በአዲስ መልክ በሚኒስቴር ደረጃ የተዋቀረው የቱሪዝም ዘርፍ ከሚያከውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል እምቅ የመስህብ ስፍራዎችን በመለየት የመዳረሻ ልማት ማከናወን ነው። በተለይ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ኋላ የቀረውን ይህን ስራ በተሻለ መልኩ በመፈፀም ኢትዮጵያ ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን አልሞ እንደሚሰራ ተነግሮለታል።
ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቀረፀ “የገበታ ለአገር” ፕሮጀክት ላይ አንድ ባለድርሻ ከመሆን ባሻገር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የራሱን እቅዶች በመንደፍ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው። የዝግጅት ክፍላችንም ከመዳረሻ ልማት ስራዎች ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎች በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙሳ ከድር ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል። መልካም ቆይታ!!
አዲስ ዘመን ፦ በ2014 ዓ.ም ቱሪዝም ሚኒስቴር ከቱሪዝም የመዳረሻ ልማት አንፃር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ምን ምን ናቸው?
አቶ ሙሳ ፦ ቱሪዝም ከአገር በቀል ኢኮኖሚ ከፍተኛ ተብለው ከተቀመጡ ከአምስቱ ዘርፎች አራተኛ ላይ ተቀምጧል። በዚህ ባገባደድነው 2014 ዓ.ም በዋናነት እንዲሆን የተደረገው መንግሥት በኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ቱሪዝሙ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዲይዝ ነው። ስለዚህ ይህንን ሃላፊነት መሸከም የሚያስችል መዋቅር እንደ አዲስ በሚኒስቴር ተደራጅቷል። በዋናነት በመንግሥት የተያዘውን ፍላጎትና የሚጠይቀውን አቅም በፋይናንስም ሆነ በሰው ሃይል የተሰጠውን ሃላፊነት መሸከም የሚያስችል መዋቅር ተግባራዊ ተደርጓል። በዚህ ዓመት እንደ ቱሪዝም ሚኒስቴር የሰራነው ዋናው ጉዳይ እሱ ነው።
ከዚህ ቀደም የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች በካፒታል በጀት አይደገፉም ነበር። እንደማንኛውም ዘርፍ መደበኛ መንግሥት በሚያቀርበው በጀት ሊሰራ እንደማይችል ታምኖበት ቀደም ሲል ከተለመደው ውጪ የካፒታል ፕሮጀክት እንዲኖረው ዘንድሮ በሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት በፀደቀው መሰረት የቱሪዝሙ ዘርፍ ከተለያየ ምንጭ ፈንድ በማሰባሰብ ልዩ ድጎማ እንዲኖረው ፈቃድ ተሰጥቶታል።
የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይጠይቃሉ። ስለዚህ ይሄንን ሃላፊነት መሸከም የሚያስችል መዋቅር ይፋ አድርገን እንደ ቱሪዝም ሚኒስቴር አዲስ መዋቅር ተግባራዊ ሆኗል።
በፕሮጀክት ደረጃ እየተመሩ ያሉትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተበስረው የተጀመሩት “የገበታ ለአገር” የመዳረሻ ልማት ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያቤቱን በቀጥታ ስለሚመለከቱት በዚያ ላይ ተሳትፎ እናደርጋለን። መንግሥት እየተከተለ ያለው ሞዴል የመዳረሻ ልማት መሰረተ ልማቶችን በቅድሚያ ሲያሟላ የግል ባለሀብቱና በአካባቢው የሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎች በተጨማሪ እንዲሳተፉ የሚያደርግ ነው። ስለዚህ ይህንን አቅም የሚደግፍ ስራ በዋናነት እያገባደድን ባለነው የ2014 ዓም ስንሰራ ቆይተናል።
ሚኒስቴሩ ሌሎች ተጠሪ ተቋማት ማለትም ቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣንና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በማቀናጀት እነዚህን ሜጋ ፕሮጀክቶች በተመለከተ የተለያዩ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል። እንደ አገር የተያዙ የመዳረሻ ልማቶች በዘርፍ ደረጃ እኛን ስለሚመለከቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ አለን።
አዲስ ዘመን፦ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረጉት ፕሮጀክቶች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላችሁ። ለመሆኑ በምን መንገድ ነው የድርሻችሁን የምትወጡት?
አቶ ሙሳ ፦ ቴክኒካል ድጋፍ እናደርጋለን። ለምሳሌ ሎጆች ላይ ለሚሳተፉ ባለሀብቶችና የተለያየ አገልግሎቶች ላይ ለሚሰሩት እንደ ከቀረጥ ነፃ አይነት ፍቃዶችን በመስጠት ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን። ከመዳረሻ ልማት ስራዎች አንፃር በገበታ ለአገር ውስጥ በዋናነት የምንሳተፈው በዚህ መልኩ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በከፍተኛ ደረጃ ከተያዙ ሜጋ ፕሮጀክቶች “ የገበታ ለአገር” መዳረሻ ልማት ፕሮጀክት ውጪ የምትሰሯቸው ተግባራትስ ምንድን ናቸው?
አቶ ሙሳ ፦ ገበታ ለአገር ላይ ከምናደርገው ቀጥተኛ ተሳትፎ በተጨማሪ በመደበኛነት ቱሪዝም ሚኒስቴር የያዛቸው ሞዴል ስራዎች አሉ። የካፒታል ፕሮጀክቱ በምክር ቤቱ ፀድቆ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው በዚህ ዓመት ነው። ይህንን ምክንያት ሳናደርግ ግን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አሳትፈን የስንቅሌ ቆርኪዎች መጠለያ ስፍራ ላይ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንንና አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት አካተን ሶስት የማህበረሰብ አቀፍ ሎጅ ግንብተን እያጠናቀቅን እንገኛለን።
እንደሚታወቀው አገራችን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ቢኖራትም በማልማት ስራው ላይ ግን በጣም ወደ ኋላ ቀርተናል። ስለዚህ የካፒታል እጥረትን ምክንያት ሳናደርግ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የየአካባቢው ማሕበረሰብን በማሳተፍ “የመንዝ ጓሳን የማሕበረሰብ አቀፍ ሎጅን” ልምድ በቀጥታ በመውሰድ ተመሳሳይ ስራዎችን በልዩ ልዩ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ላይ ለመስራት እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የስንቅሌ ቆርኪዎች የማሕበረሰብ አቀፍ ሎጅ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ሙሉ ለሙሉ በአካባቢው ሕብረተሰብ ይተዳደራል።
አዲስ ዘመን፦ ከመሰረተ ልማቱ ውጪ መሰራት ያለበት ተግባር ላይስ ምን እያከናወናችሁ ነው?
አቶ ሙሳ፦ የቱሪዝም ልማት ስራ የመሰረተ ልማት (ፊዚካል) ስራ ብቻ አይደለም። የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ቦታዎች ላይ በመገኘት እንዲነቃቁ ለማድረግ እየሞከርን ነው። የግንዛቤው ስራ እንዳለ ሆኖ ግን በጣም በመጠነኛ በጀትም ቢሆን ማሳያዎችን እየሰራን ነው። ለምሳሌ ያህል አገራችን ከቱሪዝም ዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል አንደኛው መሰራት ያለበት “ላንድ ማርክ” ነው። ይህ ማለት በሀገሪቱ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ቅርሶችን፣ ብሄራዊ ፓርኮችን እንዲሁም የማይዳሰሱትም ሆነ የሚዳሰሱ ቅርሶችን በሚገባ ማስተዋወቅ የሚችሉ ምልክቶች (ብራንዶች) የሉም። ለዚህ እንደ ሞዴል እንዲሆን ባገባደድነው 2014 ዓ.ም በአርሲ በቆጂ የኢትዮጵያ ብርቅዬ አትሌቶች መገኛ መሆኗን የሚያሳይ የብራንዲንግ ስራ ከታላቁ ሩጫ ጋር በመሆን መስራት ተችሏል። ይህ የስፖርት ቱሪዝሙን ከማልማት አንፃር እየሰራን ያለነው ነው።
በተመሳሳይ በምስራቁ የኢትዮጵያ መስመር ደግሞ በሐረርና ድሬዳዋ ላይ አካባቢዎቹን የሚያስተዋውቁ (ፕሮሞት የሚያደርጉ) “ላንድ ማርክ” ግንባታዎችን እየሰራን ነው። የሐረሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት ይቀረዋል። እነዚህን የፊዚካል ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። በልዩ ልዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉና እንደ ቱሪዝም ሀብት የማይታዩ አቅም መፍጠር የሚችሉ ነገሮችን ወደ ገበያው ለማምጣትም ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ይህን ለማሳካት ከክልል መስተዳድር አካላት እና ከቅርሶቹ ባለቤቶች ጋር ምክክር በማድረግ ስኬታማ ለመሆን ጥረት እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የግል ባለሀብቶች በመዳረሻ ልማት ላይ እንዲሳተፉ የሚደረገው ጥረት ምን ይመስላል? ምን አበረታች ነገሮችስ ታይተዋል?
አቶ ሙሳ፦ መንግሥት በቱሪዝሙ ዘርፍ ልዩ ማበረታቻዎችን ለባለሀብቶች ያደርጋል። እኛም ልዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሰነድ አቅርበን ሰባት መዳረሻዎች ያንን እድል እንዲያገኙ አድርገናል። ለምሳሌ ኢንቨስተሮች ከቀረጥ ነፃ ለስራቸው የሚውል ቁስ እንዲያስገቡ፣ የታክስ እፎይታ ለአምስት ዓመት እንዲያገኙና የመሳሰሉትን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የጸደቀ ነው። ይሄ ከመደበኛው ማበረታቻ የተለየ ነው። በተጨማሪ ለስራና አገልግሎት የሚጠቀሙባቸውን ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ይችላሉ።
እነዚህ ሰባቱ እነዚህ በዋናነት በተመረጡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ተሳትፎ ለሚያደርጉ ባለሀብቶች የተፈቀዱ ናቸው። ወንጪ፣ ጎርጎራ አቢያታ ሻላ የሚያካትቱ ናቸው። ባለሀብቶቹ ወደነዚህ ስፍራዎች ለማልማት ሲሄዱ ያለውን ልዩ ጥቅም እንዲረዱ ለማድረግ ጥረት አድርገናል፡፡ ባለሀብቶቹ ወደ እነዚህ ስፍራዎች ለማልማት ሲሄዱ ያለውን ልዩ ጥቅም እንዲረዱ ለማድረግ ጥረት አድርገናል። ተጨማሪ አስር የመዳረሻ ሰፍራዎችም መሰል ማበረታቻዎች እንዲኖራቸው ጥናት እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በገበታ ለአገር ፕሮጀክት በተያዙ የመዳረሻ ልማቶች ላይ ያላችሁ ግምገማ ምን ይመስላል? ከመሰረተ ልማት ግንባታው በተጨማሪ ባለሀብቱ ተሳትፎ ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት ምን ይመስላል?
አቶ ሙሳ ፦ በወንጪ፣ ጎርጎራና ኮይሻ ተፈጥሮን መሰረት አድርገው በሚሰሩ የመዳረሻ ልማቶች ላይ ባለሀብቶች መዋለ ንዋያቸውን አፍስሰው ለመግባት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ለምሳሌ በጎርጎራ ይህ ፍላጎት ይታያል። በነዚህ ቦታዎች ፍላጎቱ ካለው የማስተናገድ አቅም በላይም እየሆነ ነው።
አሁን እኛ ያለን ግምገማ ሶስቱም የቱሪዝም ልማት ስራዎች ተፈጥሮን ማእከል ያደረጉ በመሆናቸው በዚያ አካባቢ ላይ የሚገነቡ የመሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቁ መሆናቸውን ነው። ወንጪ ሃይቁ፣ መልክአምድሩም ሆነ እያንዳንዱ ነገር ጥንቃቄ ይጠይቃል። በተመሳሳይ ሌሎቹም እንደዚሁ ናቸው። ከዚህ አንፃር ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ከባለሀብቱ አኳያም ነገሮች ሙሉ ለሙሉ እንዲሟሉና ፍፁም እንዲሆን የመጠበቅ አዝማሚያም አስተውለናል። ያንን ወደ ጎን ትተው በተግባር እየሰሩ ያሉ ባለሀብቶችም አሉ።
በገበታ ለአገር ፕሮጀክት የሚሰሩ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች ዋንኛ ዓላማቸው ሞዴል ሆነው እነሱን መሰረት አድርገው የሚሰሩ በርካታ ፕሮጀክቶች እንዲኖሩ ነው። በኛ ግምገማም አሁን ላይ መሰል እንቅስቃሴዎች በልዩ ልዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በከተሞች እየተመለከትን ስለሆነ ግቡን በመምታት ላይ እንደሆነ እናምናለን። ይህንን ሞዴል ጅማ፣ ሀዋሳ፣ ጎንደርና የመሳሰሉት እየወሰዱት ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፦ በቀጣይ ነባርና አዳዲስ የመዳረሻ ልማቶችን ለመስራት ምን አቅዳችኋል? የቱሪዝም ሀብቶችን ከማስተዋወቅ አንፃርስ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሙሳ ከድር፦ እኛ እንደ ዘርፍ ቱሪዝም አንዱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ መለየቱ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለብን እንድናምን አድርጎናል። ስለዚህ በቀጣይ ዓመት ተግባር ላይ ይውላል ተብሎ የሚታሰበውን የካፒታል ፕሮጀክት፣ እንደ ማስተርካርድ ያሉ ድጋፎችንና ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነባሮቹ ላይ እሴት ከመጨመር አንስቶ አዳዲስ ልማቶችን በማካሄድ የቱሪዝም የመስህብ ስፍራዎች ላይ በትኩረት ይሰራል። በበጀት ዓመቱ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የመንግሥት ዋንኛ ትኩረትም የመዳረሻ ልማት ላይ ይሆናል።
ሌላው በተለመደው መንገድ ተሄዶ የኢትዮጵያን የመስህብ ሀብቶች ማስተዋወቅ ስለማይቻል የተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመሳተፍ የመዳረሻ ስፍራዎቹን፣ ሀብቶቹንና ያሉትን ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ ማስተዋወቅ በቀጣይ ከሚሰሩት ተግባራት መካከል ቀዳሚ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአገራችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የፀጥታ ችግር ነበር። ይሄ ደግሞ ቱሪዝሙን ክፉኛ ጎድቶታል ይባላል። ከላይ ያነሱልኝን ተግባራት በአግባቡ እንዳትከውኑ ይሄ ችግር ምን አስተዋጽኦ ነበረው?
አቶ ሙሳ ፡- የቱሪዝም ዘርፍ ሰላም ከሌለ በቀላሉ የሚፈረከስ “fragile” ከሚባሉት ወስጥ ነው። የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ሙሉ ለሙሉ ቱሪዝሙን አዳክሞት ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ ደግሞ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የፀጥታ ችግር ተፈጥሯል። ይሄም ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ምክንያት ሆኗል።
አሁን ግን የቱሪዝም ሚኒስቴር የተከሰተውን ችግር ተጠሪ ተቋማትን አሳትፎ በጦርነቱ የተጎዱ የመዳረሻ ቦታዎች ተጠንተዋል። የዚህም ሪፖርት ለማእከላዊው መንግሥት ደርሷል። በዚህም መሰረት ዘርፉ አስቸኳይና ወሳኝ ድጋፍ ከሚሹ ዘርፎች አንዱ ሆኖ እውቅና ተሰጥቶት ድጋፍ እንዲያገኝ እየተሰራ ነው። በተለይ ይህ የፀጥታ ችግር ምን ያህል ዘርፉን ወደ ኋላ እንደጎተተው በጥናቱ ለመመለስ ተሞክሯል።
አዲስ ዘመን፦ ዘርፉ ላይ ላሉ ዋንኛ ተዋንያን እና ለሕብረተሰቡ የሚያስተላልፉት መልክት ካለ?
አቶ ሙሳ ፦ በኛ አገር ባህልና ቱሪዝም የቅንጦት የሆነ ዘርፍ ተደርጎ ነው የሞቆጠረው። ይህ የተሳሳተ ነው፡፡ ዘርፉ ቅንጡ ዘርፍ ሳይሆን የማሕበረሰቡን ሕይወት የሚቀይር እንዲያውም በአንዳንድ አገራት በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ሀብት ግኝት (ጂዲፒ) ቀዳሚውን ድርሻ ሰጥተው የሚያሳኩበት ነው።
ኢትዮጵያም በዩኒስኮ ዓለም አቀፍ ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ በቁጥር ብዛት አንደኛ ናት። ብዙ የተፈጥሮና የባህል ሀብቶች አሉን። እነዚህን እምቅ ሀብቶች ወደ ውጤት ለመቀየር ሁሉም ባለድርሻ አካላት መሳተፍ መቻል አለባቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ አቅሙ ያላቸው ባለሀብቶች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምእራብ ጫፍ ብዙ ብሄራዊ ፓርኮች፣ ቅርሶች ታሪካዊ ስፍራዎችና ተፈጥሯዊ ቦታዎች ላይ በቀጥታ ጣልቃ ገብተው ለእድገቱ በጋራ መስራት አለባቸው የሚል መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡን ሃሳብ እናመሰግናለን!
አቶ ሙሳ ከድር፦ እኔም አመሰግናለሁ!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም