አንድ ተግባር ውጤታማ እንዲሆን ተግባሩን በትክክል በሚረዳውና ለዚያ ተግባር በቂ የሆነ እውቀት፣ ከህሎትና ሙያዊ ስነምግባር ባለው ሰው መከወን ይኖርበታል። ተግባር በእውቀት ካልታገዘ ፍሬ አልባ፤ ስራ በክህሎት ካልተሟሸ ለዛ ቢስ፤ ክንውን በሙዊ ስነ ምግባር ካልታጀበም ጎዶሎ ይሆናል። ለዚህ ነው አንድ ሙያ የሙያውን ክብር በሚመጥን መልኩ መተግበርና ሙያውን ጠንቅቆ በሚያውቀው ሰው መመራት ወይም መተግበር ይገባዋል የሚባለው።
የፋሽን ዲዛይነርነት ጥልቅ ጥበብ የተላበሰ፣ ፈጠራና የነጠረ እይታ ከስሜት ጋር መላበስን የሚፈልግ ትልቅ ሙያ ነው። በእርግጥ የሙያውን ትልቅነት ተረድተው የሚገባውን ትኩረት የሰጡት አገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን አግኝተውበታል። በአንጻሩ በፋሽን ዘርፍ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ዘግይተው የተረዱ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ላይ ዘርፉ የእድገት ውስንነት ይታይበታል።
ከተሰራበት ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እና ለኢኮኖሚያዊ እድገትም ትልቅ አበርክቶ ሊኖረው የሚችለው የፋሽን ኢንዱስትሪ የሚያበረክተውን ፋይዳ ያህል ትኩረት የተሰጠው አይመስልም። የፋሽን ዲዛይን፤ ምርት በስፋትና በጥራት በማቅረብ በአገር ውስጥ ብሎም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል። በዚህም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ለማሳደግ ይቻል ዘንድ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል። ለዚህም የዘርፉን አስፈላጊነት መረዳት፣ ለእድገቱ ምን ያስፈልገዋል የሚለውን ለመለየት፣ ጥናት ማድረግና ወሳኝ የመፍትሄ እርምጃዎች መውሰድ ወደ ውጤት ያቃርባል።
የፋሽን ዲዛይን ሙያ በኢትዮጵያ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ውስንነቶች እንደሚታዩበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ለፋሽን ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ሰፊ ገበያ ያላት ኢትዮጵያ፤ ኢንዱስትሪውን አጠናክራና ትኩረት ሰጥታ መስራት ትርፋማ እንደሚያደርጋትም ይታመናል። ኢትዮጵያ ባላት ምቹ አጋጣሚ ዘርፉ የውጪ ምንዛሬ ማመንጫና ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማድረግ እየቻለች በተለያዩ ምክንያቶች ወደፊት መራመድ ተስኗታል።
ለዚህ ዘርፍ ወሳኙና ዋነኛው ተግባር መሆን የሚገባው በቂና ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት ነው። በፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎችም ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆነው የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር መሆኑን እንደምክንያት ይጠቅሳሉ። በባለሙያዎች በቂ የሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የዘርፉን ትልቅነትና ስፋት ያህል ማሰልጠኛ ተቋማት በወጉ አለመደራጀታቸውና የዘርፉ ተዋናዮችም የሙያውን ስነምግባር ያሟላ የአገልግሎት አሰጣጥ አለመከተላቸው ነው። እንደ አጠቃላይ ዘርፉ ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑ በአገር ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዳይሆን አድርጎታል።
እንደ ዘርፉ ትልቅነትና ገበያው ላይ እንዳለው ሰፊ ፍላጎት አንጻር ትኩረት ተሰቶ ቢሰራበት የሚያስገኘው ትልቅ ፋይዳ እንዳለ የምትናገረው ዲዛይነር ሜሮን ኃብተጊዮርጊስ ናት። ስልጠና የሚሰጡ ተቋማትም ሙያዊ ስልጠናዎችና ግብዓቶችን አሟልተው መቅረብ አለባቸው ትላለች። ከዚህ ጋር ተያይዞ ለዘርፉ ወሳኝ የሆኑት የፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎች ሙያቸውን ለማሳደግ ሙያዊ ስነምግባር ተላብሰው ቢሰሩ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንደሚችልም ታስረዳለች።
የፋሽን ዲዛይን ሙያ በፊት ከነበረው አንጻር የተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኝም እጅግ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት አዳጋች እንደሆነ የምታስረዳው ሜሮን፤ ሙያዊ እውቀትና ክህሎት ሳይላበሱ ራሳቸውን “ዲዛይነር ነኝ” በሚል ወደ ስራው የሚገቡ ግለሰቦች መበራከታቸውን ታስረዳለች። ይህም ሙያው እንዳይከበርና ከጅምሩ እድገት እንዳይኖረው እንቅፋት ፈጥሯል።
በሌላ በኩል ሙያተኛውን የሚያሰለጥኑ ተቋማት ቢኖሩም የሚሰጡት ስልጠና በቂ አለመሆኑን ትገልጻለች። ዋነኛ ችግር ያለባቸው ተቋማት ደግሞ የግሉ ዘርፍ እንደሆኑ በማስረጃነት ትጠቅሳለች። በቂ የሆነ ሙያዊ ስልጠና ከሚሰጡ ተቋማት የሚወጡ ባለሙያዎች ከገበያው ስፋትና ከዘርፉ ተፈላጊነት አንጻር ቁጥራቸው ውስን ስለሆነ ተጽዕኖ መፍጠር አይችሉም።
የፋሽን ኢንዱስትሪው የሚያበረክተው ታላቅ አስተጽዖ የገባቸው አገራት ለዘርፉ በሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ተጠቃሚ ሆነዋል። ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የፋሽኑ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጋ ብትሰራ ነገር ግን የፋሽን ውጤቶችን ወደ ውጪ ባትልክ አገራዊ ፍጆታዋን መሸፈን ከቻለች ትልቅ ድል መሆኑንም ዲዛይነር ሜሮን ትጠቁማለች።
ዲዛይነር ሄለን አየነው ‹‹ሄሉ ፋሽን ዲዛይን›› የተሰኘና በዲዛይኒግ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ድርጅት አላት። በዚህ ድርጅት ውስጥም ራስዋን ጨምሮ ሶስት ጓደኞችዋ ከደንበኞቻቸው የተቀበሉትን ትዕዛዝ በማዘጋጀት እንዲሁም በአዳዲስ ዲዛይኖች የተዘጋጁ አልባሳትን ለገበያ ያቀርባሉ። ሁለት ዓመታትን ሙያውን በመማር፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት ደግሞ በፋሽን ዲዛይን ባለሙያነት የሰራችው ሄለን፤ሙያው ላይ ችግር እንዳለ ትስማማለች። የባለሙያዎችን የብቃት ችግር የፈጠረውም ሙያው ለአገራችን አዲስ በመሆኑ እንደሆነ ታስረዳለች።
በገበያው ላይ ‹‹ዲዛይነር ነን›› ብለው የሚሳተፉ ግለሰቦች ሁሉ ዲዛይነር እንዳልሆኑ የምትገልጸው ሄለን፣ አንድ ሰው ዲዛይነር ለመሰኘት የሚያስፈልገውን ሙያዊ ብቃትና ክህሎት መሆኑን ትገልጻለች። እንዴት አንድ ስፌት ብቻ የሚችል ግለሰብ “ዲዛይነር ነኝ” ብሎ እራሱን ሙያተኛ ያደርጋል? በማለትም ጥያቄ ታነሳለች። ይህም ፈጽሞ ተገቢ እንዳልሆነና የዘርፉን እድገት ወደኋላ እንደሚመልሰው ሙያቸውን አክብረው ለሚሰሩት ባለሙያዎችም እንቅፋት እንደሚፈጥር ታስረዳለች። የፋሽን ዲዛይነር ነኝ ከማለታቸው በፊት ሙያተኞቹ እራሳቸውን በሙያው ላይ ብቁ ማድረግ ይኖርባቸዋል በማለትም አስተያየትዋን ትሰጣለች።
የፋሽን ዲዛይን ሙያ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ እንዲችል ባለ ሙያዋ ወሳኝ ጉዳዮች ታነሳለች። የመጀመሪያው በሙያው ላይ ተሳታፊ የሆኑ ዲዛይነሮች ለሙያው ክብር መስጠት፣ የፋሽን ዲዛይን ሙያ ዕውቀትና ክህሎት ተላብሶ የሚሰራ መሆኑን መረዳትና የስልጠና ተቋማትንም ማዘመን እንዲሁም የሚቀበሉዋቸውን ተማሪዎች በጥራት አሰልጥነው ማስመረቅ፣ ለዘርፉ መንግስታዊ ትኩረት መስጠት መሆኑን ታስረዳለች።
የሰለጠነና በስነምግባር የታነጸ ሙያተኛ በማፍራት ትልቅ ሚና ያላቸው የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቶች ናቸው። እነዚህ ውስን ትምህርት ቤቶች የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ደረጃውን በጠበቀና ጥራት ባለው መልኩ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። የልብስ ስፌት ሙያ ያላቸው ግለሰቦች ዲዛይነር ነኝ ብለው ወደስራው እንደሚገቡ የምትገልፀው ዲዛይነር ሄለን፣ አንዳንድ የልብስ ስፌት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ሲያሰለጥኑ የልብስ ስፌት ከልብስ ዲዛይኒግ ጋር እጅግ የሰፋ ልዩነት ያለው መሆኑን ለሰልጣኞቻቸው ሊያሳውቁ ይገባልም ትላለች።
የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ለሙያው እድገትና መሻሻል ወሳኝ ጉዳይ ነው። ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ የመንግስትና የግል ተቋማት ላይ በዘርፉ ትምህርትና ስልጠናዎች ይሰጣሉ። ነገር ግን በተለይ የግል የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቶች ትምህርት በጥራት መስጠት ላይ ችግር እንደሚታይባቸው ባለሙያዎቹ ይስማማሉ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም