ከሶስት አስርት ዓመታት ባላነሰ ጊዜ በማሕበረሰብ አቀፍ ስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማሕበር ዓመታዊ ውድድሩን በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ይገኛል። ማሕበሩ ሃያ ስምንተኛ ዓመት ውድድሩን ከትናንት በስቲያ የጀመረ ሲሆን ከአስራ ሶስት ሳምንታት በላይ የተለያዩ የጤና ቡድኖችን በእግር ኳስ ውድድር የሚያፎካክር ይሆናል።
የማሕበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈራ ደንበል ውድድሩን በተመለከተ ባለፈው አርብ በአራት ኪሎ ወጣቶች ትምህርትና ስልጠና ማእከል (ወክማ) በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ በቢሾፍቱው ውድድር ለመሳተፍ ማሕበራቱ በየአካባቢያቸው የውስጥ ውድድሮችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ማሕበሩ ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት አንድ ጊዜ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮችን ካለማካሄዱ በስተቀር በሌሎቹ ዓመታት ውድድሮችን አካሂዷል። በዚህም ከውድድር ባለፈ ወደ ፌስቲቫል እያደገ መምጣቱን አቶ ተፈራ በማስታወስ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ መምጣቱን አስረድተዋል።
በውድድሩ የሚሳተፉ ማሕበራት ሁሌም በየአካባቢያቸው በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ተፈራ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ ስፖርተኞች ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰቦቻቸው ጭምር ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህም ጤናን በስፖርት እንቅስቃሴ ከመጠበቅና የመድሃኒቶች ጥገኛ እንዳይሆኑ ከማድረግ ባሻገር ቤተሰባዊ ትስስር እንዲሁም ጠንካራ ማሕበራዊ ሕይወት እንዲፈጠር ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በ1986 ዓ.ም በሁለት ቡድኖች የተጀመረው የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ ዛሬ ላይ አርባ ሁለት ማሕበራትን እያሳተፈ ይገኛል። እነዚህ ማሕበራት በየአካባቢው ከዚህ ቀደም በስፖርቱ ውስጥ ያለፉ ግለሰቦችን ያካተቱ ሲሆን ቢሾፍቱ ላይ የሚያካሂዱትን ዓመታዊ ውድድርም በሶስት የእድሜ ካታጎሪ ተከፍለው ያካሂዳሉ። ከ35 ዓመት በታች፣ ከ40 ዓመት በታችና ከ50 ዓመት በላይ እድሜ ላይ የሚገኙ የማሕበራቱ አባላት ውድድሮችን ያካሂዳሉ።
ሁሉም ውድድሮች የእግር ኳስን ሕግና ደንብ መሰረት አድርገው የሚካሄዱ ሲሆን ከአስራ ሶስት ሳምንታት በላይ በሚፈጀው ፉክክር 208 ጨዋታዎች ይከናወናሉ። በዘንድሮው ውድድር አራት አዳዲስ ማሕበራት የተካተቱ ሲሆን በመክፈቻው እለት ሃያ ያህል ጨዋታዎች በቢሾፍቱ ሰባት የተለያዩ ሜዳዎች ተከናውነዋል። እንደ አጠቃላይ ከሃያ ሺ በላይ ተመልካቾችም ይህን ውድድር ይመለከታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በውድድሩ መክፈቻ እለት አቶ ተፈራ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት፣ መንግሥት የማሕበረሰብ አቀፍ ስፖርት እንቅስቃሴን ጥቅም ተረድቶ ትኩረት በመስጠት የሕግ ማእቀፍ በማዘጋጀት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲካሄድ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመጠቆም የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማሕበርም የዚሁ አካል መሆኑን አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር ቀደም ባሉት ዓመታዊ ውድድሮቹ ከእግር ኳስ በዘለለ በሌሎች ስፖርቶች በተለይም በቤት ውስጥ ውድድሮች እንቅስቃሴ ያደርግ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተፈራ፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ከአቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ በእግር ኳስ ብቻ እንደተወሰነ ተናግረዋል። ማሕበሩ ከአባላቱ በሚያገኘው የመዋጮ ገንዘብ እንደሚንቀሳቀስ የገለጹት አቶ ተፈራ ሌሎች የገቢ ምንጮች ስለሌሉት ሴቶችን በእንቅስቃሴው ተሳታፊ ለማድረግ እንደተቸገረ አስረድተዋል። ወደ ፊት ግን ከእግር ኳስ ባሻገር ሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም ሴቶችን ተሳታፊ ለማድረግ ማሕበሩ ጥረት እንደሚያደርግ አክለዋል።
በውድድሩ መክፈቻ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት፣ የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማሕበር ባለፉት በርካታ ዓመታት በማሕበረሰብ አቀፍ ስፖርት እንቅስቃሴ አርአያ በመሆን ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። ይህ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀርም መንግሥት ለማሕበረሰብ አቀፍ ስፖርት ልዩ ትኩረት በመስጠት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲካሄድ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ይህም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን ሚኒስትር ዴኤታው ቃል የገቡ ሲሆን እንቅስቃሴውን ቀደም ብሎ የጀመረው የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማሕበር ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2014 ዓ.ም