በኢትዮጵያ አዳዲስ ባንኮች ዘርፉን እየተቀላቀሉ እንደሆነ ይታወቃል። በቅርቡም ዘርፉን ከተቀላቀሉት ውስጥ አማራ ባንክና የፀሐይ ባንክ ተጠቃሽ ናቸው። በአማራ ባንክ ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር ለሚኖረው ውድድር ራሳቸውን ከወዲሁ እንዲያዘጋጁ ጥሪ አድርገዋል።
የባንኮች ቁጥር እያደገና የቅርንጫፍ አገልግሎት መስጫቸውም እየተስፋፋ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያለው የባንክ ኢንዱስትሪ አሁን ባለበት ሁኔታ የመወዳደር አቅሙ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው። በመሆኑ ለውድድር ብቁ ይሆን ዘንድ የአገልግሎት ልህቀት ሊኖረው እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በመጀመሪያ የአገራችን ባንኮች ትክክለኛ ውድድር ምን እንደሆነ በተለይ ከአጼ ኃይለሥላሴ ወዲህ የማናውቀው ነገር ነው። የመወዳደር አቅም ሲባል ግን መለኪያው የአገልግሎት ልህቀት ነው። የአገልግሎት ልህቀት ደግሞ የሚያካትተው ሁሉንም ነገር ነው። ለአብነት ያህል በመጠን፣ በዓይነት፣ በጥራት እንዲሁም በጊዜ የሚለካው ሁሉ የአገልግሎት ልህቀት ነው። ለተገልጋዩ መስጠት የሚገባው አገልግሎት እነዚህን የተጠቀሱትን መስፈርት በማሟላት ነው።
ይህ የመጣው ከዚህ አገር ነው፤ ይህኛው እምነቱ እንዲህ ነው፤ ያኛው ደግሞ ትውልዱ ከወዲያ ነው በሚል የሚሠራ አይደለም። ባንክ ከሆነ በባንክ ሥራ ከሁሉም የተሻለ ለተጠቃሚ አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆን አለበት። በዚህም መሠረት ጥሩ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሰጥ ውድድሩ ከሚያሳድርበት ተጽዕኖ ነፃ ከመሆኑም በተጨማሪ አሸናፊ ነው። ውድድር የሚያመጣበትን ተጽዕኖ መቋቋም የሚችለው እንደእርሱ ባንክ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ቢከፈት እዚህ አገር መጥተው የሚወዳደሩት (አንዳንድ ሰዎች ይመጣሉ ብለው የሚያስቡት) ግዙፎቹን ባንኮች ነው፤ ነገር ግን እንደሱ ሳይሆን ከሁሉ አስቀድሞ ከጎረቤት አገር ከኬንያ ሊመጣ እንደሚችል መረዳት ተገቢ ነው። ከእነዚህ ቀጥሎ ደግሞ እስካሁን ድረስ ከአገራቸው ውጪ እየሠሩ ያሉ የናይጄሪያና የደቡብ አፍሪካ ባንኮች አሉ። ስለዚህ አብዛኛዎቹ ምናልባት ከሰሜን አፍሪካ፣ ከሞሮኮ ሊመጡ የሚችሉ ይኖሩ ይሆናል። እነዚህ ባንኮች አንዳንዶቹ በአብዛኛው በአፍሪካ ኢንቨስተሮች የተያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ደግሞም ዓለምአቀፍ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ይህ ማለት ካፒታሊስት ዓለም ውስጥ ያሉ እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ እና አውሮፓ አገር ውስጥ ያሉ ባንኮችም ሊመጡ ይችላሉ።
እኛ አገር ውስጥ እስካሁን ድረስ በዘርፉ እየተንጸባረቀ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው አንደኛ ውድድርን የዘርና የኃይማኖት ወይም የትውልድ ጉዳይ ማድረግ ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ይህ በአደባባይ የሚታይ ነገር መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህም አልፎ ውድድሩ የፖለቲካ መገለጫም ሆኗል ይላሉ።
‹‹እኔ ወደአገር ቤት ከመመለሴ በፊት በዚህ ጉዳይ ብዙ ሳወራ ቆይቻለሁ። አንዳንዴ ነገሩን ለማጣጣል በመንግሥት በኩል የሚጠቀሙባቸው ሁኔታዎች አሉ። እኔ ወደአገር ቤት ተመልሼ በዚህ ሥራ ውስጥ ከተሰማራሁ ወደ 30 ዓመት ገደማ ሆኖኛል። ለሦስት አስርት ዓመታት በተከታታይ ስናገር የነበረው ነገር ቢኖር አዲስ ስንቋቋም ምናልባት ለአምስት ዓመት እንዲያም ካለ ለአስር ዓመት እጅግ ይብዛ ከተባለ ደግሞ እስከ 15 ዓመት ድረስ የውጭ ተወዳዳሪዎች መጥተው እንዳይደፍቁን ትንሽ ከለላ ስጡን ብለን ነው። ይሁንና በዚህ ሁኔታ ድፍን 30 ዓመት ሊሞላን ነው። ስለዚህም የሚሰማን አጣን ይላሉ።
‹‹እኛ ያቺ አምስትም አስርም ወይም አስራ አምስትም ዓመት መንግሥት ከለላ የሚሰጥባትን ጊዜ አንደኛ ስለባንክ እውቅት፣ ስለባንክ ስልጡንነት እንድናካሂድ ነው። አንድ ባንክ ስናቋቁም ሁልጊዜ በብቸኝነት ሲሠራ ወደቆየው ወደንግድ ባንክ ሄደን የዲፓርትመንት ኃላፊ ወይም የአንድ ቅርንጫፍ ኃላፊ የሆነውን አባብለን አምጥተን ላቋቋምነው አዲስ ባንክ ሥራ አስፈጻሚ ማድረግ ነው። ነገር ግን እንደሱ ብቻ ማድረግ ሳይሆን በባንክ ሥራ በደንብ እየጎበዙ፣ እያወቁ፣ እየመጠቁ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት ነው ያለብን።›› ሲሉ ይመክራሉ።
አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ እንደሚናገሩት ከሆነ፤ እነርሱ ቀደም ሲል ሲጠይቁ የነበረው የስልጠና ሁኔታ እንዲፈጠር፣ አንዳንዶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ለባንክ ወይም ለፋይናንስ ዘርፍ ሥራ ብቁ የሚያደርግ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ ማድረግ የሚለው ነበር።
አሁን ብሔራዊ ባንክ ለውድድር ራሳችሁን አዘጋጁ የሚል ከሆነ አንዱን ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅ እያደረገ መሆን የለበትም የሚል ሀሳብ አላቸው። ሁሉንም በአንድ ዓይን እንዲያይና ለሁሉም እኩል ዕድል እንዲሰጥ ማድረግን መማር ይኖርበታል። ይህንን ቀደም ሲልም ተናግረናል። በእርግጥ ለዚህ ዓይነት ሁኔታ አገሪቱ አስቸጋሪ ናት። መንግሥት ራሱ የራሱ ባንክ አለው። ክልሎች የራሳቸው ባንኮች አሏቸው። ይህ በሆነበት ሁኔታ ብሔራዊ ባንክ እንዴት አድርጎ ነው ሁሉንም በእኩል ሊያይ የሚችለው። በጥቅሉ የማይቻል ነገር መጠየቅ ነው።
ስለዚህም የእኛን አገር ሁኔታ ያቆየነው አባጣ ጎርባጣ አድርገነው ነው። በመሆኑም ይህ ነገር እንዲህ እንዳይሆን ቀደም ብሎ አስፈላጊው ዝግጅት እንዲጀመር ነበር የተጠየቀው። ይህ ባለመሆኑ አሁን ያለንበት ቦታ ላይ ደርሰናል። አሁን ባለንበት ሁኔታ አገራችን ጥሩ ሒደት ላይ ናቸው የምንላቸው ቁንጮ ላይ የተቀመጡ ባንኮች ሦስት አራት ቢሊዮኑን እንኳን በቂ የመወዳደር አቅም የላቸውም።
ምክንያቱም የሚፈለገው ዓይነት የሰለጠነ የባንክ ባለሙያ በብዛት አያገኙም፤ የላቸውም። ልምዳቸውም ቢሆን የተወሰነ ዘመን ልምድ ነው። እስካሁንም ከአገሪቱ ውስጥ ካለው ጎጠኛ አስተሳሰብ ውስጥ ተጠቃሚዎች ናቸው። በመሆኑም ያለእሱ ጠንክረው ቆመው የውጭ ተወዳዳሪዎችን ተወዳድረው በገንዘብ አቅም፣ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ አሸንፈው ይወጣሉ ለማለት በጣም ያስቸግራል። ስለዚህ የአገራችንን ባንኮች ለውጭ ተወዳዳሪነት አላዘጋጀናቸውም።
ይህ ዝግጅት ባለመኖሩ የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ አገር ባንኮች የሚመጣባቸውን ትክክለኛ ውድድር ለመቋቋም አይቻላቸውም። ምክንያቱም ቴክኖሎጂውም፣ እውቀቱም፣ የገንዘብ ኃይሉም ወይም መጠኑም እስካሁን ድረስ የለም። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ለምን እንደዚህ ሆነ ለማለት አሁን ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ይሆናል ይላሉ።
ይሁንና መንግሥት፣ ገበያውን ለውጭ ውድድር ክፍት እናደርጋለን ብሏል። እኛ ገበያውን ከውጭ ባንኮች ዘግተንላችሁ ነው እናንተ ይህን ጠርቀም ያለ ገንዘብ ስታገኙ የቆያችሁት እያለም በማስፈራሪያ መልክ ያቀርባል የሚሉት አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፣ በዚህ ጉዳይ ግን ስህተት ናቸው ብለዋል። ስህተት ነው የማለታቸውም ምስጢር የቀድሞ ሰዎች የሚሏቸውን እያዳመጡ ነው እንጂ ባንክ ውስጥ ያለነው ሰዎች ዘግታችሁ ይህን ያህል ዓመት ጠብቁ ወይም አኑሩ ባለማለታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። እንዲያውም በባንክ ውስጥ ያሉ አካላት ቶሎ ተዘጋጅተውና ቶሎ ተወዳዳሪ ሆነው ገበያውም ተከፍቶ ማየትን ይናፍቁ እንደነበር ነው የገለጹት። ከዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ከሚመጣው የውጭ አገር ውድድር ጋር ራሳቸውን በማሰለፍ አብረው እንዲሠሩና አቅማቸውን እንዲገነቡም ፍላጎታቸው እንደነበር ይናገራሉ።
እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያው አባባል፤ ያለፈው ሁኔታ ግን ተዘግቶ የነበረው በፖለቲካ ምክንያት ነበር። በወቅቱ መንግሥት ይል የነበረው ገንዘቦች እኔ ባልኳቸውና እኔ በመረጥኳቸው አቅጣጫ እንጂ ኢንቨስተሮች በመረጡት አቅጣጫ እንዲሆኑ አልፈልግም ነው፤ ቅድሚያ የሚሆነውን ልማት የማዝበት እና የማውቀው እኔ ነኝ፤ ስለዚህ እኔ በምፈቅድበት ጊዜ ይከፈታል፤ እስከዛ ድረስ ግን እኔን የምትደግፉ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ፤ መሥራት የምትችሉትም በእዛ መልክ ነው ብሎ በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ ቆይቷል።
የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላም እንዳየነው ባንኮች እየተጠሩ ይህን ያህል ብር ለዚህ ጉዳይ እርዳታ አድርጉ፤ ይህን ያህል ብር ደግሞ ለዚህ ጉዳይ አምጡ ይባላሉ። በሩ ተከፍቶ የውጪዎቹ ባንኮችም ገብተው እና ተወዳዳሪ ብንሆን ኖሮ መንግሥት የገቡትን ባንኮች እየጠራ ይህን ያህል ብር ለዚህ ጉዳይ፤ ይህን ያህሉን ደግሞ ለዛኛው ጉዳይ ማለት ይቻል ነበር ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ። እንደዛ ማድረግ ግን በጭራሽ አይቻልም። ባንኮች ድጋፍ በሚፈልግበት ጊዜ የሚጠየቁት አገር በቀል ባንኮች በመሆናቸው ነው። ስለዚህ የባንኩ የሥራ ክፍል ለውጭ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ዓለምአቀፍ ባንኮቹ በዚህ መልኩ አይጠየቁም። በመሆኑም መንግሥት ለራሱም ሲል ነው ዘግቶት ያቆየው ይላሉ።
አሁን የባንክ ኢንዱስትሪው ለውጭ አገር ውድድር አይከፈት ማለት አይቻልም። የምንፈልገውም እንዲከፈት ነው፤ ስንጠይቅም ቆይተናል። አሁን ግን ያለንበት ሁኔታ ለዝግጅት ጊዜ በአጭሩም ቢሆን ትንሽ ስለሚያስፈልግ የውጭ ባንኮችን እዛው ውጪ ቆዩ በማለት ፈንታ በባለቤትነት መልክ ያሉ ባንኮች ውስጥ አክሲዮን እየገዛችሁ ግቡ ማለት ይቻላል። መቶ በመቶ በራሳችሁ ካፒታልና በራሳችሁ የሰው ኃይል ማቋቋም ሳይሆን በአገሪቱ ካሉ ባንኮች ጋር እየተወያያችሁና እየመረጣሁ ይበጁናል፤ አብረናቸው ልንሠራ እንችላለን ከምትሏቸው ባንኮች ጋር ካፒታል አክሲዮናቸውን በተወሰነ ደረጃ እየገዛችሁ አጋርነት ፍጠሩ ማለቱ ተመራጭ ነው። ለምሳሌ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እስከ 25 በመቶ፣ በሒደት ደግሞ እስከ 49 በመቶ ባለቤትነት መግዛት ትችላላችሁ ብሎ ሊፈቅድላቸው ይችላል። ይህ አንዱ የውጭ ባንኮችን ወደአገር ማስገቢያ ዘዴ ነው ይላሉ።
ይህ የተደረገ እንደሆነ አንደኛ የውጪ ካፒታል ይመጣል። እነዚህ የውጭ ባንኮች አገር ቤት ውስጥ ካሉት ባንኮች ጋር ባለቤትነትን ሲፈልጉ ከፍለው የሚገቡት በውጭ ምንዛሬ ነው። ስለሆነም የውጪ ካፒታል ይመጣል። እዚህ ሲመጡ ቴክኖሎጂውንና እውቀቱን ይዘው ይመጣሉ፤ ምክንያቱም ባለቤት ሲሆኑ አስተዳደር ውስጥ ይገባሉ። ስለዚህ ቴክኖሎጂውንም እውቀቱንም ይዘው ይመጣሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ በአገር ውስጥ ያሉ ባንኮች ዕድል ይኖራቸዋል፤ ለምሳሌ እስከ 49 በመቶ ድረስ ባለቤትነት ይዘው ቢቀመጡ ከአምስት ዓመት በኋላ የእስቶክ ማርኬት (ካፒታል ማርኬት) ተቋቁሞ በሥራ ላይ እንደሚሆን ተነግሮናልና የባንኮቹ ሼር እዛ ይሸጣል። ታዲያ እነዚህ ከውጭ የገቡ ባንኮች የባንኮቹን ካፒታል የበለጠ ለመያዝ ከፈለጉ በዛ መልክ ይገዙታል። ከጊዜ በኋላ መቶ በመቶም ለመያዝ ነፃነት ይኖራል ማለት ነው። በመጀመሪያ ግን በዚህ መልክ ቢገቡ ይመረጣል ባይ ነኝ። ስለዚህ አንድ ቀን ተነስተን ከዛሬ ጀምሮ መጥታችሁ በኢትዮጵያ የባንክ ገበያ ውስጥ እንዳሻችሁ ሆኑ እንዳይባል ያስፈልጋል ሲሉ ስጋታቸውን አስረድተዋል።
ከወራት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ሁለት አስርት ዓመታት ብቻቸውን የመሥራት ዕድል አጋጥሟቸው መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ዕድል ማቆየት አይቻልም፤ አገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪና ተጨማሪ ሀብት ስለሚያስፈልጋት የውጭ ባንኮች ወደአገር ቤት መምጣታቸው እንደማይቀር ይጠቅሳሉ። ስለሆነም የኢትዮጵያ ባንኮች አሠራራቸውን በማዘመን ራሳቸውን ለዚህ ውድድር ማዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበው መንግሥትም የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑንም ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባንኮቹ ያላቸው ሀብት እያደገ መምጣቱንና በአሁኑ ወቅትም 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል። በመላ አገሪቱ ያሉት የባንክ ቅርንጫፎችም ከስምንት ሺ በላይ መድረሳቸውንና ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር በ17 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል። ባንኮቹ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም 353 ቢሊዮን ብር ብድር ማቅረባቸውንም አስታውሰዋል።
በቅርቡ የአማራ ባንክ ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳሉት፤ የአማራ ባንክ ወደማህበረሰቡ በመድረስና ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻን በመሸጥ እንዲሁም ከፍተኛ የተከፈለ ካፒታል ይዞ የባንክ ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል ረገድ ቀዳሚ ነው። በቴክኖሎጂና በአገልግሎት አሰጣጥ ተወዳዳሪ እና ቀዳሚ መሆን እንዲችል ባንኩ ራሱን እንዲያዘጋጅም አሳስበዋል። ይህ ከአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ከሚታሰቡ የውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር እንደሚያስችል ያስረዳሉ። እንዲገቡ ከሚጠበቁት የውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር ትልቅ ዝግጅት ይጠብቀናል ሲሉ ተናግረው፤ ለዚህም የአማራ ባንክን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ ባንኮች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ እንደሚሉት፤ አሁን ባለንበት ሁኔታ ባንክ ለመክፈት ሕጉ የሚለው አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ነው። በአሁኑ ወቅት ይህን ካፒታል ያላሟሉ ብዙ ባንኮች አሉ። እነዚህ አምስት ቢሊዮኑን ብር ካሟሉትም ጋር ሆነ ካላሟሉት ጋር ውህደት መፍጠር ይኖርባቸዋል። ከተቋቋሙት ባንኮች ውስጥ የውጭዎቹ ባንኮች መጥተው ይገዛሉ ከተባለም ለውጭዎቹም ይሸጣሉ፤ ነገር ግን የውጭዎቹ የሚፈቀድላቸው ለመጀመሪያ ሦስት ወይም አምስት ዓመት እስከተወሰነ መቶኛ ድረስ ስለሆነ የውጭዎቹ የሚፈቀድላቸው የተሻለ የሚሆነው አቅማቸውን እያዩ አምስት ቢሊዮን መድረስ የማያስችላቸው መስሎ የታያቸው ባንኮች ከሌሎች ባንኮች ጋር እየተወያዩ አንድ ላይ መዋሃድ ነው። ይህ አፋጣኝ የሆነ አስፈላጊው ጉዳይ ነው። ለኢትዮጵያ የባንኮች ውህደት በጣም አስፈላጊ ነው። ለውጭ ገዥዎችም ትንሽ እንኳን የሚያጓጉ ሆነው እንዲታዩ ውህደት ወሳኝ ነው። ይህ በእኔ እይታ አንድ ቁም ነገር ነው ብዬ የምወስደው ነው። ከዚህ በተረፈ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅም የሚባሉት በአሁኑ ጊዜ ምናልባት ሦስት ወይም አራት ባንኮች ቢሆኑ ነው። እነዚህም ቢሆኑ ብቻቸውን አቅማቸው በቂ አይደለም። እነርሱም ራሳቸው አገር ውስጥ ካሉ ባንኮች ጋር መዋሃድ ይጠቅማቸዋል። ከውጭዎቹም ጋር ሼራቸውን በመሸጥ ከእነርሱም ጋር መቀናጀቱ ይጠቅማል።
ውድድሩን መቋቋም ያልቻሉ ባንኮች ዕጣ ፈንታቸው ሊገዛቸው ለሚችል ባንክ መሸጥ ነው። አቅም ያላቸው ባንኮች እንዲገዟቸው ማድረግ ነው። በሌላ ቋንቋ ይዘጋሉ ማለት ነው። ሌላ አማራጭ የለም።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም