መንገድ በኢትዮጵያ ዋነኛው የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ሲሆን ከሰው እና ከእቃ እንቅስቃሴ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍን በመሆኑም በአገሪቱ ዘላቂ ልማት ላይ ወሳኝ ተጽዕኖ ያለው ነው። በዚህም መነሻ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ከፍተኛ በጀት እየተመደበ መጠነ ሰፊ ስራ ተሰርቷል። ይህን ተከትሎም በመንገድ አውታር ልማት የታየ ተጨባጭ ለውጥ ቢኖርም የዘርፉ ውጤታማነት፣ ቅልጥፍና እና ዘላቂነት ከአገልግሎት እና ከአፈፃጸም ደረጃ አንጻር አሁንም ፈርጀ ብዙ ችግሮች እና ክፍተቶች እንዳሉበት ይገለጻል። የመንገድ ዘርፍ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ደግሞ ዘርፉን ከጎዱት ችግሮች አንዱ ነው።
በተለይም በመንገድ
ግንባታ
ላይ
የፌዴራል
መንግሥት
እና
የክልል
መንግሥታት
ሚና
በግልጽ
አለመቀመጡ
አንዱ
ችግር
ነው።
በዚህም
ምክንያት
ወዲህና
ወዲያ
የሚሳሳቡ
ብዙ
ጉዳዮች
አሉ።
ከፍትሃዊነት
እና
ከጥራት
አኳያ
የሚነሱ
ጉዳዮች
አሉ።
በተለይ
ከወሰን
ማስከበር
እና
ከካሳ
ጋር
ተያይዞ
የሚነሳው
ችግር
የዘርፉን
ልማት
እየጎዳው
መሆኑ
እየተጠቆመ
ይገኛል።
በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል የተባለ የመንገድ ፖሊሲ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲዘጋጅ ቆይቷል። ፖሊሲው ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወያዩበት ሲሆን፣ በቅርቡም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ተጨማሪ ግብዓት የሚሰባሰብበት የመጨረሻው የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ረቂቅ ፖሊሲውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ የትምጌታ አስራት እንደተናገሩት፤ በተለይም ለሕብረተሰቡ የመንገድ ፍላጎት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ ከመስጠት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ጉድለቶች፤ የመንገድ ፕሮጀክቶች አመራረጥን እና ፍትሃዊ የመንገድ ስርጭትን በተመለከተ የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች፣ በፌዴራል፣ በክልልና በተለያዩ ደረጃዎች የሚያዙ፣ የሚታቀዱና የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች መናበብ እና ቅንጅት ውስን መሆን፤ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ እና በወጣው ከፍተኛ ወጪ የተፈጠረውን የመንገድ ሀብት በሚጠበቀው ልክ በአግባቡ መንከባከብ አለመቻል፤ በፕሮጀክት ትግበራ ወቅት የሚያጋጥመው መዘግየትና የፕሮጀክት ወጪ ጭማሪ እንዲሁም በዘርፉ የሚሳተፉ ብቃት ያላቸውን አገር በቀል የሥራ ተቋራጮች እና አማካሪዎች በሚፈለገው ደረጃ ማፍራት አለመቻል በዘርፉ መሠራት ያለባቸውን ቀጣይ የማሻሻያ ስራዎች አስፈላጊነት የሚያመላክቱ እውነታዎች ናቸው።
በሌላ በኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የግንባታ ዋጋ፣ የወሰን ማስከበር ችግር እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ፍላጎት አካቶ ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረግ እየተወሳሰበ መምጣቱ ሌሎች ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ጋር ተደምረው ዘርፉ ሁለንተናዊ ማሻሻያ እና ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ እንደሚፈልግ ማሳያ ናቸው።
በተጨማሪም የመንገድ ዘርፍ ፖሊሲ አለመኖር የመንገድ ዘርፍ ኤጀንሲዎችን ተግባር እና ኃላፊነት እንዲሁም የሚመለከታቸውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ተቆጣጣሪ አካላት (በዋነኝነት የፖሊሲ፣ የሕግ፣ የቁጥጥር፣ የእቅድ ዝግጅት፣ የማኔጅመንት እና የኦፕሬሽን ተግባራት) በግልጽ ከመወሰንና የአስተዳደር መዋቅሩንና ተቋማዊ ማዕቀፉን ለደንበኛና ቅልጥፍና ተኮር ማኔጅመንት ምላሽ ሰጪ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር በቂ ነጻነት ኖሯቸው መስራት እንዲችሉ ከማድረግ እና ለዘርፉ የሚስያስፈልገውን ፋይናንስ በዘላቂነትና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ከማግኘት አኳያ ውሱንነት ያለበት ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ ዘላቂ የመንገድ ልማት የሚመራበት፣ ምላሽ ሰጪ የአስተዳደር መዋቅር እና ተቋማዊ ማዕቀፍ፣ የፋይናንስ ግኝትና አስተዳደር ሥርዓት፣ አጠቃላይ ዘላቂና አስተማማኝ የመንገድ ሀብት ማኔጅመንትና ወጥነት ያለው እና የተቀናጀ የእቅድ ዝግጅት የሚመራበት የመንገድ ዘርፍ ፖሊሲ ማዘጋጀት በዘርፉ ለሚካሄደው ሁለንተናዊ ሪፎርም ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ፖሊሲው በዋነኝነት በአገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የልማት አጀንዳዎች፣ በዓለምአቀፍ ስምምነቶች፣ በዘርፉ አቅም ግንባታ፣ ማዘመንና በተቋማዊ ሽግግር ዓላማዎች ላይ ተመስርቶ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ብቃትና ውጤታማነት፣ የማሕበራዊ መስተጋብርን መጎልበት እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማረጋገጥ በሚያስችል ቁመና ላይ እንዲደርስ ማድረግና በዚህ ቁመናው ለሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ታስቦ የተዘጋጀ የዘርፉን ቀጣይ አካሄድ በተመለከተ አቅጣጫ የሚሰጥ ሰነድ መሆኑም ነው የተመላከተው።
ከፖሊሲው መሰረታዊ እሳቤዎች መካከል የቀጣይ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫን፣ የፀደቀውን የትራንስፖርት ፖሊሲን፣ በረቂቅ ደረጃ ያለውን የኮንስትራክሽን ፖሊሲን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ፖሊሲዎችና ሕጎችን፣ የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማርካት በከተማና በተለይም በገጠር አካባቢዎች የበለጠ ተደራሽነት፣ የጉዞ እንቅስቃሴ እና አማካይ የጉዞ ቅርበት እንዲኖር ማድረግን የሚመለከቱትም በመሰረታዊ እሳቤዎቹ ከተካተቱት መካከል እንደሚገኙበት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
በአህጉራዊና ዓለምአቀፍ ደረጃ የጉዞ እንቅስቃሴንና የንግድ ትስስርን ለመደገፍ የመሰረተ-ልማት ዝርጋታም ሆነ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ የተደረሰባቸው ስምምነቶች፣ መግባባቶች እንዲሁም ግዴታዎችን፤ በአካባቢና በአህጉር ደረጃ ተጓዥንና ንግድን ለመደገፍ መንገድንና ትራንስፖርትን በተመለከተ የተደረሰባቸው ስምምነቶችም ከመሰረታዊ እሳቤዎቹ መካከል ተካተዋል።
ሌሎች በፖሊሲው መሰረታዊ እሳቤዎች ከተካተቱት መካከልም፤ የትራፊክ ፍሰት፣ ደረጃና መሠረታዊ ተደራሽነት ሚዛናዊ እንዲሆን ማድረግ፤ ሚዛናዊ የሀብት አጠቃቀምንና በገጠር የልማት እቅዶች መካከል ያለውን ትስስርን እንዲሁም የረጅም ጊዜ የፋይናንሲንግ እቅድን ግምት ውስጥ በማስገባት የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅድ ማዘጋጀትን፤ የመንገድ መሰረተ ልማትን ተከትለው የሚሰሩና የሚያቋርጡ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን (ዩቲሊቲዎችን) በዲዛይን ማካተትን እና በመንገድ ግንባታ ወቅት ስታንዳርዳቸውን በጠበቀ መልኩ ቦታ ማመቻቸትን ይጠቀሳሉ።
የመንገድ ዘርፍ ፖሊሲ ዋና ዓላማዎች፤ በገጠርና በከተማ አካባቢዎች የሚኖረውን ሕዝብ የጉዞ ፍላጎት መሰረት ያደረገ የመንገድ መሰረተ ልማት መኖሩን ማረጋገጥ፤ በተቀናጀና በተደጋገፈ የመንገድ ልማት መሠረት የመንገድ ትራንስፖርት ወጪን መቀነስና የተቀላጠፈ አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፤ የሴክተር ተቋማትንና ሌሎች የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶችን ኃላፊነት በግልፅ ማሳየትና የሚደጋገፉበትን አጠቃላይ አቅጣጫ ማመላከት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
የመንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ተካሂዷል፤ ከዚያ በፊት የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ እጅግ አነስተኛ የነበረ በመሆኑ አሁንም የመንገድ መሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት ይሻሉ።
አሁን ወደ አዲስ ምዕራፍ ሲገባ የመንገድ ግንባታው ዘርፍ የነበሩ ችግሮችን መገምገም፣ ዘርፉን ለማሳደግ አስቻይ ነገሮችን ማየት እንዲሁም አሁን የ 10 ዓመት እቅድ ሲዘጋጅም ሁሉንም ነገር ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። በአጭር ፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚመለሱትን መለየት ይገባል። ሕጎችን እና አካሄዶችን ጭምር መገምገምም ተገቢ ነው። በረቂቅ አዋጁ ላይ የተካሄዱ ውይይቶች አካሄዶችችን እና እይታዎችን የሚቀይሩ ናቸው።
እስካሁን የአስፋልት መንገዶች በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ነው ሲሰራ እንደቆዩ የጠቀሱት ኢንጂነር ሀብታሙ፤ ይህ አካሄድ ከዚህ በሁዋላ እንደማያዋጣም ነው የጠቆሙት። መንገድ ቶሎ መገንባት ካለብን፣ የኢትዮጵያውያንን ፍላጎት ቶሎ መመለስ ካለብን በብዙ ተቋማት በተከፋፈለ ድርሻ ነው መንገድ መገንባት ያለበት፤ ህጉም ይህንኑ ነው የሚፈቅደው ሲሉ ያብራራሉ።
ይህን ጉዳይ አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩም፣ 246ሺህ ኪሎ ሜትር እንደ ሀገር ይሰራል ይላል። ይህ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ነው። በክልል፣ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንዲሁም በሌሎች አካላት ነው። ማን ምን ይሰራል የሚለውን ዘርዝሮ ማስቀመጥ ወሳኝ በመሆኑ በፖሊሲው ላይ መቀመጡን ጠቁመዋል።
እንደ ኢንጂነር ሀብታሙ ማብራሪያ፤ ብዙ መንገድ እና ጥራት ያለው መንገድ ለመስራት ተከፋፍሎ ካልሆነ በጥቂት አካላት ሊሰራ አይችልም ከሚል መነሻ ነው። ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ነው ብዙ መንገድ መገንባት የምንችለው ከሚል ነው። ለዚህ የፖሊሲ አቅጣጫ እና የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል። ለመንገድ ልማት ገንዘብ ብቻ አይደለም የሚያስፈልገው፤ አካሄድ ያስፈልጋል።
የዘርፉን እድገት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሀገራዊ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄዎች የሚስተናገዱበትን አግባብ ፣ የተፈጠረውን ሀብት በአግባቡ የመጠበቅ ፣ የአገር ውስጥ የስራ ተቋራጮች እና አማካሪዎች አቅም በሚፈለገው መልኩ ከማሳደግ አኳያ ሰነዱ የጎላ ሚና እንደሚያበረክት ተናግረዋል። ክልሎች በመንገድ ዘርፍ ልማቱ ላይ ያላቸውን ሚና እና ሃላፊነት ማሳደግ ላይም የላቀ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል። የወሰን ማስከበር ፣ የግብዓት ችግሮች እና ሌሎችንም የዘርፉን ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ማነቆዎች ለመፍታት ፖሊሲው በላቀ ደረጃ ያግዛል ብለዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት፤ ፖሊሲው ከመንገድ ዘርፍ ጋር ተያይዞ ቀጣይ አገራዊ ግብን ታሳቢ አድርጎ የሚነሱ ችግሮችን የሚፈታ ነው። በዘርፉ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን መፍታት በቀጣይ የሚኖረውን እድገት ታሳቢ አድርጎ የባለድርሻ አካላትን ሚና እና ሃላፊነትን በግልጽ አስቀምጧል። ተቆጣጣሪ ተቋማት ከዚህ ዘርፍ የሚወስዱት ድርሻ በተመሳሳይ ይታወቃል።
የክልልና የፌዴራል ተቋማት ኃላፊነትም እንዲሁ በግልጽ ባለመቀመጡ የሚና መደበላለቅ መኖር፤ በዘርፉ ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ግልጽ በሆነ መልኩ የስራ ድርሻቸውንና የኃላፊነት ደረጃቸውን እንዲሁም የሚመሩበትን አቅጣጫ እንዳያውቁ ከማድረጉ ባሻገር በዘርፉ የሚያጋጥሙ ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታት እና ልማቱ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ ስለመሆኑ የሚመዘንበት ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ፕሮግራሞች ተተግብረው ከተጠናቀቁ በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎች እንዲነሱ ምክንያት ሲሆን ታይቷል። ስለዚህ መሰል ችግሮች እንዲፈቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ግልጽ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ እና አመራር የሚሰጥ እንድ ወጥ የፖሊሲ ሰነድ አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ የመንገድ ዘርፍን በግልጽ አቅጣጫ በመምራት ከዘላቂነት፣ ከአስተዳደር መዋቅር፣ ከፕሮጀክት አመራር፣ ከተቋማዊ ማዕቀፍ፣ ከኢኮኖሚያዊ እና የፋይናንስ ግኝትና አስተዳደር እንዲሁም ከማህበራዊ ገጽታዎች፣ ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ከምርምር እና ልማት፣ ከአጠቃላይ ተቋማዊ እና የዘርፍ አቅም ግንባታ፣ ከብቃት እና ከተጠያቂነት ጋር የተያያዙ የረጅም ጊዜ ቁልፍ ችግሮችን ለመቅረፍ ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትን የልማት አጀንዳዎች ለመደገፍ እና የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የፖሊሲ ሰነዱ ተዘጋጅቷል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በተለይም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡት የዜጎች መብት፣ የኢኮኖሚ፣ ማሕበራዊ እና የባህል መብቶች፣ የልማት መብት፣ የአካባቢ ደህንነት መብት፣ እና የመንግሥት አወቃቀር እና የፌዴራል መንግሥት ድርሻ የዚህ የመንገድ ፖሊሲ መሠረታዊ መነሻዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ሰነዱ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠንና የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል የመካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ ለማሳካት ያለውን ራዕይ መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ነው።
በሂልተን ሆቴል በተካሄደው በመንገድ ፖሊሲ እና የመንገድ አዋጅ ረቂቅ ሰነዶች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፣ ከሁለቱም ምክር ቤቶች ፣ ከክልል ባለድርሻ አካላት ፣ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፣ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ተቋማት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ታድመዋል። ታዳሚዎቹ ዘርፉ የሚመራበትን ግልጽ አቅጣጫና ቀጣይ ግብና ተልዕኮን በግልጽ ያመላከተ ሀገራዊ ሰነድ መዘጋጀቱን በመጥቀስ አድንቀዋል። በረቂቅ ፖሊሲውና በሕግ ሰነዱ ላይ ቢካተቱ ያሏቸውን የማዳበሪያ ምክረ ሃሳቦችንም አክለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው ለመንገድ ግንባታ አንዱ ማነቆ የሆነው የወሰን ማስከበር ችግር እና የካሳ ጉዳይ ነው። አዲሱ ፖሊሲ የወሰን ማስከበር እና የካሳ ጉዳዮችን ክልሎች በራሳቸው እንዲያከናውኑት የሚያደርግ ነው። ይህ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2014