን በዚህ ሁኔታ እየኖሩ ነው። በአማካይ በቀን ከ50 እስከ 100 ብር ያገኛሉ።
ምንም እንኳን ዋሻ ቆፋሪው አዛውንት ብዙ ቢያስቡም የሚነቅፋቸው አልጠፋም። «ሰው እርሻ አርሶ፤ ለመንግሥት ግብር ይከፍላል። ይህ ሰው ደግሞ መሬቱን ፆም እያሳደረ ጉልበቱን ለመሬት ይገብራል» እያሉ ከትዳር አጋራቸው ጋር ለማቃቃርም ሞክረው ነበር፤ ግን አልተሳካም። ወዲህ ደግሞ የእርሳቸውን ሃሳብ ተከትለው ዋሻ ለመቆፈር ብሎም ከከርሠ ምድር ውሃ ለማፍለቅ የተነሳሱትም በርካቶች ነበሩ። ግን ከአራት ሜትር በላይ መቆፈር አልቻሉም።
እንዲያው ‹‹የአንተ ብርታት፤ ከፈጣሪ የተቸረ ነውና›› በርታ እንዳሏቸውም ያስታውሳሉ።
አቶ ገመዳ ከራሳቸው ጥረት በተጨማሪ የመንግሥት እገዛ ፈልገው ያውቃሉ። ኃይለኛ ጎርፍ በ2010 ዓ.ም ቀጥታ ወደ ዋሻቸው የሚያስገባውንና በራሳቸው አቅም የደለደሉትን የእንጨት ድልድይ ድምጥማጡን አጠፋው። ታዲያ ለተሽከርካሪዎችም ሆነ ለእግረኞች ወደ ግቢው ለመግባት አስቸጋሪ ሆነ።
ድልድዩ ጥሩ መሸጋገሪያ እንዲሠራላቸው ቢጠይቁም ጆሮ ዳባ ልበስ አሏቸው። በወቅቱ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ በአካል ቦታውን ጎብኝተው እገዛ እንዲደረግ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ጠብ የሚል ነገር አላገኙም። የሻሸመኔ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤትም ብዙ ሊያግዛቸው ጥረት አድርጓል፤ ጥረቱ እንደተፈለገው ፍሬ ባያፈራም።
ታዲያ አቶ ገመዳ ይህን ሁሉ ሲያስቡት ቁጭታቸው ይበዛል። በተለይም ከፊደል ገበታ ጋር አለመገናኘታቸው በጣም ይፀፅታቸዋል። «ብማር ኖሮ ዛሬ የት በደረስኩ ነበር» ሲሉም ያስባሉ። ቢያንስ በዘመነ ቴክኖሎጂ ይህን ዋሻ በሚገባ አስተዋውቀው ነበር። ሌላው ቀርቶ በማህበር ተደራጅተው 50ሺ ብር ወስደው አካባቢው መዝናኛ ሊያደረጉ አስበው ቢሠሩም፤ ለኪሳራ ዳርጓቸዋል። ሙሉ ለሙሉ ዋሻ መቆፈሩን ካቆሙ አራት ዓመታት ደፍኗል።
ምንም እንኳን ዋሻው 40 ዓመታት ሲቆፍሩ የነበረ ቢሆንም፤ በመገናኛ ብዙሃን ባለመተዋወቁና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት በመንፈጋቸው ሰዎች ዋሻውን መጎብኘት ከተጀመረ ገና ሦስት ዓመቱ ነው። አንድ ሰው ዋሻው ለመጎብኘት ከ10 እስከ 15 ብር ይከፍላል። እንዲህም ሆኖ ባለፈው ዓመት በአካባቢው ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ሰዎች ብዙ ነገር አበላሽተውብኛል ይላሉ። እነዚህና ሌሎች ነገሮች እየተመላለሱባቸው በቁጭት አለንጋ እየተገረፉና ነገ መልካም ይሆናል እያሉ ዛሬም ከተስፋቸው ጋር አሉ።
አሁን አቅም ባያጥረኝ ኖሮ ይላሉ አቶ ገመዳ፤ በዓለም ላይ የምንጊዜም ተወዳዳሪ የሌለው የሰው ሠራሽ ዋሻ ባለቤት ሆኜ አገሬንና አንደ ጥንት አባቶቼ ምስጢራት እፈልጋለሁ። በእርግጥ አሁንም ዋሻውን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች ‹‹እውነት አንተ ይህን በራስህ እጅ የቆፍርከው ዋሻ ነው?›› ሲሉ እጃቸውን ከአፋቸው ላይ ጭነው በአግራሞትና በጥርጣሬ መንፈስ እንደሚጠይቋቸው ነግረውናል። አንዳንዶች ደግሞ የሰውየውን ብርታት እያደነቁ ስለነገራቸው የጥንካሬ መነሻቸው፤ የብርታት ማሳያ ምንጫቸው አድርገው እንደሚያስቧቸው ይነግራቸዋል። ይሄኔ ደግሞ የበለጠ ብርታት ሆኖ ተስፋቸውን ያለመልምላቸዋል።
አቶ ገመዳ አሁን ላይ አቅማቸው ደክሟል፤ ከቤተሰብ ጋር ባለው ሁኔታም እምብዛም ደስተኛ አይደሉም። ግን ደግሞ ልባቸው እንደ አዲስ በተስፋ ያገረሽባቸዋል፤ በቃኝ ብለው ቢያስቡም ውስጣቸው እሽ ብሎ አልተቀበላቸውም። 40 ዓመታት ሙሉ ዋሻ ሲቆፍሩ ቆይተዋል። በመሃል ቁፋሮውን ያቋረጡት ጊዜ ይቆጫቸውና አንድ ቀን ብልጭ ሲልባቸው ዶማቸውን ይዘው መሬቱን ሊቆፋፍሩት፤ በአካፋው አፈሩን ሊዝቁት ያስባሉ።
ወዲህ ግን ከቤተሰባቸው የበረታባቸው ቁጣና ተቃውሞ፤ በአካባቢያቸው የሚገኙ ሰዎችም ሆነ ተቋማት እገዛ አለመኖርና እስከ ክልል ድረስ ለፍተው አጋዥ ማጣታቸው ያበሳጫቸዋል። ከምንም በላይ ግን የታሪክ አሻራ ጥለው እያለፉ ስለሆነ ይፅናናሉ።
በአቅሜ ዋሻ ቆፍሬ ዛሬን በፅናት፤ ነገን በጉጉት የሚጠብቅ አይበገሬ ትውልድ እንዲፈጠር አርአያ ከሆንኩ ቢያንስም ኃላፊነቴን እየተወጣሁ ነው። ዛሬ ባይሳካም ነገ የታሪክ አካል ሆኖ ተመዝግቦ ስሜም በዓለም የናኘ ሊሆን ይችላል የሚል ህልም አላቸው። እኛም ህልማቸው ተሳክቶ በሀገር ውሰጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ እርሳቸውን ብሎም ሀገራቸውን የሚያስጠራ ዋሻ እንዲሆንላቸው ተመኝተን ተለየናቸው።
በእርግጥ ስድስት ወራት ህልም 40 ዓመታት ሙሉ ጉድጓድ ሲቆፍር የኖረ ሰው ስለምን ብሎ የነገ ህልም አይኖረውም? ስለምንስ እጅ ይሰጣል፤ ስለምንስ ታሪክ በደማቅ ቀለም እንደሚከትበው ይጠራጠራል። ታሪክ አንድ ቀን አቶ ገመዳ ከወዴት አሉ? ማለቷ አይቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር