የአስም ህመም /Introduction and Definition/
የአስም ህመም ተላላፊ ካልሆኑ የሳምባ ህመሞች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የህመሙ መገለጫ የአየር ቧንቧ መጥበብ ነው። ይህ የአየር ቧንቧ መጥበብ በራሱም ሆነ ወይንም በመድሀኒቱ ወደ ነበረበት የሚመለስ ነው። የአየር ቧንቧ መጥበብ መነሻው ከብዙ ሁኔታዎች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያለው ነው። እነዚህ የአስም በሽታ ለመከሰት መሠረት ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መካከል ዘር፣ የአኗኗር ዘይቤ እና የአካባቢ ሁኔታዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
የአስም ህመም ስርጭት / Prevalence/
በዓለማች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ከአስም በሽታ ጋር እንደሚኖር ይታመናል። የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሠረት በአሁኑ ሰዓት ወደ 235 ሚሊዮን ህዝብ በአስም በሽታ እየተሰቃየ ይገኛል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ህፃናት ናቸው።
የአስም በሽታ ምልክቶች አመጣጥ / pathophysiology/
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የአስም በሽታ የአየር ቧንቧ መጥበብ ሲሆን፤ ለዚህም መጥበብ መንስኤው የአየር ቧንቧ መቆጣት እና ማበጥ ነው። ይህን ተከትሎ የአየር ቧንቧው አየርን እንደተፈለገ ወደ ውጪ እና ወደ ውስጥ ለማስገባት አስቸጋሪ ያደርገዋል። ያን ጊዜ የአስም ምልክቶች ብለን የምንጠራቸውን ማለትም የማፈን ስሜት፣ ሳል፣ ሲር ሲር የሚል የፉጨት ድምፅ እንመለከታለን።
የአስም ህመም ምልክቶች እና ቀስቃሽ ምልክቶች / S/S and Triggers/
የአስም ምልክቶች ከታካሚ ታካሚ የሚለያዩ ሲሆን፤ የሚከሰትበት ፍጥነት፣ የምልክቱ ክብደት እንዲሁም ምልክቱ የሚቆይበት ጊዜም ከታካሚ ታካሚ ይለያያል። እነዚህም ምልክቶች በራሳቸው ከመከሰት ይልቅ ቀስቃሽ ወይንም አባባሽ ነገሮችን ወይንም ሁኔታዎች አሉት። ከእነዚህም መካከል በዋናነት ከሚጠቀሱት ውስጥ
• ለታካሚው የማይስማማ የዓየር ሁኔታ(ቀዝቃዛ አየር)
• ለታካሚው የማይስማማ ሽታ(አቧራ፣ የተለያዩ ብናኞች)
• የላይኛው የአየር ቧንቧ በኢንፌክሽን መጠቃት፣ የጨጓራ ህመም
• የስራ ቦታ ፀባይ (በአብዛኛው በፋብሪካ አካባቢ የሚሰሩ)
• አንዳንድ የመድሃኒት ዘሮች
• ሲጋራ ማጨስ
• ከፍተኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ቀስቃሽ ወይንም አባባሽ ምልክቶች ከብዙ በጥቂቱ ሲሆኑ። እነዚህን ተከትሎ የሚመጡ የአስም በሽታ ምልክቶች እነዚህ ናቸው።
• የመታፈን ምልክት(የአየር የማጣት ስሜት)
• ደረትን የመጫን ወይንም የደረት ህመም ስሜት
• ሳል(የማያቋርጥ ሳል፣ በብዛት ማታ ማታ የሚመጣ)
• በመተንፈስ ሰዓት የሚሰማ የፉጨት ድምፅ (ሲር ሲር የሚል ድምፅ)
ሃኪም ማየት የሚያስፈልግበት ጊዜ /when to visit/
አጣዳፊ እና ድንገተኛ የአስም ምልክቶች ለህይወት ከፍተኛ አደጋ ያለው ሲሆን የአስም በሽታ ያለው ሰው፣ እነዚህን ምልክቶች ወይንም ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በአስቸኳይ የህክምና ቦታ በመሄድና እርዳታ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
• በፍጥነት የሚባባስ የአየር የማጠር/የማጣት ስሜት/
• በአስም መድሃኒት ተወስዶ ምንም ለውጥ የሌለ እንደሆነ፤
• በቀላል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወይንም በተለመደ የዘወትር እንቅስቃሴ የሚፈጠር የአስም በሽታ ምልክት ያለ እንደሆነ፤
• የአስም ምልክቶች ከሌሎች ምልክቶች ጋር የተከሠቱ እንደሆነ (ማለትም ትኩሳት፣ ራስ ምታት ወ.ዘ.ተ)
የአስም ህመም ህክምና / Treatment Option/
የአስም በሽታ ከማይተላለፉ እና ዘለቂ የህመም ዓይነቶች ተብለው ከሚጠቀሱ የህመም ዓይነቶች አንዱ በመሆኑ የቅርብ የሆነ የህክምና ክትትል የሚያስፈልገው ነው። የአስም በሽታ በምልክቶች ክብደት እና ምልክቶቹ በሚቆይበት ጊዜ ለ3 የሚከፈሉ ሲሆን እነዚህም ቀላል፣ መካከለኛ፣ እና ከባድ ሲሆን ምልክቶቹ በሚቆዩበት ጊዜ ሲከፈል ደግሞ ቋሚ እና አልፎ አልፎ የሚከሠት በማለት ይከፈላል።
የአስም በሽታ ህክምና ከላይ የተጠቀሱት የአስም ህመም አይነቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ህክምናው ይደረጋል። ሁሉም የአስም ታማሚዎች መድሃኒት የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ እንደህመሙ መጠን በአፍ የሚወሰድ ታብሌት እስከ በደም ስር የሚሰጥ ህክምና ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በተጨማሪም ከፍተኛ የሆነ የአስም ህመም በተከሰተ ጊዜ ለታካሚው የኦክስጅን ድጋፍ ይደረግለታል።
የመከላከያ ዘዴዎች / Preventation/
የአስም ህመም ምልክቶች እንዳይከሰቱ ብዙ መንገዶች ያሉ ሲሆን በዋናነት ህመሙን ሊያስነሱ ወይም ሊያባብሱ ከሚችሉ ነገሮች እራስን ማራቅ። እንዲሁም አጋላጭ ነገሮቹን ማስወገድ ተገቢ ይሆናል። ለምሳሌ ከብናኞች እራስን መጠበቅ፤ የመኖሪያ ቦታን በተሻለ መጠን ምቹ ማድረግ፣ ከሲጋራ እንዲሁም ከሌሎች ጭሶች እራስን ማራቅ፣ ሌሎች መድሃኒቶችን ከመውሰድ በፊት የህክምና
ባለሙያ ማማከር፣ ከእንስሳት ገላ ወይም ብናኝ እራስን ማራቅ፤ ህመሙን ሊያባብሱ ከሚችሉ የኢንፌክሽን ክትባት ማግኘት ወ.ዘ.ተ ናቸው።
የአስም ህመም መዘዞች / Complications/
የአስም ህመም ህክምና ካልተደረገለት፤ ወይም ደግሞ በደንብ ምልክቶች እንዲፈጠሩ መከላከል ካልተደረገለት የሚከተሉትን መዘዞች ይዞ ሊመጣ ይችላል።
• በቂ እንቅልፍ ያለማግኘት እና ተዛማጅ ችግሮች፤
• በቋሚነት የዓየር ቧንቧ እንዲሁም አየር ከረጢቶች መጥበብ እና አለመለጠጥ/ ለበለጠ የአየር ማጠር መጋለጥ/፤
• ለከፍተኛ ውፍረት መጋለጥ፤
• እንዲሁም ለረጅም ጊዜ መድሃኒት ከመውሰድ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የጎንዮሽ ጉዳት ናቸው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011