«ተወልጄ ያደኩት በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል በመሆኑ አውሮፕላን ቀርቶ መኪና የማየት እድል አልነበረኝም። ነገር ግን በ1977 ዓ.ም በሀገራችን ተከስቶ በነበረው ድርቅ ምክንያት የቀይ መስቀል ድርጅት ሰራተኞች ለማህበረሰብ እርዳታ ወደ መንደሬ በአውሮፕላን ጎራ ብለው ነበር። እኔም አውሮፕላኑ ከሰማይ ወርዶ ምድር ላይ ሲያርፍ የተመለከትኩት ያን ጊዜ ነው» በማለት የፈጠራ ባለሙያው አቶ አስመላሽ ዘፈሩ አውሮፕላንን የተዋወቁበትን አጋጣሚ ይናገራሉ።
ወቅቱ ለማህበረሰቡ እርዳታ ለማድረግ የመጡት የቀይ መስቀል ባለሙያዎች ከአውሮፕላኑ ሲወርዱና ሲወጡ በተመስጦ ሲመለከቷቸው እንደነበር በመናገርም ከለጋነት እድሜያቸው ጀምሮ በቴክኖሎጂው ልባቸው መነደፉንና ያኔ ያዩት የአውሮፕላን ቅርጽም በአእምሮአቸው ተቀርጾ መቆየቱንና ያን አውሮፕላን ለመስራትም መነሳታቸውን ነው የሚናገሩት። እርሳቸውም የሰሩት የፈጠራ ስራ ሁለት ሰው መያዝ የሚችል 600 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቀላል አውሮፕላን ሲሆን፤ የልጅነት ህልማቸው የነበረውን የፈጠራ ስራ በ2006 ዓ.ም በሰንዳፋ ከተማ መስራታቸውን ይገልጻሉ።
በወቅቱም ስራውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ አንድ አመት ከሰባት ወር ፈጅቶባቸውም ነበር። በአለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፕላን የሰሩት ሁለቱ አሜሪካዊ ወንድማማቾች ኦሊቨር እና ዊልቨር ራይት አውሮፕላን የሰሩት የመኪና ሞተር ተጠቅመው ነበር። ምንም እንኳን አሁን ላይ እራሱን ችሎ የአውሮፕላን ሞተሮች እየተመረተ ቢገኝም፤ የፈጠራ ባለቤቱ አቶ አስመላሽም የድሮውን መንገድ በመጠቀም የመኪና ሞተርን ለአውሮፕላኑ እንዲስማማ አድርገው በመቀየር ስራውን ለመስራት መቻላቸውን ነው የሚናገሩት።
በተጨማሪም አልሙኒየም፣ የአልሚኒየም ቲዩብ፣ ጨርቅ፣ ጣውላ፣ ጎማና በጣም ጥቂት የሚባል ብረት የመሳሰሉ ጥሬ እቃዎችን የተጠቀሙ ሲሆን በአጠቃላይ የሞተር ሳይክልና የመኪና እቃዎችን እንደግብአትነት በመጠቀም የፈጠራ ስራውን መስራት እንደቻሉ ገልጸዋል። በ2006 ዓ.ም የፈጠራ ስራውን ካጠናቀቁ በኋላ የክብደት አለመመጣጠን ችግር ተከስቶ የነበረ በመሆኑ፤ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት አሁን ላይ የሰሯትንአውሮፕላን ክብደት 150 ኪሎ ግራም የምትመዝን ቀላል አውሮፕላን በማድረግም ነው የፈጠራ ስራውን አሻሽለው የሰሩት።
በአደጉ ሀገሮች አብዛኛው ቴክኖሎጂዎች በግለሰብና በኩባንያዎች እጅ የተያዙ ናቸው። ይህ ሁኔታ እራሱን የቻለ ስጋት ቢኖረውም የሀገራቱ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ግን የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ስራዎቻቸውን ወደ ኩባንያ ቀይረው ለሀገር ብሎም ለአለም የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ምንጭ ሆነዋል። ስለዚህ የእኔም ህልም የፈጠራ ስራው አድጎና ተስፋፍቶ ወደ ኩባንያ እንዲቀየርና ለሀገር እድገት የራሱን አስተዋጽኦ በብዙ መልኩ እንዲያበረክት ነው ብለዋል።
የፈጠራ ስራው የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገራችን ለማሸጋገር ብሎም የራሳችን የሆነ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት እንዲኖረን የሚያደርግ ነው ያሉት የፈጠራ ባለቤቱ፤ ይህን ቀላል አውሮፕላን በመጠቀም ብሄራዊ ፓርኮችን፣ ታሪካዊ ቦታዎችንና ከተሞችን ለቱሪስት በማስጎብኘት የጎብኚዎች ፍሰት በሀገሪቱ ከፍ እንዲል ከማድረጉም በላይ ሀገሪቱ ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት ያስችላታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚታወቀው ጥራት ያለውና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ነው። ይሄ የሚበረታታና ለሀገሪቱ ኩራት ቢሆንም፤ ይበልጥ አየር መንገዱ አትራፊ የሚሆነው ከውጭ የሚያስገባቸውን አውሮፕላኖች እራሱን ችሎ ማምረት ቢችል በመሆኑ እንደዚህ አይነት የፈጠራ ስራዎች ደግሞ ሁኔታዎችን ምቹና ቀላል ያደርጉታል። አውሮፕላን አምርተን የምንጠቀምና ለሌሎች የምንሸጥ ከሆነ በተጓዳኝ ለሸጥንላቸው ሀገሮች የጥገናና የስልጠና አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ፣ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንዲሁም ለወደፊት የፈጠራ ስራውን በጥራትና በአይነት ተሻሽሎ እንዲሰራ መንገድ ይከፍታል ባይ ናቸው።
በቀጣይም የፈጠራ ስራውን በማሻሻል የህዝብና የዕቃ ማመላለሻ አውሮፕላኖችን በሀገር ውስጥ ለማምረት መንገድ ጠራጊ የፈጠራ ስራ መሆኑንም አቶ አስመላሽ ይናገራሉ። አቶ አስመላሽ፤ እንደሚሉት አውሮፕላኑን ለማምረት የሚያስችል የምስክር ወረቀት ለማግኘት ከፍተኛ ፈተና ገጥሟቸዋል ምክንያቱም ሀገሪቱ በአለም አቀፍ የሲቪል አቬሽን ህግ ስለምትተዳደር አውሮፕላኑን ለማምረት አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የምስክር ወረቀት በማስፈለጉ ነው።
ስለዚህ የፈጠራ ስራውን በሀገሪቱ የአየር ሀይል ሲቪል አቬሽን ዘርፍ ለስፖርት፣ ለመዝናኛና ለመሰል ስራዎች የሚውሉ ቀለል ያሉ አውሮፕላኖችን አምርተው ለመጠቀም ህጉ የሚፈቅድ በመሆኑ፤ አልተራ ላይት የሚባሉ ክብደታቸው ከ250 ኪሎ ግራም በታች የሆኑ ቀላል አውሮፕላኖችን በማምረት በአየር ሀይል ስር በማስመዝገብ ወደ ሀገሪቱ የሲቪል አቬሽን በማስገባት አለማቀፍ ፈቃድ ለማግኘት ከጫፍ መድረሳቸውን ገልጸዋል። የፈጠራ ባለቤቱ አክለውም፤ አውሮፕላን ማምረት ብቻ ሳይሆን የአመራረት ሂደቱን በምን አይነት መልክ መሆን አለበት የሚለውን ታሳቢ በማድረግ እየሰሩ ሲሆን፤ የአውሮፕላኑን የተለያዩ ክፍሎች ለጥቃቅንእና አነስተኛ ተቋማት እንዲያመርቱ በመስጠት በነዚህ ተቋማት የተመረቱትን የአውሮፕላን ክፍል በመሰብሰብ የመገጣጠም ስራ ብቻ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በዚሁ አጋጣሚ ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የስራ እድል በመፍጠርና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር አስችሏል። የፈጠራ ባለቤቱ 150 ኪሎግራም የምትመዝነውን ቀላል አውሮፕላን በጅምላ የማምረቱን ሂደት በ2012 ዓ.ም ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እያካሄዱ ሲሆን ከሶስት ወር በኋላ የተሳካ በረራ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።
በረራውንም ካደረጉ በኋላ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን እንዲሁም ማህበረሰቡ በተገኘበት አውሮፕላንዋ በይፋ ስራ መጀመርዋን እንደሚያበስሩም ገልጸዋል። የፋይናንስና የቴክኒክ ችግር የፈጠራ ስራውን ለመስራት ትልቅ ፈተና ሆኖብኝ ነበር ያሉት አቶ አስመላሽ፤ የቤት እቃቸውን በመሸጥ፣ ከሚያገኙት የወር ደሞወዝ 75 በመቶውን ለፈጠራ ስራው በማዋል የልጅነት ህልማቸውን እውን ለማድረግ መብቃታቸውንም ያክላሉ።
አቶ አስመላሽ ስራውን ለመስራት ፍላጎት ቢኖራቸውም፤ ለስራው የሚያስፈልገውን ትምህርትና ስልጠና ባለማግኘታቸው 90 በመቶ የሚሆነውን ስራ ሰርተው ካጠናቀቁ በኋላ ሙከራ ሲያደርጉ አውሮፕላንዋ ወደ ፊት መሄድ ሲገባት ወደ ኋላ መሄዷን ያስታውሳሉ። ይህንን ችግር ለማለፍም ስራውን በሚሰሩበት ወቅት ሶስት ጊዜ አፍርሰው በመስራትና ከስህተታቸው በመማር አሁን አሻሽለው በመስራት ህልማቸውን እውን አድርገዋል።
የሀገር ውስጥ፣ አለም አቀፍ ሚዲያዎች እና የአካባቢው ማህበረሰብ በተገኙበት የተሳካ ሙከራ ለማድረግ ችለዋል። አቶ አስመላሽ የሰንዳፋ ከተማ አስተዳደር ያደረገላቸውን ድጋፍ ሲናገሩም የገንዘብ ድጋፍ፣ የፈጠራ ስራቸውን በከተማዋ በሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት እንዲሰሩ በማድረግ፤የፈጠራ ባለቤቱ በትምህርት ቤቱ የሚገኙ የተለያዩ ማሽኖችንና ተረፈ ምርቶችን እንዲጠቀሙ በመፍቀድ ከፍተኛ ትብብር አድርጎላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የፈጠራ ስራቸውን ለሙከራ ካበቁ በኋላ፤ በሰሩት የፈጠራ ስራ የድሮው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአሁኑ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዋንጫ ሽልማትና የ30ሺ ብር ድጋፍ አድርጎላቸዋል። እንዲሁም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለስራ ማስኬጃ የሚሆን 31ሺ ብር ድጋፍ አበርክቶላቸዋል።
መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍና ባላቸው የአላማ ጽናት አድካሚና ተስፋ አስቆራጭ የነበረውን ጉዞ አልፈው የፈጠራ ስራቸውን እውን ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በሌላ በኩል የፈጠራ ባለቤቱ ለፈጠራ ስራው የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ለመግዛት ወደ ገበያ ሲወጡ፤ ነጋዴው ማህበረሰብ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ እንደሚያደርግላቸው አንዳንዶችም ያለምንም ትርፍ እንደሚሸጡላቸው ይናገራሉ። በአጠቃላይ «የአንተ ስኬት የኛ ስኬት ነው»በማለት ማህበረሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርግልኛል ሲሉ አቶ አስመላሽ ይናገራሉ። በመጀመሪያ የፈጠራ ስራውን ለመስራት ስነሳ ባለቤቴ ለስራው ፍላጎት ካለማሳየቷም በላይ ምንም ድጋፍ አታደርግልኝም ነበር ያሉት አቶ አስመላሽ፤ አሁን ላይ ህልማቸው ፍሬ አፍርቶ ሲያዩ ግን ከጎናቸው በመሆን ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉላቸው ይገኛሉ።
በተጨማሪም የቅርብ ቤተሰቦቻቸው እና የስራ ባልደረቦቻቸው በሃሳብና በገንዘብ ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሆነ ገልጸዋል። አቶ አስመላሽ አዲሷን ሞዴል አውሮፕላን ከሶስት ወር በኋላ በተሳካ ሁኔታ ለበረራ ብቁ እንድትሆን የተለያዩ ቁሳቁሶችን የሚያሟሉበት የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ድርጅት እያፈላለጉ ሲሆን አውሮፕላኗ ለበረራ እንድትበቃ እስከ አሁን ቃል ከመግባት ውጭ በተግባር ድጋፍ ያደረገላቸው ድርጅት አላገኙም።
የፈጠራ ስራውን ከሰራሁ በኋላ የፈጠራ ስራውን አምርቼ ወደ ገበያ ለማስገባት የሚያስችለኝ የመስሪያ ቦታ አገኛለሁ ብዬ አስቤ ነበር ያሉት የፈጠራ ባለቤቱ፤ እስከ አሁን የመስሪያ ቦታ አላገኙም። የፈጠራ ስራውንም የግለሰብ ቦታ ተከራይተው እየሰሩ ይገኛሉ። ይሄ ደግሞ ለከፍተኛ ወጪ የሚያጋልጣቸው በመሆኑ፤ ስራውን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ለማምረት ካለመቻላቸውም በላይ ለከፍተኛ የፋይናንስ ችግር የሚያጋልጣቸው በመሆኑ፤መንግስት ችግራቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የመስሪያ ቦታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል። የፈጠራ ስራውን መስራት ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቋቋም አላማ ያላቸው አቶ አስመላሽ መንግስት የመስሪያ ቦታ ቢያመቻችላቸውና የፋይናንስ ድጋፍ ቢያገኙ ጥሩ ስራን ሰርተው ማለፍ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
በሶሎሞን በየነ